በሰሜን ወሎ ዞን ዋና ከተማ ወልዲያ በ2003 ዓ.ም. የተቋቋመው ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ካሉት ልዩ ልዩ የትምህርት ተቋማት አንዱ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ነው፡፡ አካባቢው በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ለህዋ ሳይንስ፣ ለኢነርጂ፣ ለአርቲፊሻል ኢንተለጀንትና ሮቦቲክስ ምቹ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በትኩረት እየሠራበት ይገኛል፡፡ የተቋሙን እንቅስቃሴ አስመልክቶ የኢንስቲትዩቱን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሔኖክ አዲስን ሔለን ተስፋዬ አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- የቴክኖሎጂ አንድ ክፍል የነበረውን ወደ ኢንስቲትዩት ለመቀየር እንዴት አሰባችሁ?
አቶ ሔኖክ፡- ዋናው ምክንያት የአካባቢው ሁኔታ ነው፡፡ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ እጅግ ምቹ በመሆኑ ኢንስቲትዩት እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ለምሳሌ በስፔስ ሳይንስ ላይ ማሂ ተራራ፣ አቡነ ዮሴፍ ተራራ የስፔስ ቴክኖሎጂ ላይ በሰፊው ቢሠራባቸው ምቹነት ይኖራቸዋል፡፡ በሌላ በኩል በኢነርጂ በመበልፀጉ በወልዲያና አካባቢው ኢነርጂ ከንፋስና ከፀሐይ ይገኛል፡፡ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንትና ሮቦቲክስ ወይም አዲስ ታዳጊ የሚባሉ ቴክኖሎጂዎች ላይም በሰፊው ለመሥራት ተቋም ማድረግ ይጠበቃል፡፡ በሌላ በኩል በዩኒቨርሲቲው ካሉት መምህራን አንድ ሦስተኛው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች ናቸው፡፡ በተጨማሪም ላቦራቶሪው ዘመናዊና አዲስ ነው፡፡ እነዚህን በከፍተኛ ደረጃ ምርምር ብንሠራባቸው አዋጭና ወደፊት ግቢውን በዚያ ልክ ከፍ ያደርገዋል ብለን ስላሰብን እየተጋን እንገኛለን፡፡ ከዚህ አንፃር ነው ወደ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ማሳደግ የተፈለገው፡፡
ሪፖርተር፡- የኢንስቲትዩት አደረጃጀት ምን ይመስላል?
አቶ ሔኖክ፡- ኢንስቲትዩቱ በሥሩ ያሉት አራት ትምህርት ቤቶች፣ የሜካኒካልና ኬሚካል ኢንጂነሪንግ፣ የኮምፒዩቲንግ፣ የኤሌክትሪካልና የኮምፒዩተር፣ እንዲሁም የሲቪልና ውኃ ሀብት ናቸው፡፡ እነዚህ አራት የየራሳቸው የሆነ የልህቀት ማዕከል ይኖራቸዋል፡፡ እስከዛሬ የነበረው የዩኒቨርሲቲዎች አሠራር አንድ ዩኒቨርሲቲ አንድ የልህቀት ማዕከል ለምሳሌ በግብርና ውስጥ በሰብል ልማት ካለ በዚያው ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ በቴክኖሎጂም ብዙ የትምህርት ክፍሎችንና ባለሙያ ይዞ፣ ግን አንድ የልህቀት ማዕከል ብቻ ይኖረዋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ሐሳብ አንድ የልህቀት ማዕከል በቂ አይደለም የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም የልህቀት ማዕከል ምህዳር ሲኖር በአንድና በሁለቱ ዩኒቨርሲቲው ሊታወቅ ይችላል፡፡ ነገር ግን እነዚያ የልህቀት ማዕከሎች ሲኖሩ በብዙ መንገድ ለችግሮች መፍትሔ አምጪ ይሆናል፡፡ ስለዚህ አንድ ልህቀት ማዕከል ብቻ መኖር የለበትም በማለት እየሠራን ነው፡፡ ካሉት የልህቀት ማዕከሎች ውስጥ በጣም የላቀውን የልህቀት ማዕከል ግንባር በማድረግ ሁሉም ተመጋጋቢ በሚያደርግ መንገድ እንሄዳለን፡፡
ሪፖርተር፡- እነዚህን የልህቀት ማዕከሎች አሁን የደረሱበት ደረጃ ምን ይመስላል?
አቶ ሔኖክ፡- አሁን ላይ ሰባት የልህቀት ማዕከላት ልንገነባ ነው፡፡ አርተፊሻል ኢንተለጀንትና ሮቦቲክስ፣ አድቫንስድ ማቴሪያል ሳይንስ፣ አግሪ ካልቸራል ሜካናይዜሽንና ሌሎችም የልህቀት ማዕከል ለመሥራት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ከፊዚክስ ጋር የሚሠራ ቢሆንም ከእኛም ጋር በጋራ ይሠራል፡፡ በስፔስ ሳይንስ ከዓለም የስፔስ መረጃ የሚሰበስበው ከደቡብ አሜሪካና አውስትራሊያ አካባቢ ነው፡፡ እዚህ አካባቢዎች ከነዳጅ በላይ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ናቸው፡፡ የስፔስ ሳይንስ መረጃ (ዳታ) መሰብሰብ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ በመሆኑ መንግሥት ትኩረት ቢያደርግበትና ዩኒቨርሲቲው እንደ ልህቀት ማዕከል አድርጎ ቢሠራበት ከነዳጅ በላይ ገቢ ማግኘት ይቻላል፡፡ የስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ለአምስት ዓመታት ተከታታይ መረጃ መሰብሰብ አለበት፡፡ የስፔስ ሳይንስ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ቢሠራበት የተሻለ ይሆናል፡፡ ሌላው አርቴፊሻል ያልሆኑ ነገሮች አንዱ የቅዱስ ላሊበላ ቅርስ ነው፡፡ በዚያም በቅርቡ ኢንስቲትዩት የሔሪቴጅ ኢንስቲትዩት (የቅርስ ጥበቃ ኢንስቲትዩት) የሚባል አቋቁመናል፡፡ ለጊዜው በቅርስ ጥበቃ፣ በታሪክና በቱሪዝም ላይ የትምህርት ክፍሎች ከፍተናል፡፡ ቅርሱን ከመጠበቅ አንፃር እነዚህ የትምህርት ዓይነቶች አስፈላጊ ናቸው፡፡ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን ቅርስ ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን የኪነ ሕንፃም ጭምር ነው፡፡ በተዘረጋው መዋቅር መሠረት የልህቀት ማዕከሎችን ወደ መሬት ማውረድ ያስፈልጋል፡፡ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድና የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ ሠርተናል፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ ኢንስቲትዩት ባደረጋችሁት ጉዞም ሆነ በልህቀት ማዕከል ምሥረታ እንቅስቃሴ ያጋጠማችሁ ተግዳሮት ምንድነው?
አቶ ሔኖክ፡- በኢትዮጵያ ሁለት መሠረታዊ ችግሮች አሉ፡፡ አንደኛው የመዋቅር (ስትራክቸራል) ሲሆን፣ ሌላው የበጀት ችግር ነው፡፡ ትናንት የነበረው፣ ዛሬ ያለውና ነገ የሚቀጥለው ሲታሰብ፣ ሁሉም ነገር የፈራረሰ መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው ትልቅ ሐሳብ ይዞ ዕውን ለማድረግ የሚሮጥበትን መንገድ የሚጠርግለት ሳይሆን፣ የሚገጥመው እንቅፋት የሚበዛው ነው፡፡ በእርግጥ በዩኒቨርሲቲው ያለው ከፍተኛ አመራር ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ወደፊት ይኼን መዋቅራዊ መስተጋብር ይቀጥላል ወይ? የሚለው ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ ከላይ ጀምሮ እስከ ዲፓርትመንት መምህር ድረስ ተናቦ የመሥራት ችግር አለ፡፡ ሁለተኛው በጀት እንደ አገርም እጥረት አለ፡፡ እስካሁን በዩኒቨርሲቲው የስትራክቸራልና በጀት ትልቁ መሠረታዊ ችግር ነው፡፡ በነዚህ መሠረታዊ ነገሮች በምንሠራው ልክ ይሆናል በጀት የምናስመድበው፡፡ እንዲሁም መዋቅራዊ መስተጋብሩ በሚሠራው ልክ የምናመጣው ይሆናል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ብዙ ላቦራቶሪዎችና ብዙ የተሠሩ አዲስ ነገሮች በደንብ ወደ ጥቅም ካስገባናቸው ያለውን ችግር ይቀርፋል ብለን እንጠብቃለን፡፡