የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ማክሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሄደው ስብሰባ፣ በምክር ቤቱ የገነፈለውን የሕዝብ ተወካዮች ሐዘንና ቁጣ ካረጋጉ በኋላ፣ የምክር ቤቱ አባላት በአንድነት ቆመው ችግሩን መቅረፍ ይገባል ሲሉ አሳሰቡ፡፡
የምክር ቤቱ ስብሰባ የተጠራው በተለያዩ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ለማሳለፍ ቢሆንም፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጉሊሶ ወረዳ፣ ጎጎላ ቃንቃ ቀበሌ ውስጥ ብሔርን መሠረት አድርጎ በተፈጸመው ጥቃት ስለተገደሉ ንፁኃን አጀንዳ ተይዞ መወያየት ይገባል፣ ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ተጠርቶ ማብራሪያ ማቅረብ አለበት የሚሉ ድምፆች ከአባላቱ ከተነሱ በኋላ፣ ጉዳዩ በአጀንዳነት ምክክር እንዲደረግበት ክፍት ተደርጓል፡፡
በዚህ ወቅትም በርካታ የምክር ቤት አባላት ሐዘናቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው በዕንባ ተውጠው፣ መንግሥት ባለበት አገር የዜጎች ግድያ ማብቃት አለመቻሉን ተችተዋል፡፡
‹‹የዛሬ ሁለት ዓመት ስንጀምር የነበረኝ ተስፋ ዛሬ የለም፣ የቆምኩለት ሕዝብ እየሞተ አመራር ሆኜ መቀጠል አልፈልግም፤›› ሲሉ የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ በመንግሥት ላይ ትችታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
‹‹የመከላከያ ሠራዊቱ ምን እየሠራ ነው? የደኅንነት ተቋምስ ምን እየሠሩ ነው?›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ አክለውም፣ ‹‹የዜጎችን ሞት ለማስቀረት ሕግ ማስከበር ያልቻለ መንግሥትና ፓርላማ ምን ይሠራል?›› ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሌሎች የምክር ቤቱ አባላትም ተመሳሳይ ጥያቄ ሲያነሱ ተደምጠዋል፡፡ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው በወከላቸው ማኅበረሰብ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በመግለጽ፣ ጥቃቱ ዛሬ እንዳልተጀመረና መንግሥት ችግሩን ሥርዓት ማስያዝ አቅቶት እየገነነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በወከላቸው ማኅበረሰብ ላይ የደረሱትን ጥቃቶች የማነፃፀር አዝማሚያውን ያስተዋሉ አንዳንድ የምክር ቤት አባላት የደረሰው ጥቃት ልብ የሚሰብር ቢሆንም፣ የምክር ቤቱ አባላት የተሸረበውን ሴራ በጥንቃቄ ማስተዋል እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
‹‹ስንነጋገር አንድ አካባቢን እንደወከለ የምክር ቤት አባል ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደወከለ የፓርላማ አባል መሆን አለበት፡፡ በጠላቶቻችን አጀንዳ አንሠራም፣ በተቀደደልን ቦይ መፍሰስ የለብንም፣ አንድ መሆን አለብን፤›› ሲሉ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት የተባሉ የምክር ቤቱ አባል አሳስበዋል፡፡
መንግሥት ዋነኛው ሴራ ጠንሳሽና አዝማች የሆነውን አካል ለይቶ በአሸባሪነት መፈረጅና ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ፣ የምክር ቤቱ አባልና የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ተስፋዬ ዳባ ናቸው፡፡
የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በሰጡት ማጠቃለያ አስተያየት፣ ‹‹በአመራርነት ስንሠራ አንጀታችንን አስረን ነው እንጂ የሁላችንም ስሜት ተጎድቷል፣ ልባችን ተሰብሯል፤›› ብለዋል፡፡
በዚህ ወቅት በጥንቃቄ ማስተዋል ከምክር ቤት አባላት እንደሚገባ የተናገሩት አፈ ጉባዔው፣ ‹‹ለመከፋፈል ዕድል መስጠት አያስፈልግም አንድ ሆነን በመቆም ፈተናውን ማለፍ አለብን፤›› ብለዋል፡፡
‹‹መንግሥት ምሕረት የሌለው ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጥርጥር የለውም፣ ይህንንም ምክር ቤቱ ይከታተላል፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
በዚሁ መሠረትም ምክር ቤቱ የራሱን ኮሚቴ አዋቅሮ ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ ተሰማርቶ ስለሁኔታው መረጃ አሰባስቦ ከተመለሰ በኋላ፣ ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ተጠርቶ ማብራሪያ እንዲሰጥ እንደሚደረግና ይህንንም መሠረት በማድረግ ምክር ቤቱ የውሳኔ ሐሳብ ለማሳለፍ በመግባባት፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የተደረገው በሐዘን ድባብ የተሞላ ውይይት ተጠናቋል፡፡