Friday, September 22, 2023

‹‹ሳንወድ ተገደን አሳፋሪ ጦርነት ውስጥ ገብተናል›› ምክትል ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ማክሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ላይ የተሰማው ዜና ድብልቅልቅ ያለ ስሜትን በኢትዮጵያውያን ላይ ፈጥሯል። በተጠቀሰው ቀን እኩለ ሌሊት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) የሕወሓት ልዩ ኃይል በትግራይ ክልል በሚገኘው የአገር መከላከያ የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ ጥቃት መክፈቱን  በመገልጽ ወታደራዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸውን አስታውቋል።

‹‹የመጨረሻው ቀዩ መስመር ታልፏልአገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ሆኗል፤›› ሲሉ አስታውቀዋል። 

ይህ መረጃ መውጣቱን ተከትሎ የተደበላለቀ ስሜት በኢትዮጵያውያን ላይ ተከስቷል። ክስተቱ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ላይ ድንጋጤን፣ ቁጣንመጨነቅን በኢትዮጵያዊያን ላይ ፈጥሯል። 

በማግሥቱ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ስለ ተፈጠረው ሁኔታ ተጨማሪ መረጃ ሰጥተዋል። ‹‹መንግሥታችን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት አዲሱን የገንዘብ ኖት ወደ መቀሌ እንዲያጓጉዙ የላከችው ሁለት አውሮፕላኖች በመቀሌ ኤርፖርት ሲደርሱ በሕወሓት ኃይል እኩይ ጉዳት ተሰንዝሮባቸዋል›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይየሕወሓት ኃይል በዚህም ሳይወሰን በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የሰሜን ዕዝ ሠራዊት አባላት ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ገልጸዋል። 

የአገር መከላከያ ሠራዊት ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ ክስተቱንና ያለበትን ሁኔታ አስመልክቶ ሐሙስ ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ  ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅና አገርን ከውጭ ወራሪ ለመከላከል በተቀመጠው የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የተከፈተው ጥቃት  ‹‹የአገር ክህደት›› ነው ሲሉ ገልጸውታል።

 የትኛውም ዓይነት የፖለቲካ ልዩነት በፖለቲካዊ መንገድ ሊፈታ ሲገባ፣ የሰሜን ዕዝ በራሱ ወገን ጥቃት እንደተከፈተበት ተናግረዋል፡፡ መከላከያ ሠራዊቱ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ በተሟላ ብቃት እየመከተ መሆኑን በመግለጽም የተከፈተው ጦርነት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚቋጭ አስታውቀዋል።

በሰሜን ያለውን ሠራዊት ለማገዝ ከተለያየ የአገሪቱ አቅጣጫ የአገር መከላከያ ሠራዊት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የተናገሩት ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ፣ በሠራዊቱ ላይ የተከፈተው ጥቃት ሕወሓት ትግራይን የጦር ቀጣና ሌሎች የአገሪቱን አካባቢዎች ደግሞ የሽብር ግንባር ለማድረግ ቆርጦ ስለመነሳቱ ማረጋገጫ እንደሆነ ገልጸዋል።

‹‹የገጠመን ነገር አሳፋሪ ነውተገደን በግድ ወደ ጦርነት ገብተናል፤›› ሲሉ ጄኔራሉ ተናግረዋል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል ላይ ያወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት  ሐሙስ ዕለት ያፀደቀ ሲሆንአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለስድስት ወራት እንደሚቆይም ተወስኗል።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽም ግብረ ኃይል በዚሁ አዋጅ የተቋቋመ ሲሆን፣ በጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል አደም መሐመድ እንደሚመራና ተጠሪነቱም   ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (/) ገልጸዋል።

ግብረ ኃይሉ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማስፋትም ሆነ የማጥበብ ሥልጣን የተሰጠው ሲሆን፣ ማንኛውንም የፀጥታ ኃይል በማስተባበር በአንድ ዕዝ ሥር እንዲመራማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ግብረ ኃይሉ መደበኛ የዜጎች መብትን ሳይገደብ አዋጁ በተጣለባቸው አካባቢዎች ላይ ተልዕኮውን ማስፈጸም የሚያስችለውን ዕርምጃ መውሰድ እንደሚል አመልክተዋል፡፡

በግብረ ኃይሉ የሚተገበሩትን ሲዘረዝሩም፣ በክልሉ ፖሊስን ጨምሮ ማንኛውም የፀጥታ ኃይል ትጥቅ እንዲፈታ እንደሚደረግ፣ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ጨምሮ አስፈላጊ ናቸው ብሎ የታመነባቸው ሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ መጣል፣ የሰዓት እላፊ ገደብ ማውጣት፣ የጦር መሣሪያ እንቅስቃሴዎችን ማስቆም፣ የመገናኛ ዘዴዎች እንዲቋረጡ ማድረግ፣ ለተልዕኮ እንቅፋት ይሆናሉ ያላቸውን መግለጫዎች መከልከል፣ ሕገ ወጥ በሆነ ተግባር ላይ ተሳትፈዋል ብሎ የጠረጠራቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች የመያዝና የማቆየት እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

ግብረ ኃይሉ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተጣለባቸው አካባቢዎች ላይ ለተልዕኮ ተፈጻሚነት ያግዙኛል ብሎ ሲያምን ሰዎችን በአንድ ቤት፣ ቦታ ወይም አካባቢ እንዲቆዩ የማድረግ ሥልጣን እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡

ቤትና አካባቢዎችን ጨምሮ መጓጓዣዎችንም በማንኛውም ጊዜ መበርበርና መፈተሽ እንዲሁም አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና መሠረተ ልማቶችን ለተልዕኮ መሳካት ያስችሉኛል ካለ ማስቆም እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡

ግብረ ኃይሉ ለተልዕኮ ተፈጻሚነት አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ማድረግ እንዲችል ሥልጣን የተሰጠው ሲሆን፣ በሒደቱ ተመጣጣኝ ዕርምጃዎችንመውሰድ ሕጋዊ መብት እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

ገዥው ብልፅግና ፓርቲ የተከሰተውን ጦርነት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የትግራይ ሕዝብ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በመሆን በአገር ላይ ክህደት ፈጽሟል ያለውን የሕወሓት ኃይል እንዲታገል ጥሪ አቅርቧል።

‹‹የትግራይ ሕዝብ ከሌሎቹ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር ጠንካራ ታሪካዊ አንድነትና ውህደት ያላቸው፣ ባህላዊና ጥንታዊ ሃይማኖታዊ እሴቶችን የሚጋሩ፣ በጋብቻና በደም የተሳሰሩ፣ በፀረ ጭቆና ትግል ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ሆነው በአንድ ጉድጓድ ክቡር መስዋዕትነት እየከፈሉ አሁን ላለንበት የአገረ መንግሥት ምሥረታ ጉልህ አሻራ ያሳረፉ ሕዝቦች ናቸው፤›› ያለው መግለጫው፣ ‹‹ሆኖም የሕወሓት አጥፊ ቡድን የሀገርንና የሕዝብን ሰላም፣ አደጋ ላይ ለመጣል የሚያደርጉት ሴራ መሆኑን አውቃችሁ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ያላችሁ ወንድማዊና ቤተሰባዊ ግንኙነታችሁ ሳይቋረጥ የትግራይን ሕዝብ የሚያለያዩ ሙከራዎችን በፅናት እንድትታገሉ የከበረ ጥሪያችንን እያቀረብን በዚህ አሸባሪ ቡድን ላይ ዕርምጃ በመውሰድ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ለማስቀጠል በምናደርገው ትግል ውስጥ ከጎናችን እንድትሆኑ፤›› ሲል ጥሪውን አቅርቧል።

 የትግራይ ክልል የፀጥታ አይሎች በአገሪቱ ከሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በጋራ በመሆን ሕዝባዊነታችሁን ጠብቃችሁ ለአንዲት ሉአላዊት አገር መከበርና ቀጣይነት ክቡር መስዋዕትነት በመክፈል ላይ መሆናችሁን ብልፅግና ፓርቲ ከልብ እንደሚገነዘብ ገልጿል።

‹‹ምንም እንኳ በክልሉ አምባገነን የሆነው የሕወሓት ቡድን በትግራይ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን እንግልትና ስቃይ የታዘባችሁ ቢሆንም ባለው ፀረ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ምክንያት ለውጡን ከሕዝባችሁ ጋር ሆናችሁ ማጣጣም ሳትችሉ ቀርታችኋል፤›› ያለው መግለጫው፣ ‹‹ሆኖም ለረዥም ዓመታት የክልሉን ሕዝብ ሰላም ደኅንነት በኃላፊነት መንፈስ ወስዳችሁ ስትጠብቁ የቆያችሁ የክልሉ ፖሊስ፣ ልዩ ኃይል አባላትና ሌሎችም በሕዝብ ትክሻ ላይ ሆኖ እየቀለደ ባለው ዘራፊና አጥፊ የሕወሓት ቡድን ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ እየተደረገ ያለውን ትግል በመቀላቀል ሕዝባዊነታችሁን እንድታረጋግጡ በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን፤›› ብሏል።

በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል የተፈጠረው ጦርነት በኢትዮጵያዊያን ላይ ከፈጠረው የተደባለቀ ስሜት ባሻገር በርካታ አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማትም አስተያየታቸውን በመስጠት ላይ ናቸው፡፡

የአሜሪካ መንግሥት ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ የትግራይ ጦር የፈጸመውን ጥቃት ያወገዘ ሲሆን፣ ሁለቱ ወገኖች የጀመሩት ጦርነት በንፁኃን ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ጥንቃቄ ሊደርግ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ኃላፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዳሳሰባቸው በመግለጽ ሁለቱም ወገኖች ልዩነቶቻቸውን በውይይት ይፈቱ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዓርብ ማምሻውን መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሕወሓት በሚመራው ኃይል ላይ በፌዴራል መንግሥት የተወሰደው ወታደራዊ ዕርምጃ የመጀመርያ ዙር በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

በተወሰደው ዕርምጃ በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የጦር ካምፖች የተከማቹ ከባድ የጦር መሣሪያዎችና ሮኬቶች በአየር ጥቃት እንዲወድሙ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የሕወሓት ቡድን የታጠቃችው ሮኬቶች እስከ 300 ኪሎ ሜትር መወንጨፍ የሚችሉ መሆናቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ቡድኑ እነዚህን ሮኬቶች ተጠቅሞ በመቀሌና አካባቢዋ ላይ ጉዳት የማድረስ ውጥን እንደነበረው ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ቀን ቀትር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በትግራይ ክልል ላይ ፌዴራል መንንግሥት እየወሰደ ያለው ወታደራዊ ዕርምጃ ሕግ ለማስከበርና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመታደግ ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -