በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ሲካሄድ የነበረው ድርድር በግብፅ እንቢተኝነት ያለ ውጤት መቋረጡን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዓርብ ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን ያቀረቡትን አዲስ የድርድር መንገድ ግብፅ ባለመቀበሏ ድርድሩ መቋረጡን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያና ሱዳን ያቀረቡት አዲስ ሐሳብ በህዳሴ ግድቡ ላይ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የአፍሪካ አገሮች ሚና እንዲጨምር የጠየቁ መሆኑን የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ ይህ ሐሳብም ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በሚለው የአፍሪካ ኅብረት መርህ መሠረት መቅረቡን ገልጸዋል።
የህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ በቀጣይ ፍሬያማ ውይይት እንዲካሄድ ከሁሉም የአፍሪካ አገሮች ሁለት ሁለት ባለሙያዎችን ባካተተ መንገድ ውይይት እንዲደረግ የሚጠይቅ ነው። ሱዳን በኢትዮጵያ ሐሳብ የተስማማች ቢሆንም፣ ግብፅ ግን ሐሳቡን ውድቅ እንዳደረገች አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።
የሱዳን መንግሥት ባወጣው መግለጫም የአፍሪካ አገሮች ባለሙያዎች ዕገዛ የሚያደርጉበትን የድርድር መድረክ ለመፍጠር የቀረበውን አዲስ ሐሳብ ግብፅ ውድቅ በማድረጓ የሦስተዮሽ ድርድሩ መቋረጡን አስታውቋል።
በመሆኑም ድርድሩ የደረሰበትን ደረጃ አስመልክቶ ሦስቱም አገሮች ለአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ለሆኑት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ ሪፖርት በማቅረብ ቀጣይ አቅጣጫ እንዲሰጡበት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።