የተመጣጠነ የምግብ እጥረትን ለመከላከል ጥቅም ላይ የሚውል በውኃማ አካላት ላይ የሚገኝ ደቂቅ አልጌ፣ በሳይንሳዊ አጠራሩ ‹‹Arthrospira Fusiformis›› በኢትዮጵያ ማምረት ተጀመረ፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ከተመጣጠነ ምግብ አጥረት የሚመጣውን መቀንጨር ለመከላከል፣ ደቂቅ አልጌ የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ማምረት መጀመሩን ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡
የደቂቅ አልጌ አካላት ውስጥ ብረት፣ አሚኖ አሲድ፣ ማግኒዥየምና ሌሎች የአዕምሮና የሰውነት የዕድገት ደረጃን በትክክል የሚያሳድጉ ንጥረ ነገሮችን መያዙን፣ ለእርጉዝ እናቶችና ሕፃናት እንዲሁም ለአዋቂዎች የሚመከር መሆኑን የደቂቅ አልጌ ቤተ ሙከራ ፕሮጀክት ኃላፊ ሀብቴ ጀቤሳ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እየተመረተ ያለው የደቂቅ አልጌ በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ በብዛት የሚገኝ መሆኑንና በአካባቢው በብዛት በመኖሩ ወደ ትግበራ ለመግባት አመቺ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ኃላፊ እንዳስረዱት አንደ ሰው በሁለት ዓመት ዕድሜው ያጋጠመው መቀንጨር የማይስተካከል ከሆነ፣ የሰውነት ክብደቱና የአዕምሮ ንቃተ ህሊና ዝቅተኛ ይሆናል፡፡ ደቂቅ አልጌ ሴቶች ከእርግዝና ጀምሮ ልጅ ተወልዶ ሁለት ዓመት እስኪሞላው በአግባቡ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል፣ በአዕምሮ የተሻለ አስተሳሰብና በንቃተ ህሊናው ከፍተኛ የሆነ ትውልድ ለማፍራት ያግዛል ብለዋል፡፡
ሀብቴ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ በአብዛኛው በጎልማሳ የዕድሜ ክልል ላይ የሚገኘው ኅብረተሰብ በመቀንጨር የተጠቃ መሆኑን፣ በአማካይ 67 በመቶ የሚሆነው አካላዊና አዕምሮአዊ ንቃተ ህሊና በተፈለገው ደረጃ እንዳላደገ ጥናቶች ያሳያሉ ሲሉ አክለዋል፡፡ መቀንጨር (የአልሚ ምግብ እጥረት) ለመቀነስ ደቂቅ አልጌ ማምረትና ጥቅም ላይ ማዋል የሚመጣውን ትውልድ ለመታደግ እንደሚያስችል የፕሮጀክቱ ዋና ኃላፊ አስረድተዋል፡፡
ደቂቅ አልጌ በውኃ ውስጥ የሚገኝ ሕዋስ ሲሆን፣ በተፈጥሮ መሬት ላይ ተዘርተው ከሚገኙ ምግቦች በበለጠ አልሚነት እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በዓለም ገበያ ከፍተኛ ተፈላጊነት እንዳለው የሚነርለት ደቂቅ ሕዋሳትን የያዘው አልጌ በኢትዮጵያ በብዛት አምርቶ ለኅብረተሰቡ ለማሰራጨት ብዙ ርቀት መጓዝ እንደሚያስፈልግ ሀብቴ (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡ የዚህ ደቂቅ አልጌ (Arthrospira Fusitormis) ጠቀሜታ መቀንጨርን ከመከላከል በተጨማሪ ለከንፈር ቀለምና የምግብ ቀለም ለማምረት፣ በእርጅና ምክንያት የሚመጣን የቆዳ መሸብሸብ ለመከላከልና ሌሎች ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ሀብቴ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡
ከሕፃናትና እናቶች በተጨማሪ ለማንኛውም ሰው ለአዕምሮ ንቃተ ህሊና፣ ለፀጉር ዕድገት ጭምር ጥቅም እንዳለው ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ካሳሁን ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ደቂቅ አልጌ በከፍተኛ ሁኔታ ለማምረት ከመንግሥት በተጨማሪ የባለሀብቶች ተሳታፊነት የጎላ መሆን እንዳለበትና በቀጣይ ኢንቨስተሮች በዘርፉ ለመጋበዝ ዕቅድ እንዳላቸውም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 388/2008 የተቋቋመ ምርምር ተቋም ነው፡፡