ሥራ ሳይጀምር በሥራ ላይ ከሚገኙ ባንኮች የላቀውን የተከፈለ ካፒታል በማሰባሰብ ገበያውን እንደሚቀላቀል የሚጠበቀው አማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር፣ በሀብት አሰባሰብም ሆነ በባለአክሲዮኖች ብዛት ታሪካዊ ሊባል የሚችል ውጤት አስመዝግቧል፡፡ በአገሪቱ የባንክ ሕግ መሠረት አማራ ባንክ ለምሥረታ የሚያስፈልገውን 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ማሟላት የቻለው፣ የአክሲዮን ሽያጭ በጀመረ በሦስተኛው ወር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የአክሲዮን ሽያጩን በማራዘም ገና ሳይመሠረት 4.8 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ማሰባሰብ ችሏል፡፡ በምሥረታ ላይ የሚገኘው አማራ ባንክ፣ ይህንን ያህል ሀብት አሰባስቦ ምሥረታውን በይፋ ሳያካሂድ እስካሁን መቆየቱ ጥያቄ ቢፈጥርም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ምሥረታውን ባሰበው ጊዜ ማካሄድ እንዳልቻለ የባንኩ አደራጆች ይገልጻሉ፡፡ ከሰሞኑ ምሥረታውን እያጠናቀቀ የሚገኘው የአማራ ባንክ፣ በአንድ ዓመት ከሁለት ወራት ቆይታው ያከናወናቸውንና መጪውን የምሥረታ ጉባዔ ለማካሄድ ስለመዘጋጀቱ ይፋ በተደረገበት መግለጫ፣ የምሥረታ ጉባዔውን በውክልና ለማካሄድ እንደተወሰነ አስታውቋል፡፡ በውሳኔው መሠረት እስከ ኅዳር 2013 ዓ.ም. መጨረሻ የመሥራቾችን ውክልና በማጠናቀቅ ጉባዔውን ለማካሄድ ስለማቀዱ፣ የአማራ ባንክ አደራጅ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፈንታ ገልጸዋል፡፡ ዳዊት ታዬ በዚሁ ጉዳይ ላይ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የአማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ የሆነውን ካፒታል በማሰባሰቡ ሥራ የሚጀምርበት ጊዜ መቼ እንደሆነ እየተጠበቀ ነው፡፡ መሥራች ጉባዔውን በማካሄድ ሥራውን ለመጀመር ዘግይቷል የሚሉ አስተያየቶች እየተሰሙ ነው፡፡ ምሥረታው ለምን ዘገየ?
አቶ መላኩ፡- ይህ ሁሉንም ለውጥ በአንድ ምሽት ለማየት ከመፈለግ የመነጨ ነው፡፡ ይህ አዎንታዊ ነው፡፡ ሊሆን ግን አይችልም፡፡ ወደ እውነታው ስንመጣ፣ አማራ ባንክ እንቅስቃሴ ከጀመረ አንድ ዓመት ከሁለት ወራት ሆኖታል፡፡ ኮሮና ከመምጣቱ በፊት በሰባት ወራት ውስጥ ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል በማሰባሰብ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ባለአክሲዮኖችን ማካተት ችሏል፡፡ በሰባት ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲህ ተሠርቶ አያውቅም፡፡ ይህ ታሪካዊ ነው፡፡ በዓመታት እንኳ እንዲህ ባለ ደረጃ አልተሠራም፡፡ ስለዚህ ፍላጎት አንድ ነገር ሆኖ፣ ዋናው ግን ወደ ኅሊና መምጣት ነው፡፡ እውነታው ደግሞ ሌላ ነገር ነው፡፡ እስካሁን ተመሥርተው ወደ ሥራ የገቡ ባንኮች ምን ያህል ጊዜ ነው የፈጀባቸው? በአንድ ዓመት ጣጣውን ጨርሶ ወደ ሥራ የገባ አለ? ከዚህ አንፃር መመዘን ያስፈልጋል፡፡ ፍላጎቱ ከፍተኛ ስለሆነ ከዚያ አኳያ የሚሰነዘር አስተያየት ነው፡፡ ኮቪድ-19 ባይኖር ኖሮ አራት ቢሊዮን ብር ሰብስበን ምሥረታ ልናደርግ የተዘጋጀነው በሰባት ወራት ውስጥ ነበር፡፡ ኮቪድ ሲመጣ ስብሰባ ማካሄድ አልቻልንም፡፡ በመስከረም 2013 ዓ.ም. ስብሰባዎች ለማካሄድ የሚያስችል መመርያ እስኪወጣ ድረስ ስብሰባችንን ማካሄድ እንደምንችል ጥናት አድርገን ሐሳብ ብናቀርብም አልተሳካም፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ነው የገደበን እንጂ ምሥረታውን በተባለው ጊዜ ማካሄድ እንችል ነበር፡፡ ሁለተኛ ይህ የተነሳሳው የካፒታል ማሰባሰብ ሥራ በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በነገራችን ላይ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሕግ ለመመሥረት የሚያስፈልገው የ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ ይህን ይዘን ሥራ መጀመር እንችል ነበር፡፡ መለኪያው ይህ ብቻ ከሆነ ወዲያው ወደ ሥራ መግባት እንችል ነበር፡፡ በዚህ ካፒታል መጀመር ግን ዘላቂ ሆኖ ለመጓዝ አያስችልም፡፡ ስለዚህ ካፒታል ለማዋጣት የተነሳሳውን ፍላጎት አልፈልግም ብሎ መዝጋት ነው? ወይስ የተሻለና የበለጠ ሀብት ማሰባሰብ ነው የሚጠቅመው? ሀብት ማሰባሰቡ ተጀምሮ ከሚቆም ይልቅ በዚያው መቀጠሉ ባንኩ የተሻለ አቅም ይዞ እንዲነሳ ዕድል ሰጥቶታል፡፡ ስለዚህ በእኔ እምነት ተጓቷል፣ ተራዝሟል ለሚለው ምልከታ አንዱ ምክንያት ከመቻኮል የመነጨ ነው፡፡ ሁለተኛው በባንኩ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ለማሳረፍ የሚነሱ ነገሮች ስላሉ እንጂ ዘገየ ሊባል አይችልም፡፡ ባለው ሁኔታ እንዴት አድርጎ ጉባዔውን ማካሄድ ይቻል ነበር ብሎ ማሰቡ ጥሩ ነው፡፡ ስለዚህ በምንም ሁኔታ ዘግይቷል የሚያስብል አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ከአንድ ዓመት በላይ በባንኩ ምሥረታ ሒደት ላይ ቆይታችኋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ምን ሠራችሁ? ከአክሲዮን ሽያጭ አንፃር ምን ደረጃ ላይ ናችሁ?
አቶ መላኩ፡- የአክሲዮን ሽያጩን የጀመርነው ነሐሴ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ነው፡፡ ሽያጩ ከተጀመረ በኋላ የምሥረታ ጉባዔውን ለማካሄድ ሚያዝያ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. አቅደን ነበር፡፡ ሦስት ጊዜ የአክሲዮን ሽያጩን አራዝመናል፡፡ ያራዘምነው ያልገዙ በርካታ ሰዎች ስላሉ ይራዘም የሚል ጥያቄ ስለቀረበ ነው፡፡ የተነሳሳው የሕዝብ ስሜት ለሀብት ማሰባሰብ ሥራ ይጠቅም ስለነበር ይህንን ዕድል መጠቀም እንደሚዋጣ በማመናችን ጭምር የአክሲዮን ሽያጭ ጊዜ ማራዘሚያዎችን አድርገናል፡፡ በተጨማሪም በባንኩ ውስጥ ዳያስፖራውን ለማካተት ስለተፈለገ ዳያስፖራዎች አክሲዮን እንዲገዙ ለማስቻል የሽያጭ ጊዜውን ማራዘሙ ተገቢ ነበር፡፡ ነገር ግን ዳያስፖራዎች በባንክ ውስጥ እንዲሳተፉ የሚያስችለው ሕግ የወጣው ጳጉሜን 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ነው፡፡ ዳያስፖራዎች በባንክ ውስጥ መሳተፍ የሚያስችሏቸውን ማስፈጸሚያ ሰነዶች የወጡት የካቲት 2012 ዓ.ም. ነው፡፡ ስለዚህ ማስፈጸሚያው እስኪወጣ መጠበቅ ስለነበረብን የአክሲዮን ሽያጩ እንዲራዘም ተደርጓል፡፡ ይህንን በማድረጋችንም የባንኩን ካፒታል ለማሳደግና አቅሙን ከፍ ለማድረግ አስችሏል፡፡ ኢኮኖሚው ከመንግሥት ቁጥጥር ነፃ እየሆነ ሲሄድ በትልቅ ካፒታል ለሚሠሩ ባንኮች ሕልውናና አዋጪነት ላይ በእጅጉ ይጠቅማቸዋል፡፡ ዘርፉ ክፍት መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ስለዚህ የተሻለ ካፒታል መሰብሰብ አስፈላጊ በመሆኑ ያንን አሳክተናል ብለን እናምናለን፡፡
ሪፖርተር፡- በመነሻ ዕቅዳችሁ የአክሲዮን ሽያጩን ለመጠናቀቅ ያቀዳችሁት ኅዳር 2011 ዓ.ም. ነበር፡፡ የአክሲዮን ሽያጩን ካራዘማችሁ በኋላ የተገኘው ውጤት ምን ይመስላል?
አቶ መላኩ፡- እስከ ኅዳር 2012 ዓ.ም. ድረስ ባለአክሲዮኖች የገዙትና የተፈረመው ካፒታል 2.6 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ የተከፈለው የካፒታል መጠን ደግሞ 1.9 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ አክሲዮኖቹን የገዙ ሰዎችና ኩባንያዎች ብዛት 70 ሺሕ የሚጠጉ ነበሩ፡፡ የአክሲዮን ሽያጩን ባራዘምንባቸው ጊዜያት በአማካይ በአንድ ቢሊዮን ብር ሽያጩ እያደገ ነበር፡፡ በኮሮና ምክንያት አቁመን እንኳ እስከ 800 ሚሊዮን ብር አክሲዮን ሸጠናል፡፡ አሁን ባለው ደረጃ የተፈረመ ካፒታሉ 6.4 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የተከፈለው የካፒታል መጠን 4.8 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ አክሲዮኖችን የገዙት ሰዎች ቁጥር ከ155 ሺሕ በላይ ደርሷል፡፡ ይህ የካፒታል መጠን እስከ አክሲዮን ሽያጩ መዝጊያ ድረስ ይህ እያደገ እንደሚሄድ እናምናለን፡፡ አሁን በያዝነው ዕቅድ የአክሲዮን ሽያጩ መዝጊያ ጊዜ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ መጠን ባለአክሲዮኖችን ያሰባሰበ ተቋም የለም፡፡ ከ155 ሺሕ ባለ አክሲዮኖችን በአንድ ቦታ ለስብሰባ መጥራት አዳጋች በመሆኑ ማስተዳደሩ ከባድ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ምሥረታ ለማካሄድ ፈታኝ መሆኑ ስለማይቀር እዚህ ላይ ምን እየሠራችሁ ነው?
አቶ መላኩ፡- ጉባዔውን ለማካሄድ አማራጭ ሐሳቦችን በማጥናት የተለያዩ ሥራዎች ሠርተናል፡፡ ከጉባዔው መካሄድ ጀምሮ ትልቅ ፈተና የሚሆነው አክሲዮኖችን ማስተዳደር ነው፡፡ በአገራችን ታሪክ ያልታየና 155 ሺሕ ባለአክሲዮኖችን ያሰባሰበ ባንክ ነው፡፡ ይህንን የአክሲዮን ማስተዳደር ጉዳይ እንዴት እንሄድበታለን? የሚለውን ከመረጃ ማጥራት ጀምረን እየሠራንበት ነው፡፡ ጉባዔውን ለማካሄድ ሌላኛው ተግዳሮት የነበረው የንግድ ሕጉ ነው፡፡ ሕጉ ከ50 ዓመታት በላይ ቆይቷል፡፡ በሕጉ አክሲዮንን በተመለከተ የተጠቀሰው አክሲዮን የገዙ ሰዎች መሥራች ጉባዔያቸውን በአካል በመገኘት ወይም በወኪሎቻቸው ይገኛሉ ይላል፡፡ በዚያን ጊዜ ሕጉ ሲወጣ የነበረው እውነታና አሁን ያለንበት ሁኔታ የተለያየ ነው፡፡ ሕጉ በአካል መገኘትን ብቻ ነው የሚፈቅደው፡፡ ቴክኖሎጂን አይፈቅድም፡፡ የ155 ሺሕ ባለአክሲዮኖችን የሚያስተናግድ መሠረተ ልማት አለን ወይ? የሚለው ሲነሳ ሕጉ የማይመልሰው ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በዚህ ምክንያት 155 ሺሕ ሰው እንዴት ይሰበሰባል? ፎረም ለማሟላት 50 +1 በሚለው መሠረት ከሰባ ሺሕ በላይ ሰዎች እንዴት መሰብሰብ ይቻላል የሚለው ችግር ነው፡፡ በኮቪድ ምክንያት የተጣለው የመሰብሰብ ክልከላ ሌላ ችግር ነበር፡፡ በእኛ በኩል ግን ጉባዔውን ለማካሄድ ቴክኖሎጂን ከመጠቀም ጀምሮ ያሉ አማራጮችን አቅርበን ነበር፡፡ ይህ ጉዳይ ከንግድ ሕጉ መሻሻል ጋር ይታያል ተብሎ ነበር፡፡ ይህ እስኪሆን ከመጠበቅ ጉባዔውን ለማካሄድ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ያስፈልጋል ብለን መሥራች ጉባዔውን ለማካሄድ የሚያስችል ዕድል በመኖሩ፣ ይህንን ለመተግበር እየተዘጋጀን ነው፡፡ የንግድ ሕጉ ውክልናን እንዲሁም ከዚህ በፊት ብሔራዊ ባንክ ባወጣው መመርያ መሠረት አንድ ሰው ሊወከል የሚችለው የተከፈለ ካፒታሉን አሥር በመቶ ነው ስለተሻሻለ የምሥረታ ጉባዔውን በውክልና እናካሂዳለን፡፡ መስከረም 27 ቀን 2013 ዓ.ም. የወጣው የብሔራዊ ባንክ መመርያ ይህንን ገደብ በማንሳቱና ያለ ገደብ ውክልና መስጠት ስለሚቻል፣ ጠቅላላ ጉባዔውን ውክልና ሰጥተን ማካሄድ እንደምንችል በማወቃችን ለዚሁ እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ ስለዚህ በውክልና ስብሰባውን ለማካሄድ ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋግረናል፡፡ አሳታፊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ወስነናል፡፡ ሕጎች እስኪሻሻሉ ከቆየን ጊዜ ስለሚወስድ በአጭር ጊዜ ሥራ ለመጀመር በዚህ መንገድ እንሄዳለን፡፡ ሁሉንም በወከለ መንገድ ለማካሄድ አሁን የደረስንበት መደምደሚያ 34 የባንኩ አደራጆች ውክልና እንዲሰጠን በማድረግ ጉባዔውን ለማካሄድ ነው፡፡ ሕዝቡ ከመንግሥት ቀጥሎ አደራጃችን ስለሆነ፣ ውክልና ሰጥቶን በቶሎ ወደ ሥራ እንዲገባ እናደርጋለን፡፡ እዚህ ላይ ማኅበረሰቡ በየአካባቢው በውክልና የጉባዔው ተሳታፊ እንደሆን የሚያስችለው በር እንዳይዘጋ በማድረግ ሁሉንም በወኪል የባንኩ ምሥረታ እንዲደረግ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የውክልና አሰጣጡ እንዴት ይሆናል?
አቶ መላኩ፡- በአንድና በሦስት መንገዶች ውክልና ሊሰጥ እንደሚችል እናምናለን፡፡ ከፌዴራል ሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ጋር ውይይት ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ስለዚህ በፌዴራል ደረጃ ኤጀንሲው አዲስ አበባና ድሬዳዋ ላይ ለዚህ ተብሎ በሚከፈት መስኮት ማንኛውም አክሲዮን የገዛ በቡድን እየሆነ ውክልናውን እንዲሰጥ ነው የምንጠይቀው፡፡ በአማራ ክልል በዞንና በትልቅ ከተሞች፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ባገኘነው ውክልና መሠረት በፌዴራል የሰነዶችና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ስለሚገኝ ውክልናውን ለአደራጆች መስጠት ይቻላል፡፡ ከዚህ ውጭ ባሉ ክልሎችና ከተሞች ባሉት የሰነዶችና ምዝገባ ማረጋገጫ ከአገልግሎት መስጫ እየተገኙ አገልገሎት መስጠት ይችላሉ፡፡ በውጭ አገር ያሉ ባለአክሲዮኖችም በውጭ አገር የውክልና አሰጣጥ ባለው ሥርዓት ውክልናውን እየሰጡ በፖስታ ቤት ይልኩልናል የሚል አሠራሮች ተዘርግተዋል፡፡ በዚህ መንገድ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከኅዳር 1 እስከ 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውክልናው ይሰጣል ብለን ነው ያስቀመጥነው፡፡ በአማራ ክልል በተመረጡ ከተሞች ከኅዳር 15 እስከ 30 ውክልናው ይሰጣል፡፡ በአጠቃላይ በሁሉም አካባቢ ላሉት የውክልና አሰጣጡ ከኅዳር 1 እስከ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ይጠናቀቃል ብለን እናስባለን፡፡ ለውክልና አሰጣጡ ለሚያስፈልገው ወጪ ደግሞ በምሥረታ ላይ ያለው የአማራ ባንክ ይሸፍናል፡፡
ሪፖርተር፡- በዚህ መንገድ ውክልና አሰጣጡ ከተጠናቀቀ የምሥረታ ጉባዔያችሁን በምን ያህል ጊዜ አካሄዳችሁ ወደ ሥራ ትገባላችሁ?
አቶ መላኩ፡- በእኛ እምነት በኅዳር 2013 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የውክልናው ሥራ ካለቀ ታኅሳስ 2013 ዓ.ም. ላይ ጉባዔውን እናካሂዳለን ብለን እናስባለን፡፡ እስከ ታኅሳስ መጨረሻ የምሥረታ ጉባዔው ከተካሄደ ከዚያ በኋላ በሦስት ወራት ውስጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቶ ሥራ መጀመር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ የአማራ ባንክ ሥራ የሚጀምርበት ጊዜ ከ2013 ዓ.ም. አያልፍም ማለት ይችላል?
አቶ መላኩ፡- ይህ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ሰዎች ሊረዱት የሚገባው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ ከመንግሥት ነፃ እየተደረገ ሲሄድ የካፒታል አቅምህ ጠንካራ ካልሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ ወይ ካፒታልህን ማሳደግ አለብህ ወይም መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ውህደት ነው፡፡ አሁን ባለው ግን አማራ ባንክ ቢያንስ ይህንን አልፏል፡፡ እንዲያውም ከአሁን ካሉት ባንኮች የተከፈለ ካፒታል ይበልጣል፡፡ አማራ ባንክ አሁን የደረሰበት የተከፈለ የካፒታል መጠን 4.8 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ ትውልደ ኢትዮጵያውን የገዙትን አይጨምርም፡፡ አሁንም አክሲዮኖች እየተገዙ ነው፡፡ እስከ አክሲዮን ሽያጩ መዝጊያ ድረስ ብዙ ለውጥ ይኖራል፡፡ ብዙ ትልልቅ ባለሀብቶች ገንዘባቸው እንዳይታሰርባቸው በሚል የቆዩ አሉ፡፡ ብዙዎችንም አነጋገርናልና ወደ መዝጊያው እንገባለን ብለዋል፡፡ የካፒታል መጠን ከዚህም ይጨምራል፡፡ ስለዚህ በከፍተኛ ካፒታል ወደ ሥራ መግባት ለህልውናህ ይጠቅማል፡፡፡
ሪፖርተር፡- 20 ያህል አዳዲስ ባንኮች ወደ ገበያ እንደሚገቡ ይጠበቃል፡፡ ባንኮቹ አነስተኛ በሚባል ካፒታል የሚገቡ ናቸው፡፡ በርካቶቹም ብሔርና ዘርን መሠረት በማድረግ እንደሚመሠረቱ ይነሳል፡፡ ይህ እናንተንም ስለሚመለከት ምን አስተያየት አለዎት?
አቶ መላኩ፡- አዎን ብዛት ያላቸው ባንኮች እየመጡ ነው ተብሏል፡፡ ጠንካራ ካፒታል ካልያዙ ተቋቁመው መዝለቅ ሊከብዳቸው ይችላል፡፡ ውህደት መፍጠር ግድ ሊላቸውም ይችላል፡፡ በእኛ በኩል ግን የተሻለ ካፒታል ይዘን ስለምንገባ መዋሀድ ሳይስፈልግ ራሱን ይዞ ሊሄድ ይችላል፡፡ በዘር ያልከው ነገር በተለይ ሀብት ከማሰባሰብ አንፃር ትልቅ አቅም አለው፡፡ በአማራ ባንክ በኩል እኛ ሁሉንም ነገር ስናስረዳ ቆይተናል፡፡ ባንኩ ሁሉንም አቃፊ ነው፡፡ የልማት ፍላጎት ነው፡፡ አካባቢውን እያለማ ኢትዮጵያን ማልማት ነው ዓላማው፡፡ ለዚህም ነው ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች አክሲዮን የገዙት፡፡ በዘር ታጥረው የሚሠሩት ዳራቸው ይሄው ብቻ ከሆነና፣ ከአጭር ጊዜ አንፃር ሀብት ለማሰባሰብ ከሆነ ሊጠቅም ይችላል፡፡ ከረዥም ጊዜ አንፃር ግን የባንክ አቅምና ብቃትን ያመጣል፡፡ ከዚህ በኋላ አቅም የሚሆንህ ዕውቀት ነው፡፡ አማራ ባንክ የሚያስበው ምርጥ የሚባለውን ቴክኖሎጂ ይዞ ለመሥራት ነው፡፡ በአገር ውስጥ ብቻ የሚታጠር ሳይሆን፣ በአፍሪካና በዓለም ትርጉም ያለው ባንክ እንዲሆን ነው የምናስበው፡፡
ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ታሪክ 155 ሺሕ ባለአክሲዮኖችን የያዘ ኩባንያ ትልቅ ተቋም ፈጥራችኋል፡፡ ይህን ያህል አቅም ይዛችሁ ለኢንዱስትሪው ምን የምታመጡለት አዲስ ነገር ይኖራል?
አቶ መላኩ፡- በተቻለ መጠን አዳዲስ ነገሮች ይኖሩናል፡፡ ከዚህ በኋላ ወደፊት መዝለቅ የሚቻለው በቴክኖሎጂ ነው፡፡ ሀብት ስላሰባሰብክ ብቻ ህልውናህን አረጋግጠህ አትቆይም፡፡ መኖር የምትችለው፣ አቅምና ብቃትህን የሚጨምረው በቴክኖሎጂ ስትታገዝ ነው፡፡ የትም ዓለም ብትሄድ፣ የባንክ አገልግሎትን የተሻለ ለማድረግ የሚጠቅሙት ቴክኖሎጂን ነው፡፡ እኛም በዓለም ምርጥ የሚባለውን ቴክኖሎጂ በማምጣት ለመሥራት አቅደናል፡፡ የሰው ኃይል ሌላው ቁልፍ ነገር ነው፡፡ የቱንም ቴክኖሎጂ ብትይዝ፣ የሰው ኃይል ግድ ነው፡፡ ሦስተኛ ይዘኸው የምትቀርበው የአገልግሎት ዓይነትና የአገልግሎት አሰጣጥህ ነው፡፡ ዝቅተኛውንና የተወሰኑ ባለሀብቶችን መፍጠር ሳይሆን፣ ዝቅተኛውና መካከለኛውን ማኅረበረሰብ ወደ ባለሀብትነት የሚመጣበትን መንገድ ማመቻቸት ዋነኛው ሚና ነው፡፡ እንደሚታየው አብዛኛው አክሲዮን የገዛው ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ ባለአክሲዮኖች እንዴት ወደ ባለሀብትነት ይመጣሉ የሚለውን ለመመለስ አዳዲስ ሐሳቦችንና አገልግሎቶችን ይዘህ መምጣት አለብህ፡፡ የምናሸንፈው በዚህ አካሄድ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አክሲዮን ሽያጫችሁን ስታራዝሙ በነበረበት ወቅት እንደ ምክንያት የተቀመጠው ዳያስፖራውንም ለማሳተፍ የሚለው ነበር፡፡ ለዳያስፖራው ምን ያህል አክሲዮን ሸጣችሁ? ሽያጩ በውጭ ምንዛሪ የተካሄደ ነበር?
አቶ መላኩ፡- ያሰብነውን ያህል አላገኘንም፡፡ ባደረግነው ቅስቀሳ ብዙ ሽያጭ ይፈጸማል ብለን ነበር፡፡ ሽያጩ ጥሩና አሁንም እየተሸጠ ቢሆንም፣ ያስብነውን ያህል አይደለም፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ ለማየት ሞክረናል፡፡ በየካቲት ወር ለዳያስፖራ ተብሎ የአክሲዮን ሽያጩ በተራዘመበት ጊዜ ኮሮና ተቀሰቀሰ፡፡ ላለመግዛታቸው በዋና ምክንያትነት ሲነሱ የነበሩት በኮቪድ ሳቢያ የእንቅስቃሴ ገደብ መደረጉ፣ የሥራ ዕድል ዋስትናና የመሳሰሉት ችግሮች ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ያለው የመሸጫ መንገድ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም አለመሆኑ ነው፡፡ ለዳያስፖራው አክሲዮን የሚሸጠው በውጭ ምንዛሪ ነው፡፡ የወጣው መመርያም እዚህ ላይ ግልጽ ነው፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሆነው የውጭ ዜግነት ያላቸው አክሲዮን የሚገዙት በውጭ ምንዛሪ ነው፡፡ ዜግነት ያልቀየሩ ግን በብር መግዛት ይችላሉ፡፡ ይህንን መመርያ መሠረት በማድረግ ነው ሽያጩን የምናካሂደው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይህ መመርያ ከመውጣቱ በፊት አንዳንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን በብር ገዝተው ነበር፡፡ እዚህ ላይ መግለጽ የምፈልገው ወደ ሕጉ እንድንመለስ ነው፡፡ አንዳንድ ባንኮች አዋጅ ወጥቷል በማለት በብር የሸጡላቸው አሉ፡፡ ስለዚህ በእኛ በኩል በብር የገዛችሁ ዳያስፖራዎች ገንዘባችሁ ተመላሽ ይደረጋል ወይም እዚህ ላሉ ወገኖቻችሁ እንድታስተላልፉ ይደረጋል ማለት እንፈልጋለን፡፡
ሪፖርተር፡- በእስካሁኑ ሒደታችሁ ወጪያችሁን በተመለከተ አጠቃላይ ካሰባሰባችሁት ሀብት ለአገልግሎት ክፍያ ከተዋጣው 8.8 ሚሊዮን ብር ብቻ እንደተጠቀማችሁ ገልጻችኋል፡፡ ይህ ያልተለመደ ነው፡፡ እስካሁን ስትሳተፉ የነበረውም ያለ ክፍያ በፈቃደኝነት ነው፡፡ ይህም ብዙ ያልተለመደ ነው፡፡
አቶ መላኩ፡- አብዛኛውን ጊዜ አክሲዮኖች ሲደራጁ ከአገልግሎት ጋር የተያያዙ በርካታ ገንዘቦች በተለያየ መንገድ ወጪ ይደረጋሉ፡፡ ለመሥራቾች የሚከፈል እየተባለ የሚወጣ ወጪ አለ፡፡ በእኛ በኩል ይህንን አቁመናል፡፡ ሕዝብ ሲጠቀም እንጠቀማለን ብለን ነው እየሠራን ያለነው፡፡ ተቋም ግንባታ ላይ እናተኩር ብለን ነው የምንሠራው፡፡ ትልቁ ነገር የአክሲዮን ኩባንያ ሲቋቋም ለአጭር ጊዜ የምታገኘውን ጥቅም ካሰብክ አይሆንም፡፡ ግቡ ሕዝብን መጥቀም ነው፡፡ እኛ አሁን ላይ ጥቅም አለማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ የራሳችንን ገንዘብ እያወጣንና ጊዜያችንንም እየሰጠን ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ትልቅ ተቋም ይዘህ መሥራቱ ጭንቀቱ ራሱ ይገድልሃል፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ አደራጆች እስካሁን ምንም ዓይነት ክፍያ አልወሰዳችሁም ማለት ነው?
አቶ መላኩ፡- እስካሁን ምንም የወሰድነው ነገር የለም፡፡ በነፃ ነው እየሠራን ያለነው፡፡ ከዚህ በኋላ ቦርድ ሲመጣ የእሱ ሥራ ይሆናል፡፡ አደራጆች ግን ምንም ዓይነት ክፍያ አልወሰዱም፡፡ ከአክሲዮን ሽያጭ የተሰበሰበው የአገልግሎት ክፍያ ከ317 ሚሊዮን ብር በላይ ቢሆንም፣ ለማስተዋወቅ፣ ለቢሮ ኪራይና ለመሳሰሉት ከወጣው 8.8 ሚሊዮን ብር በቀር ለአደራጅ የተከፈለ ነገር የለም፡፡ በነፃ ነው የምናገለግለው፡፡ የበጎ ፈቃደኝነት ዓላማ ካላቸው አስተባባሪ ተቋም መፍጠር ይችላሉ፡፡ ብዙ ተግዳሮቶች ቢኖሩትም በፈቃደኝነት የምትሠራው ሥራ አገር ሊለውጡ የሚችሉ ውጤቶችን ልታበረክትበት ትችላለህ፡፡