Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትአሠልጣኝ ውበቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ‹‹እኔ›› የሚለው የአጨዋወት ዘይቤ የለውም አሉ

አሠልጣኝ ውበቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ‹‹እኔ›› የሚለው የአጨዋወት ዘይቤ የለውም አሉ

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ለአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ከኒጀር ጋር ከመጋጠሙ በፊት፣ የመጨረሻውን የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ከሱዳን ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ከትናንት በስቲያ ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ተጫውቷል፡፡ ጨዋታው ሁለት እኩል በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡

የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንደ አውሮፓና ሌሎች መሰል ብሔራዊ ቡድኖች የ‹‹እኔ›› የሚለው የአጨዋወት ዘይቤ  የለውም ሲሉ ከጨዋታው በፊት ተናግረዋል፡፡

አሠልጣኙ ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 26 በፌዴሬሽኑ የስብሰባ አዳራሽ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የሱዳኑ የወዳጅነት ጨዋታ ምናልባትም ከኒጀር ጋር ላለባቸው ወሳኝ የማጣሪያ ጨዋታ ቀዳሚ ተሠላፊዎቻቸው የሚለዩበት እንደሚሆን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ከሱዳኑ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ቀደም ብሎ የዛምቢያን ብሔራዊ ቡድን ሁለት ጊዜ ገጥመው በሁለቱም ሽንፈትን ማስተናገዳቸው ቢታወቅም፣ ጨዋታውን በሚመለከት አሠልጣኙ በአሸናፊነትና ተሸናፊነት መንፈስ እንዳልተመለከቱት ገልጸዋል፡፡ ምክንያቱን አስመልክቶ አሠልጣኙ፣ ቡድናቸው ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ሁሉንም ተጨዋቾቻቸው ወደ ሜዳ እንዲገቡ በማድረግ በምን ዓይነት አቋም ላይ እንደሚገኙ ከማየት ባለፈ ሌላ ግብ እንዳልነበራቸው አመልክተዋል፡፡ በጨዋታው የተሳተፉት ሁሉም ተጨዋቾች ለሰባት ወራት ያህል ከውድድር የራቁ እንደመሆናቸው መጠን፣ በምን ዓይነት ሥነ ልቦና ውስጥ እንደሚገኙ በመመልከት ቀጣይ ዝግጅታቸው ምን መምሰል እንዳለበት ለመወሰን የተጠቀሙበት ጨዋታ እንደነበረ ጭምር ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ትኩረት ሰጥተው የተናገሩት አሠልጣኝ ውበቱ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ከእግር ኳስ ሥልጠና ጋር በተገናኘ እንደ አውሮፓና መሰል አገሮች በቋሚነት ሊያሠራ የሚችል የሥልጠና ሰነድ የለንም፡፡ የነበረውም ሆነ አሁን ያለው በተለይም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደረጃ እንዲያሠለጥኑ ጥሪ የሚደረግላቸው አሠልጣኞች የየራሳቸው የጨዋታ ዘይቤ ያላቸው እንደ መሆናቸው መጠን ባለው ማዕቀፍ ተመዝግበው ነው ወደ ብሔራዊ ቡድኑ የሚመጡት፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ የተረጋጋና ወጥ ብሔራዊ ቡድን እንዳይኖር አድርጎ ቆይቷል፡፡  ችግሩ አሁንም እልባት አግኝቷል ብዬ አልምንም፤›› ብለዋል፡፡

አሠልጣኙ በአውሮፓ አገሮች ዋንጫ በተለይም በዩሮ 2000 በአሁን ወቅት ከውጤት ባሻገር ማራኪና ውበት ያለው እግር ኳስ በመጫወት በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀሰው ጀርመን ወጥነት ያለው የሥልጠና ሰነድ ለአንድ አገር ብሔራዊ ቡድን ምን ያህል ጥቅም እንዳለው በምሳሌነት አቅርበዋል፡፡

ለወትሮ ለተመልካች የማይመች እግር ኳስ በመጫወት ትታወቅ የነበረችው ጀርመን፣ በአሁኑ ወቅት ዩሮ 2000 ላይ በጀመረችው የእግር ኳስ አብዮት የራሷ የሆነ የምትታወቅበት የአጨዋወት ዘይቤና ሐሳብ ይዛ ለአሠልጣኞቿም ሆነ ለተጨዋቾቿ ቋሚና ወጥ የሆነ የሥልጠናና የጨዋታ ፍልስፍና ካላቸው ተርታ እንድትመደብ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ሲኤምሲ አካባቢ ባስገነባው የምሥራቅ አፍሪካ ወጣቶች የእግር ኳስ አካዴሚ ተቀምጠው ለአንድ ወር ያህል ዝግጅት ሲያደርጉ የቆዩት አሠልጣኝ ውበቱ፣ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሆነው፣ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ለእግር ኳሱ ማዕከላዊነቱን የጠበቀ የሥልጠና ማንዋል (ሰነድ) አስፈላጊነትን ሲናገሩ የመጀመርያው ያደርጋቸዋል፡፡

እሳቸውን ጨምሮ በሙያው ውስጥ በመሥራት ላይ የሚገኙ ሙያተኞች ኢትዮጵያን የሚገልጽ ሊያሠራ የሚችል ሰነድ ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸው የሚናገሩት የዋሊያዎቹ አሠልጣኝ፣ ይህ ዕውን ቢሆን አሰልጣኙም ሆነ ተጨዋቾቹ በተቀመጠው ሰነድ መሠረት ሁሉም ከራሱ  አስተሳሰብ ጋር በማቀናጀት በቂ ዝግጅት ለማድረግ አስፈላጊ እንደሆነና እንደሚያምኑበትም ጭምር በመግለጫቸው አክለዋል፡፡

አሠልጣኙ የብሔራዊ ቡድኑን ኃላፊነት የተረከቡት ይህ የሥልጠና ሰነድ በሌለበት እንደመሆኑ፣ ሊከተሉት የሚያስቡት የአጨዋወት ዘይቤ ምን ሊመስል ይችላል የሚል ጥያቄም በዕለቱ ቀርቦላቸው ነበር፡፡

‹‹ተጨዋቾቼ አቅሙ ቢኖራቸው እንዲጫወቱልኝ የምፈልገው የአገሪቱን ተጨዋቾች አቅምና ብቃት እንዲሁም የአጨዋወት ዘይቤ የሚገልጽ ቢሆን እመርጣለሁ፡፡ ለዚህ በማሳያነት የምጠቅሰው የዛምቢያውን የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ነው፡፡ ምክንያቱም ከጨዋታው በፊት የነበረኝ የአጨዋወት ሐሳብ ሌላ ነበር፡፡ ሐሳቤ የተለወጠው በጨዋታው ላይ የዛምቢያ ቡድን ሜዳ ላይ የነበራቸውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ከተመለከትኩ በኋላ ነው፡፡ በረዣዥም ኳሶች አንድ ለአንድ ብዙ ልዩነቶች እንደነበሩ እኔ ብቻ ሳይሆን ጨዋታውን የተመለከተ ሁሉ የሚፈርደው የአደባባይ ሚስጥር ነበር፤›› በማለት በሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል የነበረው የአካል ብቃት ልዩነቱ  ግልጽ እንደነበር ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡

በመጨረሻም አሠልጣኙ በቅርቡ ከኒጀር ጋር የሚጠብቃቸውን ጨዋታ በሚመለከት ሲናገሩ፣ በተቻለ መጠን የተጋጣሚያቸውን እንቅስቃሴ መሠረት ያደረገ እንቅስቃሴና አጨዋወት ለመከተል ሐሳብ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

የአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን ባለፈው ዓርብ ከሱዳን አቻው ጋር ባደረገው ሦስተኛ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ከዛምቢያው ጨዋታ የተሻለ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ታይቷል፡፡ ይሁንና ቡድኑ አሁንም የቆሙ ኳሶችን ወደ ጎል በመቀየር ረገድ ገና ብዙ እንደሚቀረው፣ ምናልባትም ይህ ድክመቱ በሚቀሩት ጥቂት የልምምድ ቀናት የማይሻሻል ከሆነ አስቸጋሪ እንደሚሆንበት የሚናገሩ አልጠፉም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...