Friday, December 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ዘርፈ ብዙ ችግሮች ላሉባት ኢትዮጵያ ጦርነት መፍትሔ አይሆንም!

ኢትዮጵያ በፍፁም የማያስፈልግ ጦርነት ውስጥ ተገዳ እየገባች ነው፡፡ እነ ሶሪያ፣ የመን፣ ሊቢያና መሰል የፈራረሱ አገሮች ተርታ ውስጥ የሚከታትን ጦርነት በፍጥነት ማስወገድ ይገባል፡፡ ተነግረው የማያልቁ በርካታ ችግሮች ላሉባት አገር ጦርነት መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ መሀል ሦስተኛ ወገኖች ጣልቃ ሊገቡ ስለሚችሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል፡፡ የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ያሳስባል፡፡ በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ እንዲያገኝ ጥረት ቢደረግም፣ የትግራይ ልዩ ኃይል በሰሜን ዕዝ ላይ በከፈተው ጥቃት ምክንያት የአንድ አገር ልጆች ወደ እርስ በርስ ጦርነት ማምራታቸው በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ የጦርነት አባዜ ያለባቸውና ለሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ጀርባቸውን ሰጥተው አገር ማመስ በሚፈልጉ ኃይሎች ምክንያት፣ የሰላማዊ ሰዎች ደኅንነት ለአደጋ ሲጋለጥ ኢትዮጵያዊያን በጋራ ሆነው መመካከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ጦርነትን አማራጭ በማድረግ የሚፈልጉትን ዓላማ ለማሳካት የሚቅበዘበዙ ወገኖች፣ አሁንም ጊዜው አልረፈደምና ለሰላማዊ ንግግርና ድርድር ትኩረት እንዲሰጡ ይጠየቃሉ፡፡ ኢትዮጵያን የጦርነት አውድማ ማድረግና መላው ሕዝቧን ሰላሙንና ደኅንነቱን መንሳት የሚጠቅመው፣ ለታሪካዊ ጠላቶች ብቻ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ጦርነት ሕይወት ከመቅጠፍና የአገር ሀብት ከማውደም ውጪ ለማንም እንደማይበጅ የታወቀ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ያስመረረውን ጦርነት በ21ኛው ክፍለ ዘመን በመቀስቀስ፣ የሕዝብን ደኅንነት ለአደጋ ያጋለጡ ኃይሎች ከድርጊታቸው መቆጠብ አለባቸው፡፡ በተለይ ልጆቻቸውንና የቅርብ ሰዎቻቸውን ወደ ውጭ ያሸሹና ውጭ አገር ሆነው የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ፣ ምስኪኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ እሳት ውስጥ ለመማገድ የሚያደርጉት አደገኛ እንቅስቃሴ በጦር ወንጀለኝነት እንደሚያስጠይቃቸው ማወቅ አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍሬያማ የሆነ የውይይትና የድርድር ባህል እንዲዳብር፣ ከትምህርትና ከልምድ የተገኝ ዕውቀትን በማዳረስ የሕዝቡን ተስፋ ማለምለም ሲገባ ወደ ጦርነት ማምራት በሕዝብ ላይ ከባድ ችግር ያስከትላል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በዕብሪት በተወጠሩና በጉልበት ተመክተው ሕዝባችንን በጦርነት ለመማገድ የሚቅበዘበዙ ኃይሎችን በቃችሁ ማለት አለባቸው፡፡ የሕዝብና የአገር ሰላም ተቃውሶ በነፃነት መኖር አይቻልም፡፡ በጣም የሚያሳዝነው ግን ብዙዎቹ የጦርነት ጉሰማ ተዋንያን ለሕዝብ ደንታ የሌላቸው ናቸው፡፡ የጦርነቱ ገፈት ቀማሾች ግን ምስኪን ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህንን አደገኛ ደባ ለማክሸፍ የተጀመረው ጦርነት በፍጥነት እንዲቆም መተባበር አለባቸው፡፡ ከሥልጣናቸው ውጪ ሌላ ነገር የማይታያቸው ጀብደኞች የአገር ሰላም አቃውሰው የሕዝቡን ደኅንነት አደጋ ውስጥ እንዳይከቱ፣ በተቻለ መጠን ለአገር ህልውና መጠበቅ በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ኢትዮጵያን የሰላም፣ የፍትሕና የነፃነት አገር ማድረግ የሚቻለው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንጂ፣ አሁን እንደሚታየው ጦርነት ቀስቅሶ ሕዝቡን ደም በሚያቃቡ ጀብደኞች ፍላጎት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም፣ ነፃነት፣ ፍትሕና እኩልነት ነው፡፡ ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በማፈንገጥ አገርን የጦርነት አውድማ ማድረግ ከጥፋት በስተቀር ትርፍ የለውም፡፡ ሕዝቡን ከድህነት ማጥ ውስጥ ለማውጣት የሚያስፈልገው ማኅበራዊ ፍትሕ የሰፈነበት ሥርዓት ብቻ ነው፡፡ ይህ ሥርዓት የሚገነባው በሠለጠነ አስተሳሰብ እንጂ ዘመን ባለፈበት አስተሳሰብና በጠመንጃ አምላኪነት አይደለም፡፡ ለአገር የሚበጅ ሥርዓት ዕውን ሊሆን የሚችለው በሕዝብ ድምፅ ብቻ እንጂ በጀብደኝነት አይደለም፡፡ ሆኖም አያውቅም፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በማይመጥን ኋላቀር አስተሳሰብና በጀብደኝነት መንፈስ ለሕዝብ ቆሜያለሁ ማለት ቀልድ ነው፡፡ ለሥልጣን ሲባል ብቻ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ በሕዝብ ስም መነገድ የለየለት ቁማርተኝነት ነው፡፡ የሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት አደጋ ውስጥ በመክተት ዓላማን ለማሳካት የሚደረግ አደገኛ ሙከራ መቀልበስ አለበት፡፡ ከጦርነት ውድመት እንጂ ልማት አይገኝም፡፡

በፌዴራል መንግሥቱና በተለይ በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መካከል ከፍጥጫ ታልፎ ጦርነት መጀመሩ፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ ሕገወጥ የሆኑ ድርጊቶች መበራከታቸው፣ ንፁኃን በማንነታቸው ምክንያት መጨፍጨፋቸውና ንብረታቸው መውደሙ፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች እርስ በርስ ሆድና ጀርባ መሆናቸውና በሕዝቡ ውስጥ መረጋጋት ለመፍጠር የሚደረጉ ጥረቶች አናሳ መሆን፣ ኢትዮጵያን ለታሪካዊ ጠላቶች ጥቃቶች ተጋላጭ እንደሚያደርጓት ለማንም ቅን ዜጋ የተሰወረ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮችን ጉያዋ ውስጥ ታቅፋ ጎኗ በጦር እየተወጋ ነው፡፡ የፖለቲካ ሥልጣን ተገዳዳሪነት በሠለጠነ መንገድ አልከናወን ብሎ ከአገር በላይ ግላዊና ቡድናዊ ጥቅምና መሳሳብ ላይ ትኩረት ሲደረግ፣ ይህንን ችግራችንን እንደ ሠርግና ምላሽ የሚያዩ ታሪካዊ ጠላቶች ክፍተቱን በሚገባ እንደሚጠቀሙበት ለአፍታ እንኳ መጠራጠር አይገባም፡፡ ለሕዝብ ሰላምና ለአገር ህልውና ሲባል ለሰላም ቅድሚያ መስጠት የግድ ነው፡፡ ጦርነት የኢትዮጵያን ችግሮች ከመፍታት ይልቅ የበለጠ በማባባስ ቀውስ ያስከትላል፡፡

መቼም ቢሆን መዘንጋት የሌለበት ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ያላት አገር መሆኗ ነው፡፡ ይህን ተስፋ የማለምለምና ወደ ውጤት የመቀየር ኃላፊነት የኢትዮጵያዊያን ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻቸውን አክብረው በአንድነት ለአንድ የጋራ ብሔራዊ ዓላማ መቆም ሲችሉ፣ ተዓምር መሥራት እንደማያቅታቸው የዓለም ጥቁር ሕዝቦች መኩሪያ የሆነው ታላቁ ፀረ ኮሎኒያሊስት የዓድዋ ጦርነት ድል ምስክር ነው፡፡ ይህ በዘመኑም ሆነ ከዚያ በኋላ ባሉ ዓመታት ዓለም በታላቅ አክብሮት የሚዘክረው ድል፣ ኢትዮጵያዊያን መተባበር ከቻሉ ምንም ዓይነት ኃይል እንደማያቆማቸው ህያው ምስክር ነው፡፡ ማንም ሊያስተባብለውም የማይቃጣው ሀቅ ነው፡፡ በአሁኑ ዘመን የተኳረፉትን የማቀራረብ፣ የማይነጋገሩትን በግንባር በማገናኘት የማወያየት፣ ዓይንህ ለአፈር የተባሉትን ዓይን ለዓይን የማገጣጠም፣ በአጠቃላይ በአንድ ጣራ ሥር መገናኘት የማይፈልጉትን በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ የማገናኘትና መሰል በጎ እንቅስቃሴዎች ለአገር በሚያስቡ የተለያዩ አካላት በፍጥነት መጀመር አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለጊዜው እንጂ መገናኘትና መነጋገር ሲጀምሩ መቀራረብ እንደማያዳግታቸው ይታወቃል፡፡ ጊዜያዊ እልህ፣ ንዴት፣ ቁጣና ቂምን ወደ ጎን ብሎ ወንድም ከወንድሙ፣ እህት ከእህቷ ተገናኝተው መነጋገር አለባቸው፡፡ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች የተሰማሩ ወገኖችም ከሐሰተኛ ወሬዎች በመታቀብ ገንቢ ተግባራት ላይ ቢያተኩሩ፣ አሁን የሚታየው አሳሳቢ ሁኔታ ወደር ወደሌለው ውጤት መለወጡ አይቀርም፡፡ ኢትዮጵያዊያንም የሚያምርባቸው ይህ ዓይነቱ ሥልጡን መንገድ ስለሆነ፣ ቅንነት በተሞላበት መንፈስ በመቀራረብ ይህንን አደገኛ ጦርነት ያስወግዱ፡፡ ለኢትዮጵያ አይበጃትምና፡፡

ማንም ቢሆን ልብ ሊለው የሚገባ ዋና ጉዳይ፣ የኢትዮጵያን ህልውና ለምንም ነገር መደራደሪያ ማድረግ እንደማይቻል ነው፡፡ ጠባብ ቡድናዊ ፍላጎትን በማስቀደም ሰላሟን መፈታተን ጠላትነት ነው፡፡ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሆኖ በማሴር ቀውስ መፍጠር የኢትዮጵያውያን መገለጫ አይደለም፡፡ ኢትዮጵዊያን ፍላጎታቸውን ከኢትዮጵያ ህልውና በታች አድርገው፣ የፈለጉት ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች መሳተፍ የሚችሉትም፣ ብሔራዊ ደኅንነቷንና ጥቅሞቿን ሳይጎዱ ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገሩ ህልውና ላይ የመጣን ማንኛውንም ጥቃትም ሆነ ሴራ ስለማይታገስ፣ ከአጥፊና ከአውዳሚ ድርጊቶች መታቀብ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና ሲነካ እጁን አጣጥፎ የሚቀመጥ የለምና፡፡ ኢትዮጵያን ከሥልጣን፣ ከጥቅማ ጥቅም፣ ውሉ ከማይታወቅ በጀብደኝነት ከተሞላ የቡድንተኝነት ስሜት፣ ከክልላዊ ወሰን ጥበትና ስፋት፣ ከማንነትና ከሃይማኖታዊ አጥር፣ ከዓርማዎችና ከምልክቶች ልክፍት፣ እንዲሁም መያዣና መጨበጫ ከሌላቸው ዘመኑን ከማይመጥኑ ዕሳቤዎች በላይ ማክበር ይገባል፡፡ አንድነቷ እንደ ብረት የጠነከረ፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ያላት፣ በኢኮኖሚ የዳበረችና ለሁሉም ሕዝቧ የምትመች ዴሞክራሲያዊት አገር መገንባት የሚቻለው በዚህ ቁመና ላይ መገኘት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ አሁን በየቦታው እንደሚታየውና እንደሚሰማው በጠባብ ቡድናዊ ፍላጎት ላይ ብቻ በማተኮር አገር ማተራመስ ዕርባና ቢስ ከመሆኑም በላይ፣ ይባስ ብሎ ጦርነት ቀስቅሶ አገር ለማፍረስ መወራጨት ተቀባይነት የሌለው አደገኛ ድርጊት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ለኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ጦርነት መፍትሔ እንዳልሆነ መተማመን ይገባል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...