ዛሬ የምንጓዘው ከፒያሳ ሜክሲኮ ነው። ጎዳናውን ትውስታ እየናጠው ሁለትና ሦስት አሥርት ዓመታትን ተንሸራቶ ሄዶ የተካከዘ ይመስላል። እውነት ግን ከጎዳና ሌላ ማን አመጣጣችንን አብጠርጥሮ ይረዳው ይሆን? ጠመዝማዛው፣ ከፍታውና ዝቅታው ስንቱን አስገብሮ ስንቱን በአጭር እንዳስቀረው፣ ስንቱንስ ዕድሜ ቀጥሎለት ለዛሬ እንዳደረሰው ስታስቡ አይገርማችሁም? እውነት እንዳመጣጣችንና አካሄዳችን እዚህስ መድረሳችን እኮ የፈጣሪን ምሕረት በእጅጉ የሚያሳይ በተዓምር የተሞላ ነው። ጎዳናና ሕይወት መመሳሰላቸው ገዝፎብኝ በቆምኩበት ድንገት የመጣችው ታክሲ ስትቆም ዘልዬ ገባሁ። ‹‹የሞላ በበራሪ….›› እያለ ወያላው ሲጮህ አብረው የበረሩና ያልተኖሩ ዕድሜዎች በየጎዳናቸው መቅረታቸው፣ በሜዳና በሸንተረሩ መክሰማቸው ዘልቆ ልቤን ይነካው ጀመር። ‹‹ስትርቂኝ ስርቅሽ እልፍ እየተጓዝን፣ ዞረን ብንተያይ ብዙ ተዛዘብን፤›› አለ የድሮ ሰው፡፡ ድሮ ሲባል ደግሞ ድንገት ትዝታቸው ሽው የሚልብን ስንትና ስንት ነገሮች አሉ ግን፡፡ የድሮ ናፍቆት እኮ አይለቅም!
እበራለሁ ያለው ታክሲ ተገትሮ ቀረ። ‹‹ኧረ ሾፌር እንቀሳቀስ…›› ይለዋል አጠገቡ የተቀመጠ ተሳፋሪ። ሾፌሩ ባልሰማ ፊቱን አዙሮ ወያላው የማይደርስባቸውን ሥፍራዎች ሲጣራ ይስቃል፡፡ እሱ ይሳቅ ምናለበት የቸኮልነው እናራለን እንጂ፡፡ የቸኮሉ ወያላው በገባላቸው ቃል ወይም በራሪ ሲባሉ በሰሙት መሠረት ባለመሆኑ ይቁነጠነጣሉ። ወይ መብረር? ማዝገም የሚባለውንም የምታውቅ አትመስልም ታክሲዋ። ሁለት ተሳፈሪዎች ገብተው ሲቀመጡ ገና ያልተያዙ አምስት መቀመጫዎች ነበሩ። ‹‹ሾፌር እባክህ እየሄድክ ብትጭን?›› አለች አንዷ የታከታት። ዞር ብሎ አያትና፣ ‹‹እሺ ከከፈልሽኝ እሄዳለሁ…›› ብሏት ወያላውን፣ ‹‹የአምስት ሰው ተቀበላትና እንውጣ…›› አለው። ‹‹እንዴ! እንዴት ያለ ቀልደኛ ናችሁ? ራሳችሁ በራሪ ብላችሁ ደግሞ በዘገያችሁት…›› ስትለው፣ ‹‹እንኳን እኛ ፈጣኑ መንግሥታችንስ ቢሆን መቼ ባሰበው ፍጥነት መብረር ያልቻለው ለምን ይመስልሻል? ማውራትና መሥራት ስለማይገናኙ ነዋ…›› ብሏት ትንሽ መንቀሳቀስ ጀመርን። ‹‹ሰው ምነው ከመንግሥት ራስ አልወርድ አለ?›› ቢል አንዱ ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹ምናልባት መንግሥት በቃሉ አልተገኘ ይሆናላ!›› ብሎ እንደ ውጭ ዜጋ አስተያየት ሲሰጥ ሰማሁት። ወይ አሽሙር አትሉም!
ታክሲዋ በስንት ልምምጥና ጉትጎታ መንቀሳቀስ ጀመረች። ሾፌሩ ለምን ተናገራችሁኝ ዓይነት ንፍትፍት ብሎ አጓጉል እየሆነ ያሽከረክር ጀምሯል። ‹‹አሁንስ መናገር የእሳት ላይ ቤንዚን ሆነ…›› አለ አንዱ ምን መከራ ነው የመጣብን ዓይነት ትክት ብሎ። ‹‹አይበልና ግን አሁን…›› አለ አንዱ ወግ አዋቂ መሳይ ጎልማሳ፡፡ ‹‹በዚህ ቀዥቃዣ ሾፌር ሰበብ እዚሁ ጭጭ ብንል የት አቤት ይባላል?›› አለ እንደ ቀልድም እንደ ምርም የሆነ ፊቱን እያሳየን። ‹‹እንግዲህ ካለቀልን ወዲያ የት አቤት ይባላል?›› ብሎ አንዱ ጣል አደረገበት። ‹‹ማለቴ ይህችም ኑሮ ሆና ሲኖሩ ቆይተው በመኪና አደጋ ሞቱ ነው የሚባለው? ወይስ ለመኖር ሲሉ በመኪና አደጋ ተሰው ነው የሚባልልን?›› ቢል ፈገግ እያልን አየነው። ወዲያው ወያላው፣ ‹‹በሞት ላይ ማሟረት ደግ ባይሆንም፣ ከመሞት መሰዋት ከዓመት ዓመት እንድትታወስ ያደርጋልና እሱ ሳይሻል አይቀርም…›› አለውና ዞሮ ብሩን ይቆጥር ጀመር። በቆጠረው ብር ልክ ቀኑን በአግባቡ ቢጠቀም የት በደረሰ ነበር እያልኩ ሳስብ አንዱ ከኋላዬ፣ ‹‹ወይ የገንዘብ ነገር ሰው የራሱ ያልሆነውን በስስት ሲቆጥር እንዴት ያምርበታል ጎበዝ!›› ብሎ አሳቀን። ‹‹የሰው ወርቅ አያደምቅ›› ነው እንጂ ነገሩ!
ጉዟችን እንደ ቀጠለ ነው። ወያላው ሒሳብ ይቀበላል፣ መልስ ይመልሳል። በተቻለው መጠን ከተሳፋሪዎች ጋር ጭቅጭቅና ንትርክ ላለመፍጠር የሚጥር ይመስላል። ድንገት ከፊቴ የተቀመጡ ሁለት ጓደኛሞች ይህን ሲያወሩ ሰማኋቸው። ‹‹ሰማኸኝ ወይ?›› አለው አንደኛው። ‹‹ምኑን?›› ብሎ ጠየቀው። ‹‹እንጃ ትናንት ያንን ጥሬ ሥጋ ከበላሁ በኋላ ሆዴ ልክ አይደለም…›› አለው ሆዱን እያሻሸ። ‹‹ምነው ያንን የመሰለ የሐረር ሰንጋ ጮማና ብሩንዶ ሰበብ ማድረግ የለብህም። ምናልባት ዞር ብለህ የቀላቀልክበት ሌላ ነገር ይሆናል እንጂ…›› ብሎ ይቀልድበት ያዘ። ‹‹አንተ ደግሞ ቁምነገር ሲያወሩህ ትቀላቅላህ…›› ቢለው ሕመሙን እያሰበ ተጨንቆ፣ ‹‹ታዲያ ብቀላቅልስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ልጆች የተሰውለት ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ነው እኮ። እኔ ምለው ምናለበት በግልጽ ከዓባይ ጋር አብራችሁ ልትገድቧቸው ያሰባችኋቸውን መብቶች ብታሳውቁን?›› ዓይል መሰላችሁ በምፀት እያየው? ወዲያው ያኛው ተቀበለና፣ ‹‹ለእሱም መዋጮው ይከብዳችኋል ብለን ነዋ…›› ሲለው ተሳሳቁ። የሰማን እንዳልሰማን ሆነን ወደ ልቦናችን ሮጥን። ‹‹ዘመድ ከዘመዱ አህያ ካመዱ፣ ምንም ቢባባሉ ጥርስ አይሳበሩ…›› ብለን ብናልፋቸውስ፡፡ ያውም ጠላት በቀላ ዓይኑ እያፈጠጠ ነዋ!
ሾፌሩ አሁንም ትኩረታችንን ነፍገነው አርፈህ ንዳ ያልነው ይመስል ከነከነው። ሙዚቃውን ያለ ቅጥ ከፍቶ ይበጠብጠን ጀመር። ‹ኧረ ሾፌር ስለጉልበትህ አምላክ ብለህ ቀነስ አድርገው?› አሉት ሁለት ወጣት ተሳፋሪዎች እየተቀባበሉ። እሱ ምን በወጣው! ያልሰማ መስሎ ራሱን እየነቀነቀ ታክሲዋን ያስፈተልካታል። ባዶ መጯጯህ መሆኑን የታዘበ አንድ ተሳፋሪ፣ ‹‹እሱ ምን ያድርግ እሾህን በእሾህ መሆኑ እኮ ነው። በአሁን ጊዜ እኮ ጩኸትን በጩኸት፣ ጉልበትን በጉልበት ካልሆነ መከባበርና መቻቻል እየራቀን መጥቷል…›› ብሎ ተናገረ። እየሰሙ እንዳልሰሙ የሚሆኑት በዝተው ያሰለቹት የመሰለ አንድ ጎልማሳ ደግሞ፣ ‹‹ለጊዜው ነው እንጂ ጩኸቱ የሚያይለው፣ ለጊዜው ነው እንጂ እርግጫው የሚጎዳው….›› እያለ ደረደረልን፡፡ ክራር መቃኘት ነው የቀረው!
የታክሲዋ እረፍቶች ወራጅና ተሳፋሪ ብቻ ናቸው። ወያላው አውርዶ ሲጭንና ጭኖ ሲያወርድ ምንም መሰልቸትና መታከት አይታይበትም። ለነገሩ እንዴት ይታይበት ኖሯል? አንዳንዱን ተግባርና ሐሳብ ለምደነው ምን አታካች ቢሆን ሳይታወቀን ዕድሜያችንን እንጨርስበት አይደል እንዴ? ሲቆይ እየለመድነው እኮ ዛሬ የአገር ነቀርሳ የሆነብን ስንቱ ነው? ሙስና፣ ምቀኝነት፣ የሥልጣን ጥማት፣ አፍራሽነት፣ ጠባብነት፣ ጽንፈኝነት፣ ንፉግነት፣ ወዘተ ኧረ ስንቱ። መያዣ መጨበጫ ያጣው ነገር ሁሉ ከልምድ የተወለደ መሆኑን ሲታሰብ ጭንቅ ይለን ይጀምራል። ልምድ እንዴት ያለው ክፉ ነው እናንተዬ!
አንዲት እናት ታክሲዋን አስቁመው ተሳፈሩ። ከገቡ በኋላ ወበቁን እያማረሩ ልብሳቸውን ያራግቡ ጀመር። ‹‹ይሞቃል አይደል?›› አለ ወያላው። ‹‹ውይ… ውይ… ያውም በጥቅምት እንዲህ ያለ የቀትር ፀሐይ?›› እያሉ አሁንም ቁና ቁና መተንፈሳቸውን ቀጠሉ። ‹‹አዎ ጥቅምት ምሽቱ እንጂ ቀኑ ድሮም ሞቅ ያለ ነው። አይደል እንዴ?›› አላቸው አጠገባቸው ያለው ጎልማሳ ደግሞ። ዞረው በፈገግታ ቃኙት። ነገረኛ እንደ ከበባቸው ሲረዱ እሳቸውም አንደበታቸውን ይቃኙ ጀመር። ‹‹ወይ የዛሬ ልጆች?›› ብለው፣ ‹‹እሱማ ፀሐይ የወጣልን እኮ ክረምት አልቆ በጋ ሲገባ ነው። እሱ በቃችሁ ያለን ይመሥገነውና። ብቻ ያዝልቅልን…›› ብለው ትንሽ ዝም ሲሉ ወያላው፣ ‹‹አዎ ያዝልቅልን የኑሮ ውድነቱን፣ ሥራ አጥነቱንና የመልካም አስተዳደር ዕጦቱን ይቅረፍልን፡፡ የታክሲ ታሪፍ ደግሞ ይጨምርልን…›› አለ፡፡ የአጉል ብልጠት መጨረሻው ድሮስ እንዲህ አይደል!
በግርምታችን መሀል ጥያቄ ሰማን። ጥያቄውን የምታነሳው ትንሽዬ ሕፃን ልጅ ናት። ‹‹ማሚ! ማሚ! ለምንድን ነው የምትስቂው?›› ብላ ጠየቀቻት። እኛም ለምን እንደ ሳቀች እንዴት እንደምታብራራላት ለማወቅ ቸኩለን ጆሯችንን ቀስረናል። እናትየዋ ጥያቄው እየበረታባት መጣ። ‹‹ለምንድን ነው የሳቅሽው ንገሪኝ?›› አለቻት። እናት እንዴት አድርጋ ልትነግራት እንደማትችል ስለገባት፣ ‹‹ይኼ ለአንቺ አይሆንም ስለኑሮ ውድነት ነው…›› ብላ መለሰችላት። ልጅቷም ትንሽ ስታስብ ቆይታ፣ ‹‹ታዲያ ኑሮ ከተወደደ መናደድ እንጂ ምኑ ያስቃል?›› ስትላት ታክሲዋ በሳቅ ማዕበል ተናወጠች። አጠገቤ ያለች አንድ ሸጋ ወጣት፣ ‹‹አይ ልጅ መሆን እቅጩን በግልጽ ያናግራል…›› ስትለኝ ብሰማትም ሳልመልስላት ቀረሁ። ‹‹እንደ ሕፃናት ካልሆናችሁ መንግሥተ ሰማይ አትገቡም፤›› ያለው ክርስቶስ ያስደንቃል እኮ፡፡ ስንት ተዓምራት አሉ መሰላችሁ!
ከሳቃችን አረፍ ብለን በዝምታ ወደ ራሳችን ስንተነፍስ አሁንም ሾፌሩ ከጨዋታችን እንዳልተቀላቀለን ታዘብኩ። እስካሁን እንዳኮረፈን ቀጥሏል። አንዳንዱን ሲያስችለው! ይኼኔ አንዱ እንዲህ ጨዋታ ጀመረ፣ ‹‹እኔ የዚህ ዘመን ነገር በጣም አሳስቦኛል:: ኧረ ለመሆኑ እንዲህ እርስ በርስ ተጠማምደን ምን ልንሆን ነው?›› ብሎ ጠየቀ። ይኼኔ አንዱ ተቀብሎ፣ ‹‹አልሰሜን ግባ በለው! እርስ በርስ በነገር መወጋጋትና መናጨት ለዘመናት የሠለጠንበት ትልቁ ሙያችን መሆኑን አታውቅም እንዴ?›› ብሎ ጥያቄውን በጥያቄ መለሰለት። ደግሞ ሌላው ተነሳ፣ ‹‹እውነት ለመናገር እኮ እርስ በርስ ብንናጀስም ራሳችንን ለጠላት ጣልቃ ገብነት የማጋለጥ ታሪክ እንደሌለን ልቦናችን ያውቀዋል…›› ብሎ ሳይጨርስ በእንጥልጥል ተወው። በእንጥልጥል የተተወውን ነገር ብዛት ስናስብ ሌላ ራስ ምታት ባይጀምረን አይገርምም!
መውረጃችን ሲቃረብ ጭራሽ የሾፌሩ ኩርፊያና ንጭንጭ እየባሰበት ሄደ። ‹‹ለመሆኑ…›› አለ አንዱ ተሳፋሪ አጠገቡ ተቀምጦ፣ ‹‹እንዲህ ከሰው ሁሉ ጋር ተናጅሰህ ትችለዋለህ?›› ብሎ ጠየቀው። ይኼኔ ሙዚቃውን ቀነስ አድርጎ አተኩሮ እያየው፣ ‹‹ሰው እኮ ምሥጋና የማያውቅ ሆነ እኮ። እርሜን ያለ መስመሬ ለእነሱ ብዬ ብጭን ሲያጣድፉኝ አታይም እንዴ? ይኼው እስካሁን ሳልሞላ ነው የመጣሁት…›› ብሎ ዞረና ገልመጥ አደረገን። ሴትየዋ ቀበል አድርገው፣ ‹‹አይዞህ እኛም ያለ አንተ፣ አንተም ያለ እኛ የትም አንደርስ። በአገር ደረጃም ቢሆን ሕዝብ ያለ መሪው፣ መሪው ደግሞ ያለ ሕዝቡ የተለየ ኑሮ አለው እንዴ? ሁለቱ ድርና ማግ ሆነው ካልተቀራረቡና ካልተግባቡ ሁሉም ነገር እየቀዘቀዘ ታሪክ ይሆንና ትዝታ ሆኖ ያርፋል። ስለዚህ ራስን ከሰው ጋር ማቀራረብ፣ ማቻቻልና ጉድለትን መድፈን ነው መፍትሔው። አይመስልህም?›› ሲሉት መቼስ የእናት ምክር ሆኖበት ነው መሰል፣ ‹‹ልክ ነው እሱስ!›› ብሎ ተቀበላቸው። ‹‹ታሪክ ትዝታ እንዳይሆን›› ያሉት ልቤን ነካው፡፡ ‹‹ታሪክ ሠሪው ሰፊው ሕዝብ ነው›› የሚባለው መፈክር ተረት በሆነበት ዘመን እንዲህ ዓይነቱ ምክር ይመቻል፡፡ ‹‹ጆሮ ያለው ይስማ›› እንዲሉ! መልካም ጉዞ!