ሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በትግራይ ክልል ላይ ያወጣው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደበኛ የዜጎችን መብት እንደማይገድብ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ገለጸ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ካፀደቀ በኋላ፣ ስለ አዋጁ ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ የሰጡት የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ዋና ዓቃቤ ሕግ ጌዴዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) አዋጁን የሚያስፈጽም ግብረ ኃይል መቋቋሙንና በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማ ዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድ እንደሚመራ ተናግረዋል፡፡
አዋጁ የታወጀው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው እንደሆነ ጠቁመው፣ አስፈጻሚው ግብረ ኃይል የተሰጠውን ሥልጣንና ተግባርም ገልጸዋል፡፡ በኤታ ማዦር ሹሙ የሚመራው ግብረ ኃይል ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሲሆን፣ አዋጁ ለስድስት ወራት እንደሚቆይና ግብረ ኃይሉ የማስፋትም ሆነ የማጥበብ ሥልጣን እንደሰጠው ጠቁመዋል፡፡ ግብረ ኃይሉ ማንኛውንም የፀጥታ ኃይል በማስተባበር በአንድ ዕዝ ሥር እንዲመራ ማድረግ እንደሚችልም ዋና ዓቃቤ ሕጉ ተናግረዋል፡፡
ግብረ ኃይሉ ተልዕኮውን በሚተገብርበት ወቅት አስፈላጊ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ድንጋጌዎች ማውጣትና መተግበር እንደሚችልም አክለዋል፡፡ ግብረ ኃይሉ የዜጎችን መደበኛ መብት ሳይገድብ አዋጁ በተጣለባቸው አካባቢዎች ላይ ተልዕኮውን ማስፈጸም የሚያስችለው ዕርምጃ መውሰድ እንደሚችልም ጌዴዮን (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ ፖሊስን ጨምሮ ከማንኛውም የፀጥታ ኃይል ትጥቅ ማስፈታት እንደሚችልም አክለዋል፡፡
ግብረ ኃይሉ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ጨምሮ የሰዓት እላፊ፣ የጦር መሣሪያ እንቅስቃሴ፣ መገናኛ ዘዴዎች እንዲቋረጡ ማድረግና ሌሎችም ለተልዕኮ እንቅፋት ይፈጥራሉ ብሎ ያመነባቸውን ነገሮች ገደብ የመጣልና ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖችን ይዞ የማቆየት ሥልጣን እንዳለው አብራርተዋል፡፡ አዋጁ ተግባራዊ በሚደረግባቸው አካባቢዎች ተልዕኮ ተፈጻሚነት እንደሚያግዙት ካመነ በአንድ ቤት፣ ቦታ ወይም አካባቢ እንዲቆዩ የማድረግ ሥልጣንም እንደተሰጠው ጌዴዮን (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ቤት፣ አካባቢዎችና መጓጓዣዎችን በማንኛውም ጊዜ መበርበርና መፈተሽ፣ እንዲሁም አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና መሠረተ ልማቶችን ለተልዕኮ መሳካት ከጠቆሙት ማስቆም እንደሚችልም አክለዋል፡፡ ተመጣጣኝ ዕርምጃ መውሰድ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡