Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉከመለያየት አንድነት መብለጡን ነጋሪ ያስፈልገናል ወይ?

ከመለያየት አንድነት መብለጡን ነጋሪ ያስፈልገናል ወይ?

ቀን:

በአስናቀ ዘመድኩን

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን ከፍተኛ የሕዝብ ፍላጎት መሠረት ኢትዮጵያለውጥ ምህዋር ውስጥ ትገኛለች፡፡ አባጣ ጎርባጣ በበዛበት በዚህ የለውጥ ጉዞ በርካታ ተስፋ ሰጪ ነገሮችም ይስተዋላሉ፡፡ በዚህ ሒደትም የፍላጎት ግጭቶችና የፖለቲካ ውዝግቦች በማጋጠማቸው ዜጎች ለሰላም ዕጦት መጋለጣቸው የታወቀ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እየተከፈቱ ንፁኃን ሲጨፈጨፉ፣ፈናቀሉና ለከፍተኛ የሥነ ልቡና ጉዳት ሲጋለጡ በስፋት እየታየ ነው፡፡ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይም ቀላል የማይባል ጉዳት መድረሱ ይታወቃል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ጦረኛው ሕወሓት የጦርነት ነጋሪት ሲጎስም ሰንብቶ ለይቶለት ጦርነት ጀምሯል፡፡ የትግራይን ሕዝብ ከተቀረው ወገኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመነጠል ሰብዓዊ ጋሻ አድርጎት እየነገደበት ነው፡፡ ይህ ነውረኛና አምባገነን ቡድን በሕዝብ ላይ እየቀለደና አገር ለማፍረስ ጦርነት እየከፈተ ቢሆንም፣ በብልኃትና በከፍተኛ ጥበብ አከርካሪውን በመስበር ሕዝቡን ዕፎይ ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡

በዚህ ላይ የፖለቲካ ምኅዳሩና የዴሞክራሲው መስተጋብር አመርቂ ለውጥ እንዲያሳይ ጥረት ቢደረግም አሁንም የጥላቻ ንግግር፣ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ውዝግብና አሉባልታ የአብሮነታችን እንቅፋት መሆናቸው አልቀረም፡፡ ጦርነትን በሩቁ ካልሆነ አጠገቡ ሆነው የማያውቁ ጭምር ግፋ በለው እያሉ አገርን ለማፍረስ እየተባበሩ ሲሆን፣ በተለይ ከሥልጣን ውጪ ምንም የማይታያቸው ስመ ፖለቲከኞች ሴራ እየጎነጎኑ ሕዝቡን እርስ በርስ ለማፋጀት እያሴሩ ነው፡፡

በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) በማኅበራዊ ድረ ገጽ አጠቃቀም ዙሪያ ጠበቅ ያለ መመርያ መውጣት እንዳለበት፣ ዜጎችም ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ የመጠቀም ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ማሳሰባቸው አይዘነጋም፡፡ ይህንን ተከትሎም ሕግ መውጣቱ እንዲሁ ይታወሳል፡፡ ከዚህም በላይ ግን የሃይማኖት አባቶች በተለያዩ ጊዜያት ባወጧቸው መግለጫዎች ጥላቻ እንዲወገድ ብዙ ብለዋል፡፡ ታዋቂ ሰዎችና የአገር ሽማግሌዎች ሳይቀሩ ለሰላም መስፈን ተማፅኖ አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ከዕለት ወደ ዕለት ጥላቻ እየተባዛ ወደ ጦርነት እያመራን ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚከፋፍልና አገር አልባ የሚያደርጉ ድርጊቶች ካልተገቱ ወደ አደገኛ ቀውስ መግባታችን አይቀርም፡፡

አገራችን ከነበረችበት ጥልቅ የጭቆናና የበደል ታሪኳ ተላቃ እነሆ በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ መራመድ ከጀመረች ከሁለት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ ቢያንስ ጭፍኑና ጨካኙ የኢሕአዴግ ሥርዓት በሕዝባዊ ተቃውሞ ከተወገደ በኋላ መሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአሁኑን ቅርጿን ከያዘች ወዲህ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ልዩ ልዩ ሃይማኖቶችና ታሪኮችን ሰብስባ የያዘች ምድር ነች፡፡ በጂኦግራፊ አቀማመጧም ሆነ በተፈጥሮ ፀጋዋ ጠላት የበዛባት፣ በዚያው ልክም ሕዝቦቿ ለዘመናት ሉዓላዊነቷን በደምና በአጥንታቸው ያስከበሩላት የጀግንነት ምድር ናት፡፡

በዚያው ልክ ከማንም የላቀ ሀብት ኖሯት፣ ከማንም በታች ሆና በድህነትና በኋላ ቀርነት የኖረች፣ ከማንም ያላነሰ ታታሪና አገር ወዳድ ሕዝብ እያላት በድህነት ስትማቅቅ የዘለቀች አገርም ነች፡፡ መደማመጥና ሥልጡን የፖለቲካ ባህል ባለመገንባቱም፣ እርስ በርስ ሲፋጁ የነበሩ ትውልዶችም ያለፉባት ናት፡፡ የዚያ መዘዝ በዚያው የታሪክ ምዕራፏ ባለመቋጨቱም እስካሁኑ ትውልድ ውዝግቡና ተቃርኖው ዘልቆ ከትርምስ ለመላቀቅ አልተቻለም፡፡ ምንም ቢሆን ግን፣ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት መኖራቸውና አገራቸውን አስከብረው እዚህ ደረጃ ማድረሳቸውን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡          

ኢትዮጵያ ሀብቷ ዕልፍ ነው፡፡ በከርሰ ምድር ውስጥ ያለውን ሀብት ትተን እንኳን በሕዝቦቿ መካከል ያለውንና ዓለምን የሚያስደምመውን ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርስ ወይም  የብዙኃነት ሀብት ብንመለከት፣ እንደ ኢትዮጵያ የታደለ አገር ማግኘት ሲበዛ ብርቅ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ይህ ሀብቷ ለዘመናት ውበቷና ጌጧ ሳይሆን ቆይቷል፡፡ የጭቆናና የተዛባ ታሪክ ሰለባ በመሆናችንም እርስ በርስ ስንባላባት መቆየታችንም አይዘነጋም፡፡ አስከፊው እውነት አሁን እየገጠመን ያለው ደግም የጋራ ሀብቶቻችንን የጋራ ዕድላችንን ለመወሰን ተሳስበን ማድረግ ሲገባን፣ በክልልና በመንደር ታጥረን ወደ ቀውስ የምናመራ በመሆናችን ነው፡፡ ኧረ ጎበዝ? ቆም ብለን እናስብ የሚያስብለውም ለዚህ ነው፡፡

በእርግጥ ይህ የማንነት ውዝግብም ሆነ የጥላቻ ፖለቲካ ዛሬ ብቻ የመጣብን አይደለም፡፡ ይልቁንም ከጥንት በተለይም ከቅኝ ገዥዎች ሴራ በኋላ በላያችን ላይ እንደ ተነዛብን የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ፡፡ ይህ የተዛባ የእርስ በርስ ግንኙነት መታረም በነበረበት ጊዜ ባለመታረሙ፣ መስተካከል በነበረበት አጋጣሚም ሳይስተካከል በመቅረቱ፣ የአገራችን ዕድገት እንደ ግመል ሽንት የኋልዮሽ ሲፈስ እንደኖረ ሊዘነጋ አይችልም፡፡ ቢያንስ አሁን በዕርቅና አብሮነት ጉዞ ተደማምጦ ማስተካከል የሚገባው ይህን እውነት በሆነ ነበር፡፡ ግን አይመስልም፡፡

እንደ አንድ አገር ሕዝቦች ከተማ/ገጠር፣ ቆላ/ደጋ፣ ዳር/መሀል ሳይባል አንዳችን ለሌላችን እኩል ማስፈለጋችን ሳይገለጥልን፣ ወይም እንዲገለጥልን ሳንፈልግ ለዘመናት በመኖራችን መድረስ በነበርንበት ሥፍራ ላይ ሳንደርስ ኖረናል፡፡ ይኼ እንደ አገር ሊያንገበግበንና ሊያስቆጨን ሲገባ፣ አሁንም ስለመለያየትና ውዝግብ ብሎም ስለግጭትና ትርምስ መስበክ እጅግ አሳፋሪና ኋላቀር አስተሳሰብ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ አሁን  የደረስንበትን ሁሉን አቀፍ ዕድገት ከማስቀጠልና ፍትሐዊነቱን አረጋፈግጦ ከማስፋት ይልቅ፣ ወደኋላ እንደ መመለስ ያለ ጭቃ ውስጥ መግባት ሊኮነን ይገባዋል፡፡  በ21ኛው ክፍለ ዘመን የጦርነት ነጋሪት መጎሰምና ሕዝባችንን ወደ ዕልቂት መውሰድ ሊወገዝ ይገባዋል፡፡

በመሠረቱ ሁላችንም የዚህች አገር ዜጎች በተለይም የአዲሱ ትውልድ አባላት ይህ አደገኛና አውዳሚ ጦርነት በፍጥነት መገታት አለበት ማለት ይገባናል ስንል፣ በቅንነትና በመተሳሰብ ጎዶሏችንን ለመሙላት ነው፡፡ እውነት ለመናገር የደርግ ሥርዓት ወድቆ በዚች አገር ላይ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሲጀምር፣ በሕዝብ ልጆች ደምና ላብ በተመሠረተ ተጋድሎ ነበር፡፡ 1984 .. ሁሉንም የአገራችን የፖለቲካ ኃይሎች ያሳተፈ ሕገ መንግሥት መቅረፅ ባይቻልም፣ ከብዙ ችግሮቹ ጋር ለበርካታ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዕውቅና የሰጠ ሰነድ እንደነበርም ሊካድ አይችልም፡፡ ያም ሆኖ የተገነባው ሥርዓትና የተቀረፀው ሕገ መንግሥት በአፈጻጸም ጭምር ተዳክሞ፣ ለዛሬዋ ኢትዮጵያ መሠረት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ድረስ ለሚታዩ ትልልቅ ክፍተቶች በር ከፍቷል፡፡ ይህንን ቁስላችንን አክመን የጋራ የሆነ ዘመኑን የዋጀ ሕገ መንግሥት ማደራጀት ሲገባን፣ በሚያሳዝን ሁኔታ አገር ለማፍረስ እየማሰንን ነው፡፡

እኔ በበኩሌ የማምነው ይህ ሥርዓትና ሕገ መንግሥት ለአሁኗም ብቻ ሳይሆን ለወደፊቷ ኢትዮጵያ ዋስትና ሊሰጥ የሚችለው ግን፣ እንዳለፉት ጊዜያት ጭራሹን ጠፍቶ አዲስ በመጻፍ ሳይሆን በሕገ መንግሥቱ መሠረት ዳግም ማሻሻል ሲቻል ነው፡፡ አፍሪካ የቅርብ ዓመታት የዴሞክራሲ ልምምድ አላት ስንል በተደጋጋሚ ጊዜ ሕገ መንግሥት ሊያሻሽሉ ይችላሉ እንጂ እያፈረሱ ሲገነቡ እንዳልነበሩ የሚታወቅ ነው፡፡ ለሆነም እኛም ከበረታንና ከተደማመጥን በዚህ ሕገ መንግሥት 26 ዓመታት አብረን መጓዝ ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊትም እያሻሻልንና ጎዶሎዎችን እየሞላን ዕልፍ ዘመን ተያይዘን እንጓዝበታለን፡፡ ለዚህም ነው አብረን ከመጣነው ይልቅ ገና አብረን የምንጓዘው ይበልጣል የሚባለው፡፡

አሁን ላይ ለውጥ እየተጀመረ እንኳን በግልጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ ገና ወደፊት አብረን የምንጓዘው ዘመን ይልቃል ሲባል ግን የምንጓዝበት መንገድ አልጋ በአልጋ ነው ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አሁንም ድረስ ለሕገ መንግሥታዊነትም ሆነ ለአገሪቱ ጉዞ አደጋ የሆኑ ችግሮች ገና መልክ መልክ አልያዙምና ነው፡፡ እነዚህ እንከኖች ከፅንፈኛ ብሔርተኝነት፣ ከማኅበራዊ የትስስር ገጾች የጥላቻ ማስፋፋት፣ የእኔ ብቻ ነው ትክክል ከማለትና የዕርቅ መንገድን ከመሳት ጋር ያላቸው ዝምድናን ለይቶ ለማረም መረባረብ ያስፈልገናል፡፡ እንደ መንግሥትም እንደ ሕዝብም፡፡

በእርግጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተፈቃቅደውና ተከባብረው በአንድ ላይ ለመኖር የጋራ ሰነድ ካፀደቁ 26 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህ የጋራ ሰነድ የጋራ ቤት ለመገንባት ውል ያሰሩበት የጋራ ፍኖተ ካርታቸው፣ የቃል ኪዳንም ማሰሪያቸው ጭምር ቢሆንም፣ በድንጋጌውም ሆነ በአፈጻጸሙ ምንም ችግር የሌለው ነበር ሊባል አይችልም፡፡ ከሕገ መንግሥቱ የሚመነጩ ችግሮችን በጥናት ላይ ተመሥርቶ መፈተሽም ያስፈልጋል፡፡

በቀዳሚነት የአስተዳደር ወሰንና የክልል አስተዳደርን ከጎሳና ብሔር ጋር ብቻ ማቆራኘቱ የውድቀቱ መጀመርያ ነው፡፡ የአገሪቱን ዋና ከተማና የኦሮሚያ ክልልን ጉዳይ የያዘበት መንገድ፣ የፌዴራል መንግሥት የሥራ ቋንቋ አጠቃቀም፣ የአንቀጽ 39 ጉዳይና መሰል ድንጋጌዎችም በጥንቃቄ ዳግም መታየት ያለባቸው ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ አሁን ያለው የለውጥ አመራር ያለው ቁርጠኝነት አጋዥ ስለሆነ፣ መላው የፖለቲካ ኃይሎችና ሕዝቡም በሆደ ሰፊነት በመጪው ዘመን በጋራ የምንኖርበትን ዘላቂ መንገድ አገናዝቦ መታገል ይጠበቅባቸዋል፡፡ የተበላሸውን ከማቃናት ይልቅ ጦር ለመማዘዝ ማሰፍሰፍ ጤነኝነት አይደለም፡፡

አንዳንድ የመስኩ ምሁራን አሁን ያለው ሕገ መንግሥት አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመፍጠር ግብ ያለው ነው ይላሉ፡፡ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ቀኖና ላይ የተመሠረተ ሕገ መንግሥት በመሆኑ፣ አሳታፊና አቃፊ አይደለም በሚል የሚተቹትም ትንሽ አይደሉም፡፡ ምንም ተባለ ምን እንደታሰበው ወደ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ መሄድ ያለበት ጉዞ በሚፈለገው ፍጥነት እየተተገበረ ካለመሆኑም ባሻገር፣ እንደ ሕዝብ ረዥም ርቀት አስተሳስሮን እንዲቀጥልም መደረግ አለበት፡፡

በእርግጥ መንግሥትም ቀደም ካለው ጊዜ አንስቶ ለኢኮኖሚ አንድነት የተሰጠውን ትኩረት ያህል ለፖለቲካ አንድነቱ አልተሰጠም ሲል ቆይቷል፡፡ ችግርን ማመን ወይም ችግሮችን መለየት የመፍትሔ ግማሽ አካል ነውና በስሜት ሳይሆን፣ በተጨባጩ መነጋገርና ቁርጠኝነት ለዘለቄታው የሚጠቅም ሕገ መንግሥትን አሻሽሎ ለትውልድ ማስተላለፍ የለውጥ ሁሉ ቁልፉ ኃላፊነት ነው፡፡ ስለሆነም ከዚህ በኋላ አብረን የምንሄደው ጉዞና ዘመን ይልቃልና ከወዲሁ መሠራት ያለበት ሁሉ በሁሉም ወገኖች ሊሠራ ይገባል፡፡

የማይካደው እውነት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በልዩነት ውስጥ አንድነት የነበራቸው በኢፍትሐዊ አገዛዞችም ዘመን ጭምር ነበር፡፡ ድርብ ጭቆና ያለባቸው ወገኖች ቢኖሩም ያልተጨቆነ ሕዝብም እንዳልነበረ ይታወቃል፡፡ ይሁንና እንደ በገዥዎች የከፋፍለህ ግዛ ሴራ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ካለመተዋወቅ፣ ካለመከባበርና ተቻችሎ ካለመኖር የተነሳ እኔ እበልጣለሁ በመባባልና ዝቅ ከፍ በመደራረግ ዘመናትን በግድ እንዲገፉ ተደርገዋል። ግጭት ውስጥ ገብተው ጥቃትም ተሰናዝረዋል። ቢያንስ ያን ምዕራፍ ከሞላ ጎደል ከበርካታ ዓመታት በፊት ተሻግረነው ሊያገረሽ አይገባም፡፡ እንዲያውም በመነጋገርና በዴሞክራሲያዊነት እያረቀቅነው መሄድ ይጠበቅብናል፡፡

በተለያዩ ፅንፈኛ ፖለቲከኞችና የሥልጣን ጥመኞች ስብከት ግን ወደ የተዛባ ግንኙነት ትርክትና የግጭት አዙሪት ለመግባት መንደርደር፣ ፍፁም ሊወገዝ የሚገባው ነው፡፡ አሁን በተለያዩ አካባቢዎች የሚታየው በማንነት እየተለዩ መገደል፣ ከአካባቢያቸው መሰደድ፣ መገለልና መሸማቀቅ ሊያሳዝነን የሚገባው ሁላችንንም ሊሆን ይገባል፡፡ ይህ ክስተት እየተባባሰ ከሄደ ለልማት ሊኖር የሚገባውን ተነሳሽነት ማወኩ አይቀሬ ነው፡፡ ድርቅና ረሃብም ይቀሰቀሳል፡፡ የአገር ገጽታ ከመበላሸቱ ባሻገር ወደ ተሻለ የአገር ግንባታ ምዕራፍ የሚደረገው ጉዞም ይስተጓጎላል። ከዚህ በባሰም መውጣት የማይቻልበት ቀውስ ውስጥ መግባት ይከተላል፡፡

በመሠረቱ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱም ቢሆን ከፍፁም አሀዳዊነት ተላቆ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ብዙ ትግልና መስዋዕትነት ተከፍሎበታል። ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ፣ እርስ በርሳቸው ከመተዋወቅም አልፈው ለጋራ አገራቸው ልማት በኅብረት ለመሥራትና በፍትሐዊነት ተጠቃሚ ለመሆን እንዲነሳሱ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ አስተዋጽኦ አላዳረገም ሊባልም አይችልም፡፡ ነገር ግን አሁን የምናየው የፌዴራሊዝም ሥርዓት፣ ኢትዮጵያዊያንን በማንነት በመከፋፈል የክልል አጥር ማበጀቱ መፍትሔ ካልተበጀለት አደገኛ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

አሁን በተደረሰበት የታሪክ ምዕራፍ ግን የሁሉም ሕዝቦች ዓላማ በአንድ አገር በመተባበር፣ በእኩልነትና በፍትሐዊነት መኖር እንዲሆን አመቺ የሆነ ፌዴራሊዝም በጋራ ሊደራጅ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከጠባብ ብሔርተኝነትና ለእኔ ብቻ ከማለት በመውጣት በመተሳሰብና በጋራ መኖር ይጠበቅብናል። ሁሉንም ብሔራዊ ጉዳዮቻችንን ለመወሰን በጋራ ስንቀመጥ መፍትሔው እጃችን ላይ እንደሆነ መረዳት አለብን፡፡

ፖለቲከኞች ወደ ራሳቸው ፍላጎት እየጠመዘዙት እንጂ፣ ከዚህ በኋላ አሀዳዊነትም ሆነ ጨፍላቂነት አብቅቶላቸዋል፡፡ ማንም ያለ ፍላጎቱ ተገዶ አንድ ቀን መቀጠል አይፈልግም፡፡ የኃይል ሚዛን ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ይህ አስተሳሰብ የሁሉም ሕዝቦች ሆኗል፡፡ ዛሬም ሆነ ወደፊት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፍላጎት ሥርዓቱ ለአንዱ ሰጥቶ ሌላውን የሚከለክል ሳይሆን፣ ሁሉንም በእኩልነት የሚያስተናግድ እንዲሆን ነው የሚባለውም ከዚሁ እውነታ አንፃር ነው።

እናም ይህን ፍላጎታቸውንና እምነታቸውን ማክበርና ማስከበር መንግሥትና የመንግሥት ኃላፊዎች በትኩረት የሚከታተሉትና የሚሠሩበት ሊሆን ይገባል። በተለይ የፖለቲካ መሪዎችና ድርጅቶች በዚህ ላይ ተመሥረተው አብሮነትን፣ ዕድገትንና ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚረዱ መንገዶችን መጥረግ ነው የሚበጃቸው፡፡

የለውጡ መሪ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) ደጋግመው እንደተናገሩትም ሆነ እንዳሳሰቡት፣ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ኃይሎች አሁን ያለውን ፌዴራላዊ ሥርዓትና ውጤቶቹን ማጣጣል ሳይሆን ተጋግዞ ለመሥራት፣ የተዛነፈ ካለም ለማረም ተቀራርቦ መነጋገር ያስፈልጋቸዋል። መንግሥትም ለዚህ አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል። ስለዚህ እንደ ፖለቲከኛ፣ እንደ ሕዝብም ሆነ እንደ መንግሥት የቆምንበትን መሠረት ፈትሾ ለዘላቂ ጥቅምና ነገ ትውልድ ስለሚኖርባት የጋራ አገር አስቦ መሥራት ያስፈልገናል፡፡ ኢትዮጵያዊያንን በማንነት እየከፋፈሉ ለማፋጀት ማድባት ዘመን ያለፈበት አስነዋሪ ድርጊት ነው፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ልጆቿን በጉያዋ አቅፋ እንደያዘች የህዳሴ ጉዞዋን ትቀጥላለች እንጂ፣ ወደ ቀድሞዋ አስከፊ ሁኔታ መመለስ ፈፅሞ አትፈልግም፡፡ ከዚያ ለመውጣትም በተለያዩ ጊዜያትና ሥፍራዎች ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል፡፡ ፅንፈኛና አፍራሽ ኃይሎች ውዥንብር ከመንዛት ባይወጡም፣ ልጆቿ ተቻችለውና ተከባብረው ለመኖር በቃል ኪዳን ተሳስረዋል፡፡ አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር በጋራ በሚገነቧት አገር በጋራ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተማምነውና ተሳስበው እንዲዘልቁ ማድረግ ግን፣ የመንግሥትና የዚህ ትውልድ ቀዳሚ ኃላፊነት ነው፣ መሆንም ይኖርበታል፡፡

በርካታ መፈታት ያለባቸው ችግሮች ቢኖሩም አሁን በኢትዮጵያ ብርሃን ፈንጥቋል፡፡ ልጆቿ ከድቅድቅ ጭለማ ወጥተው የብርሃን፣ የዕድገትና የብልፅግና ጎዳናውን እየዘለቁት ይገኛሉ። ነገር ግን በደንብ ሳይነጋ ማጨለምን የሚያልሙ ኃይሎች ከፊታቸው ተደቅነዋል። ሳይነጋ ጨለማ በህልም እንጂ በዕውን ሊሆን እንደማይችል ያልተረዱ እነዚህ ኃይሎች፣ የብርሃኑ ጭላንጭል ደማቅና ብሩህ ሳይሆን በጅምር ሊያስቀሩት ይደክማሉ። አሁንም በመንደር አስተሳሰብና በጥቃቅን የሠፈር አጀንዳዎች ጦር ሊያማዝዙን ይሻሉ፡፡ እነዚህን ማሳፈርና ማስቆም ብሎም ትልቁን አገራዊ ኅብረትና አብሮነት ማማተር ያለብንም እኛውና እኛው ብቻ ነን፡፡ በዚህ ላይ መንግሥትም ቆፍጣና አቋም ይዞ ሕግን ማስከበር ይጠበቅበታል፡፡ በሰይፍ የሚመኩ በሰይፍ ይወድቃሉና ጦረኞች ለጊዜው እንጂ መጨረሻቸው ውርደት ነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን ጦርነት ተወግዶ በሰላም ለመኖር ከአንድነታቸው በላይ ዋስትና እንደሌላቸው ሊጠራጠሩ አይገባም፡፡ ስለሆነም ዋነኛ መርሐቸው ሕግን ማክበርና ማስከበር እንደሆነ መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ሰሞኑን በአንዳንድ አካባቢዎች የተስተዋሉ እጅግ በጣም አደገኛ ጥቃቶችና ሕገወጥነቶችም ሆኑ ሌሎች ዳር የወጡና የተወለካከፉ አስተሳሰቦችን  እንደማይቀበሉ፣ ለአገራቸውና ለጋራ ብሔራዊ ፍላጎታቸው ታማኝና ዘብ በመሆን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ሁሉም የአገራችን ሕዝቦች በግልም ሆነ እንደ ቡድን  እኩልነታቸውን፣ አንድነታቸውንና በጋራ ለልማትና ለዕድገት መቆማቸውን ማረጋገጥ የሚችሉት በዚሁ መንገድ ብቻ ነውና፡፡ ከመለያየት አንድነታችን መብለጡን ነጋሪ እንደማያሻን በተግባር ማስመስከር አለብን፡፡ የጦርነት ነጋሪት ጎሳሚዎችን አሳፍረን አንድነታችንን በማረጋገጥ አገራችንን ወደ ዕድገት ጎዳና እንድታመራ እንረባረብ፡፡

ሰላም ለአገራችን ይሁን!

ከአዘጋጁ፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ