Thursday, April 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከሰይፍ እንራቅ!

አገር አስከፊ ወደ ሆነው ግጭት ገብታለች፡፡ ነገሮች ወደ ግጭት እንዳያመሩ አነሰም በዛ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ጥረቶች ውጤት ሊያጡ ባለመቻላቸው ይኸው የጥይት ድምፅ መሰማት ጀምሯል፡፡ በጥቂቶች እምቢተኝነት ወንድሞች መተላለቃቸው ያሳዝናል፡፡ በጥቂት ግትሮች ሕፃናት ለጦርነት ሲማገዱ እያየን ነው፡፡ መረገም ነው፡፡

የእልኸኝነትና እንቢተኝነት ጦስ አገር ወደ ኋላ እንድትጎተት ምክንያት ሊሆን ነው፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት የትግራይ አርሶ አደሮችን ማሳያ እየተንከባከበ፣ የደረሱ ሰብሎች እያጨደና እየከመረ ሲያግዝ ዓይተናል፡፡ የደረሰው የገበሬው ሰብል በአንበጣ መንጋ እንዳይበላ ከሕዝብ እኩል ላይ ታች ሲል ከርሟል፡፡ ከመቼው ጥቃት ተሰነዘረበት የሚለውን ለማመን የሚከብድ ወሬ መስማትም ወገን በወገኑ ላይ ይፈጽመዋል ብሎ ማሰብም የማይሆነ ነገር ነበር፡፡ ያልጠበቀው ሆነ፡፡ አብሮ የኖረው የወገን ጠባቂ በወገኑ ልጆች ተወጋ፡፡ ይህ የሚያሳዝን መርዶ ነው፡፡  

ለሁለት አሥርታት በትግራይ የከተመው የአገር መከላከያ ሠራዊት ውለታው ጥቃት የሆነው ከፖለቲካ ፍጆታ ውጭ ማሰብ በማይችሉ ኃይሎች ነው፡፡ ውለታው ተረስቶ የኃይል ዕርምጃ ይወሰድበታል ተብሎ ባይገመትም፣ ባልታሰበ አሳቻ ጊዜ፣ ያውም በምሽት የጥቃት ሰለባ ሆነ፡፡ የሚፈራው ጦርነትም ተነሳ፡፡ እርግጥ ይህ ጦርነት የመግጠም ሳይሆን፣ ሕግ የማስከበር ዕርምጃ ነው በሚለው ብያኔ ላይ በርካቶች ይስማማሉ፡፡ በዚሁ ብያኔ አግባብ ጦርነቱን እንመልከተው፡፡ መከላከያ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ከፌዴራል መንግሥት ባፈነገጠው የሕወሓት ቡድን መሆኑ ከታወቀ በኋላ መንግሥት ወደማይፈልገው ጦርነት ሕግ ለማስከበር ሲል ለመግባት መገደዱን አስታውቋል፡፡

ባለፉት 20 ዓመታት ክልሉንና አገሩን ሲጠብቅ የቆየው ሠራዊት፣ ሳያስበው በራሱ ወገን እንደተመታ የሚያረዳው ዜና አስደንጋጭ ነበር፡፡ ለአገር ደንታ ቢስ የሆነ አካል ጦርነት ማስነሳቱ አንገት ያስደፋል፡፡ በዚህ ጦስ ኢትዮጵያ ዳግም መታወቂያዋ እንዲሻክር የሚስገድድ ሁኔታ ውስጥ ወድቃለች፡፡ የዓለም ዓይኖችና ጆሮዎች የኢትዮጵያን የጥፋትና የዕልቂት ዜና ለመቃረም አሰፍስፈዋል፡፡ የሙትና ቁስለኛ ቁጥር ለመዘገብ ይንቆራጠጣሉ፡፡

በየትኛውም መንገድ ጦርነት የሰላም አማራጭ አይደለም፡፡ አገሪቱ የገባችበት ጦርነት ከዚህም በላይ ያሳምማታል፡፡ የጦርነት ክፋቱ ሰላማዊ ሰዎችን ከመጉዳት አይመለስም፡፡ ሕይወት ያጠፋል፡፡ ሀብትና ንብረት ያወድማል፡፡ ወጥቶ መግባትን ያሳጣል፡፡ ኢኮኖሚን ያሽመደምዳል፡፡ ልማትን ያውካል፡፡ አሥሬ ጠላቴ ድህነት እያለ ሲምል የኖረ ሁሉ ጦርነትን አማራጭ ማድረጉ ከክፋትም በላይ ነው፡፡

 ፈጣሪም እንዳያዝንብኝ፣ ሕዝብም እንዳይቀየመኝ፣ ከመንግሥትና ከባለሥልጣናት ባልስማማ እንኳ ለሰላም ሲባል እንጎዳ ብሎ ነገሮችን ማለፍ የማይችል አካል መጨፋጨፍን መርጧል፡፡ አለመታደል ነው፡፡ ታሪክ የሚፈርደው ዕርምጃ ነው፡፡ የሰላም አማራጭን በረባ ባልረባው በመርገጥ አገርና ሕዝብን ወደ ጦርነት መማገድ በታሪክ ይቅር የማያስብል ከባድ ስህተት ነው፡፡ ለጦርነቱ ምክንያት የሆኑ አካላት የሚወክሉት ሕዝብ የቱንም ያህል ቢሆን ተጎጂ እንደሚሆን ሳያውቁት ቀርተው አይደለም፡፡ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› ዓይነት የይዋጣልን ጠበኛ ግትርነት ደም ማፋሰሱ ያሳምማል፡፡  

የኢትዮጵያን ሰላም የሚፈልግ አካል ጥቅሙ ቀርቶበትና ተበድሎም ቢሆን ሰላማዊ መንገድን መከተል ይገባው ነበር፡፡ መንግሥት በድሎትም ከሆነ ከጦርነት ይልቅ መንግሥት የፈጸመውን በደል በማሳወቅ ማሳጣት ይበጀው ነበር፡፡ ርዕታዊና ሕዝባዊ ተቀባይነት የሚገኘው ጦር በመስበቅ ሳይሆን፣ ሕዝብን በመታደግ ነው፡፡ መንግሥት ከእኔ በላይ ላሳር በማለት ጦር አዝምቶ ቢሆን፣ እምቢ ያለኝን እቀጣለሁ በማለት ቀድሞ ቢነሳ እንኳ ትክክለኛ ነኝ የሚል አካል ነገሮችን በማብረድና በማስከን አማራጮችን መከተል፣ ሕዝብ እንዳይጎዳ መጣር ይገባው ነበር፡፡ እውነትን የያዘ አካል የፕሮፓጋንዳ ጋጋታ ሳያስፈልገው የያዘው እውነት ከእርሱ በላይ በተናገረለት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከመንግሥት በላይ ኃይል አለኝ አሳያችኋለሁ በማለት ለጦርነት መንደርደሩ እውነታ እንደሌለው የሚያሳይና እጅጉን የሚያስከፋ የክፋት አማራጭ ነው፡፡ በጥቂቶች ዕብሪት ግን ብዙኃን መጎዳት የለባቸውም፡፡ መንግሥት ቢበድል እንኳ ቃታ መሳብ የለየለት አላዋቂነት ነው፡፡

አገርን ለጥፋት ያበቁ አካላት አስተማሪ ቅጣት ይገባቸዋል፡፡ የትግራይን ሕዝብ ከዚህ ማጥ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ጦርነት ባለበት ወቅት ኢኮኖሚ አብሮ ይታመማል፡፡ ይወጋል፡፡ ጦርነት ነውና ባይፈለግም ጉዳት ይኖራልና ይህንን  ጉዳት መቀነስ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት መጠበቅ ሁሉ ግድ ይላል፡፡ ወቅታዊውን ሁኔታ ተከታትሎ በትግራይ ክልል ተፈጻሚ የሚሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአግባቡ በማስፈጸም ረገድም የመንግሥት ኃላፊነት ከፍተኛ ነው፡፡ ሕግ ነውና ሕጉን ለመተግበር የሕዝቡም ተባባሪነት በእጅጉ ይፈለጋል፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ለሕዝብ ስለመሆኑ ማወቅም ተገቢ በመሆኑ ከገባንበት ቀውስ ለመውጣት የተሻለውን ሁሉ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ በየትኛውም ወቅት በጦርነት ጊዜ የሚያጋጥም ነው፡፡ በጦር ሜዳ ከሚከፈለው መስዋዕትነት ባልተናነሰ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችም የሚጠብቁንን ጦርነቶች በአግባቡ ለማሸነፍ ደግሞ ሁሉም የበኩሉን ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

እንደ ሸማች እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች መክበር በሚፈልጉ ሆዳሞች የሚጠቃበት ዕድል ይሰፋልና በግብይት ውስጥ ችግር እንዳይፈጠር ተግቶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ገበያው የተረጋጋ እንዲሆንና ሸማቾች በስግብግብ እጆ እንዳይወድቁ በማድረግ በዚህ ጊዜ ኃላፊነታቸው ድርብ መሆን አለበት፡፡ ከትናንት በስቲያ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ እንዳስታወቀው አጋጣሚውን ለመጠቀም የሚደረግ መሯሯጥ ስለመኖሩና ይህንን በሚያደርጉት ላይ ዕርምጃ እወስዳለሁ ማለቱ ተገቢ ቢሆንም ዜጎች ያለንበት ወቅት አውቀው ኢኮኖሚያዊ ጦርነት ከመፍጠር ቢታቀቡና የዜግነት ድርሻቸውን እንዲወጡ   ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ አገር አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ባለችበት ሰዓት አገርን ለመከላከል በግንባር መግጠም ባይቻል በተሰማራንበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ በሀቅ መሥራት ኃላፊነትን መወጣትና አገርን ማገዝ በመሆኑ አጋጣሚዎችን ላልተገባ ነገር የመጠቀም ልምዶችን ማቆም የግድ ይላል፡፡ ለሁሉ ግን አሁን ከገባንበት አጣብቂኝ እንወጣ ዘንድ ሁሉም የበኩሉን ያድርግ አገራችንን ሰላም ማለቱ ተገቢ ነው፡፡

ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ የለም፡፡ ከጦርነት የሚያተርፍ የጦር ነጋዴ ብቻ ነው፡፡ በእኛ ሁኔታ አገር ለነገ ተስፋዎቿ የሆኑ ጨቅላዎች ጠመንጃ ተሸክመው መማገድ እጅግ ኢሰብዓዊነት ነው፡፡ አሁንም ለአገር ፅናትና ለሕዝብ ደኅንነት የሚያስብ ሁሉ ለሰላም ይሰለፍ፡፡ ከሰይፍ ይሰብሰብ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት