ክለቡ ለቀድሞ ተጨዋቾች የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል
የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ የበላይ ጠባቂ እንዲሆኑ የቀረበላቸውን ጥያቁ መቀበላቸው ታወቀ፡፡ ክለቡ ለቀድሞ ተጨዋቾች የገንዘብ ድጋፍ ከማድረጉ በተጨማሪ ክለቡን በበጎ ፈቃዳቸው ላገለገሉ ሰዎች የዕውቅናና የምስጋና ሰርተፊኬት መስጠቱ ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) የክለቡ የበላይ ጠባቂ እንደሚሆኑ ያረጋገጡት፣ በተወካያቸው አቶ ለማ ደጋፋ አማካይነት ባስተላለፉት መልዕክት ነው፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን ክለቡ ከተመሠረተበት ከ1968 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ባለው በዕውቀታቸው፣ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው ዕገዛ ላደረጉ ግለሰቦች፣ የክለቡ ባለውለታ የቀድሞ ተጨዋቾች የዕውቅናና የምስጋና እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ቡና የቦርድ አባል አቶ ይስማሸዋ ሥዩም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ለክለቡ አገልግሎት ሰጥተው በአሁኑ ወቅት በሕይወት ለሌሉና በሕይወት ለሚገኙ የቀድሞ ተጨዋቾች አሰግድ ተስፋዬ፣ ተሾመ ተፈራ፣ አሸናፊ በጋሻውና ተስፋዬ ጅማ ለእያንዳንዳቸው 100 ሺሕ ብር የገንዘብ ድጋፍ የተደረገላቸው መሆኑም አቶ ይስማሸዋ ገልጸዋል፡፡