Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ኢትዮጵያ 2050›› የ30 ዓመታት መፍትሔ የተለመ የምሁራን ስብስብ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከምሕንድስና፣ ከኢኮኖሚ፣ ከግብርና ብሎም ከልዩ ልዩ አካዴሚ በተለይም ከሳይንስ፣ ከቴክኖሎጂና ከማኅበረሰብ ጥናት ዘርፎች በሙያቸው አማካይነት የተሰባሰቡ ምሁራን ለመጪዎቹ ሰላሳ ዓመታት የኢትዮጵያን ግዙፍ ችግሮችና መልካም ዕድሎች በመቃኘት የመፍትሔ ሐሳቦችን የሚያመላክቱበት መድረክ እየፈጠሩ ነው፡፡

‹‹ኢትዮጵያ 2050›› የሚል መጠሪያ የተሰጠውን ዓላማ በማነሳሳት ‹‹ብሉ ሪባን ፓናል›› የተሰኘው የምሁራን ቡድን ከወራት በፊት ጉባዔውን በአዲስ አበባ አካሂዶ ነበር፡፡ በጉባዔው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሁራን በአገር ካሉት ጋር ተጣምረው የሚንቀሳቀሱበት ‹‹ኢትዮጵያ 2050›› መድረክ ትላልቅ ፈተናዎችና መልካም አጋጣሚዎችን በመተንተንና መፍትሔ በማስቀመጥ የሚንቀሳቀስ ገለልተኛ አካል ነው፡፡

ብሉ ሪባን ፓናል የገለልተኛ ባለሙያዎች ስብስብ በመሆን ሲያስፈልግ በመንግሥት ተሰይሞ፣ ግን ደግሞ ገለልተኛነቱንና ነፃነቱን አስጠብቆ ሊንቀሳቀስ የሚችል የባለሙያዎች ስብስብ እንደሆነ፣ የዚህ ዓይነቱ ስብስብ መነሻ ከሆነው የአሜሪካ እንቅስቃሴ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በአሜሪካ የሰማያዊው ሪባን ኮሚቴ ወይም ፓናል ወይም ኮሚሽን እየተባለ የሚጠራ የተለዩ ባለሙያዎች ስብስብ በአንድ የተወሰነ ጉዳይ ላይ ጥናትና ምርምር እንዲያደርጉ መሰባሰባቸው የተለመደ ነው፡፡

እነዚህ ባለሙያዎች የፖለቲካ ተፅዕኖ ሳይኖርባቸው የመንቀሳቀስ ነፃነት ያላቸው ሲሆኑ፣ መንግሥትም ገለልተኛነታቸውን መሠረት ያደረገ የትንታኔና የጥናት ሥራ እንዲሠሩ ሊመድባቸው ይችላል፡፡ በአሜሪካ ተሞክሮ፣ የ‹‹ዋረን ኮሚሽን›› በመባል የሚታወቅ ገለልተኛ መርማሪ አካል ተመሥርቶ ነበር፡፡ ይህ ኮሚሽን የፕሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲን ግድያ እንዲመረምር የተመሠረተ ነበር፡፡ የአሜሪካውን የሽብር ጥቃት ማለትም 9/11 የሚመረምር፣ 9/11 ኮሚሽን የተሰኘ መርማሪ አካል ተመሥርቶ፣ በኢትዮጵያ ሚሊኒየም መባቻ የተሰነዘረውን የአሸባሪዎች ጥቃት መርምሯል፡፡ ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህም ያለፉ ሰፋፊ አገራዊ አጀንዳዎችን እየቃኙ ያጠኑ፣ የመረመሩና አቅጣጫ ያመላከቱ ኮሚቴዎች ወይም የባለሙያዎች ስብስቦች ሙያዊ ምክረ ሐሳቦችን ሲያቀርቡ ኖረዋል፡፡ በኢትዮጵያም የዚህ ዓይነት አካሄድ ያለው የ‹‹ብሉ ሪባን ፓናል›› እንቅስቃሴ ከጀመረ ሰነባብቶ፣ ትልቅ ጉባዔም ዘርግቶ የወደፊት የሥጋትና የልማት መንገዶችን እያጠና ምክር ማቅረብ ጀምሯል፡፡

ቅዳሜ ጥቅምት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ስለ ፓናሉ እንቅስቃሴዎች የሚያስረዳ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡ የፓናሉ ሰብሳቢዎችና የ‹‹ኢትዮጵያ 2050›› አራማጆች እንደሚሉት፣ የ30 ዓመታቱ ጉዞ፣ የሚቃኝባቸውን አሥር ዋና ዋና የትኩረት መስኮች አስቀምጠዋል፡፡ የሕዝብ ፈጣን ዕድገት በኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ አስመልክቶ ሊከሰቱ የሚችሉትን ታላላቅ ተግዳሮቶችና በተጓዳኝም መልካም አጋጣሚዎችን በማጤን የረዥም ጊዜ መሠረታዊ መፍትሔዎችን አሥር የትኩረት አቅጣጫዎች አካታች ዕምርታዊ ሽግግር ለማድረግ አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር በግብዓትነት የታቀደ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ ነው፡፡

ሰማያዊው ቡድን ወይም ብሉ ሪባን ፓናል የለያቸው አሥሩ ፈታኝ ተግዳሮቶች በማለት የለያቸው የምግብ ዋስትና የንፁህ ውኃ አቅርቦትና ፍትሐዊ የውኃ ሽፋን፣  አስተማማኝ የኃይል ዋስትና፣ ተደራሽ የጤና እንክብካቤ፣ የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን መሠረተ ልማት መስፋፋት (ዲጂታል ኢኮኖሚ) ከፍተኛ ማኑፋክቸሪንግየተፋጠነ የከተሞች ዕድገት ትምህርት፣ የሠራተኛው ኃይልን ማሳደግና በውሳኔ አሰጣጥ ተሳታፊነት ማጠናከርየትራንስፖርት መሠረተ ልማት፣ ዘላቂነትና አካባቢያዊ ደኅንነትን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በመፍትሔ አቅጣጫነት ምሁራኑ ያሰቀመጧቸው ሐሳቦችም ተመላክተዋል፡፡ ከከተሜ መስፋፋት እስከ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለው የከተማ ነዋሪነት መስፋፋት የውኃምግብጤናኃይል ተዛምዶና ተደጋጋፊነት የኢኮኖሚ ዕድገትየተቋማትና የማኅበረሰብ ልማት የፆታ እኩልነት ናቸው፡፡

እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ተብላልተው፣ ኢትዮጵያ በመጪዎቹ 30 ዓመታት ውስጥ ከሰሃራ በታች አገሮች ይልቅ የተሻለ ኢኮኖሚ የሚኖራት ታላቅ ኢትዮጵያን አሻግሮ የሚያየው የባለሙያዎች ቡድን አባላት ሰፊ የጥናት ውጤቶቻቸው የተካተቱበትን ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ይህ የምሁራኑ ስብስብ ከወራት በፊት ባካሄደው የኢትዮጵያ 2050 ጉባዔ ወቅት ከ450 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሙያዎች ታድመውበታል፡፡ የጥናት ጽሑፎቻቸውን አቅርበው ተወያይተዋል፡፡ የጉባዔው ጥናታዊ ጽሑፎችና ምልከታዎችም በጥራዝ ተሰንደው ለመንግሥት ተሰጥተዋል፡፡

ባለፈው ዓመት የተመሠረተው ሰማያዊው ቡድን፣ በኒውዮርክ ሲቲ ዩኒቨርሲቲ ታላቅ ዕውቅና የተቸራቸውና በፕሮፌሰርነት እያገለገሉ የሚገኙት ደብረ ወርቅ ዘውዴ (ዶ/ር) በእሳቸው የሚመራው ዓለም አቀፉ የኢትዮጵያ 2050 ቡድን፣ 11 አባላት ያሉትና ተጨማሪ 45 ባለሙያዎችን በማሳተፍ የብሉ ሪባን ፓናል የጥናት ውጤቱን ለመንግሥት አስረክቧል፡፡ የኢትዮጵያውን ክንፍ የሚመሩት ደግሞ ተስፋዬ ወርቅነህ (ኢንጂነር) ናቸው፡፡ የፓናሉ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ በምሕንድስናው መስክ በተለይም በመንገድ ሥራ የበርካታ ዓመታት ተሞክሮ አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ መሐንዲሶች ማኅበርንም በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ ቆይተዋል፡፡

ኢትዮጵያን በ30 ዓመታት ውስጥ በኢኮኖሚና በቴክኖሎጂ የዳበረች ታላቅ አገር ሆና የማየት ትልም ያስቀመጠው ይህ የባለሙያዎች ቡድን፣ ከ30 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር አሁን ላይ 115 ሚሊዮን እንደደረሰ ከሚገመተው በላይ እ.ኤ.አ. በ2050 ከ205 ሚሊዮን በላይ እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡ ይህ በመሆኑም በከተማ አኗኗር፣ በምግብ አቅርቦት፣ በሕክምና፣ በትምህርትና በሌሎችም አቅርቦቶችና ፍላጎቶች ላይ የሚያሳርፋቸውን ጫናዎች መሸከም የሚችል ትልቅ ኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ መሠረት መገንባት ወሳኝ እንደሆነ ምሁራኑ እየመከሩ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች