Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአስቀጣሪ ኤጀንሲዎች በደል የተማረሩ ሠራተኞች መፍትሔ ካላገኙ ሠልፍ ለመውጣት እንደሚገደዱ አስጠነቀቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በኩል ተቀጥረው በተለያዩ ተቋማት እያገለገሉ የሚገኙ በርካታ ዜጎች በየጊዜው የሚደርስባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተባባሰ በመምጣቱ፣ መንግሥት በሁለት ሳምንት ውስጥ ተጨባጭ መፍትሔ ካልሰጣቸውና የተጠራቀመ ችግራቸውን ካልፈታላቸው ለተቃውሞ አደባባይ እንደሚወጡ አሳሰቡ፡፡

  በኤጀንሲዎቹ የሚፈጸሙ በደሎች ሊገቱ ባለመቻላቸው፣ የሠራተኞቹ ተወካዮች ከኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ጋር በመነጋገር የአቋም መግለጫ አውጥተዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ከተካሄደው ምክክር በኋላ በወጣው የአቋም መግለጫ መሠረት፣ መንግሥት አስቸኳይ መፍትሔ የማስቀመጥ ግዴታ እንዳለበት ጥሪ ቀርቦለታል፡፡

በአስቀጣሪ ኤጀንሲዎች በኩል በሚቀጠሩ ሠራተኞች ላይ ይፈጸማል የተባለው የመብት ረገጣ እንዲቆም በተደጋጋሚ የቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ባለመገኘታቸው ተበዳዮቹ የማያቋረጥ አቤቱታቸውን አሁንም ድረስ ለማሰማት መገደዳቸውን ተወካዮቻቸው አስታውቀዋል፡፡

በቱሪዝም፣ ሆቴሎችና ጠቅላላ አገልግሎች ሠራተኛ ማኅበራት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን በኩል ለመንግሥት እንዲደርስላቸው ያወጡት የአቋም መግለጫ ዓርብ ጥቅምት 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በደብዳቤ እንዲደርሰው ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር ከፌዴሬሽኑ ባገኘው መረጃ መሠረት፣ በኤጀንሲዎች በኩል እየተፈጸመ ያለው ድርጊት በኢሠማኮ በኩል ተገምግሞ መንግሥት ዕርምጃ መውሰድ እንዳለበት በመታመኑ፣ የዘርፉን ሠራተኞች መብት እንዲያስጠብቅ ጥሪ የተላለፈበት መልዕክት ለመንግሥት ቀርቦለታል፡፡

በሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የሚደርሰውን የመብት እረገጣ ለማስቆምና ለመፍታት ጥረት አለመደረጉን በመጥቀስ፣ ችግሩ መንግሥት ተገቢውን የማስተካከያ ዕርምጃ ባለመውሰዱ ምክንያት እየተባባሰ የመጣ የመብት ጥሰት እንደሆነ የሠራተኞቹ ማኅበራት ፌደሬሽን ባወጣው መግለጫ አስፍሯል፡፡

የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በአገሪቱ ሕገ መንግሥት የተደነገጉ መብቶችን እየተጋፉ እንደሚገኙ ማሳያ ከተደረጉ ነጥቦች መካከል በሰው መነገድ ክልክል እንደሆነ የሰፈረውን ይጠቅሳሉ፡፡ በሥራና ሠራተኛ አዋጅም ስለ ሠራተኛና ስለ ግል አገልግሎት ያስቀመጠውን በመተላለፍ ኤጀንሲዎቹ በሠራተኞች ላይ ሕገወጥ የጉልበት ብዝበዛ እያካሄዱ እንደሚገኙ ፌደሬሽኑ ይገልጻል፡፡ ‹‹ዘመናዊ ባርነት እየተካሄደ ነው›› በማለት ፌደሬሽኑ ባወጣው የአቋም መግለጫ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

ኤጀንሲዎች ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቀርቦላቸው ምላሽ ከመስጠት ይልቅ፣ የመብት ረገጣም ሆነ የባርነት ያህል አስከፊ የሆነው ተግባራቸው አጠናክሮ እንደመጣ በማስታወቅ፣ ይህ ድርጊት እንዲቆም ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ ባለመቻሉ ፌዴሬሽኑና አባላቱ ተቃውሟቸውን በሠልፍ አደባባይ ወጥተው ለመግለጽ እንደሚገደዱ አስጠንቅቋል፡፡

‹‹መንግሥት በኤጀንሲዎች በኩል ተቀጥረን የምንሠራ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሠራተኞችን ችግር ሰምቶ ተገቢውን ሕጋዊ አሠራር እንዲያሰፍንልንና መፍትሔ እንዲሰጠን እንጠይቃለን፤›› በማለት ፌደሬሽኑ በአቋም መግለጫው አመላክቷል፡፡ በአቋም መግለጫው እንዲፈጸሙ ከተጠየቁ ነጥቦች መካከል፣ የኤጀንሲ ሠራተኞች እንደማንኛውም የአገሪቱ ሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞች በሕገ መንግሥቱና በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ የተሰጣቸው መብት እንዲከበርላቸው፣ በነፃ የመደራጀትና የመደራደር መብታቸው ካለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲከበርላቸው የሚለው ይገኝበታል፡፡  

እንዲሁም ከታኅሳስ ወር 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣው መመርያም እንዲከበር ተጠይቋል፡፡ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በአገር ውስጥ የሥራ ሥምሪት አገልግሎት ስለሚሰጡበት አግባብ የሚደነግገው መመርያ በቀጣሪዎች እንዲከበር ማኅበራቱ ጠይቀዋል፡፡ መመርያው ኤጀንሲዎቹ ከቀጣሪ ድርጅት ጋር በሚፈጽሙት የአገልግሎት ውል ስምምነት ውስጥ ለሠራተኛው ከሚከፈለው ጠቅላላ ከፍያ ላይ ከ80 በመቶ ያነሰ መክፈል እንደሌለባቸው ያስቀምጣል፡፡ ኤጀንሲዎች ግን ይህንን በመተላለፍ የመመርያውን ድንጋጌዎች እየጣሱ በመሆናቸው፣ በሕግ የተቀመጠው የሥራ ክፍያ  መመርያው ከወጣ ከታኅሳስ ወር 2012 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲከፈላቸው የሠራተኞቹ ፌዴሬሽን አሳስቧል፡፡

መንግሥት የሚያወጣቸው ሕጎች ሥራ ላይ እንዲውሉና የማስፈጸም ኃላፊነት የተጣለባቸው አካላትም ግዴታቸውን እንዲወጡ ተጠይቀዋል፡፡ በሁሉም ኤጀንሲዎች ችግር ባይኖርባቸውም፣ በአንዳንዶቹ ሥር ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች ለተመሳሳይ ሥራ የሚከፈላቸው ክፍያ ላይ ልዩነት ሲደረግ እየታየ ነው፡፡ በሕጉ መሠረት ግን ለተመሳሳይ ሥራ ያለምንም ልዩነት እኩል ክፍያ መክፈል እንደሚገባ ተጠይቋል፡፡  

በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ መሠረት የሥራ አካባቢ ለጤንነትና ለደኅንነት ሥጋት መሆን እንደማይኖርበት ተቀምጧል፡፡ ሠራተኞች በቀን ለስምንት ሰዓት፣ በሳምንት ከ48 ሰዓት ለማይበልጥ ጊዜ መሥራት እንዳለባቸው በአዋጅ ቢደነገግም እየተተገበረ አይደለም፡፡  አንድ ሠራተኛ በወር እስከ 192 ሰዓት መሥራት ሲጠበቅበት ኤጀንሲዎች ግን ከ240 ሰዓት በላይ እንዲሠራ እያስገደዱት ይህ ሕገወጥ ተግባራቸው ተመልካች እንዲያገኝ፣ ሕጉም አስፈጻሚና ተቆጣጣሪ እንዲኖረው ኢሠማኮና በሥሩ የሚገኘው ፌዴሬሽን ጠይቀዋል፡፡

እንዲህ ያሉት ሕገወጥ ተግባራት እንዲቆሙ ያሳሰቡት እነዚህ አካላት፣ ያስቀመጧቸው የመብት ጥያቄዎች በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ በሕጉ መሠረት ምላሽ እንዲያገኙ ቀነ ገደብ አስቀምጠዋል፡፡ ሕግ በማያከብሩ ኤጀንሲዎች ላይም ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቀዋል፡፡

ጥያቄዎቻቸው ካልተመለሱ ግን ‹‹ለኮሮና የሚደረገውን ጥንቃቄ ባከበረና መንግሥት በሚፈቅደው መሠረት ብሶታችንን በሰላማዊ ሠልፍ ለመንግሥትና ለሕዝብ ለመግለጽ ወስነናል፤›› ያሉ ሲሆን፣ ሰላማዊ ሠልፉን ለማካሄድ የቱሪዝም፣ የሆቴሎችና የጠቅላላ አገልግሎት ሠራተኛ ማኅበራት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽንና ኢሠማኮ እንደሚያስተባብሩት አስታውቀዋል፡፡ የአቋም መግለጫው ለመንግሥት አካላት መድረሱን፣ ኢሠማኮና ፌዴሬሽኑም ክትትል እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሥራና ሠራተኞች ኤጀንሲዎች በኩል የሚቀጠሩ ሠራተኞች በመንግሥትና በግል ተቋማት እንዲሁም በኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ ናቸው፡፡ በጥበቃ ሥራ፣ በፅዳት፣ በሾፌርነትና ተላላኪነት፣ በኦፕሬተርና በመሳሰሉት  መስኮች የተሰማሩ ይገኙበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች