በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው ወታደራዊ ግጭት እንዳሳሰባት ሱዳን አስታወቀች፡፡
የሱዳን ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ሰኞ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ላ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንደገመገመ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የሱዳን ጦር መሪ የሆኑት ሜጄር ጄኔራል ያሲን ኢብራሂም በደኅንነት ምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው ጦነትና ውጤቱ አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሱዳን መንግሥት በኢትዮጵያ ያለው አሳሳቢ ሁኔታ ከጦርነት መፍትሔ ይልቅ በውይይት መፈታት እንዳለበት በማመን ጥሪ ማቅረቡን የሚገልጸው የአገሪቱ መግለጫ፣ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችም ሆኑ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ችግሩን ለመፍታት እንዲጥሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የድርድር ጥያቄዎችን እንደማይቀበል በይፋ አቋሙን የገለጸ ሲሆን፣ መከላከያ ሠራዊቱ ላይ ጥቃት መሰንዘር ለድርድር የማይቀርብ ጥፋት እንደሆነ አስታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለሱዳን መንግሥት መልዕክት መላካቸው ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አድርገው ሰሞኑን የሾሟቸውን አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ወደ ሱዳን ዛሬ ኅዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም. መላካቸው ተገልጿል፡፡ አቶ ገዱ ለሱዳን መንግሥት ያደረሱት መልዕክት ይዘት ምን እንደሆነ ግን የታወቀ ነገር የለም፡፡ አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች እንደዘገቡት በምዕራብ ትግራይ ያለው ሁኔታ ያሠጋቸው ኢትዮጵያውያን ወደ ሱዳን በመሰደድ ላይ ሲሆኑ የሱዳን መንግሥት ደግሞ ይህንኑ ሁኔታ በመሥጋት ስድስት ሺሕ ወታደሮችን በድንበር ላይ እንዳሰፈረ ገልጸዋል፡፡