Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአዋሬ አካባቢ ለአደጋ ተጋላጭነቱ እየታወቀ ዕርምጃ ባለመወሰዱ   በተደጋጋሚ ጉዳት እየደረሰበት መሆኑ ተነገረ

አዋሬ አካባቢ ለአደጋ ተጋላጭነቱ እየታወቀ ዕርምጃ ባለመወሰዱ   በተደጋጋሚ ጉዳት እየደረሰበት መሆኑ ተነገረ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ በየካ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ አካባቢዎች የአዋሬ አካባቢ ቁጥር አንድ የአደጋ ተጋላጭ መሆኑን አጥንቶ፣ ለሚመለከታቸው አካላት የመፍትሔ ዕርምጃ እንዲወስዱ ምክረ ሐሳብ ቢያቀርብም፣ ተግባራዊ ባለመደረጉ በተደጋጋሚ አደጋ እያጋጠመው መሆኑን  አስታውቀዋል፡፡

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዋሬ አካባቢ የደረሰውን የእሳት አደጋ አስመልክቶ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የአካባቢው የአደጋ ተጋላጭነቱ በኮሚሽኑ በኩል ተጠንቶ ነበር ብለዋል፡፡ ከጥናት ባለፈም ከየካ ክፍለ ከተማ፣ ከወረዳውና ከኅብረተሰቡ ጋር ውይይት መደረጉንም አስረድተዋል፡፡

አካባቢው በጣም ለአደጋ የተጋለጠ ስለሆነ ነዋሪዎች ወደ ሌላ ሥፍራ የሚዘዋወሩበትን ምክረ ሐሳብ ኮሚሽኑ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ይህ በሚመለከታቸው አካላት ተግባራዊ አለመደረጉን ገልጸወዋል፡፡

እሳቸው በወቅቱ የኮሚሽኑ ባልደረባ ባይሆኑም ያገኙትን መረጃ ጠቅሰው እንዳስታወሱት፣ በሥፍራው በ2004 ዓ.ም. ከፍተኛ የእሳት አደጋ ተከስቶ ነበር፡፡

አካባቢው ለአደጋ ተጋላጭ በመሆኑ በኮሚሽኑ በኩል ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን፣ ሆኖም ይህ ተግባራዊ ባለመሆኑ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 አዋሬ ገበያ ማዕከል ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሌሊቱ 10፡54 ሰዓት ላይ መንስዔው ባልታወቀው የእሳት አደጋ፣ አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን ገልጸዋል፡፡ ኮሚሽኑ ከኅብረተሰቡ፣ ከአዲስ አበባና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመተባበር 130 ሺሕ ሊትር ውኃ ተጠቅሞ አደጋውን ከማለዳው በ1፡50 ሰዓት ላይ በመቆጣጠሩ አራት ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ማትረፉንም አክለዋል፡፡ በአደጋው የሞትም ሆነ የአካል ጉዳት አልደረሰም ብለዋል፡፡

በማግሥቱ ጥቅምት 25 ቀን ደግሞ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 15 ቦሌ አራብሳ በሚገኝ የብሎኬት ሼድ ውስጥ አደጋ ያጋጠመ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ የ200 ሺሕ ብር ንብረት ጉዳት ደርሶበታል፡፡ 400 ሺሕ ብር ያህል ደግሞ ለማትረፍ መቻሉን አቶ ጉልላት ገልጸዋል፡፡

የኮሚሽኑን የሩብ ዓመት አስመልክቶ አቶ ጉልላት እንደገለጹት፣ ከሐምሌ 1 እስከ መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባና በዙሪያዋ 96 አደጋዎች ተከስተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 45 የእሳት ሲሆኑ፣ 51 የተለያዩ ድንገተኛ አደጋዎች ናቸው፡፡ አጠቃላይ ከተመዘገቡት አደጋዎች 87 በአዲስ አበባ የቀሩት ደግሞ በኦሮሚያ ልዩ ዞን ውስጥ ናቸው፡፡ በአደጋዎቹ 23 ሰዎች መሞታቸውን፣ 37 ሰዎች መጎዳታቸውን፣ 44 ሰዎችን ደግሞ ማትረፍ መቻሉ ተገልጿል፡፡

በንብረት ላይ በደረሰ ጉዳት 46,318,120 ብር የሚገመት ንብረት የወደመ ሲሆን፣ 511,000,505 ብር የሚገመት ንብረት ለማዳን መቻሉንም አክለዋል፡፡ ወቅቱ ፀሐይና ንፋስ የበዛበት መሆኑን በማስታወስም፣ ኅብረተሰቡ እሳት ሊያስነሱ የሚችሉ ቁሳቁሶችን በጥንቃቄ እንዲይዝ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...