Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲያቋቁም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ...

የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲያቋቁም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ ወሰነ

ቀን:

አየር ኃይል ሰው አልባ ተዋጊዎችን ጥቅም ላይ ማዋሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታወቁ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ጣልቃ እንዲገባና ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ያቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ ተቀብሎ በሙሉ ድምፅፀደቀ፡፡

ምክር ቤቱ ቅዳሜ ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤትና ሥራ አስፈጻሚ እንዲታገድ የወሰነ ሲሆን፣ የፌዴራል መንግሥት ክልሉን የሚመራ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲያቋቁም ወስኗል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔውን ያሳለፈው በአዋጅ ቁጥር 359/1995 መሠረት እንደሆነ ታውቋል፡፡

አዋጁ የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ የወጣ ሲሆን፣ በአንድ የክልል ተሳትፎ ወይም ዕውቅና ሕገ መንግሥቱን ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ባለማክበር የሚደረግ እንቅስቃሴ፣ ማለትም በትጥቅ የተደገፈ የአመፅ እንቅስቃሴ፣ ከሌላ ክልል ወይም ሕዝብ ጋር የተፈጠሩ ችግሮች ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት ያልተቻለ እነደሆነ፣ እንዲሁም የአገሪቱን ሰላምና ፀጥታ የሚያናጋ ከሆነ የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ እንዲገባ የሚያደርጉ የሕግ አግባቦች ናቸው፡፡

‹‹ከዚህ ድንጋጌ አንፃር ሕገወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት የፈጸመውና እየፈጸመ ያለው ድርጊት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ ተጨማሪ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ ተረጋግጧል፡፡ በዚሁ መሠረት የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) ድንጋጌ መሠረት፣ ማንኛውም ክልል ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የማዘዝ ሥልጣን እንዳለው የተደነገገ በመሆኑ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ሥልጣንና ተግባር ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 251/93 አንቀጽ 36 (1) መሠረት የፌዴሬሽን ክር ቤት በአንድ ክልል ውስጥ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ ወድቋል ብሎ ሲያምን የፌዴራሉ መንግሥት ተገቢና ተመጣጣኝ ዕርምጃ እንዲወስድ ማዘዝ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 13 (4) ክር ቤቱ የፌዴራል መንግሥቱን ጣልቃ መግባት አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው እንደሆነ፣ ጣልቃ እንዲገባ ሊያዝ እንደሚችል በመደንገጉ ሕገወጡ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊና የፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት በመፈጸም የፌዴሬሽኑን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ ስለሆነ፣ ይህንን ድርጊት ማስቆም ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል፤›› ሲል ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በቀረበለት የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምፅ ያፀደቀው ሲሆን፣ የምክር ቤቱ አባላት ውሳኔው ተገቢና ወቅታዊ በመሆኑ ተፈጻሚ መሆን ይገባዋል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የሕወሓት ቡድን አገር እንዳትረጋጋና በሰላም ዕጦት እንድትማቅቅ እየሠራ በመሆኑ ከልክ ያለፈ ትዕግሥት ያሳየው የፌደራል መንግሥትበአስቸኳይ የክልሉን ምክር ቤትና አስፈጻሚ ከኃላፊነት በማገድ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲያቋቁም ወስኗል፡፡

በዚህም መሠረት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር የተጣጣመና አደጋውን ለማስወገድ እንዲቻል የፌደራል ፖሊስን ወይም የአገር መከላከያ ሠራዊትን፣ ወይም ሁለቱንም በክልሉ እንዲያሰማራ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡

በተጨማሪም ሕገወጡን የክልሉ ምክር ቤትና የክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል ታግዶ፣ ለፌደራል መንግሥቱ ተጠሪ የሆነና በአዋጅ 359/1995 አንቀጽ 15 ላይ የተቀመጡት ሥልጣንና ተግባራት የሚኖሩት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም መወሰኑን የምክር ቤቱ መግለጫ ያመለክታል፡፡

የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ከሌሎች አግባብነት ካላቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር በመተባበር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ሁኔታ ለማስወገድ የሚያስችሉ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ፣ በተጨማሪም ለክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል የተሰጡትን ተግባሮች እንደሚኖሩትም ምግለጫው አመልክቷል፡፡

ከእነዚም መካከል አስፈጸሚ አካሉን መምራት፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ኃላፊዎች መመደብ፣ ሕግና ሥርዓት መተግበሩን ማረጋገጥ፣ አግባብ ባለው ሕግ መሠረት በክልሉ ምርጫ የሚከናወንበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ የክልሉንቅድና በጀት ማፅደቅ፣ በፌዴራል መንግሥቱሚሰጡ ሌሎች ተግባራትን ማከናወን ይገኙበታል፡፡

ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን የምክር ቤቱ ውሳኔዎች አፈጻጸምና ክልሉ የሚገኝበት ሁኔታ አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ አስፈላጊነቱ ለፌዴሬሽን ክር ቤት በየሦስት ወሩ ሪፖርት እንዲያቀርብ ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ ለመላው የአገሪቱ ሕዝብ ባስተላለፈው ጥሪ፣ ‹‹መላው የትግራይ ሕዝብና የአገራችን ሕዝቦች ሕገወጡ ቡድን የፈጸመውን ኢሕገ መንግሥታዊና አስነዋሪ ድርጊት በማውገዝ፣ የአገርን ሉዓላዊ ክብር ለማስጠበቅ ከራስ በፊት ለሕዝብና ለአገር በሚል መርህ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ካለውና የኩራታችን ምንጭ ከሆነው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጨምሮ፣ ከፌደራሉ መንግሥትና ከሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ጎን እንዲቆም የፌዴሬሽን ክር ቤት ጥሪውን ያቀርባል፤›› ብሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ዓርብ ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ላይ በሰጡት መግለጫ፣ የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል በሚገኘው የሕወሓት እምቢተኛ ኃይል ላይ የወሰደው ወታደራዊ ዕርምጃ የመጀመሪው ዙር መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተከማቹ ከ300 ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ መወንጨፍ የሚችሉ ሮኬቶችና ሌሎች ከባድ መሣሪያዎች በአየር ጥቃት እንዲወድሙ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በኤርትራ ድንበሮች አካባቢ ይገኝ የነበረው የአገር መከላከያ ሠራዊት የኃይል አሠላለፉን ቀይሮ የተቃጣበትን ጥቃት በመመከት ወደ መሀል እያጠቃ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

አየር ኃይል ሰው አልባ ተዋጊ ጀቶችን በመጠቀም ጥቃቱን እንደፈጸመ የገለጹት ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ በዚህም ጥቃቱ ዒላማውን የጠበቀ መሆን ችሏል ብለዋል፡፡

በቀጣይም ጥቃቱ እንደሚቀጥል  አረጋግጠው፣ በክልሉ እየተወሰደ ያለው ወታደራዊ ዕርምጃ በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...