Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየመንግሥት ሌቦች ጥድፊያን ማን ይግታው?

የመንግሥት ሌቦች ጥድፊያን ማን ይግታው?

ቀን:

በተቆርቋሪ የጤና ሙያተኞች

ግልጽ ደብዳቤ ለወ/ሮ አዳነች አቤቤ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ

ክብርት ከንቲባ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተሾሙ ገና የወራት ዕድሜ ያስቆጠሩ ቢሆንም፣ ከተሾሙበት ዕለት ጀምሮ እያበረከቱት ላለው ሕዝባዊ አስተዋጽኦ ያለንን አክብሮት መግለጽን እናስቀድማለን፡፡ እኛ በጤናው ዘርፍ የተሠማራን ተቆርቋሪ ሙያተኞች እንደ ከተማይቱ ነዋሪና የጤና ባለሙያ ለአገራችን ዕድገትና ብልፅግና የበኩላችንን አስተዋጽኦ እያበረከትን እንገኛለን፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እስከታች ባሉ መዋቅሮች አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተሠሩ የመዋቅር ማሻሻያ ባለፉት ዓመታት ኅብረተሰቡን ተደራጅተው ሲዘርፉና ሲያዘርፉ የነበሩ አካላት ከሞላ ጎደል የወሳኝነት ሚናቸውን ተነጥቀው  ያፈገፈጉ መሆኑ  ይታወቃል፡፡

ሆኖም ዓለም አቀፋዊ ወረርሽኝ የሆነውን ኮቪድ-19 በአገራችን በመከሰቱ ምክንያት የለውጡ መንግሥትና ሕዝብ በአመዛኙ ትኩረቱን በሽታውን መከላከልና አክሞ ማዳን ላይ በማድረጉ፣ ይህንን ክፍተት መንግሥት ጉያ ሥር ላሉ ሌቦች አመቺ መደላድልን ፈጥሯል፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት ተደራጅተው ሲበዘብዙ የነበሩ ሥነ ምግባር የጎደላቸው አንዳንድ የቀድሞ አመራሮች በዚህ ወቅት አጋጣሚውን እንደማይገኝ ዕድል በመጠቀም እንደገና የከተማችንን መንግሥታዊ ተቋማት በመቆጣጠር ሒደት ላይ መሆናቸውን እየታዘብን እንገኛለን፡፡ በዚህ አካሄድ ከቀጠሉ ከዚህ ቀደም በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ ያደራጇቸውን ሴሎችና ለውጡ የመጣባቸው ግን ከሥልጣናቸው ያልተነኩ የእነርሱ የጥቅም ተጋሪዎች የሆኑትን በመጠቀም ያጡትን የሴክተሮች የከፍተኛ የአመራርነት ሚናን መልሶ በመቆጣጠር፣ ለውጡንና ለውጡን ተከትሎ የመጡትን አበረታች ጅምሮች ወደ የመቀልበስ ተግባር እየተገባ መሆኑን በማየታችን ይህንን ግልጽ ደብዳቤ ለመጻፍ ተገደናል፡፡ ክብርት ከንቲባ፣ እርስዎም ያቀረብነውን አቤቱታ ተገቢውን ማጣራት በማድረግ የእርምት ዕርምጃ እንዲወሰድ እንደሚያደርጉ እናምናለን፡፡

ክብርት ከንቲባ፣ ሕዝባችን የለውጡን ፋይዳና ቀጣይነት ከሚለካባቸው መንገዶች አንዱና ዋነኛው መንገድ ባለፈው ሥርዓት ውስጥ አምርሮ ሲታገላቸውና ሲያነውራቸው የነበሩ በኅብረተሰቡ፣ በሴክተር መሥርያ ቤቶችና በመሳሰሉት ውስጥ የሚታወቁ ሙሰኞችና የተደራጁ የማፍያ ቡድኖች ላይ በመጣው ለውጥና በተወሰደው ዕርምጃ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ኅብረተሰቡ ያነወራቸውና ያስወገዳቸው ሙሰኞች በአንዳንድ የአዲስ አበባ የመንግሥት ሴክተር መሥርያ ቤቶች ወደነበሩበት የአመራርና የውሳኔ ሰጭነት ሚና እየተመለሱ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ይህን እውነታ በግልጽ ለማስረዳት ከዚህ በፊት የአዲስ አበባን ጤና ቢሮ ተቆጣጥሮ ሲዘርፍ የነበረን የማፍያ ቡድን ያደረሳቸውን ጉዳትና በአሁን ወቅት ወደ ቀድሞ የሥልጣን እርከንና የዝርፊያ ሚናቸው ኔትወርካቸውን በመጠቀም እንዴት እየተመለሱ እንዳለ በማሳያነት እንደሚከተለው በማስረጃ በማስደገፍ እናቀርባለን፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ ከዚህ ቀደም ከማፍያው ቡድን ጋር በነበረ አሰቃቂ ትግል ከግል ጥቅምና ሥልጣን በፊት የኅብረተሰብን ጥቅም በማስቀደም፣ በተለያዩ እርከኖች ላይ ሆናችሁ የታገላችሁ ለከፈላችሁት መስዋዕትነት በጤና ባለሙያዎች ስም እናመሠግናለን፡፡ በተጨማሪም ለሃቅ፣ ለፍትሕና ለርዕትህ ስትታገሉ ለነበራችሁና በዚሁ ኔትወርክ ቡድን በራሳችሁና በቤተሰባችሁ ላይ የተለያዩ ጥቃቶችና አደጋዎች ማለትም ከሥራ መባረር፣ ከኃላፊነት መነሳት፣ የቤተሰብ መበተን፣ ለከፋ የጤና መታወክ መዳረግ፣ ለስም መጥፋትና ለመሳሰሉት ለተዳረጋችሁ ሁሉ ያልተዘመረላችሁ ጀግኖች መሆናችሁን እንገልጻለን፡፡ ነገር ግን ሲደረግ የነበረው ትግል ከለውጡ ጋር ከሞላ ጎደል ውጤት አሳይቶ የነበረ ቢመስልም፣ በአሁኑ ወቅት የማፍያው ቡድን ወደ ቀድሞ ቦታው እየተመለሰ በመሆኑ ይህንን ለመጻፍ ተገደናል፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት ምን ዓይነት ሙስናና ብልሹ አሠራር ሠፍኖ ስለመቆየቱ ለጉዳዩ አዲስ ለሆኑ ወገኖችና ለክቡር ከንቲባ ጠቅላላ ግንዛቤ እንዲረዳ ያህል፣ በተለያዩ ጊዜያት በመገናኛ ብዙኃን የተዘገቡትን እንደ አንድ አብነት ከዚህ በታች ሊንካቸውን አስቀምጠናል፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዓይናችን ፕሮግራም ርዕስ ፈውስ የሚያሻው ፈዋሽ  ነሐሴ 11 ቀን 2010 (https://youtu.be/u_exk0y5ATw)፣ የኢትዮጵያ ቴሊቪዥን አሳሽ ፕሮግራም ርዕስ ተጠቃሚው ማነው? (https://youtu.be/6RxwfR9gB2w)፣ የኢትዮጵያ ቴለተቪዥን (https://youtu.be/HDiE0fYMYvo)፣ በተለያዩ ወቅቶች የወጡ ጋዜጦች ውስጥ አዲስ አድማስ፣ ሪፖርተር (WWW.ethiopianreporter.com/article/18510) 5 April 2000፣ ወዘተ. በተለያዩ ወቅቶች በሴክተሩ ሠራተኞች ለፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን የቀረቡ ሰነዶች፣ በተለያዩ ወቅቶች የተገኙ የኦዲት ግኝቶች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኤፍኤም ራዲዮ ስለከነማ መደብር የተላለፈ ከሐምሌ እስከ ነሐሴ 2008 የተቋሙ ሠራተኞች ምልከታ፣

በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የታዩ ብልሽቶች

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴክተር መሥርያ ቤቶች ከዚህ በፊት አንዳንድ መሪዎች የሚሾሙት ባላቸው ዕውቀትና ችሎታ ሳይሆን ለአገዛዙ ባላቸው ታማኝነትና በእከክልኝ ልከክህ ትስስር መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ አሠራር መሠረት በጤና ቢሮ አመራርነት ተሹመው በአሰቃቂ መረብ ቢሮውን በመተብተብ ተቋሙን ሲዘርፉና ሲያዘርፉ የኖሩ በአሁን ሰዓት ለውጡ የድጋሚ ዕድል ከሰጣቸው አመራሮች ጋር በመቀናጀት፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ውስጥ ከሚገኙ ኃላፊዎች አንዱ ሆነው ተሹመዋል፡፡

በሕዝብና በጤና ባለሙያዎች ቆራጥ ትግል በጎደፈ ሥነ ምግባራቸው ምክንያት ከሥልጣናቸው እንዲሻሩ ተደርገው የነበሩ አመራሮች፣ ከዛሬ ነገ ላጠፉት ጥፋቶች ለፍትሕ ይቀርባሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩ ጊዜ ጠብቀው ሲያደርጉት የነበረው ድርጊት ተረስቶልናል በሚል አድብቶ ይጠብቅ የነበረውን ኔትወርካቸውን ተጠቅመው መሾማቸው የለውጡ አንድ ተግዳሮት አደርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡

ክብርት ከንቲባ ሹመቱን አስቂኝና አስገራሚ የሚያደርገው በኢትዮጵያ ካሉ የመንግሥት ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ብቁና የተደራጀ የተማረ ማኅበረሰብ ገንብቶታል ከሚባለውና የተማሩ ኃይሎችን ለአገራችን በማመንጨት የሚታወቀው ትምህርት ቢሮ ውስጥ፣ እንደዚህ ዓይነት ግለሰቦች በፎርጅድ የትምህርት ማስረጃ (የአንድ ዓመት የሥልጠና ሰርተፊኬት ብቻ ያላቸውና ምንም ዓይነት ተጨማሪ የትምህርት ዝግጅት የሌላቸው ማስተርስ አለኝ የሚሉት ውሸትና ይህም ከዚህ በፊት የተረጋገጠ መሆኑ ይሰመርበት) የአመራርነትን ቦታ እንዲይዙ መደረጉ ነው፡፡

 የመደመር አስተሳሰብ በተለይ ለትምህርት ካለው ከፍተኛ ትኩረት አንፃር ስናየው፣ ይህ ድርጊታቸው የሚያሳየው ለውጡን ሆን ተብሎ የማቀጨጭና የማዳከም ብሎም ለውጡን እስከ ታችኛው መዋቅር እንዳይደርስ በህቡዕ ተደራጅተው እየሠሩ መሆኑንና አዲሱን ሲስተምን በመቀልበስ እንደተለመደው በቁጥጥራቸው ሥር ወደ ማድረግ እየተሸጋገሩ መሆኑን ነው፡፡ ሹመቱ ለአገራችን፣ ለከተማችን ሕዝብ፣ ለትውልድና ለዚህ አንጋፋና በምሁራን ለተሞላ ትምህርት ቢሮና ሠራተኞች የሚያስተላልፈው መልዕክት አዎንታዊ አይደለም፡፡ በፍጥነት ተጣርቶ እርምት እንዲወሰድና ለውጡን የመታደግ ሥራ እንዲሠራ ስንል እንጠይቃለን፡፡

ቡድኑ የከፍተኛ የመንግሥት አመራሮችን ስም ለሕገወጥ ተግባሩ ማስፈጸሚያነት መጠቀሙ

ከለውጡ በፊት፣ ‹‹ከከንቲባው ጋር ጓደኛ ነኝ፣ ምክትል ከንቲባው አማካሪዬ ነው›› በሚል ሰውን በማስፈራራትና በማሸማቀቅ በኔትወርክ የተሳሰረ ዝርፊያ ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ መኖራቸው ዕሙን ነው፡፡ አሁንም ከለውጡ በኋላ በተለይ  የእርስዎ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አድርገው የሾሙትን ግለሰብ ስም በመጥቀስና የተሾሙት ግለሰብ ከለውጡ በፊት የጻፉትን የሥነ ግጥም መጽሐፍ ለጤናው ሴክተር ሠራተኞች በግድ እንዲገዙ በማድረግ የዋሉላቸውን ውለታ በማስታወስ፣ ባለፉት ጊዜያት አምርረው ሲታገሉዋቸው የነበሩ ግለሰቦችን በለመዱት መንገድ በማስፈራራት ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚሁ ግለሰብ የተዋለላቸውን ውለታ በመቁጠርም ዳግም በጤናው ሴክተር ላይ እንደሚያሾሟቸው በሰፊው በጤናው ሴክተር በአደራጁት ኔትወርክ እየተነገረና የተለያዩ ዛቻዎችና ማሸማቀቂያዎች እየደረሱ ይገኛሉ፡፡

የማፊያ ቡድኑ ኅብረተሰቡ ላይ ያነጣጠረ ምዝበራዎች ጥቂቶቹ

በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ የከነማ መድኃኒት መደብሮች ለኅብረተሰቡ ጥራት ያላቸውን መድኃኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የማቅረብ ተልዕኮ ያላቸው መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ የቡድኑ አባላቶች የቦርድ ሰብሳቢና አባል በሆኑበት በእነዚያ የከነማ ፋርማሲ የዝርፊያ ዓመታት የደረሱ ጉዳቶች በተደጋጋሚ ኮሚቴ ተዋቅሮ የተጠና ነበር፡፡ የጥናቶቹ ግኝቶች እንደሚያሳዩት የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውና ምንጫቸው ያልታወቁ መድኃኒቶች በሽያጭ ላይ ይገኙ እንደነበር ነው፡፡ የቡድኑ አባላት ሥልጣናቸውን በመጠቀም አብዛኛው መድኃኒት መጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውንና  ሊያልፍባቸው ሲል ያለ ጨረታ ከግል የመድኃኒት መደብሮች እንዲገዙ በማድረግ፣ የከነማ መድኃኒት መደብሮች ጊዜያቸው ያለፈባቸውን መድኃኒቶች ማራገፊያ ተቋም አድርጓቸው ነበር፡፡ በአጠቃላይ በከተማው ሕዝብ ላይ የተበላሹ መድኃኒቶች  እንዲሸጡ በማድረግና ይቅር የማይባል ከፍተኛ ወንጀልም ፈጽመዋል፡፡ ይህ ድርጊት ከሕግ ብቻ ሳይሆን ከሞራልም አንፃር የቡድኑን ማንነት በግልጽ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ በተለያዩ ጊዜያቶች የተደረጉ ጥናቶችና የተደረሱባቸውን ግኝቶች በተመለከተ ከጤና ቢሮና ከፀረ ሙስና ተቋም ማስረጃዎችን ማግኝት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም፣ ለአዲስ አበባ ኦዲተር ቢሮ በከነማ ሠራተኞች የገቡ ማስረጃዎችን ማየት ይቻላል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኤፍኤም ራዲዮ ስለከነማ መድኃኒት መደብር በነሐሴ ወር 2008 ዓ.ም. በጋዜጠኛው የተላለፈ የሠራተኞች ምስክርነትም ከማኅደር በማስወጣት ማዳመጥ ይቻላል፡፡

ቡድኑ የከተማውን ጤና ቢሮ በተቆጣጠረበት ወቅት አባላቶቹን በተለያዩ የመንግሥት ሆሲፒታሎች ላይ የአመራርነትን ሚና በመስጠት፣ ከላይ በከነማ መድኃኒት መደብሮች ላይ ሲፈጽም የነበረውን ዝርፊያ ወደ ሆስፒታሎቹ በማዞር አስፋፍቶት ነበር፡፡ የተበላሹ መድኃኒቶችን ወደ ሆስፒታሎች ማስገባት ብቻም ሳይሆን፣ መድኃኒቶቹን ከሚገባቸው ዋጋ በላይ በመክፈልና በሆስፒታሎቹ መድኃኒት መደብሮች ውስጥ መድኃኒቶቹ ከግል የመድኃኒት መሸጫዎች አንፃር ሲለካ እንኳ፣ በአራትና በአምስት እጥፍ የተወደደና ልዩነት እንዲኖረው በማድረግ ዝርፍያ ሲፈጽሙ ኖረዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ድርጊታቸው ያንገፈገፋቸው የየሆስፒታሎቹ ሠራተኞች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በዓይናችንና አሳሽ በተሰኙ ፕሮግራሞች ላይ ሀቁን በእዚያን ወቅት ከለውጡ በፊት የማጋለጡን ሥራ የሠሩ መሆኑ ይታወሳል (ይህን ማስረጃ በቀጣዩ ሊንክ ማየት ይቻላል https://youtu.be/HDiE0fYMYvo, https://youtu.be/6RxwfR9gB2w እና https://youtu.be/u_exk0y5ATw)፡፡

በወቅቱ በቢሮው ሥር ከስድስት ቢሊየን ብር በላይ በጀት የተያዘላቸው የሆስፒታልና የጤና ጣቢያ ግንባታዎች ተግባር መኖሩ ይታወሳል፡፡ በአገራችን ደረጃ ግንባታን በተመለከተ የታዩ ሌብነቶች በቡድኑ ተፈጽመዋል፡፡ በተጨማሪም በወቅቱ የጤና ተቋማቶችን ለማጠናከር በብዙ ሚሊዮን ብሮች የሚገዙ የሕክምና መሣሪያዎች ግዥ ከተፈጸሙ በኋላ፣ ለታቀደላቸው ተቋማት ሳይደርሱ የውኃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል፡፡

ክብርት ከንቲባ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ውስጥ ዓመታዊ ወጪው ከ100 ሚሊዮን ብሮች በላየሆነ በውጭ መንግሥት የሚደገፍ ፕሮጀክት አለ፡፡ የከተማውን የጤና ሙያተኛ ማሠልጠንና አቅም መገንባት የፕሮጀክቱ ዋነኛ ዓላማው ሲሆን፣ ገንዘቡም ለዚሁ ዓላማ ማስፈጸሚያነት እንዲውል ታስቦ የተመደበ ነው፡፡ ነገር ግን ይኼው ቡድን ይህንን  ገንዘብ ከቡድኑ ጋር ግንኙነት ላለው የግል ማኅበር እንዲዘዋወር በማድረግና የቢሮው ሥልጠናዎችና ስብሰባዎች በእነሱ ጓደኞች ሕንፃ ላይ እንዲደረግ በማመቻቸት፣ ያላግባብ ከፍተኛ ሚሊዮን ብሮች እንዲባክኑ ተደርገዋል፡፡ ይህ ተግባር በቅርቡ በአዲሱ አመራር ተደርሶበት እንዲቋረጥ የተደረገ ቢሆንም፣ ጉዳዩን ተከትሎ፣ ከሕግ አንፃር ግን የተወሰደ ዕርምጃ አለመኖሩ ለተደራጁት ሌቦች የልብ ልብ ሰጥቷል፡፡

ለከተማችን አዲስ አበባ በውጭ መንግሥታትና በተለያዩ ተራድኦ ድርጅቶች አማካይነት በነፃ ሲለገሱ የነበሩ ኮንደሞችን ልክ በኤችአይቪ ጽሕፈት ቤት እንደተገዙ በማስመሰል፣ ከመንግሥት ካዝና ገንዘብ ወጪ በማድረግና ኮንደሙም ገቢ ሲደረግ ተገዝቶ እንደ መጣ  ገቢና ወጪ ደረሰኞችን በማዘጋጀት ብዙ ሚሊዮን ብሮች ሲዘርፉ ቆይተዋል፡፡ በተጨማሪም ከአንዳንድ በኤችአይቪ ላይ ከሚሠሩ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ ገንዘቦች ተመዝብረዋል (ይህን ለፀረ ሙስና ኮሚሽን በገባው ሰነድ ላይ በግልጽ ይታያል)፡፡ ከላይ የተገለጹት ዝርፊያዎች ከብዙ በጥቂቱ እንደ ማሳያ መሆኑ ይታወቅ፡፡

ከገንዘብ ባሻገር የቢሮውን የሲቪል ሰርቪስ አደረጃጀት ተገቢው የሙያ ክህሎት በሌላቸው የቡድኑ አባላት ሲሞሉት በመክረማቸው ቢሮው ዋናውን ተልእኮ ለማሳካት ከፍተኛ የሆነ የአቅም ማነስ ተስተውሎበታል (ይህንን በተገቢው ለመረዳት ሊንኩን ይጠቀሙ www.ethiopianreporter.com/article/18510)፡፡

በጤና ሚኒስቴር ውስጥ ቡድኑ የዘረጋው መረብ 

አገራችን ኢትዮጵያ በሰለጠኑበት የጤና ሙያ ኅብረተሰባቸውን በማገልገል እስከ ሕይወት ፍፃሜ ድረስ ተጋድሎ የፈጸሙ ቀናና ታማኝ የጤና ሙያተኞች ያፈራች አገር ናት፡፡ ይህም በክፍለ ዘመን ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ   በግልጽ እየታየ ይገኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በአገራችን ይህንን ወረርሽኝ በመከላከል ሕይወታቸውን ለከፈሉ እንደ ሲኒየር ፋርማሲስት አልማዝ ምትኩና ነርስ አንበሳ ውድም ዮሐንስ ነብስ ይማርልን እያልን ያለንን ከፍተኛ አክብሮት መግለጽ እንወዳለን፡፡

ኮቪድን ለመከላከል የጤና ባለሙዎች እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ የጠየቀ ተጋድሎ ሲያደርጉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በዘርፉ በአመራርነት ተቀምጠው የግል ጥቅማቸውን የሚያስገድዱ መኖራቸው አሳዛኝ ነው፡፡ በፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ውስጥ የኮቪድ ወረርሽኝን የሕክምና አገልግሎት እንዲያስተባብሩ ኃላፊነት ካለባቸው ዳይሬክቶሬቶች ውስጥ አንዳንድ ዳይሬክተሮች የተጣለባቸውን ኃላፊነት ችላ ብለው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ አፍሪካ በተባለ የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመደበኛ መርሐ ግብር ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ፡፡ ትምህርት መማር በጎና የሚበረታታ ሆኖ ሳለ የሚያሳዝነው ግን በዚህ ፈታኝ ወቅት ሁሉም ሙያተኛ የኮቪድን በሽታ ለመቆጣጠር ርብርብ ሲያደርግ፣ እነዚህ ግለሰቦች ግን በቴሊቪዥንና በስብሰባ ፊታቸውን አሳይተው የመንግሥትን የሥራ ሰዓት የሚያሳልፉት በሥራ ገበታቸው ላይ ሳይሆን ከትምህርታቸው ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በማከናወን መሆኑ ያስገርማል፡፡

በተጨማሪም በሲቪል ሰርቪሱ ሕግ መሠረት ማንኛውም ሠራተኛ በሥራ ሰዓት ሥራው ገበታ ላይ መገኘት ግዴታው ነው፡፡ እነዚህ ቡድኖች ግን የሚማሩት በመንግሥትና በሕዝብ የሥራ ሰዓትን በመጠቀም መሆኑና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም በቀን መርሐ ግብር በመንግሥትና በሕዝብ የሥራ ሰዓት የመማር ፈቃድ ያልተሰጣቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህም በሲቪል ሰርቪሱ ሕግ መሠረት ወንጀልና የሚያስቀጣ ተግባር ነው፡፡

በፌዴራል ጤና ጥበቃ ውስጥ ያለው የቡድኑ ቅርንጫፍ መነሻው ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሲሆን አሁን ያለበትን ቦታ የተቆጣጠረው ሕጋዊ አሠራሮችን በመሻርና የኔትወርኩን ጉልበት በመጠቀም ነው፡፡ ይህ ቡድን በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ውስጥ እያለ በከተማይቱ ውስጥ የሚገኙትን የመንግሥት ሆስፒታሎችን የሕክምና አገልግሎት አስጣጥን መምራትና መቆጣጠር ኃላፊነቱ የነበረ ቢሆንም፣ በወቅቱ በሆስፒታሎቹ ውስጥ ሲፈጸሙ ለነበሩ ዓይን ያወጡ ዝርፊያዎች በማስተባበርና ሽፋን በመስጠት አስተዋጽኦ በማበርከት የድርሻቸውን የሚቀራመቱ ግለሰቦች ስብስብ ነው፡፡

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት አስፈላጊ የሆነውን የሕክምና አገልግሎት የሚመሩ ግለሰብ በዚህ ደረጃ ኅብረተሰብን በመናቅ የግል ጥቅማቸውን በማስቀደም፣ የመንግሥትን የሥራ ሰዓቶች በመሸራረፍ ሕዝባችን ላይ ላደረሱትና እያደረሱት ላሉት አደጋ ሊጠየቁ ይገባል፡፡ በተለይም በሙያቸው እስከ ሕይወት መሰዋዕትነት በመክፈል ተጋድሎ ለፈጸሙትና ለመፈጸም ለተዘጋጁት ውድና ብርቅዬ የጤና ሙያተኞችን ሞራልና ሥነ ልቦና ሲባል እነዚህን ቀልደኞች ተገቢውን አስተዳደራዊ የእርምት ዕርምጃ መውሰዱ ለነገ የሚባል አይሆንም፡፡

ክብርትነትዎ የምንጠይቅዎት

በከተማችንና በሴክተራችን እውነተኛ ለውጥ ማምጣት የምንችለው ሥር ነቀል ለውጥ ሲደረግ ብቻ ነው፡፡ የቢሮውን ዋናና ምክትል ኃላፊን ብቻ መቀየር የተሟላ ለውጥ እንደማያመጣ በቅርቡ በተደረገው ሽግሽግ ማስተዋል ችለናል፡፡ የአሁኑ የቢሮው ኃላፊዎች ወደ ቢሮው ሲመጡ አዲስ በመሆናቸው የሚጠይቁትም፣ የሚያማክሩትም በሙስናና በብልሹ አሠራር የተጨማለቁና በኔትወርክ የተሳሰረውን ኃይል ነው፡፡

ይህ ኃይል ደግሞ ምንም ዓይነት አጋጣሚዎችን የግል ጥቅሙን ለማጋበስ ከመጠቀም የዘለለ ፍላጎት ያለው አይደለም፡፡ የቢሮውም የአደረጃጀት ለውጥ ሲደረግ በቢሮው ያለው የተደራጀ ኃይል እነሱ ስለነበሩ በሚፈልገው መልኩ ተጠቅመውበታል፡፡ ይህ ኃይል አጋጣሚዎችን ከራሱ ጥቅም አንፃር ብቻ የሚያይና የመጣበትም መንገድ ከትምህርት ዝግጅትና ክህሎት አንፃር ሳይሆን ለቡድኑ ዝርፊያ ባለው ታማኝነት በመሆኑ የሕዝብን የጤና ጉዳይ የማስፈጸም አቅምና ዝግጁነቱ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ይኼንን ቡድን በደንብ ለሚያውቅና አዲስ የመጡ አመራሮች ግንብ ሲገፉ ማየት እንዴት የሚያሳዝን ነው፡፡

እኛ የምንጠይቀው ቢሮው እንደ አዲስ ጠንካራ መካከለኛ አመራሮችንና በቂ የትምህርት ዝግጅት ያላቸውን ሙያተኞች ከሆስፒታል፣ ከጤና ጣቢያና ከክፍለ ከተማ በማምጣት እንደ አዲስ እንዲደራጅ ነው፡፡ ሥር ያለው ጠንካራ ሪፎርም በሴክተራችንና በከተማችን ካልተተገበረ የከተማውን መልካም አስተዳደር በተለይ በጤና ሴክተሩ ላይ የመሳካቱ ጉዳይ አጠያያቂ ይሆናል፡፡ ለውጡ እንደመጣ ሸሽተው የነበሩት ቡድኖች ሁኔታውን ካጤኑ በኋላ አደረጃጀት ወደ መቆጣጠር መሸጋገራቸው የሚያሳየን ሀቅ ይህንኑ ነው፡፡

የትምህርት ቢሮው ጽሕፈት ቤት የትምህርት ዝግጅቱና ብቃቱ በሌላቸው ሰዎች መመራት ስለሌለበት፣ በአስቸኳይ ማስተካከያ ማድረግ ትውልድን ከማዳን አኳያ በይደር የሚታለፍ መሆን የለበትም ብለን እናምናለን፡፡ በቅርቡ የፌዴራል የፀረ ሙስናና የፌዴራል ፖሊስ መሥሪያ ቤቶች እንደገለጹት፣ በተለያዩ የመንግሥት ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የተፈጸሙ ሌብነቶችን በመለየትና በማጣራት ለፍርድ እንደሚቀርቡ ነው፡፡ እንደ አንድ የጤና ባለሙያ ይህንን ጽሑፍ የጻፍነው ከላይ በተጠቀሱ መረጃና ማስረጃዎች ላይ በመንተራስ ተቋማቱ ተገቢውን እርምት ወስደው ሥራቸውን በትክክለኛ መንገድ ይፈጽማሉ በሚል ሙሉ እምነት ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡– ጽሑፉ የጸሐፊዎቹን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...