Monday, September 25, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያዊያን በማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጭፍጨፋዎችን ተባብረው ማስቆም አለባቸው!

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ በጣም ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ ነው፡፡ መንግሥት የሌለበት አገር ይመስል በተለያዩ ጊዜያትና በተለያዩ ሥፍራዎች በማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጭፍጨፋዎችን ማስቆም አልተቻለም፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ውስጥ እየገባ ነው፡፡ የተያዘው ዓመት ከባተ ወዲህ በተደጋጋሚ በመተከልና በጉራፈርዳ በአማራ ተወላጆች ላይ የተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች፣ ሰሞኑን ደግሞ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን በጉሊሶ ወረዳ ተጠናክረው ሲቀጥሉ መንግሥት ምን እየሠራ ነው መባል አለበት፡፡ የሕዝብን ሰላምንና ደኅንነትን ማስከበር አቅቶ ንፁኃን በማንነታቸው ብቻ ተለይተው በቦምብና በመትረየስ በጅምላ ሲፈጁ፣ መንግሥት መግለጫ ከማውጣት ባሻገር ፈጣን ዕርምጃ መውሰድ ካልቻለ የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ ያሳስባል፡፡ ተጨባጭና ተግባራዊ ዕርምጃ ሳይወሰድ መግለጫ ማንጋጋት ተገቢ አይደለም፡፡ መንግሥት ምን እየተከናወነ እንደሆነ በፍጥነት ለሕዝብ ማስታወቅ አለበት፡፡ ከመንግሥት ውጪ ትጥቅ ይዘው አገር የሚያምሱ ኃይሎች እነማን እንደሆኑና የመሸጉባቸው አካባቢዎች በሚገባ እየታወቁ፣ በተደጋጋሚ ንፁኃን በማንነታቸው ምክንያት እየተጨፈጨፉ በፍፁም ዝም ማለት አይቻልም፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በስፋት የሚስተዋሉ በማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች፣ የማያዳግም ዕርምጃ ተወስዶ በፍጥነት መቆም አለባቸው፡፡ ለማየት ወይም ለመስማት የሚዘገንኑ ጭካኔ የተሞላባቸው ጭፍጨፋዎች፣ ውድመቶችና ማፈናቀሎች በዚህ ሁኔታ ከቀጠሉ አገር ከማፍረስ አይመለሱም፡፡ ሰሞኑን ከፍተኛ የፀጥታ ሥጋት ካለበት አካባቢ የመከላከያ ሠራዊቱ ለምን እንዲወጣ እንደተደረገ፣ እንዲሁም በምትኩ የክልሉ የፀጥታ ኃይል በፍጥነት ያልተሰማራበትን ምክንያት መንግሥት በግልጽ ማስረዳት አለበት፡፡ ከአቅሙ በላይ የሆነ ችግር ካለም መሸፋፈን የለበትም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ይህንን ነውረኛ የጭካኔ ድርጊት ከማውገዝ ባለፈ፣ ካሁን በኋላ እንዳይደገም ተባብረው ማስቆም አለባቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ፈጽሞ መቀጠል አይቻልም፡፡

የመንግሥት ዋነኛ ሥራ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ይህንን ተግባሩን እንዲወጣ ቢጎተጎትም ሊሰማ ባለመቻሉ፣ በማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጭፍጨፋዎች እየተፈጸሙ በርካታ ንፁኃን አልቀዋል፡፡ አሁንም እጅግ ዘግናኝ በሆነ ጭካኔ እያለቁ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ውስጥ የሚከቱ አደገኛ ድርጊቶችን ለማስቆም አለመቻል፣ በታሪክ የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ያን ያህል ለማያሳስቡ ጉዳዮች ከመጠን በላይ ትኩረት እየተሰጠ፣ኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ውስጥ የሚከቱ ድርጊቶች ችላ በመባላቸው አደገኛ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፡፡ በየትኛውም ሥፍራ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለደኅንነታቸው ሥጋት እየተሰማቸው ነው፡፡ ለሕዝብ ሰላም፣ ደኅንነትና ለኢትዮጵያ ህልውና ሲባል በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚስተዋሉ አደገኛ ድርጊቶች፣ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ከሕዝብና ከአገር በላይ ምንም የሚቀድም ነገር የለምና፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት ካልቻለ፣ የአገር ህልውና አደጋ ውስጥ መግባቱ መጠርጠር የለበትም፡፡ ኢትዮጵያን የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት አምባ ማድረግ ሲገባ፣ በየአቅጣጫው በማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን በሕግም በኃይልም ማስቆም ካልተቻለ መዘዙ የከፋ ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የተባበረ ድምፃቸውን በማሰማት መንግሥትን ማስገደድ አለባቸው፡፡

ኢትዮጵያ አጣብቂኝ ውስጥ ሆና መጪውን ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ያለው፣ የምርጫው ዋነኛ ተዋንያን ይሆናሉ ተብለው በሚታሰቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ስምምነት ሳይኖር ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ በፊት የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ዛሬም እንደ አዲስ እያነሷቸው ነው፡፡ ብሔራዊ መግባባት ሳይኖር ምን ዓይነት ምርጫ ነው የሚካሄደው የሚሉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ሰላም በሌለበት ምን ዓይነት ምርጫ ሊካሄድ ይችላል የሚለውም የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ በሰላማዊ ጥሪው መሠረት ወደ አገር ቤት ከተመለሱት መሀል ከእነ ትጥቁ አገር ውስጥ የገባው የኦነግ ክንፍ፣ ዛሬም ዜጎችን በጠራራ ፀሐይ ይፈጃል፡፡ ለሕዝብ ደኅንነትና ለአገር ህልውና ሥጋት በመፍጠር ከዚህ ቀደም ሰላማዊ የነበሩ አካባቢዎችን የጦርነት አውድማ እያደረገ ነው፡፡ ሰላማዊ ሰዎች በጅምላ እየተገደሉና ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉ አገር ከፍተኛ አደጋ ተደቅኖባታል፡፡ ገና ከጅምሩ ትጥቁን ፈቶ የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ተዋናይ መሆን ሲገባው፣ ‹‹ማነው ፈቺው? ማነው አስፈቺው?›› ብሎ ምዕራብ ወለጋን ከተቆጣጠረ ጀምሮ፣ የተፈጠረው ቸልተኝነት ከባድ መስዋዕትነት አስከፍሏል፡፡ ከዚያ በኋላ ‹‹ኦነግ ሸኔ›› በሚባለው ስያሜ ከበስተጀርባው ከመሸጉ ኃይሎች ጋር የጭፍጨፋና የውድመት መለያ ሆኖ ዘግናኝ ዕልቂቶች እየተፈጸሙ ነው፡፡ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት በሰጣቸው መግለጫዎች ዕርምጃ እንደሚወስድ ቢያስታውቅም፣ ጭራሽ አሁን የመከላከያ ሠራዊት ምክንያቱ ሳይታወቅ ገና ከመውጣቱ ንፁኃን በቦምብና በመትረየስ ሲያልቁ የአካባቢው የመንግሥትና የፀጥታ መዋቅሮች ምን እየሠሩ ነበር? የፌዴራል መንግሥቱስ የት ነበር? ይኼ ጉዳይ በሚገባ ተብራርቶ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ሊደረግ ይገባል፡፡ በኢትዮጵያዊያን ሕይወት ላይ መቆመር ማብቃት አለበት፡፡

ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን በማጥበብ የጋራ ዓላማ ሊኖራቸው የሚገባው፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊት አገር ለመገንባት ነው፡፡ ኢትዮጵያ  ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብቷንና በወጣት የተገነባውን የሰው ኃይሏን በብቃት መጠቀም የምትችል አገር መሆኗን ማስመስከር የሚቻለው፣ አንድነቷ የተጠበቀ ታላቅ አገር የመገንባት የጋራ ራዕይ ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያንን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በመልክዓ ምድር፣ በፖለቲካ አቋምና በመሳሰሉት በመከፋፈል አገርን ማዳከም የሚጠቅመው ለጠላት ብቻ ነው፡፡ አገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ግን ልዩነትን አክብሮ የጋራ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ይተባበራል፡፡ ከዚህ ውጪ ሕዝቡን የሚያጋጩ አጀንዳዎች እየፈጠሩ ማስተጋባት ፀረ ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ልዩነትን እያራገቡ አንድነትን ማራከስ ጠላትነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያንን የሚከፋፍል አጀንዳ የት እየተፈበረከ አገሪቱን ለማተራመስ እንደሚውል መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የዓባይን ውኃ ከምንጩ ለመቆጣጠር ከምትሻው ግብፅ ጀምሮ፣ በተለያዩ ጉዳይ አስፈጻሚዎች የሚሸረቡ ሴራዎች ምክንያታቸው ምን ይሆን ብሎ ለማወቅ አለመሞከር የሚጎዳው ኢትዮጵያውያንና አገራቸውን ነው፡፡ ፖለቲከኞች ለሥልጣን ሲሉ ብቻ የሴራ ፖለቲካ የሚያዳውሩ ከሆነ፣ እነሱም የታሪካዊ ጠላቶች ሰለባ መሆናቸውን ማወቅ አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ በማንነት እየከፋፈሉ ለማፋጀት የሚጎነጎነው ሴራ መምከን አለበት፡፡

የኢትዮጵያ አንድነት መሠረቱ የተጣለው በአንድ ወገን ብቻ ነው የሚል ትርክት ውስጥ ያሉ ወገኖች ካሉ ተሳስተዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት የተገነባው በአራቱም ማዕዘናት ለዘመናት በኖሩ ኢትዮጵያዊያን መስዋዕትነት ነው፡፡ ይህንን በመስዋዕትነት የተገነባ አንድነት በተለያዩ ዘዴዎች ለመፈረካከስ መሞከር፣ ጠቡ የሚሆነው የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ከ110 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊያን ጋር ነው፡፡ እነዚህ አስተዋይ ኢትዮጵያዊያን የትኛውም ብሔር፣ እምነት፣ ቋንቋ፣ ባህልና ሌሎች እሴቶች ጥቃት እንዲፈጸምባቸው አይፈቅዱም፡፡ ልዩነቶችን አክብረው፣ እርስ በርስ ተጋብተውና ተዋልደው እዚህ የደረሱት ኢትዮጵያዊያን አንዳቸው ለሌላቸው መከታ ሆነው ነው፡፡ ይህ በጋራ እሴቶችና መስተጋብሮች የተገመደ አንድነት በቀላሉ አይበጣጠስም ተብሎ ነበር የሚታሰበው፡፡ አሁን ግን አንዱን በሌላው ላይ በማስነሳት የጥፋት ፖለቲካ የሚያራምዱ እየበዙ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በጋራ ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን ድባቅ እየመቱ የአገራቸውን አንድነት ሲያስጠብቁ የኖሩት፣ እርስ በርስ በነበራቸው ከፍተኛ ፍቅር እንደሆነ ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት የፍቅራቸው፣ የመከባበራቸው፣ የመደጋገፋቸውና የአብሮነታቸው መገለጫ ይህ መሰሉ ጨዋነት እንጂ፣ አሁን የሚስተዋለው የዘቀጠ ነውረኛና አሳፋሪ ድርጊት አይደለም፡፡

ለኢትዮጵያ አንዳችም የረባ አስተዋጽኦ ያልነበራቸው ግለሰቦችና ስብስቦች፣ ይህንን የመሰለ ፀጋ እየገፈፉ ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጭፍጨፋ ሲፈጽሙ በመተባበር ማስቆም አገራቸውን ከሚወዱ ኢትዮጵያዊያን የሚጠበቅ ተጋድሎ ነው፡፡ በየጊዜው አዳዲስ የጥፋት አጀንዳዎችን እየፈበረኩ አገርን ለማፍረስ የሚሯሯጡ ኃይሎች ይበቃችኋል መባል አለባቸው፡፡ የጥንቶቹ ኢትዮጵያዊያን ሕግ አክባሪ፣ ፈሪኃ ፈጣሪ፣ አስተዋዮችና ጨዋዎች በመሆናቸው አገራቸውን በጋራ ሲጠብቁ ኖረዋል፡፡ የዚህ ዘመን ትውልድም በሞራልና በሥነ ምግባር ታንፆ አገሩን መታደግ አለበት፡፡ የጠላት ተላላኪ ሆነው የአገር አንድነትን የሚያፈራርሱ ነውረኞች በሕግ አደብ እንዲገዙ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በአገር ህልውና ላይ ድርድር የለም መባል ይኖርበታል፡፡ በተለይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድማንነት ላይ ያነጣጠረ ግድያና ውድመት የሚፈጽሙና የሚያስፈጽሙ ኃይሎች፣ በኃይል ጭምር አደብ እንዲገዙ መደረግ አለባቸው፡፡ ለኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ናቸውና፡፡ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ዘመን ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ያለባቸው ለአገራቸው ህልውና ነው፡፡ ኢትዮጵያ የነፃነት፣ የእኩልነትና የፍትሕ አገር መሆን አለባት፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በክብር፣ በፍቅርና በደስታ ማኖር የምትችል አገር በጋራ መገንባት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሰላሟን እያደፈረሱ የግድያና የውድመት መናኸሪያ ሊያደርጓት የሚፈልጉ ኃይሎችን፣ ኢትዮጵያዊያን ተባብረው ሊታገሏቸው የግድ ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ አገሪቱ ውስጥ ምን እየተከናወነ እንደሆነ፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለሚወስደው የማያዳግም ተግባራዊ ዕርምጃ በግልጽ ለሕዝብ መናገር አለበት፡፡ የመግለጫ ጋጋታ ፋይዳ የለውም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ግን በማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጭፍጨፋዎችን ተባብረው ማስቆም አለባቸው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...