Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምትራምፕ እና ባይደን በ2020 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ

ትራምፕ እና ባይደን በ2020 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ

ቀን:

አሜሪካውያን ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት የሚመራቸውን በመምረጥ ላይ ናቸው፡፡ አሜሪካ ለአሠርታት አስተናግዳው አታውቅም በተባለለት ውጥረት የነገሠበት የ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕና ከተፎካካሪያቸው ዴሞክራቱ ጆ ባይደን ለመምረጥ 100 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ሪፖርተር ለኅትመት እስከገባበት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. አመሻሽ ድረስ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡

በብሔራዊ ምርጫው በአሜሪካ ፖለቲካ ከ1970ዎቹ ወዲህ ታዋቂ የሆኑት ጆ ባይደን የመሪነቱን ሥፍራ የያዙ ሲሆን፣ ወሳኝ በሆኑ ግዛቶችም ባይደን ቢመሩም ላለፉት አራት ዓመታት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በነበሩት ትራምፕና በእሳቸው በኩል ያሉት ልዩነቶች ጠባብ ናቸው፡፡

የአሜሪካ ምርጫ በአንድ ቀን ተደርጎ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ቅድመ ምርጫም ዋጋ አለው፡፡ በቅድመ ምርጫው ባይደን 52 በመቶ ትራምፕ 44 በመቶ ቢያገኙም ይህ የምርጫውን ውጤት ለማሳወቅ ላይረዳ ይችላል፡፡

- Advertisement -

በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን የአሜሪካ ግዛቶች እንደ ሕዝብ ብዛታቸው ተከፋፍለው ከያዙት 538 አጠቃላይ ድምፅ ቢያንስ 270 ድምፅ ማግኘት ይጠይቃል፡፡ ይህ የምርጫ ሥርዓት ደግሞ አንድ ተፎካካሪ በብሔራዊ ደረጃ ብዙ ግዛቶች ላይ አሸንፎ፣ ነገር ግን በርካታ ድምፅ ባላቸው ግዛቶች ላይ ከተሸነፈ እ.ኤ.አ. በ2016 ሂላሪ ክሊንተን እንደገጠማቸው ዓይነት ሽንፈት ሊገጥመው ይችላል፡፡

ትራምፕ እና ባይደን በ2020 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ

አሪዞና 11፣ ዊስኮንሲን 10፣ ሚቺጋን 10፣ ፔንሲልቪያና 20፣ ኦሃዮ 18፣ ኖርዝ ካሮሊና 15፣ ጆርጂያ 16 እና ፍሎሪዳ 29 ድምፅ በመያዝ ከፍተኛ ፉክክር የሚደረግባቸው ግዛቶች መሆናቸውን የአሜሪካ መንግሥት የምርጫ ድረ ገጽ ያሳያል፡፡

የትናንቱ ምርጫ በአሜሪካ ታሪክ ነጥብ ጥሎ እንደሚያልፍ ይጠበቃል፡፡ ሲኤንኤን እንደሚለው፣ ትራምፕ በምርጫው ካሸነፉ አሜሪካ ባለፉት 100 ዓመታት ገጥሟት የማያውቅ የጤና ቀውስ ውስጥ ትገባለች፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በኮቪድ-19 ምክንያት እየተጎዳ ያለውን ኢኮኖሚው ወደነበረበት ለመመለስ ሲሉ ሲሊንደር ላይ እሳት የማርከፍከፍ ያህል አገሪቷን ክፍት ስለሚያደርጉ ነው፡፡

ባይደን አሜሪካ ያጣችውን የመምራት ሞራል ለመመለስ እንደሚሠሩ ይጠበቃል፡፡ በትራምፕ አመራር በዘርና በማኅበራዊ ሕይወት የተከፋፈሉ አሜሪካውያንን መንፈስ ለማደስም እንዲሁ፡፡

የ77 ዓመቱ ዴሞክራት ባይደን በብሔራዊ ምርጫው በሰፊ ልዩነት እየመሩ ቢሆንም ፕሬዚዳንት ለመሆን ወሳኝ በሆኑት ግዛቶች ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ምርጫው ትናንት ይጀመር እንጂ በዕለቱ ቆጠራው ተጠናቆ ውጤት ሊታወቅ እንደማይችል የዘገበው ቢቢሲ፣ የአላስካ ግዛት ምርጫ ከሌሎቹ ባለው የሰዓት ልዩነት ምክንያት እስከ ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 25 ቀን ድረስ እንደሚሄድና በአንዳንድ ግዛቶች በመልዕክት የሚፈጸሙ ድምፆች ቆጠራ ቶሎ ላይጠናቀቅ እንደሚችልም ተገምቷል፡፡

ትራምፕና ባይደን የሚለያዩባቸው ጉዳዮች

ሚስተር ትራምፕና ሚስተር ባይደን ከሚለያዩባቸው አጀንዳዎች ሦስቱ በቀዳሚነት ይነሳሉ፡፡ በዓለም ከተከሰተ ከአሥር ወራት በላይ ያስቆጠረውና መድኃኒትም ሆነ ክትባት ያልተገኘለት ኖቭል ኮሮና ቫይረስ በሁለቱ ዕጩዎች በኩል ያለው ዕይታ የተራራቀ ነው፡፡

በኮቪድ-19 ተጠቅተው የነበሩት ትራምፕ ለቫይረሱ ይህንንም ያህል ቦታ አይሰጡትም፡፡ ሆኖም በአሜሪካ እስከ ጥቅምት 24 ቀን ድረስ 9.2 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 231,551 ሰዎች ሞተዋል፡፡

ትራምፕ ቫይረሱ በአሜሪካ መግባቱ እንደተረጋገጠ ግብረ ኃይል አቋቁመው የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ይህንን በመተው ‹‹መጠንቀቅና አገርን ለሁሉም ነገር ክፍት ማድረግ›› ወደሚለው አሠራር ተሸጋግረዋል፡፡ ለቫይረሱ ክትባትና መድኃኒት በፍጥነት እንዲሠራ በማለትም ለፕሮጀክቱ አሥር ቢሊዮን ዶላር መድበዋል፡፡ ሆኖም በአሜሪካ ሰሞኑን በቀን አንድ ሺሕ ሰው ያህል እየሞተ ነው፡፡ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ተጠቂዎችም በቀን እየተመዘገቡ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የምርጫው ዘመቻ ሚና ተጫውቷል፡፡

ሚስተር ባይደን ብሔራዊ የቫይረሱ ንክኪ ልየታ ፕሮግራም መዘርጋት፣ በእያንዳንዱ ግዛት አሥር የመመርመርያ ማዕከል ማቋቋም፣ ለሁሉም ነፃ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማድረግ የሚለውን ያራምዳሉ፡፡ ትራምፕ ቦታ የማይሰጡት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) በባይደን ትልቅ ስፍራ የተሰጠው ነው፡፡ ባይደን በመላ አሜሪካ ማስክ መደረግ አለበት የሚለውን የሚደግፉ ናቸው፡፡

በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ያላቸው አመለካከትም የተለያየ ነው፡፡ ትራምፕ  የአየር ንብረት ለውጡን ችግር ካባባሱት በቀዳሚነት የሚቀመጠውን ታዳሽ ያልሆነ ኃይል መጠቀም አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡ ፍላጎታቸውም ታዳሽ ያልሆነ ኃይልን ማስፋፋት ነው፡፡ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነትም አሜሪካን አሰርዘዋል፡፡ ባይደን ቢመረጡ በቅድሚያ ከሚሠሯቸው ሥራዎች አንዱ አሜሪካን መልሰው ከፓሪሱ ስምምነት ማስገባት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2050 አሜሪካ ዜሮ የበካይ ጋዝ ትነት እንዲኖራት ማድረግም ዓላማቸው ነው፡፡

በኢኮኖሚው ዘርፍ ሚስተር ትራምፕ አሥር ሚሊዮን የሥራ ዕድል በአሥር ወራት ለመፍጠር ቃል ገብተዋል፡፡ አንድ ሚሊዮን አዳዲስ አነስተኛ ንግዶችንም እንዲሁ፡፡ የገቢ ግብር ታክስ መቀነስ፣ ኩባንያዎች ሠራተኞቻቸውን እንዲያቆዩ የታክስ ማበረታቻ ማድረግም ይገኝበታል፡፡

ሚስተር ባይደን ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ላይ ታክስ መጨመር፣ ይህም በዓመት ከ400 ሺሕ ዶላር በላይ የሚያገኙትን ብቻ የሚመለከት እንደሚሆን አሳውቀዋል፡፡ ገቢውም የሕዝብ አገልግሎት ዘርፉን ለማስፋፋት ይውላል ብለዋል፡፡ የፌዴራል ተቀጣሪዎች ዝቅተኛ ክፍያ ላይ በሰዓት 15 ዶላር እንዲሆን ማድረግም ይገኝበታል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...