Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኮሜርሻል ኖሚኒስ በትራንስፖርት ዘርፍ ሊሰማራ መሆኑን ገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሲሳይ ሳህሉ

ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በሦስተኛ ወገን አገልግሎት ሰጪነት ሲሠራ የቆየው ኮሜርሻል ኖሚኒስ፣ በትራንስፖርት ዘርፍ ለመሰማራት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ መሠረት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አማካይነት ተቋቁሞ የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት ላይ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡ ድርጅቱ የሰው ኃይል በማቅረብ፣ በሀብት አስተዳዳሪነት፣ ትዕይንት በማዘጋጀትና ሌሎች የሦስተኛ ወገን ሥራዎችን አካቶ ከ12 ዓይነት በላይ የአገልግሎት ዓይነቶችን በማቅረብ የሚታወቀው ኮሜርሻል ኖሚኒስ፣ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኙ መሰል ተቋማት መካከል በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ አሥር ተቋማት ውስጥ ለመካተት እንደሚሠራ ሐሙስ፣ ኅዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሪፖርተር ጋር ቆይታ የነበራቸው የተቋሙ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ዋቅቶላ ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ የአገሪቱን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ በተያዘው ዓመት ለሙከራ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎችን ሥራ ለማስጀመር ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር እየተወያየ እንደሚገኝ ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡

በ100 ተሽከርካሪዎች የሙከራ አገልግሎት ለመጀመር ያቀደው ተቋሙ፣ ዘመናዊ ተሽካርካሪዎችን ከውጭ በማስገባት ከአዲስ አበባ ከተማ ባሻገር በሚገኙ ከተሞች ጭምር በማሰማራት የትራንስፖርት ችግርን ለማቃለል ያግዛል ያለውን እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ኮሜርሻል ኖሚኒስ ከትራንስፖርት በተጨማሪ በውጭ አገር ለሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው መሥራት የሚችሉ በተለያዩ የሙያ ዓይነቶች የሠለጠኑና በርካታ ሠራተኞችን በውል ስምምነት አማካይነት ለማቅረብ ጥናት እያካሄደ እንደሚገኝ አቶ አሰፋ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ይህም በየጊዜው ተመርቀው ነገር ግን የሥራ አማራጮችን አጥተው የተቀመጡ ዜጎችን በትልቁ ይጠቅማል ብለን እናስባለን፤›› ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ በተዘው ዓመት ጥናቱን በማጠናቀቅ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመነጋገር ከታች የትምህርት ደረጃ ጀምሮ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ባለው የትምህርት ርከን ተመርቀው ያለሥራ የተቀመጡ ዜጎችን ወደ ውጭ በመላክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የሚሠራበት እንቅስቃሴ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በሥሩ ለሚያስተዳድራቸው ከ30,000 በላይ ሠራተኞችን ጨምሮ ለሌሎችም  ተቋማት አገልግሎት መሥጠት ለሚችሉ ዜጎች እንደ ሥልጠና ማዕከል በመሆን የሚያገልግል የሥልጠና ማዕከል የመገንባት ዕቅድ የያዘው ኮሜርሺያል ኖሚኒስ በመጪዎቹ ዓመታት ውስጥ በምሥራቅ አፍሪካ ተመራጭ የሦስተኛ ወገን አገልግሎት ሰጪ ተቋም ሆኖ ለመገኘት እየሠራ እንደሚገኝ አቶ አሰፋ ገልጸዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች