Friday, June 9, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሊመጣ ከሚችል የኬሚካል አደጋ የሚታደግ ባለቤት አለን?

በበላይ ወልደየስ (ፕሮፌሰር)

ሰው ልጅ ለመኖር አየር፣ ውኃና ምግብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ በአሁኑ ጊዜ ዘመናዊ ኑሮ ለመኖር የኬሚካል ምርቶች በተጨማሪ ያስፈልጉታል፡፡ በኬሚካል አፀግብሮት (Reaction) በአብዛኛው ካርቦንና ሃይድሮጂን (Hydrocarbon) አዘል ንጥረ ነገሮች የሆኑትን ኬሚካሎች ላይ ለውጥ በማድረግ በአካባቢያችን በአሁኑ ጊዜ ዕለት በዕለት የምንጠቀምባቸውን የኬሚካል ምርቶች እናገኛለን፡፡

ከተቀጣጣይ ንጥረ ነገሮች ከተመረቱት የኬሚካል ምርቶች ውስጥ መድኃኒት፣ ማዳበሪያ፣ ነዳጅ፣ ፀረ ተባይ፣ የምንጠቀምበት እርሳስ፣ እስኪሪብቶ፣ ወረቀት፣ የኮምፒዩተርና የሞባይል መያዣዎች፣ የውኃ ቱቦና መያዣ፣ ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ መስኮት፣ በር፣ የግድግዳ ቀለም፣ ሲሚንቶ፣ የወለል ምንጣፍ፣ የሽንት ቤት ቁሳቁስ ወዘተ ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም መኪና፣ አውሮፕላን፣ መርከብ፣ ወዘተ ከ90 በመቶ በላይ የሚሠራው ከኬሚካል ውጤቶች ቁስ (Fiberglass ) ነው፡፡ ለዚህ ነው በአሁኑ ጊዜ ኑሮ ያለኬሚካል ምርቶች የማይታሰብ ነው የሚባለው፡፡ የኬሚካል ምርቶች በሚመረቱበትም ጊዜ ሆነ በሚቀመጡበት ጊዜ ካለአግባብ ንክኪ እርስ በርሳቸውም ሆነ ባዕድ አካላት ካጋጠማቸው በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ አደጋውም የእሳት መነሳት፣ ፍንዳታ፣ የጋስ ፍትለካ፣ ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ምሳሌም በቅርቡ የሆነው በለንደን ፎቅ ሕንፃ ላይ የተነሳው እሳት፣ እሳቱን ማጥፋት ተስኖ፣ ሙሉ በሙሉ እንደ ጧፍ ከሦስት ቀን በላይ ሲቀልጥ ያየነው የሚታወስ ነው፡፡

በአጠቃላይ አነጋገር፣ የኬሚካል ምርቶች ለሰው ልጅ ጥቅም እንደሚሰጡ ሁሉ መርዝም ናቸው፡፡ መርዝነታቸው ከሰው ጋር በቀጥታ ሲነካካ፣ ሲዋጥ ወይም ሲጠጣ ሊከሰት ይችላል፡፡ ክስተቱም ወዲያውኑ ወይም ከጊዜ በኋላ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ ሰው አንድ ሊትር ሜታኖል የተባለውን አረቄ ቢጠጣ ወዲያውኑ እውር ይሆናል፡፡ ትንሽ ግራም ሳይናይድ (Cyanide) ቢወስድ ወዲያው ሊሞት ይችላል፡፡ በሌላ በኩል እርሳስ (Pb-lead) ከተባለ ንጥረ ነገር ጋራ ለብዙ ጊዜ አብረን ብንሠራ ከጊዜ በኋላ የጉበት ካንሰር ሊይዘን ይችላል፡፡ እንዲሁም ፀረ ሕዋስ የኬሚካል ምርቶች (pesticides) ሰው በሚረጭበት ጊዜ ወደ ሳንባው ከገባ ከጊዜ በኋላ የመተንፈስ ችግር የሚያስከተል ካንሰር ሊይዘው ይችላል፡፡ ወይም በተለምዶ የጋራዥ ሠራተኞች በአፋቸው ቤንዚን እየያዙ የሚሠሩት፣ ወደፊት ምናልባት በቤንዚኑ ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮች ተንነው በመግባት፣ ከደም ጋራ ተያይዞ ለሚመጣው ካንሰር (leukemia) ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ማለትም የኬሚካል ምርቶች ጥቃት ወዲያውኑ ባለመድረሱ፣ ብዙ ሰው በመዘናጋት፣ የኬሚካል ምርቶችን ሲደፍሩና ቀላል የማይባል ዋጋ ሲከፍሉ ይታያሉ፡፡ በአጠቃላይ የኬሚካል ምርቶች መርዛማነት በሰው ልጅ ላይ በጥቅሉ በአራት በኩል ማለትም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በመድኃኒትና በሬዲዮ አክቲቭ (radioactive chemicals) የሚመጡ ናቸው፡፡ በመድኃኒትና በሬዲዮ አክቲቭ የሚመጡት ብዙ ሰው አደገኝነታቸውን የሚያውቅ ሲሆን፣ በከፍተኛ ሁኔታ በግብርና እና በኢንዱስትሪ የሚጠቀምባቸውን አደገኛ የኬሚካል ምርቶች ግን ብዙ ሰው ስለማያውቃቸው የመዳፈር ጠባይ በማሳየት በቀላሉ ለአደጋ ይጋለጣል፡፡

አብዛኛው የኬሚካል ምርቶች የተገነቡት ከሃይድሮጂንና ከካርቦንና ከኦክስጂን በመሆኑ በውስጣቸው በሚነሳ የጋስ ማፈትለክም ሆነ ውህደት በሚፈጠረው ግፊት (pressure) እና ሙቀት (heat) የእሳትና የፍንዳታ ምንጭ ይሆናሉ፡፡ በዚህም የኬሚካል ምርቶችን በማጓጓዝ፣ በማከማቸትም ሆነ በምንጠቀማቸው ጊዜ ባህሪያቸውን አውቀን ጥንቃቄ ካላደረግን ለከፍተኛ አደጋ ሊዳርጉ ይችላሉ፡፡ እንደ ምሳሌም ከማዳበሪያ በተለይ አሞኒየም ናይትሬት በተከማቸበት ቦታ ከተቀጣጣይ ነገር ካልጠበቅነው በቀላሉ እንደ ቦንብ በመፈንዳት በሰው ላይ ከፍተኛ እልቂት ከማስከተሉም በላይ በንብረት ላይም ውድመት ያስከትላል፡፡ ሰሞኑን የተከሰተው የቤይሩት ፍንዳታ ከ190 ሰዎች በላይ ሕይወትና ከ3000 በላይ ሰዎች መጎዳት፣ የዚህ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡

እንደዚህ ዓይነቶች ድርጊት በመፍራት፣ አገሮች የኬሚካል ምርቶችን አደገኛነት እንዲያውቁት አምራች ድርጅቶች፣ ምርቶቹ ሲመረቱ፣ ሲከማቹ፣ ሲጓጓዙና ሲቀመጡ ምን መደረግ እንዳለባቸው፣ በተጨማሪም በምርቶቹ አማካይነት አደጋ ቢነሳ፣ ለመከላከል የሚያስፈልገውን ግብዓት አዘጋጅተው ያቀርባሉ፡፡ ወደ አገራችን በምንመጣበት ጊዜ ግን የኬሚካል ማምረቻ ፋብሪካዎች በሚገነቡበት ጊዜ ፋብሪካዎቹ ሊያስከትሉት የሚችሉትን አደጋ አውቆ ጥንቃቄ እንዲደረግ የሚቆጣጠር አካል የለም፡፡ እንደ ምሳሌ ለማንሳት፣ እኔ ከኢትዮጵያ በኩል የቴክኒካል አማካሪ ቡድን መሪ ሆኜ በያዩ ከከሰል ዩሪያ ማዳበሪያ ለማምረት የፋብሪካ ግንባታ ለማሠራት፣ ዲዛይኑን ቻይናዎቹ እንዲሠሩ ሰጠናቸው፡፡ ቻይናዎቹም በእኛ ቁጥጥር የከሰል ማውጫውንና የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካዎቹ ሁለቱም ለእሳት መነሳትም ሆነ ፍንዳታ በባህሪያቸው የተነሳ የተጋለጡ ስለሆኑ፣ ተራርቀው እንዲገነቡ ንድፍ (design) አዘጋጁ፡፡ ተራርቀው እንዲገነቡ በዲዛይኑ የቀረበው እሳትም ሆነ ፍንዳታ ቢከሰት፣ አንዱ ላይ የተከሰተው ወደ ሌላኛው እንዳይተላለፍ በማሰብ ነበር፡፡ በዚህም ንድፍ መሠረት መንግሥት ሜቴክ እንዲገነባ ሥራውን ሰጠው፡፡ ሜቴክም ወጪ አድናለሁ (በውስጥ ግን ለሰዎች ሥራ ለመፍጠር ነው) በማለት በከፍተኛ ወጪ ተራራ ንዶ ሁለቱንም ፋብሪካዎች በአንድ ቦታ መገንባት ጀመረ፡፡ እኛም ይኼንን እንዳወቅን ብንጮህ፣ የሜቴክ መልስ ‹‹የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ጠባቦችና ትምክህተኞች ስለሆኑ ከእኛ በላይ ዕወቀት ያለው በአገሪቱ ውስጥ ባለሙያ አለ ብለው ስለማያምኑ ነው እንጂ ችግሩ አይከሰትም›› ብለው ቁጭ አሉ፡፡ እነሱን ሃይ የሚል በማፈላለግ ለብዙ ሚኒስትሮች ብነግር ሁሉም ‹‹እንዴት እንደዚህ ይሆናል፣ እናንተ የምትነገሩዋቸውን መስማት አለባቸው›› እያሉ እየነገሩን፣ ይኼንኑ የሜቴክን ኃላፊዎች በፊት ለፊት ለመናገር በመፍራታቸው ሳይናገሩ አለፉት፡፡ እኛም ለማን አቤት እንደምንል ግራ ገብቶን እያለ፣ ደግነቱ ሜቴክ ሲወድቅ ፕሮጀክቱም አብሮ ቀረ፡፡ በዚህም ለኢትዮጵያ የማዳበሪያ አቅርቦትን በከፊል ፈትቶ የውጭ ምንዛሪን የሚያድንላት ፋብሪካ ለማቋቋም ከአሥራ አምስት ዓመት በላይ የለፋንበት በመቅረቱ ብንቆጭም በሌላ በኩል ሜቴክ የማምረቻ ፋብሪካውን ባለማጠናቀቁ ለዘመናት ሲያባንነን ይኖር የነበረውን አስቀረልን፡፡

እንግዲህ የኬሚካል ምርት ሊያመጣ የሚችለውን ችግር ለሚያውቅና ሰሞኑን በቤይሩት ያጋጠመውን ፍንዳታ ላየ ምንም ዝግጅት በሌለበት በአገራችን ቢከሰት ምን ሊሆን እንደሚችል ሲገምት እንቅልፍ የሚያሳጣ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ፣ በአገራችን በአሁኑ ጊዜ ባሉት የኬሚካል ምርቶች ላይ እሳት ቢነሳ፣ ፍንዳታ ቢከሰት ብቁ ዝግጅት ኖሮት በፍጥነት የሚከላከል የእሳት አደጋ አለ ተብሎ ስለማይታመን ነው፡፡ እዚህ ላይ መረገጥ ያለበት በተለምዶ እንደሚከናወነው በኬሚካል ምርት ላይ የሚነሳ እሳት በውኃ ብቻ አይጠፋም፡፡ እንዲያውም ውኃ ብቻ መጠቀም ሊያባብሰው ይችላል፡፡ በተጨማሪም እያንዳንዱ ኬሚካል ከተገነባበት ንጥረ ነገር አኳያ የሚያመጣውን አደጋ በቁጥጥር ለማዋል የራሱ ማስወገጃ ዓይነት አለው፡፡ ለዚህም ለምሳሌ በኬሚካል ምርቶች ላይ ለሚነሱ የእሳት አደጋ ማጥፊያ የተለያዩ ኬሚካሎች አሉ፡፡ እንደ አብነት ለኬሚካል ምርቶች እሳት ለማጥፋት ከምንጠቀምባቸው ለመጥቀስ የተደባለቀ ፎም (foam)፣ ደረቅ ኬሚካልስ ለምሳሌ ሞኖአሞኒየም ፎስፌት (mono-ammonium phosphate)፤ ሶድየም ካርቦኔት (sodium carbonate)]፤ ወዘተ፡፡ ፈሳሽ ኬሚካልስ ለምሳሌ፣ ፓታሺየም አሲቴት (potassium acetate) ፖታሺየም ካርቦኔት (potassium carbonate)፡፡ ጋስ ለምሳሌ ካርቦን ዳይኦክሳይድ (Carbon Dioxide)፤ ሃሎትሮን-1 (Halotron1) ወዘተ. የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ እንግዲህ በኬሚካል ምርቶች ላይ የሚነሳ እሳትን ለማጥፋት፣ የመጀመሪያ ቅድመ ሁኔታ የሚሆነው፣ የምርቱን ባህሪ አውቆ አስፈላጊውን የእሳት ማጥፊያ ኬሚካል መጠቀም የግድ ነው፡፡ ስለዚህ የእሳት አደጋ መከላከያ ድርጅቶች በአካባቢያቸው ያሉትን ኬሚካሎች ባህሪ አውቀው፣ እሳት ቢነሳ ወዲያውኑ ለመቆጣጠር ተገቢውን የእሳት ማጥፊያ ኬሚካሎች አዘጋጅቶ መጠበቅ አለባቸው፡፡ ከዚህም በላይ የኬሚካል ምርቶች በሚቀመጡበትም ጊዜ ይሁን በሚጓጓዙበት ጊዜ አደጋ ሊያስከትሉ ስለሚችሉ፣ አንዳንዶቹን ከፀሐይ ተሰውረው መቀመጥ አንዳንዶቹን ደግሞ በፈሳሽ ውስጥ ማስቀመጥ የግድ ይላል፡፡ ለምሳሌ ሶዲየም የተባለው ንጥረ ነገር የሚቀመጠው እንደ ኬሮዚን በመሳሰሉት ውስጥ ነው፡፡

በሌላ በኩል የእሳት አደጋን መከላከያ ብቻ ማጠናከር አንዳንድ ከኬሚካል ምርቶች የሚመጡትን አደጋዎች ሙሉ በሙሉ አያድንም፡፡ በኬሚካል ምርቶቹ ባህሪ የተነሳ የሚያስከትሉትን አደጋ ለማስወገድ የግድ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ስለሚፈልጉ የት መወገድ እንዳለባቸው፣ የኬሚካል ምርቶቹ ሲመጡም ሆነ ሲመረቱ መታወቅ አለበት፡፡ በተለይ አንዳንድ ኬሚካሎች ሊወገዱ የሚችሉት በጣት በሚቆጠሩ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ደረጃ ባላቸው አገሮች በሚገኙ ቤተ ሙከራዎች ስለሆነ እነዚህን ቦታዎች አሰቀድሞ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ እንደ ምሳሌም ለመጥቀስ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ተባይና አረም ማጥፊያ (pesticides) በመርከብ ወደ ኔዘርላንድ ልካ እንዳስወገደች የሚታወቅ ነው፡፡  በአደገኝነታቸው ከሚታወቁት ኬሚካሎች ውስጥ ከኑክሌር ማብላያ ውስጥ የሚቀሩት ዝቃጮች አንዱ ሲሆኑ፣ እነዚህን ማስወገድ የሚቻለው፣ በሠለጠኑ ባለሙያዎች በሚታገዙ ጥቂት ቤተ ሙከራዎች ወይም ሰው በማይኖርበት ቦታ በጥልቅ ጉድጓድ በመቅበር ነው፡፡

እንግዲህ በግልጽ እንነጋገር ከተባለ ከላይ እንዳየነው የኬሚካል ምርቶችን አደጋ ለመቆጣጠር በኃላፊነት የሚሠራ ክፍል በኢትዮጵያ መኖሩ ያጠራጥራል፡፡ እስከነጭራሹ የለም፡፡ ይኼንን የምለው እኛ በሥራችን ምክንያት ብዙ የኬሚካል ምርቶች ወደ አገር ውስጥ ስናስገባ፣ ጉምሩክ ቀረጥ እንድንከፍል ከሚጠይቀን በስተቀር፣ ስለኬሚካሉ ሁኔታ የሚያይ ሌላ አካል የለም፡፡ አንዳንዴ ድርጅቶች ያዙና በጉምሩክና በእነሱ መካከል በተከሰተ አለመግባባት ወራትን እንዲያውም ዓመታትን በጉምሩክ ግምጃ ቤት ተጥለው የሚኖሩ ኬሚካሎች አይጠፉም፡፡ እነዚህም ኬሚካሎች ወደፊት ምን አደጋ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ማንም የሚጠይቅ የለም፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ከጉምሩክ ጋራ በተያያዘ እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው አሁንም የቤይሩቱ ፍንዳታ ነው፡፡ እስካሁን እንዴት እንደተፈጸመ የተቋቋመው አጣሪ ግብረ ኃይል ባይገልጽም በቅድመ ምርመራ እንደታወቀው ወደ 3000 ቶን የሚጠጋ አሞኒየም ናይትሬት ማዳበሪያ ለሽያጭ ከሩሲያ ወደ አፍሪካ በመርከብ (አንጎላ?) በቤይሩት ወደብ በኩል ይላካል፡፡ ቤይሩት ሲደርስ ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት ሻጭና ገዥ ባለመስማማታቸው ለጉምሩክ የሚያስፈልገውን ክፍያ የሚከፍል ጠፍቶ ከመርከብ ተራግፎ ለብዙ ዓመታት በወደቡ ግምጃ ቤት ተረስቶ ይቀመጣል፡፡ በኋላ ግን ፍንዳታው ሲከሰት ያ የተረሳው ማዳበሪያ መሆኑ ታወቀ፡፡ ይኼ የሆነ ድርጊት የሚያሳስበን በአገራችን በየቦታው ያሉ የጉምሩክ መሥሪያ ቤቶች ምናልባት አደገኝነቱን ባለማወቅ ያስቀመጡት የኬሚካል ምርት አንድ ቀን ቢፈነዳ ተጠያቂው ሊያከራክር እንደሚችል ነው?፡፡

በአጠቃላይ የኬሚካል ምርቶች የሚያስከትሉት አደጋ ለመከላከል የእያንዳንዱን ባህሪ ማወቅ ቅድመ ሥራ ሆኖ  በአገሪቱ ያሉትንም ሆነ ወደፊት የሚገቡትን መዝግቦ በመያዝና የት እንደሚቀመጡ አውቆ በአደጋ ጊዜ ለመከላከል የሚያስችል አቅም መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ይኼንንም በባለቤትነት የሚያስተባብር አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ማቋቋም ጊዜ የማይሰጠው ነው፡፡ የባለሥልጣኑም ዓላማ ከሚሆኑት ውስጥ ኬሚካሎች በአገር ውስጥ ሲመረቱም ሆነ በየብስ፣ በአየርም ሆነ በባህር የሚመጡትን መዝግቦ መያዝ፣ ኬሚካሎቹ የት አንዳሉ ማወቅ፣ የእያንዳንዱ ኬሚካል ባህሪ የሚገልጽ በደንብ የተጻፈ ሰነድ አብሮ መኖሩን ማረጋገጥ፣ ኬሚካሎቹ አደጋ ቢያስከትሉ አደጋውን ለማሰወገድ የሚያስችል ቁሶች በአደጋ መከላከያ ውስጥ ተዘጋጅተው መኖራቸውን ማረጋገጥ፣ ከአገር ውጪ ሊወገዱ የሚገባቸውን መለየትና የት አገር ማስወገድ እንደሚቻል ማወቅ ወዘተ ይገኙበታል፡፡ አገሪቱም ይኼንን መሥሪያ ቤት በፍጥነት አቋቁማ ሊመጣ የሚችለውን የኬሚካል አደጋ ማስቀረት ይጠበቅባታል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!!

ከአዘጋጁ ጸሐፊው በላይ ወልደየስ (/ር፣ ኢንጂነር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ   የአዲስ አበባ ቴክኖሎጂ  ኢንስቲትዩት  የኬሚካል ኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles