Sunday, December 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ያንዣበበው የሥጋት ደመና ይገፈፍ!

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉዋቸው መልዕክቶች፣ በትግራይ ክልል የሚከናወነው ሕግ የማስከበር ተግባር የሚያበቃው፣ የሕወሓት አመራሮች ለሕግ ሲቀርቡና በክልሉ ሕጋዊ አስተዳደር ሲመሠረት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ይህም ዘመቻ በፍጥነት ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ሥጋት የገባቸው ወገኖችን በሚመለከት፣ ሥጋታቸው የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ካለመረዳት የመነጨ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመከናወን ላይ ያለው ሕግ የማስከበር ተግባር ዓላማ፣ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን ተጠያቂዎችን ለሕግ ለማቅረብ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ሕግ የማስከበሩ ሥምሪት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅም አመልክተዋል፡፡ በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት መካከል ለረዥም ጊዜ ይስተዋል የነበረው የቃላት ጦርነት ወደ ውጊያ ከተሸጋገረ በኋላ፣ የተደበላለቁ ስሜቶች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ አገሪቱ ለይቶላት ወደ እርስ በርስ ጦርነት በማምራት ለአፍሪካ ቀንድ ልትተርፍ ትችላለች የሚል ሥጋት ይሰማል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ በሕወሓት መራሹ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ላይ የጀመረውን ዘመቻ በፍጥነት በማጠናቀቅ ሰላም እንዲሰፍን የብዙዎች ምኞት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጦርነቱ መጀመሩ የሚያስፈራቸው ወገኖች አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት በሥጋትና በተስፋ የታጀቡ ስሜቶች መኖራቸው የግድ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የተጀመረው ጦርነት በፍጥነት ተጠናቆ፣ ያንዣበበው ሥጋት ቢወገድ ደግሞ ሁሉንም ወገኖች ያስማማል፡፡ በአገር ላይ እያንዣበበ ያለው የሥጋት ደመና በፍጥነት መገፈፍ አለበት፡፡

  አገር ሳትወድ ተገዳ ወደ ጦርነት ስትገባ የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ደኅንነት ለአደጋ ከመጋለጡም በላይ፣ በአገር ላይ ሊከተል የሚችለው ውድመትና የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት እንቅልፍ ይነሳል፡፡ አሁን የተጀመረው ዘመቻ በተቻለ ፍጥነት መጠናቀቅ አለበት የሚባለው፣ ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር ሊያስከትል የሚችለው ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ከባድ ስለሚሆን ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው አንድነት፣ ሰላምና ዕድገት ከመቼውም ጊዜ በላይ መጨነቅ አለባቸው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ከሕዝብና ከአገር ደኅንነትና ህልውና በላይ ራሳቸውን አሳብጠው እንዳሻን መሆን አለብን የሚሉ ኃይሎች ቦታ ሊኖራቸው አይገባም፡፡ ከሰላማዊ ውይይትና ድርድር በማፈንገጥ በጉልበት ዓላማቸውን ሊያስፈጽሙ የሚፈልጉ ቡድኖችም ሆኑ ስብስቦች፣ በሕግ የበላይነት ሥር መኖር ካልፈለጉ ሕግ የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡  ያንዣበበው የሥጋት ደመና መገፈፍ አለበት፡፡

  በአንድ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹አዲሱ ትውልድ በአሮጌ አስተሳሰብ አይመራም›› ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ ይህንን አባባል ብዙዎች ተጋርተውትም ነበር፡፡ በአሮጌ አስተሳሰብ አገር ለማፍረስ የሚጥሩ ወገኖች፣ አዲሱን ትውልድ እንዳይበክሉ መሠራት አለበት፡፡ አዲሱ ትውልድ ጥራት ያለው ትምህርት፣ ሥነ ምግባርና ሞራላዊ እሴቶች እንዲላበስ ሲደረግ የአገር ፍቅር ስሜት ይሰርፅበታል፡፡ ልዩነቶችን በግጭት ሳይሆን በሰላማዊና በሠለጠነ መንገድ እንዴት መፍታት እንደሚችል ይረዳል፡፡ በስሜታዊነት ሳይሆን በምክንያታዊነት ይመራል፡፡ ታሪክን ሲመረምር የጎራ አሠላለፍ ውስጥ ሆኖ ሳይሆን ሳይንሳዊ አሠራሮችን ይከተላል፡፡ አገርን ከሚያጠፉ ይልቅ የሚያለሙ ተግባራት ውስጥ ይገኛል፡፡ ለሐሳብ ልዕልና እንጂ ለጉልበት ሥፍራ አይሰጥም፡፡ በሐሰተኛ ወሬ ሳይደናበር እውነትን ማረጋገጥ ላይ ያተኩራል፡፡ በተጣራ ማስረጃ እንጂ በግርድፍ መረጃ አይታለልም፡፡ በአጠቃላይ ለፍትሕ፣ ለነፃነትና ለእኩልነት እንጂ ለአምባገነንነት አያጎበድድም፡፡ ለአገር ታላላቅ ጉዳዮችና ለተቋማት ግንባታ ትኩረት ይሰጣል እንጂ ለግለሰቦች ተክለ ሰብዕና አይዋደቅም፡፡ ይህንን የመሰለ ብቁና ንቁ ትውልድ ማፍራት ይገባል፡፡ ሰብዕናው የተሞረደ ልሂቅ ትውልድ ሲፈጠር የአገር ገጽታ ይለወጣል፡፡ ለዚህ ዕውን መሆን ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ መሠረቱን መጣል፣ ኢትዮጵያን ካንዣበበባት የሥጋት አደጋ ለመከላከል ያስችላል፡፡

  ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ዓውድ ውስጥ የብሔርና የሌሎች ልዩነቶችን ውጥረት ማርገብ ይገባል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ሁሉንም አሳታፊ፣ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የበለጠ የሚያጎናፅፍ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክር፣ ለአንዲት ጠንካራ ኢትዮጵያ መገንባት ዕገዛ የሚያደርግ፣ ከፋፋይነትንና ግጭትን የሚያስወግድ፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ የሚገዛ የፖለቲካ ግንኙነትን የሚያዳብር፣ ለሌብነትና ለዘረፋ ያሰፈሰፉ ኃይሎችንና የጠላት ተላላኪዎችን የሚያጋልጥ፣ የነፃነትና የእኩልነት የጋራ መብቶችን የሚያቀዳጅ፣ በኢትዮጵያ ምድር ፍትሕ የሚያረጋግጥ፣ ጀብደኝነትንና ጦረኝነትን የማይቀበል፣ ወዘተ እንዲሆን በአንድነትና በትብብር መሥራት የኢትዮጵያዊያን ግዴታም ኃላፊነትም መሆን አለበት፡፡ ከግላዊና ከቡድናዊ ጠባብ አስተሳሰብ ውስጥ በመውጣት፣ ለኢትዮጵያዊያን በሙሉ የምትመች አገር ለመገንባት መነሳት የግድ ሊሆን ይገባል፡፡ ለዘመናት ሲፈነጭ የኖረው አምባገነንነት ዳግም እንዳይመለስ በኅብረት መቆም ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መሠረት አብሮ የመሥራትን ባህል ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ የኢትዮጵያዊያን ፋንታ ነው፡፡ ከ30 ዓመታት በኋላ 200 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ የሚታሰበው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በተረጋጋ የፖለቲካ ምኅዳርና እያደገ በሚሄድ ኢኮኖሚ ካልተደገፈ በስተቀር ከባድ ችግር እንደሚገጥመው መረዳት የግድ ይሆናል፡፡ ይህንን በመገንዘብ ኢትዮጵያን ከሥጋት ቀጣናነት በፍጥነት ማላቀቅ ተገቢ ነው፡፡

  መንግሥት የአገሪቱን ዝግ የፖለቲካ ምኅዳር መክፈቱ፣ በእስርም ሆነ በስደት የነበሩ ወገኖች ወደ አገር ቤት ተመልሰው ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር እንዲያደርጉ መፍቀዱ፣ አፋኝና አሳሪ ሕጎች እንዲሻሻሉ ማድረጉና በአጠቃላይ የተሻለ ሥርዓት ለመገንባት የሚረዳ ጥርጊያ ማመቻቸቱ ትልቅ ዕርምጃ እንደሆነ መካድ አይቻልም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ተስፋዋ የበለጠ እንዲፈካና አስተማማኝ እንዲሆን፣ በሰላምና በመረጋጋት ጉዳይ ላይ ትልቅ ተግባር ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ ሰላምና መረጋጋት የሚሰፍነው ሕግና ሥርዓት በማስከበር ነው፡፡ ሰላምና መረጋጋት ሲኖር የተቀዛቀዘው ኢኮኖሚ ይነቃቃል፡፡ ከአቅም በታች የሚያመርቱ በሙሉ ኃይላቸው ይሠራሉ፡፡ ምርትና ምርታማነት ይጨምራል፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በራስ መተማመን መንፈስ ሥራቸውን ያከናውናሉ፡፡ የግንባታና የማስፋፊያ ሥራዎች በስፋት ይጀመራሉ፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሥራ አጥ ወጣቶች ወደ ሥራ ይሰማራሉ፡፡ በኮሮና ወረርሽኝም ሆነ በሰላም ዕጦት መማር ያልቻሉ የከፍተኛም ሆነ የሌሎች ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ ይመለሳሉ፡፡ በበርካታ የአገሪቱ ከተሞችና ከተማ ቀመስ ገጠሮች እየተፈጸሙ ያሉ አደገኛ ወንጀሎች ይቀንሳሉ፣ እንዲሁም ይወገዳሉ፡፡ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር የሚያሴሩ በሕግ አደብ ይገዛሉ፡፡ መንግሥት በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ሲያከናውን፣ የኢኮኖሚውም ሆነ የፖለቲካው ሪፎርም ይቀላጠፋል፡፡ የሕግ የበላይነት ጥቅሙ ይኼ መሆኑን መገንዘብ ይበጃል፡፡ ከዚህ ውጪ የአገርን ሰላም ማደፍረስና ቀውስ መፍጠር በሕግ አደብ መግዛት ይኖርበታል፡፡ የሥጋት ደመናው እንዲገፈፍ ያስችላል፡፡

  የአገሪቱ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ለሕግና ለሥርዓት መገዛት አለባቸው፡፡ ካሁን በኋላ ዓላማን በኃይል ወይም በሴራ ለማስፈጸም የሚደረግ መታበይ ለውርደት ነው የሚዳርገው፡፡ ኃይል አለን ብለው ሲመኩ የነበሩ ጉልበተኞች በሕዝባዊ አመፅ ብትንትናቸው እንደወጣ የራሳችን ታሪክ ደጋግሞ አስተምሮናል፡፡ ጠመንጃ በመወልወልና ይዋጣልን በማለት መፎከር ለዘመኑ አይመጥንም፡፡ ዓላማን በጉልበት ለማስፈጸም ሲባል ብቻ ሕገወጥ መሆን ያስጠይቃል፡፡ በሕዝብ ስም እየማሉ ሕዝብን ጦርነት ውስጥ ለመማገድ አቅልን መሳት፣ በራስ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ መስጠት ነው፡፡ በሠለጠነ ዘመን የጦር መሣሪያ አንግቦ ጦርነት መቀስቀስ ከባድ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ በሕዝብ ሕይወትና በአገር ህልውና ላይ አደጋ መጋበዝ የሥልጡን ፖለቲከኞች ተግባር አይደለም፡፡ ያለ ጦርነት ዓላማቸውን ማስፈጸም የማይችሉ የሚመስላቸው ኃይሎች፣ ድርጊታቸው ሕዝብንና አገርን ችግር ውስጥ እንደሚከት መገንዘብ አለባቸው፡፡ በዕብሪትና በጥጋብ ከገቡበት አደገኛ መንገድ በፍጥነት ካልተመለሱ፣ በሕግም በታሪክም የሚያስጠይቃቸው ወንጀል እየፈጸሙ እንደሆነ ሊያውቁት ይገባል፡፡ አገርን በማተራመስ ሥጋት መፍጠር ተቀባይነት የሌለው ከመሆኑም በላይ፣ በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበው የሥጋት ደመና መገፈፍ አለበት!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አነስተኛ ካፒታል ያላቸው ባንኮች በመዋሃድ አቅም እንዲፈጥሩ ጉምቱው የፋይናንስ ባለሙያ መከሩ

  የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ እንዳይገቡ የሚከለክለውን ሕግ የማሻሻል...

  በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

  በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

  ከባንኮች ጋር ለሚደረገው የጥሬ ገንዘብ ርክክብ የክፍያ ተመን ወጣ

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከባንኮች ጋር ለሚያደርገው የብር ኖት ርክክብ...

  ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ምንም ዓይነት ግብይት እንዳይደረግ ከለከለ

  የውጭ ዜጎች መያዝ የሚፈቀድላቸው የገንዘብ መጠን ከእጥፍ በላይ ከፍ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...

  ዘንድሮ የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን በበይነ መረብ ለማድረግ ዝግጅት መጀመሩ ተገለጸ

  በሁሉም መደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሐ ግብሮች የሚመረቁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ምሁራንና ልሂቃን ከአስተዋዩ ሕዝብ ታሪክ ተማሩ!

  አገራዊ ምክክሩን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ የኢትዮጵያን የትናንት ትውልዶችና የዛሬውን ይዘት መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ያለፉት ዘመናት ትውልዶች ለአገራቸው የነበራቸው ቀናዒነት የፈለቀበት...

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...