በበቀለ ሹሜ
ክፍልፋይ ወገንተኛትና አፈናቃይነት የአፈጻጸም ችግር አይደለም፣ ወይም ይህ ሰውዬ አላውቅበት ብሎ ያመጣው አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ለብሔር ጥያቄ መፍትሔ ነው ያለው የሕወሓት ‹መድኃኒት›› ያመጣው መዘዝና የተከለው ጠንቅ ነው፡፡ ይህ ሲባል የብሔረሰቦች ጥያቄንና መብትን ማዋደቃችን አይደለም፡፡ የብሔረሰቦች መብት መከበር ለዚህም የሚስማማ የመንግሥት ዓይነት ማደራጀት (ከአሀዳዊ ይልቅ ፌዴራላዊ) ተገቢም፣ የተሻለ አማራጭም እንዲያውም አማራጭ የሌለው ግዴታ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የብሔረሰቦች መብት መከበር በኢትዮጵያ ምንም አማራጭ የሌለው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያን አንድነት ያጠናከሩ የሚመስላቸው አንዳንድ ወገኖች የአንድነት መነሻና መሠረት መሆን የሚገባውን የብሔረሰቦች መብት መካዳቸው፣ ወይም የዜግነት መብት ተቀጥያ ማድረጋቸው የኢትዮጵያን አንድነት አለማገዙን ሊያውቁት ይገባል፡፡
ለብሔር ጥያቄ መልስ እሰጣለሁ ካለ የሕወሓት/ኢሕአዴግ የፖለቲካ ተግባር የተወለዱትን ችግሮች በአጭሩ ብናስቀምጣቸው በጎጆኝነት የእኔ የሆነና ያልሆነ ሕዝብ ብሎ መለየት፣ ከዚሁ ጋር የእኔ ብሔረሰብ የሚሉትን መሬት በመተሳሰብ ውስጥ መጠመድ፣ የእኔ የተባለ ሕዝብና መሬት ለይቶ ገዥነትንና በሊታነትን መቆጣጠር፣ በዚህም አማካይነት ጎጆኛ አዕምሮን ማስፋፋት (ከውጥንቅጥ ከተሜ አደግነትና ከአማራነት ጋር የተዛመደ ኢትዮጵያዊነት ላይ ያተኮረን ዕይታ በብሔር ማንነት በማፈርና ሌላውን በመዋጥ ትምክህታዊነት እየቀጠቀጡ ወደ ጎጆኛነት መበጣጠስ)፣ የአካባቢን ኅብረተሰብ በቤተኛነትና በባይተዋርነት ማንጓለል፣ ከዚህም ባስ ሲል ማፈናቀል፣ ብሔረሰብ/አካባቢ የለዩ የንግድ ተቋማትን ፈጥሮ አካባቢ አለፍ የሀብት ሽሚያ ውስጥ መግባት፣ ምድሬ በሚሉት ሥፍራ ውስጥ ግን በባይተዋርነት በዝባዥነት በፈረጁት ላይ አትነግድብን የሚል ቅዋሜና ውድመት ማድረስ ተብለው መጠቃለል ይችላሉ፡፡
እነዚህ ጣጣዎች ሥርዓቱ ያመጣቸው ሳይሆኑ ከአፈጻጸም/ከአያያዝ የፈለቁ ናቸው ባይነት እውነት መናገር? ወይስ በእውነታ ላይ ዓይን ጨፍኖ ምኞታዊነትን ሙጥኝ ማለትና ሕመምን መደበቅ? አዕምሯቸውን ያልዘጉ የራሳቸውን መደምደሚያ መቅረፅ እንዲችሉ ጥቂት ነገሮችን እናክል፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትና ፌዴራላዊ አወቃቀሩ ጎጇዊ ብሔርተኛነትንና የኢትዮጵያን እውነታ የማስተናገድ ዲቃላ ውጤቶች እንደ መሆናቸው፣ የችግር ምንጭነታቸው ድርሻ ከፊል ነው፡፡ እነሱ ራሳቸው የብሔርተኝነት ከፊል ውጤት እንደ መሆናቸው የችግር እናትነቱን ሥፍራ የሚወስደው ጎጇዊ ብሔርተኝት ነው፡፡
ብሔርተኝነት ‹‹ሀ›› ብሎ የሚጀምረው ሕዝቤ፣ ብሔሬ ወይም ብሔረሰቤ ብሎ ነው፡፡ ይህንን ብሎ ሲነሳ ሌላውን የእኔ ያልሆነ ሌላ ሕዝብ፣ የእነሱ ሕዝብ ብሎ መለየቱ ነው፡፡ በብሔሰብ ማንነት አለማፈርና መብትን አስከብሮ ከሌላው ጋር መኖር ከብሔርተኝነት ጋር በጣም የተለያየ ነገር ነው፡፡ ብሔርተኝት ብሔረሰባዊ መብትን አስከብሮ ከመኗኗር ያለፈ፣ ፕሮግራምን ነድፎ የያዘ ፖለቲካ ነው፡፡ በንቅናቄ መልክም ሆነ በፓርቲ መልክ ተደራጅቶ ወደ ሥልጣን ሲሄድም ሆነ፣ በሥልጣን ላይ ሆኖ ፕሮግራሙን እያናፈሰ ይቀሰቅሳል ይመለምላል፡፡ ሻዕቢያ፣ ኦነግም ሆነ ሕወሓት ሕዝቤ/መሬቴ ማለት የጀመሩት ገና በጎረቤት አገር ውስጥም ሆነ በበረሃ ውስጥ ሲላወሱ ነው፡፡ የይዞታ ካርታ የሠሩት ሁሉ ለሥልጣን ከመብቃታቸው በፊት ነበር፡፡ በ1983 ዓ.ም. ሻዕቢያ ድል መታሁ ሲል ከያዘው ውጪ ቀረኝ የሚለውን መሬት በመቆጣጠር እንቅስቃሴ ውስጥ ተጠምዶም ነበር፡፡ የኦነግ ዋና ሩጫም በአካልም በርዕዮተ ዓለምም የኦሮሞ ያለውን መሬት መቆጣጠር ነበር፡፡ ትግራይን ከመቆጣጠር አልፎ አዲስ አበባ የገባውና ኢሕአዴጋዊ የኢትዮጵያ ገዥነትን ያቀደው ሕወሓት ግን፣ በየብሔረሰቡ ብሔርተኞች በመብራት እየፈለጉ የመሻረክ፣ የማደራጀትና የማራባት አብሮም እነ ኦነግን ከመሳሰሉ ተቀናቃኞች ጋር የመሽቀዳደም ሥራ ነበረበት፡፡ በቤተኛነትና በመጤነት ማጥመድና ማፈናቀል በተግባር የተጀመረውም ገና በጠዋቱ ከ1983 ዓ.ም. ማክተሚያ ጀምሮ አማራን በነፍጠኝነት ከማዋከብ ጋር ነው፡፡ በ1983 ዓ.ም. የነሐሴው ቻርተር መሠረት በተካሄደው ሽንሸናም ሆነ በ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት በፀደቀው አወቃቀር ውስጥ፣ ሚዛን ያጡ እንደ ሐረርና ጋምቤላ ያሉ ሚጢጢዎችና ኦሮሚያና አማራ የሚባሉ ግዙፎች እንዲፈጠሩ ምክንያት የሆነውም፣ ከአጠራር አንስቶ ድርሻህ ቤትህ ይህ ነው የሚል መልዕክት የሚረጭን የ‹‹ክልል›› ስያሜን ያመጣውም ጎጆኛ ብሔርተኝነት ነው፡፡
የሐምሌ 15 ቀን 1983 ዓ.ም. ቻርተር በአንቀጽ 2 (ለ) ላይ ‹‹እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ በራሱ የተወሰነ መልክዓ ምድራዊ ክልል ውስጥ›› (ሰረዝ የተጨመረ) ቁልጭ አድርጎ ድርሻን ይናገራል፡፡ የ1987 ዓ.ም. የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 40 (3) ላይ በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ ያለ መሬት የመላው ሕዝቦቿ መሆኑን በመደንገግ በማያሻማ አኳኋን አንድ አገርነትን ያወጀ ቢሆንም፣ እያንዳንዱ ክልል ‹‹አገር›› አከልነትን እንዲያስብ የሚመች ድጥም አለበት፡፡ በአንቀጽ 39 (1-3) ‹‹የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች››ን መብት ሲያስቀምጥ የቀነሰው ነገር ቢኖር፣ ‹‹በራሱ›› የምትለዋን የባለቤትነት ገላጭ ነው፡፡ አንቀጽ (1) ላይ ባለው የክልሎች ዝርዝር በመጀመርያዎቹ አምስት ተራዎች ውስጥ ‹‹የትግራይ ክልል›› በማለት ዓይነት የአካባቢውን ስም ተከትሎ ‹‹ክልል›› የሚለው ቃል ይመጣል፡፡ ከስድስተኛው እስከ ስምንተኛው ተራ ውስጥ ላይ ዓይነተ ብዙነት ይጠቆማል፡፡ በተለይም ስምንተኛው ተራ ላይ ‹‹የጋምቤላ ሕዝቦች›› ሲባል እስከ አምስተኛ ተራ ቁጥር ‹‹ሕዝቦች›› አለመታከሉ፣ ሌሎቹ ከግዙፉ ብሔረሰብ እኩል ባለመብት እንዳልሆኑ ታስቦ ይሆን የሚል ጥያቄ የሚጭር ነው፡፡ ዘጠነኛው ላይ ደግሞ በነጠላ ‹‹የሐረሪ ሕዝብ ክልል›› መባሉ ቁርጥ ባለ አነጋገር የሐረሪ ድርሻ ለማለት የተፈለገ ያህል ያስገርማል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ በዚህ መልክ ይቀመጥ እንጂ፣ ክልሎቹን የሚገዙት ብሔርተኛ ፓርቲዎች ሰዎች ሲናገሩም ሲጽፉም ‹‹ብሔራዊ ክልል›› ማለታቸው የተለመደ ነው፡፡ የመለመዱ ብዛት፣ እኛንም በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ‹‹ብሔራዊ ክልል›› ተብሎ የተጻፈ እስኪመስለን ህሊናችንን ተጭኖ ኖሯል፣ ሕገ መንግሥቱን እስከ እናማመሳክር ድረስ፡፡
‹‹የትግራይ ብሔራዊ ክልል››፣ ‹‹የሶማሌ ብሔራዊ ክልል››፣ ‹‹የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል››፣ ወዘተ እየተባለ ሲነገር ቁልጭ ባለ መልክ ስለይዞታ መወራቱ ነው፡፡ እነዚህን ይዞታዎች የሚገዙት ብሔርተኛ ቡድኖች አጠራርም ባለ ‹‹ይዞታው››ን ሕዝብ የሚያሳውቅ ነው፡፡ የሚገርመው ታዲያ ‹‹ብሔራዊ ክልል›› የተሰኘው አጠራር በደቡብ ሕዝቦች ክልልም ላይ የተለመደ መሆኑ ነው፡፡
ሌላም የሚደንቅ ነገር አለ፡፡ በኢሕዴን ውስጥ የነበሩ አማራ ፖለቲከኞች ወደ ብሔረ አማራ ንቅናቄነት ወርደው በዚያው መቅለጣቸው፣ ነባር የብሔር ጭቆና ቁስልና እህህታ ያልነበረባቸው መሆኑ ብርታት እንኳ ሆኗቸው የሚገዙት ክልል ኅብረ ብሔራዊ ግቢ የመሆኑን እውነታ፣ ውስጣዊ የብሔረሰቦች አስተዳደሮች በመፍጠርና ከአማርኛ ውጪ በአገውኛ፣ በኦሮሚኛና በትግርኛ ሥርጭት በማካሄድ እንደገለጹ ሁሉ፣ የክልልሉንም የፓርቲያቸውንም መጠሪያ አርመው በአስተዳደር ግቢያቸው ውስጥ ያሉ ሕዝቦችን ኦሮሞ ነሽ ትግሬ ብሎ ያላስቀረ፣ ሁሉንም አካታች የፓርቲ ባህርይ በመያዝ ለቀሪዎቹ ብሔርተኛ ፓርቲዎች አርዓያ ሳይሆኑ መቅረታቸው ለምን የሚያሰኝ ይመስለኛል፡፡
የኢትዮጵያ መላ ሕዝቦች የዴሞክራሲ አገዛዝ ግንባታ ዕድል የተስተጓጎለው ሕወሓት/ኢሕአዴግ ሠራዊቱን የአገሪቱ የታጠቀ ኃይል ማደራጃ ሲያደርግ ነበር፡፡ ከዴሞክራሲ በመለስም፣ አገሪቱ ባላት የሙያና የዕውቀት አቅም ሙስናን እየታገሉ ዕድገትን የማራመድ አቅሞች ክፉኛ የመጎሳቆልና የመባከን ቀውስ ውስጥ የገቡትም፣ የከተማ ኢኮኖሚና ማኅበረሰብ ይቅርና የረባ ትምህርት ቀመስ የሰው ኃይል እንኳ ያልፈጠሩ ብሔረሰቦች ራሳቸውን የቻሉ ክልል ሲደረጉ፣ በሌሎች ሻል ያለ አቅም ባላባቸው አካባቢዎችም ቢሆን አድርጉ የተባሉትን ለማድረግ የሚመቹ እበላ ባዮችን እያግበሰበሱ በ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ማጥመቅ ሲካሄድና ከበረሃ የመጡ ታጋዮችን ከአቋራጭና ከሩጫ ሥልጠና/ትምህርት ጋር ወታደራዊ ባልሆኑ አውታራትም ውስጥ መሰግሰግ ሲመጣ ነበር፡፡ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ማቅረብ ከደርግ ጊዜ በበለጠ በሩ ወለል ያለለትም. የአቋራጭና የጥድፊያ ትምህርት ሲጀመርና ለወራት ሳይማሩ ለፈተና መቅረብና የይስሙላ ማሟያ ፈተና ወስዶ ማለፍ በመደበኛ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ‹‹ፍትሐዊ መብት›› ሲደረግ ነበር፡፡
ብሔርተኛ ቡድኖች በቻርተራዊ/ሕገ መንግሥታዊ የክልል ይዞታዎች ገዥ ሲሆኑና ክልሎች ውስጥ ክፍልፋይ ብሔርተኝነት እየተስፋፋ ሲሄድ፣ በዚያው ልክ የዕውቀትና የሙያ ብቃት የለሽነት ጎሰኛ አድሏዊነትን ተገን አድርጎ መሹለክለክ ቻለ፡፡ ‹‹ትምክህተኞች››ን ከጥቅምና ከእኩል መብት በመግፋትና የጭቁን ብሔረሰቦችን ያለፈ ተበዳይነትን በማካካስ ሽፋን ውስጥ፣ ተጠያቂነት የሌለበት ዘረፋም እየተባዛ ሄደ፡፡ በአማራ ላይ የተጀመረው ‹‹መጤ›› እየተባሉ እስከ መፈናቀል የሄደ መገፋትም በስተኋላ ለትግራዩ፣ ለኦሮሞው፣ ለጉራጌው፣ ለወላይታው፣ ለሶማሌው፣ ለኑዌሩ፣ ለአኙዋኩ፣ ወዘተ ሁሉ የሚደርሰውና ሁሉም አካባቢ የሚፈጽመው ለመሆን በቃ፡፡ በአጭሩ የጎጆ ብሔርተኛ ፖለቲካና ገዥነትን ስሙን ‹‹ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኛነት›› አልነው፣ አላልነው በኢትዮጵያ የ27 ዓመታት ልምድ እንደታየው፣ ጎሰኛ አድሏዊነትን በአስተሳሰብም በተግባርም የሚያራባ፣ ለብሔረሰቦች መብትና እኩልነት ዋስትና የማይሆን፣ የሙያ ሥነ ምግባርንም ሆነ የሰውነትና የዜግነት መብቶችን ለፍርድ አቅርቦ የሚያንገላታ ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ በኢትዮጵያ እውነታ የብሔረሰቦች መብቶች መከበርና እኩልነት የሚገኘው ከብሔርተኛ ገዥነትና ከብሔርተኝነት ሳይሆን፣ ከዴሞክራሲና ከዴሞክራትነት መሆኑ ቁልጭ እያለ ወጥቷል፡፡ ይህ ማጠቃለያ የኢትዮጵያን እውነታ ጠልቆ ከመመርመር የተገኘ ንድፈ ሐሳብ ሳይሆን፣ በሩብ ምዕት ዓመት ልምድ ጎጆኛ ብሔርተኛነት ያሳያቸውን ፀባያት ከማስተዋልና ይኼው ልምድ እንደ ዕጣን ዛፍ ያፈጨጨልንን ትምህርት ከመውሰድ ያላለፈ ነው፡፡
አኅጉር አቋርጦ የተሰደደ ፀጉረ ልውጥ ዜግነት ሲያገኝ በምናይበት፣ ከዚያም አልፎ የስደተኛ ልጅ በመወለድ ብቻ ባለሙሉ መብት የአገር ልጅነትን ተቀዳጅቶ ፕሬዚዳንት ሲሆን ባየንበት ዓለም ውስጥ እየኖርን፣ እኛ ግን ለረዥም ዘመን የተወራረሰ ማኅበራዊ ጀርባችንን ስተንና የዛሬ ብሔረሰባዊ ገጽታችንን በጠበቀ ጎጆኛነት ተቀንብበን እንገኛለን፡፡ የዚህ አመለካከት እስረኛ ሆነን የፌዴራል አካላት ያከፋፈሉንን የጎጆ መሬት ቅርጫ ማረጋገጫ እስካደረግን ድረስ (ለዚህ ዓይነት አሳቻ ጉዞ ሕገ መንግሥቱና አከፋፈሉ ያላቸው ከፊል አጋዥነት እስካልታረመ ድረስ)፣ በአንድ አገር ውስጥ ብዙ ‹‹አገሮች››፣ በአንድ ዜግነት ውስጥ ብዙ ‹‹ዜግነቶች›› መኖራቸው እያላተመን መኖሩ/ማስፈራቱ አይቀየርም፡፡ ይህ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ መደረግ ያለበት ጊዜውን ጠብቆ ሕገ መንግሥት ማሻሻል የሚያስችል መግባባት ውስጥ ስንደርስ ብቻ ሳይሆን፣ ሕገ መንግሥት ማሻሻል የሚያስችል ዝግጅት ለማድረግ ከበቃን በኋላ መሆን አለበት፡፡
በዚያው ልክ መብቶችን በሁሉም ሥፍራ እኩል የማስከበር ጉዳይ ፈተና መሆኑ ይቀጥላል፡፡ በ‹‹ክልሎች›› ውስጥ የሚገኙ በተወሰነ ሥፍራ ከምቸት ብለው የሚገኙ ግን ከባይተዋር የተቆጠሩ ማኅበረሰቦች ውለው አድረው ያለንበት መሬት ለእኛም የማንነት ይዞታችን ነው የሚል ጣጣ እንዳያመጡ፣ ክምችታቸውን በቅየጣም ሆነ በማፈናቀል የማሳሳትና በ‹‹ባለቤት›› ማኅበረሰብ/ማኅበረሰቦች ቋንቋ ውስጥ እንዲኖሩ የማድረግ ተግባር ይፈታተናል፡፡ አካባቢያዊ ሥልጣን የተወሰነ ማኅበረሰቦች ርስት እስከሆነ ድረስም ‹‹ርስተኞች›› ጨቋኝነት ውስጥ መቆየታቸው ‹‹ባይተዋሮቹ››ም መንጓለላቸው ይቀጥላል፡፡
ሕገ መንግሥቱ ምንም አለ ምን በተግባር እየሠራ ያለው ግንዛቤ ወሰንን የውስጣዊ አገር ድርሻ ማረጋገጫ አድርጎ የሚያይ እስከሆነ ድረስ፣ የወሰን ጉዳይ ተዋሳኝ ሕዝቦች በተስማሙበት አኳኋን ተፈታ/ችካል ያዘ ቢባል እንኳ የወሰን ውዝግብና ግጭት በቀላሉ የማይላቀቁት ሆኖ ሄድ መለስ ማለቱ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም መሬታችን እላፊ ሄደ ብሎ ነገር የሚገምድና ድጋፍ አሰባስቦ ወሰን ለማስቀየር የሚሞክር ክፍል ከተዋሳኞቹ ወገኖች ውስጥ አይታጣምና፡፡ በተለይ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪነትን ገጽታ ተመርኩዞ ማካለል በተካሄደበትና ከአንድ የበለጠ ቋንቋና ባህል ተጋሪነት በሚታይበት አካባቢ ቀዳሚው ገጽታ ሌላ ነበር፣ የአሁኑ ገጽታ የፍልሰትና የስደት ወይም የሌላ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ውጤት ነው የሚል መቃወሚያ አያጣውም፡፡
የእነ ሐረሪና የእነ ጋምቤላ፣ ወዘተ የሕዝብ ብዛትና የስፋት ሚጢጢነት ሌሎችም እኛስ ከማን አንሰን ክልል የማንሆን የሚል መነሳሳት ውስጥ እንዲገቡ አርዓያ ሆነው ከመቆማቸው በላይ፣ በልዩ ዕገዛ የማይጣጣ የልማት መዛነፍ የሚታይባቸው ሆነው መቆየታቸውም ሌላ ገመና ነው፡፡ የ‹አንዳንድ› ክልል ገዥዎች እንዲህ በድሎትና በዘረፋ ቅልጥልጣቸው ሲወጣ፣ ‹‹ልማቱ›› መሬት ውስጥ በተቀበረ ሙቀጫ ወቅጣ የምታበላውን ሴት አሳረኛ ኑሮ መዳሰስ እንኳ ለምን ሳይችል ቀረ? ለዚህ ዓይነቱ ጉድ አከላለሉ አላዋጣም?
እነዚህን የመሳሰሉ ችግሮችን ለመወጣት ብሔረሰባዊ ማንነትን ተቀዳሚ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ተከታይ ካደረገ አመለካከት መውጣት ወሳኝ ነው፡፡ ድርጊት (የታሪክ ክንዋኔዎችን ጨምሮ)፣ የአድራጊና የድርጊት ተቀባይ ቀላል መስተጋብር አይደለም፡፡ በድንጋይ ፈለጣ ሒደት ውስጥ የተፈለጥልኝና አልፈለጥም ግብግብ አለ፡፡ በፈላጩ በኩል የመሣሪያና የዘዴ ስህተት እስካለ ድረስ ትግሉ ከንቱ ድካም ከመሆን ባለፈ፣ በራስ አካልና በአካባቢ ላይ ያልተፈለገ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ ፈለጣ የሚከናወነው የጉልበትና የዘዴ ብልጫ የተገኘበትን ያህል ነው፡፡ ሰዎች በተናጠልም ሆነ በቡድን የሚያካሂዱት እንቅስቃሴ በቀጥታም ይሁን በኢቀጥተኛ መንገዶች ሁለት መስተጋብራዊ ውጤቶችን ያስከትላል፡፡ ሰዎች በማኅበራዊና በተፈጥሯዊ አካባቢያቸው ላይ የለውጥ አሻራ ያሳርፋሉ፡፡ እንቅስቃሴያቸው የጠየቃቸው መስተጋብራዊ ልፋት፣ የልፋታቸው መሳካትና አለመሳካት ደረጃና አነሰም በዛ የተለወጠ አካባቢያቸው በራሳቸው በሰዎቹ ላይም ለውጥ ያስከትላል፡፡ የዛሬው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና መልክዓ ምድርም የረዥም ዘመን ድርጊታዊ መስተጋብሮች ውጤት ነው፡፡ የዚህ መስተጋብር አድማስ ከዛሬዋ ኢትየጵያ አድማስ ርቆ ባህር የተሻገረና የብዙ ሰበዞችን ቀጥተኛና ኢቀጥተኛ ተራክቦዎችን ያስተናበረ ሒደት ነበር፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ የደረሰችበትን ምዕራፍ እንደ “ፐ” ብንወስደው፣ ቀደምት ታሪካችንን ደግሞ ጥንት ጥንት የሆነ ትንሽ ቦታ ላይ በ“ሀ” እና በኢ“ሀ” ሰበዞች መስተጋብር እንደጀመረ አድርገን ብናስብ፣ “ሀ” እና ኢ“ሀ” ተራክበው/ተላልሰው “ለ”ን በውጤትነት አስገኙ ልንል እንችላለን፡፡ በ“ለ” ውስጥ ቀዳሚዎቹ “ሀ” እና ኢ“ሀ” በተቀየረ መላላስ በ“ለ”ነት ውስጥ ታዝለዋል፡፡ “ለ” ደግሞ የራሱን መስተጋብር ከኢ“ለ” ጋር ያደርግና ወደ “ሐ” እውነታ ይወስደናል፡፡ በዚህ ዓይነት ተወራራሽ ጉዞ ዛሬ የደረስንበትን የኢትዮጵያ እውነታ እንዲወክል የመደብነው “ፐ” አንድ ቀላል ምልክት አይሆንም፡፡ ከ“ሀ” እና ከኢ“ሀ” መስተጋብር ተነስተን የተጓዝንባቸውን በፊደላት የተገለጹ እርከኖችን ሁሉ ቀዳሚያቸውንና ለጣቂያቸው ባካተተበት መልክ አላልሶ ይዟል፡፡ “ፐ” ከ“ሀ” እስከ “ፈ” ባሉ ጉዞዎች የታነፀ እርከን ነው እንደ ማለት ነው፡፡ በሌላ አባባል በሰሜናዊ ምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ሲጋጩ፣ እሳት ሲያቀጣጥሉ፣ ሲያተራምሱ፣ እሳት ሲያጠፉ፣ ሲያሸራርቡ፣ ሲመኖጫጭሩ፣ ሲያደበላልቁ፣ ወዘተ የነበሩ የድርጊት ሰንሰለቶች ሁሉ ዛሬ ግፈኛ/ጨካኝ የምንላቸው ጦርነቶች፣ ጭፍጨፋዎች፣ ባሪያ ፍንገላዎች፣ አካል ቅርጠፋዎች፣ ሰለባዎች፣ የሰው ሥጋ እስከ መብላት ያደረሱ ረሃቦች፣ የወረርሽኝ ሰደድና ርፍረፋዎቻቸው፣ ፍልሰቶች ሁሉ የእርስ በርስ ተራክቧቸውና ተፅዕኗቸው ሳይጠፋ ዛሬ ያለንን የአገር፣ የኅብረተሰብና የባህል ይዘት ለማነፅ ችለዋል፡፡ ዛሬ ባለን ቅንብር ውስጥ እጅግ በጣም ሩቅ የሆኑ የታሪክ ጣቶች ሁሉ አሉበት፡፡
ዛሬ በኦሮሞ፣ በጌዴኦ፣ በኮንሶ፣ በሲዳማ፣ በሐድያ፣ በአማራ፣ በአገው፣ በትግራይ፣ ወዘተ፣ ወዘተ መልክ የተገለጽነው የሕዝብ ጥንቅሮች የብዙ መዘናነቅ ውጤት ነን፡፡ ዛሬ የተገዳደሉትና ከኑሯቸው የተፈናቀሉት ኦሮሞዎች፣ ሶማሌዎች፣ ጌዴኦዎች፣ ከንሶዎች፣ አማሮች፣ ቅማንቶች፣ ወዘተ የቅርብ ዘመዳሞች ናቸው፡፡ በተለይ አማራና ኦሮሞ በጥንቅር ታሪካቸው ከሁሉም የአገሪቱ ሕዝቦች የተቀመሙ ሊባሉ የሚችሉ ናቸው፡፡ የልዩ ልዩ ብሔረሰብ መቀመሚያም ሆኖ ይሁን ብዙ ብሔረሰቦችን እየዘገነ ራሱን አባዝቶ፣ በአገሪቱ ውስጥ በሰፊው የተዘረጋው ኦሮሞ በዛሬው ኦሮሚያ ካርታ የሚሰፈር ነው? ከአገውነት፣ ከኦሮሞነትና ከአማራነት ጋር የተወራረሰው፣ ለጉራጌነትም ሆነ ለመንዜነት ድርሻ አዋጥቷል የሚባልለትና በመላ ኢትዮጵያ ውስጥ ተሠራጭቶ የመኖር ታሪክ ያለው ትግሬ ትግራይን እምዬ የሚል አስተሳሰብ አይጠበውም? ወላይታ፣ በርታ፣ ጉምዝ፣ አኙዋክ፣ ወዘተ ነባርነታቸው ዛሬ ተከማችተው በሚገኙባቸው ሥፍራዎች የሚለካ ነው? በጦርነት፣ በምርኮና በባሪያ ፍንገላ ታሪክ ውስጥ ደቡባዊ ምዕራባዊ ሕዝቦች ያልተረጩበትና ያልተለዋወሱበት፣ እትብታቸው ያልተቀበረበት፣ አፅማቸው ያላረፈበት (በሌላ አባባል ታሪካቸው ያልተዘረጋበት) የኢትዮጵያ መሬት የለም፡፡
የምኒልክን ዘመቻ በብርቱ የተጋተሩትና በብዙ ሺዎች በባርነት የመጋዝ ቅጣት የወረደባቸው ወላይታዎች ያልተበተኑበት፣ ዕንባቸውንና ላባቸውን ያልጠጣ፣ ዘራቸው ያልተቀየጠበት ማኅበራዊ ቅንብር በኢትዮጵያ ምድር የለም፡፡ በተለይ አዲስ አበባ ከተማ በግንባታዋም ሆነ በማኅበራዊ ጥንቅር ታሪኳ ውስጥ የወላይታዎችንና የምዕራባዊ ዳር ሰዎችን ጉልህ አሻራ ይዛለች፡፡ እነዚህ ቀላል ምሳሌዎች በኢትዮጵያ ኅብረተሰባዊና መልክዓ ምድራዊ ግንባታ ውስጥ በክፉም በደግም አስተዋፅኦ ያላደረገና ለእኩል ባለቤትነት የሚያንስ ማኅበረሰብ እንደ ሌለ፣ ዛሬ ባለ የጥንቅር ቆዳ ላይ ተመሥርቶ የአገር ባለቤትነትንና ባይተዋርነትን መለካትም ትልቅ ስህተት እንደሆነ የሚያሳዩ ይመስለኛል፡፡ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ማኅበረሰባዊ ካርታ የጀርባ ታሪክ ውስጥ የሁላችንም ሱታፌ፣ የዘር ውላጅና የባህል ፍንጥቅጣቂ እንዳለ ከተረዳን ዛሬ ሥፍራ ለይተን አባራሪና ተባራሪ ለመሆን ባበቃን ግልብ አስተሳሰብ የምናፍርበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም፡፡
ሁለት ቦታ ከተቆረጥን በኋላም የደም ጎርፍ ከመፍጠርና ከመጠቃቃት ያላመለጥነው ዘመዳሞቹ የኤርትራና የኢትዮጵያ ልጆችም፣ በቅሌታችን አፋችንን የምንይዝበት ጊዜም ይኼው እየመጣ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ በደም ግብርና በፀብ የማቀቅንበትን የቅኝ ግዛት አጥር ሰብረን ነፃ አልወጣንም፡፡ አንድ ቀን፣ ወደፊት ግን ይህ ነፃነት መምጣቱ አይቀርም፡፡ ታሪክ የሚያስተምረን ነገር ቢኖር ጥልም ሆነ ፍቅር፣ የአገር ቅርፅም ሆነ ስፋትና ጥበት ቆሞ የሚቀር ነገር እንዳልሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያለችበት አፍሪካ ቀንድ በተራክቦው የተለወጠ ነገር ይዞ መምጣቱ አይቀርም፡፡
ቅድም በ“ፐ” የወከልናት የዛሬዋ ኢትዮጵያም “ፐ” ላይ ደርቃ አትቀርም፡፡ ጦርነት፣ ምርኮ፣ ፍልሰት፣ መዋዋጥ፣ ወዘተ እያጎባጎበ ያጎናፀፈንን አጠቃላይ ማንነት አኮስሰን የዛሬ የብሔረሰብ ገጽታ ላይ ተሰክተን ከዚህች እስከዚህች ድረስ አንተን የማይጨምር የእኔ ብቻ በሚል ክፍፍል ውስጥ እስከቆየን ድረስ፣ በቅራኔዎችና በግጭቶች እንግልት አሳራችንን ከማብዛትና ከማራዘም በቀር የምናተርፈው የለም፡፡ እስካሁን ያለፍንበት የ27 ዓመታት ልምድም አፍ አውጥቶ አመለካከታችንን እንድናርም እየመከረን ነው፡፡ ምክሩን ከሰማን ተያይዞ ሰላምንና ግስጋሴን ማጣጣም ይሰምርልናል፡፡ የታሪክን ምክር አልሰማ ካልን ተበታትኖ ሲዖል ውስጥ መግባት ምን እንደሆነ እናያለን፡፡
የሶማሌ ክልል (የ2010) መራር ልምድ በመንታ ሻማነቱ ወደር የለውም፡፡ አንዱ የሻማው ክፍል የሶማሌ ሕዝብ በአንድ ግለሰብና ማፊያዊ ባህርይ ባለው ቡድኑ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ግፍ ሲቀበል መቆየቱ፣ በብሔርነቱ ተከልሎ በብሔር በተደራጀ ፓርቲ መገዛት የሕዝብን ራስ በራስ መተዳደርን እንደማያቀዳጅ፣ የሕዝብ አስተዳደርን መቀዳጀት ማለት ዴሞክራሲ ውስጥ መግባትና ሁሉን አሳታፊ የሕዝብ አስተዳደርን ገንብቶ የሰው ልጆችንና የዜጎችን እኩልነት መኖር መሆኑን ከየትኛውም አካባቢ በላቀ ደረጃ አስተምሯል፡፡ ሌላው የሻማው ክፍል ደግሞ በብሔር አጥር ውስጥ መግባትና በብሔር ፖለቲካ ውስጥ መዋኘት ምን ያህል በብሔር አድሎኝነትና ጥላቻ ህሊናን ሊመርዝ፣ ከዚያም ብሶ ፈላጭ ቆራጮችና ሌቦች ሃይማኖቶችንና ብሔረሰቦችን ያነካካ ፍጅት እስከ መደገስ ድረስ ሊያወናብዱበት እንደሚችሉ በሰቅጣጭ ጭካኔዎች አድምቆ አሳይቷል፡፡ በዚህም አማካይነት የሁሉም አካባቢ ሕዝቦችና ወጣቶች በቶሎ ዓይናቸውን እንዲገልጡ፣ አሁን ለዴሞክራሲ እንግዳ በመሆናችን ደረጃ ላይ በብሔርተኝነት ድጥ ተንሸራትቶ ፈላጭ ቆራጭነት ውስጥ እንደገና ላለመውደቅም ሆነ ትርምስ ውስጥ ላለመስመጥ ዋስትናችን የዴሞክራሲ ሥርዓት፣ የዜጎችን እኩልነትና የሰው ልጆችን መብት አጥብቆ መያዝ እንደሆነ፣ ይህንንም ለማድረግ ኅብረ ብሔራዊ ጉድኝት በአካባቢ ደረጃ መፍጠር የበለጠ አቅም እንደሚያስገኝ በውስጠ ታዋቂ አስተምሯል፡፡ ለምሳሌ ሶማሌና ምሥራቅ ኦሮሚያ ቢጎዳኙ በአንድ ድንጋይ ሁለት ውጤት ከማግኘት በቀር የሚታጣ መብት አይኖርም፡፡
በአንድ የጋራ አስተዳደር ውስጥ ባለ ክፍላዊ የአስተዳደር አካባቢዎቻቸው ውስጥ በየቋንቋቸው ከመሥራታቸው ሌላ፣ አንዳቸው የሌላቸውን ቋንቋ የመማር ዕድል ሊያመቻቹ ይችላሉ፡፡ ልሳነ ብዙ ከመሆን ዕድል በላይ ደግሞ፣ መጎዳኘታቸው ኅብረ ብሔራዊ እኛነትን፣ ኅብረ ብሔራዊ የጋራ አስተዳደርን፣ የጋራ የፖሊስና የጋራ የዳኝነት አውታራትን ስለሚያስገኝላቸው ብሔርተኛ አድሏዊነትን ለመታገል ጥሩ አቅም ያገኛሉ፡፡ ቢያንስ ዴሞክራሲና በእኩልነት መተያየት ባህላችን እስኪሆን ድረስ እንደ ምሳሌው እየተቀናጁ በኅብረ ብሔራዊ ግቢ ውስጥ መኖር ለሁላችንም አስፈላጊ ሳይሆን ይቀራል? ቢሆንስ ግን ለዚህ ዓይነት መፍትሔ የዛሬ ህሊናችን ተዘጋጅቷል? ወይስ አሁን በምንገኝበት የአወቃቀር ግቢ ውስጥ ሆነን ዴሞክራሲያዊና ኢአግላይ የአመለካከት፣ የፓርቲና የመንግሥት አውታራት ማሻሻያ በማድረግ የብሔረሰቦች ሰላም፣ የዜጎችና የሰዎች መብት የተከበረበት ኑሮ መምራት እንችላለን? ወጣት ምሁራን አስቀድሞ አቋም በተደረገ ደረቅ አመለካከት ሳይታሰሩና ሳይጋረዱ ግማሽ ሊጥ፣ ግማሽ ብስል የሆነ ድምዳሜ ለማድረግ ሳይቸኩሉ ነባራዊና ህሊናዊ እውነታችንን ይመርምሩ እስኪ!!!
እንዲህ ያለ መነጋገርና መደማመጥ ያስችላል ተብሎ የታመነበት ለውጥና ሽግግር ውስጥ ብንገባም፣ ደም መቃባትና መፈናቀል በእስካሁኑ ብቻ ሊያበቃልን አልቻለም፡፡ በራሱ በለውጡ ውስጥ በኖርናቸው ዓመታት እንኳን፣ የመጋጨት ባይተዋር ተደርጎ የመንጓለያ፣ የመፈናቀልና የመጠቃት መከራን ያልቀመሰ የለም፡፡ ብሔርተኝነት ውስጥ ፅንፈኝነትና በቀልተኝነት ጥርሱን አውጥቶ ሕዝቡን አጭዷል፡፡ ለውጡንና ሽግግሩንም ጎድቷል፡፡
አሁን አዲስ ሕይወትና መልክ ይዞ ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ደቡብ ጉራፈርዳ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ፣ ወለጋ ጉሊሶ እያለ ከአንዱ ሲሉት ወደ አንዱ የሚሄድ ማንነት ላይ ያተኮረ አረመኔያዊ ግድያ ከዛሬ 30 ዓመት ከተተከለው ክፍልፋይነት ሕዝብን ቤተኛና ባይተዋር አድርጎ ‹‹ካቆራረጠው›› መዘዝ የመነጨ ቢሆንም፣ ዓላማው ግን የተለየና ይበልጥ አደገኛ ነው፡፡ የዚህ የአሁኑ ዙር አረመኔያዊ ግድያ ዒላማ የአማራ ክልል ሕዝብን አጭሶና የጭካኔ አዘቅት ውስጥ አውርዶ ከዚያም በኦሮሚያ ላይ በቀል እንዲጀመር፣ በዚህም አማካይነት የተያዘው የአማራና የኦሮሞ ፓርቲዎችና ምሁራን ምክር እንዲከሽፍ፣ በኦሮሚያ አካባቢ ሙሉ የማፅዳትና የበቀል ፍጅት እንዲጀምር፣ በዚህም ብልፅግና ፓርቲም ኢትዮጵያም ተተርትረው ድብልቅልቃቸው እንዲወጣ ማድረግ ነው፡፡ የተደገሰልንን ይህንን የመሰለ የአገር ሞት የምንቋቋመው ዴሞክራሲን ራሱን በማደላደልና በማቋቋም ነው፡፡
ዴሞክራሲን ለማደላደልና ለማቋቋም ያልቻልነው ደግሞ መንግሥታዊ የሥልጣን መዋቅሮችን ከአንድ ፓርቲ ወገናዊነት ተላቀው እንዲደራጁ ባለመድረጋችን፣ ይልቁንም በፓርቲ መቃኘታቸውን ትክክኛና አስፈላጊ አድርጎ ከማዋቀራችንም በላይ፣ የሕዝቦችን ማኅበራዊ ህሊና በፓርቲ አስተሳሰብ መቆጣጠርን ትግሉ አድርጎ ይዞ የቀጠለ ገዥ በመኖሩ ነበር፡፡ የችግራችን አናት ይህ ሆኖ እያለም አንድ ላይ መሆን አንድ ላይ መያያዝ አቅቶን ኖሯል፡፡ ብሔርተኛ አስተሳሰብና አገዛዝ ደጋፊዎችንም ተቃዋሚዎችንም በጥላቻ ስሜት እየመረዘ፣ አዕምሮና ማኅበራዊ ግንኙነቶቻችን ለመከታተፍ ከሩብ ምዕት ዓመት በላይ ዕድሜ አግኝቶ አምሶናል፡፡ ብሔርተኛ ፖለቲካ፣ አገዛዝና አደረጃጀት ያደረሰብን መከታተፍን የመናቆር ሥነ ልቦና ጭፍን ብሔረሰባዊ ጥቃትንና መበቃቀል ውስጥ ዘፍቆናል፡፡
ከዚህ ለመውጣት አሁንም በዋናው ጉዳይ ላይ እንስማማ፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ በማናቸውም ዓይነት ጥያቄ ለውጡና ሽግግሩ የሚይዘውን የሚጨብጠውን እንዲያጣና ራሱን ለውጡን በማጨናገፍ ሳይሆን፣ ለለውጡ ሰላም በመስጠትና ለውጡ ዴሞክራሲን እንዲያደላድል ማድረግ ነው፡፡ በሕገ መንግሥታዊው መዋቅር ውስጥ ኢትዮጵያን እውነተኛ ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ሪፐብክ ማድረግ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡