በሲሳይ ሳህሉ
በምግብ ራስን ለመቻል ያግዛሉ ተብለው በመንግሥት የተያዙ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች፣ በሲሚንቶ እጥረት ምክንያት መዘግየት እንደገጠማቸው የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
መንግሥት በተያዘው በጀት ዓመት 16 ቢሊዮን ብር በጀት በመመደብ ከ350 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት ሊያለሙ የሚችሉ 52 የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ያቀደ ቢሆንም፣ ከፍተኛ የሆነ የሲሚንቶ እጥረት መስተጓጎል እየፈጠረባቸው እንደሆነ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) የተቋሙን የሦስት ወራት ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኞ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. የተፈጥሮ ሀብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሲሚንቶ እጥረትን ለመቅረፍ በአገር ውስጥ ከሚመረተው በተጨማሪ፣ በ2013 በጀት ዓመት 30 ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ ባለፈው ወር የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን መንግሥት የሚጠበቀውን አገራዊ ዕድገት ያመጣሉ ከተባሉት ዕቅዶች ውስጥ አንዱ የሆነውን የግብርና ምርታማነት ለማሳደግ፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡና ለመገንባት በዕቅድ ላይ ያሉ የመስኖ ፕሮጀክቶችን የሚደግፍ የሲሚንቶ ምርት እጥረት መኖሩን ተጠቁሟል፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት በምክር ቤቱ ፀድቆ ከነበረው የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በጀት 14 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከ8.5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ተመላሽ እንደነበር የገለጹት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ፈቲያ የሱፍ፣ ዘንድሮ ለመስኖ የተመደበው ገንዘብ በተገቢው ሁኔታ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር የሲሚንቶ ችግርን በመቅረፍ የፕሮጀክቶቹን ግንባታ በወቅቱ እንዲያጠናቅቅ አሳስበዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከክልሎች ጋር ባሉ አለመግባባቶችና የቆዩ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች ዲዛይን ችግር፣ የታሰበውን ሥራ በሚፈለገው ፍጥነት እንዳይሄድ እንዳደረገው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጠቁሟል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያ ከ3.7 እስከ 4.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በመስኖ ሊለማ የሚችል ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከሰባት እስከ አሥር በመቶ እየለማ ነው፡፡ መንግሥትም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመስኖ ፕሮጀክቶችን በሰፊው በመገንባትና አገራዊ ምርታማነትን በማሳደግ፣ ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ግዥ በአጭር ጊዜ የማስቆም ዕቅድ ይዟል፡፡