Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊትኩረት የሚሻው ታሪካዊው የሾንኬ መንደር

ትኩረት የሚሻው ታሪካዊው የሾንኬ መንደር

ቀን:

በመንደሩ ላይ ለመድረስ ያለው አማራጭ የጭነት መኪና ነው፡፡ የመንደሩ እንስቶች ገበያ ዘልቀው ከተገበያዩ በኋላ ለመመለስም የጭነት አይሱዙ ላይ መሰቀል ይጠበቅባቸዋል፡፡

በአይሱዙ ከ40 እስከ 50 እና ከዚያ በላይ የመንደሩ ሰዎችን ይይዛል፡፡ ምንም እንኳን የጭነት አይሱዙ መኪናው ለሕዝብ ማመላለሻነት እንዲያገለግል ባይሠራም ለመንደሩ ነዋሪዎች ግን ከእግር ጉዞ ገላግሏቸዋል፡፡

የዚህ የትራንስፖርት አገልግሎት ለእንግዳ ሰው አስገራሚ ቢሆንም ለአካባቢው ግን ለረዥም ዓመታት የተለመደ ነው፡፡ ሴቶች የአይሱዙ ጫፍ  ወይም በሾፌሮች አጠራር ስፖንዳ  ላይ ጉብ ይላሉ፡፡ መኪናው በሚችለው ልክ ሳይሆን ሰዎች የሚንጠለጠሉበት ካጡ ብቻ ‹‹ሞላ›› ተብሎ ጉዞ ይጀመራል፡፡

በዚህ የትራንስፖርት አገልግሎት መቀመጥ የሚባል ቅንጦትና ድሎት ነው፡፡ ምናልባት ሊቀመጡ የሚችሉት ሾፌሩና ጋቢና የተቀመጡ ዕድለኛ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ መኪናው ላይ ተንጠለጠለም፣ ቆመ የሚሄዱትም ጋቢናም ያለው ሁሉም እኩል ክፍያ ይፈጽማሉ፡፡

በአካባቢው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ጥቂቶች ናቸው፡፡ እነርሱም የጭነት ማመላለሻ አይሱዙዎች ብቻ ናቸው፡፡ ወደ መንደሩ ለመሄድ ከእነዚህ የጭነት መኪናዎች በተጨማሪ  ባለ ሦስት እግር ባጃጆች በስተቀር መንገዱን  የሚደፍር  የለም ፡፡

ምናልባት የመንደሩን ታሪክና ባህል ለመጎብኘት ቱሪስቶችን ይዘው ከሚመጡ መኪናዎች በስተቀር ሌሎች የትራንስፖርት አማራጮችን ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ ይህ አካባቢ ከአዲስ አበባ 350 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ደዋጨፍ ወረዳ ጅሮታ ቀበሌ የሚገኘው መንደር ታሪካዊና ለዓይን ማራኪ ሥፍራ ነው፡፡

ይህችን አነስተኛ  መንደር ለመጎብኘት ከከሚሴ ከተማ ወጣ ብላ ከምትገኘው ከጅሮታ ቀበሌ ውጣ ውረድ የበዛባትና ቁልቁለትና አቀበት ያለበትን 25 ኪሎ ሜትር መጓዝን ይጠይቃል፡፡ መንደሩ ‹‹ሾንኬ›› ይባላል፡፡ የሾንኬ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ ከፍታማ ነው፡፡ ይህም ከጠላት ለመሸሽና ለመከላከል እንደሆነ የመንደሩ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ አካባቢ የሚኖሩት ደግሞ ጥንታዊዎቹ አርጎባዎች ናቸው፡፡

የሾንኬ መንደር ከ850 ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ ይነገርለታል፡፡ ወደ ሾንኬ ለመጓዝ እጅግ አዳጋችና አድካሚ ቢሆንም መንደሩ በኪን ሕነፃ ያማረና ከሚኖሩበት  ከፍታማ ቦታ ሆነው ሲመለከቱት የዓይን ምግብ በመሆኑ ድካም ያስረሳል፡፡

አርጎባዎች የሚኖሩት በሾንኬ ብቻ አይደለም ከመንደሯ ወጣ ያለችውና ቀድማ የተቆረቆረችው ‹ጠለሀ› መንደር መኖሯንም የአካባቢው አባት ያስረዳሉ፡፡

የጠለሀ መንደር ልክ እንደ ሾንኬ የቤት አሠራር ማራኪ ቢሆንም በመሠረተ ልማት በኩል ያልተሟላና ጠለሀ ምንም ዓይነት መግቢያ መንገድ እንደሌለው ይነገራል፡፡

ከሚሴና አካባቢዋ ላይ እጅግ የሚያምሩና የተዋቡ እንስቶች ሲታዩ “አርጎባ ትሆናለች” የሚል ግምት እንደሚሰጥ የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡ ‹ሾንኬ› መንደር የሚኖሩት አርጎባዎች በቁጥር ከ200 እስከ 300 መቶ አባወራዎች ይሆናሉ፡፡

የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ ከተማ በመፍለስና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑበት ምክንያት ተብሎ ይጠቀሳል፡፡

በሌላ በኩል የሾንኬ መንደር መሠረተ ልማቱ ያልተሟላ በመሆኑ ወደ ከተማ ቀረብ ለማለት የተገደዱም እንዳሉ የመንደሩ ነዋሪዎች ገልጸው፣ ውኃና መብራት፣ መንገድ፣ የጤና ተቋም በአካባቢው ባለመኖሩ የጤና እክል ሲያጋጥማቸው ረዥሙንና አሰልቺውን የሾንኬ የኮሮኮንች መንገድ ማቋረጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ሕፃናት፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞች እክል ገጥሟቸው ወደ ከተማ ከሄዱ ትራንስፖርት የሚጠቀሙት በጭነት ማመላለሻ ነው፡፡

የሾንኬ መንደር መመሥረት ዋነኛ ምክንያት ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ፈጣሪን የሚማፀኑበት መስጊድ ከመሥራት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሃጂ መሐመድ ኢስማኤል በጅሮታ ቀበሌ በምትገኘው የሾንኬ መንደር አባት ናቸው፡፡ ሃጂ መሐመድ በአርጎብኛ ቋንቋ ስለመንደሩ መሠረተ ልማት እንዲህ ይላሉ፡፡

‹‹ከአርጎባ ጋር ለማስተላለፍ የምንከጅል ሾንኬ አይመጥ ሁለታ መሀራ ዓብይብ በኃይለ ሥላሴ ዘመን ሀፍታ ጠያራ ጉድ አረፈች፡፡ እቶቢን መድን በደረግ አይመጡለታም ጥናት ኢሉላይ፣ አገሩን አይለይ፡፡ ግሩም ነው ጥሩ ነው ይሉለይ፡፡ ጥይቃ አሉላይ፡፡ ውኃ፣ ኤይማ፣ ትምህርት ቤት፣ ጥገኛ እንዲገባስ ጠይቁለይ ተግባሩ ኤያታ፡፡ ኢንሻአላህ ይመጣል ይመጣል አሉለይ ተግባሉ አረይይነይ፡፡››

ትርጓሜውም ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ በሾንኬ መንደርና አካባቢዋ ጥናት እናደርጋለን፣ አገሩ ግሩም ነው እያሉ ይጎበኛሉ፡፡ በመንግሥቱ ኃይለማርያም ጊዜም እንዲሁ፡፡ ውኃ፣ ጤና፣ ትምህርት ቤትና ሌሎችም መሠረተ ልማት ይሠራል እየተባለ ቃል ይገባ ነበር ነገር ግን እስካሁን አላየንም የሚል ነው፡፡

ሃጂ መሐመድ በዕድሜ ዘመናቸው የመሠረተ ልማት ችግር ይፈታል በሚል ተስፋ እያደረጉ ቢኖሩም እስኪሸብቱ ድረስ ተግባራዊ አለመደረጉን ይናገራሉ፡፡ የአካባቢው የሚኖሩ ሴቶች ምጥ ሲመጣባቸው አቅራቢያቸው ጤና ተቋም ባለመኖሩ አምቡላንስ መንደሩ ላይ እስኪደርስ ረዥም ሰዓት እንደሚወስድም ይገልጻሉ፡፡

የወረዳው የባህልና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ኑሩ ይማም እንደተናገሩት በተለያየ ምክንያት ተጓቶ የቆየው የመንገድ መሠረተ ልማት በ2013 ዓ.ም. ለማስጀመር እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡

የመንደሩ አመቺ አለመሆን፣ የአመራሮች የተዛባ አመለካከትና ሌሎችንም ችግሮች የጠቀሱት አቶ ኑር፣ በዘንድሮው የበጀት ዓመት የክልሉ መንግሥት የመንገድ ችግር እንደሚቀርፍ ቃል መግባቱን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል የመንደሩ ታሪካዊነትና ጥንታዊነት እንዳይበላሽ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከፍተኛ ሥራ መሠራቱን የገለጹት ኃላፊው፣ እስካሁን መንደሩ ታሪካዊ ይዘቱ እንዳይበላሽ ትልቅ ሥራ ተሠርቷል ይላሉ፡፡ ዘንድሮ የመንገድ መሠረተ ልማት ከተሟላ በቀጣይ ሌሎቹን ለማሟላት ከፍተኛ ግፊት እየተደረገ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

አርጎባዎች ከሾንኬ መንደር በተጨማሪ በአፋር፣ ሐረር፣ አዳማ፣ ትግራይና በሌሎች አካባቢ እንደሚኖሩም ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...