Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትዋሊያዎቹ ከኒጀር ጋር ላለባቸው ወሳኝ ጨዋታ ኒያሚ ገብተዋል

ዋሊያዎቹ ከኒጀር ጋር ላለባቸው ወሳኝ ጨዋታ ኒያሚ ገብተዋል

ቀን:

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) በ2021 በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ምድብ ማጣሪያ በዚህ ሳምንት ይጀመራል፡፡ 23 ተጨዋቾችን የያዘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ከነገ በስቲያ ዓርብ ኅዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም. የኒጀር አቻውን ለመግጠም ከትናንት በስቲያ የአገሪቱ መዲና ኒያሚ ገብቷል፡፡

በአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት መባቻ የቻይና ግዛት በሆነችው ሁዋን ከተማ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በዚህ ሳምንት ሲጀምር፣ በአጠቃላይ 48 አገሮች በመርሐ ግብሩ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል፡፡ ካፍ ወረርሽኙን ምክንያት በማድረግ አንሳተፍም የሚሉ አገሮች ቢኖሩ ውጤቱ በፎርፌ የሚጠናቀቅ ይሆናል ማለቱ ተሰምቷል፡፡

በሁለቱም የማጣሪያ ጨዋታ ሽንፈትን ያስተናገደችው የኢትዮጵያ ተጋጣሚ ኒጀር፣ በ61 ዓመቱ ፈረንሣዊ ዣን ሚሸል እየተመራች ጠንካራ ዝግጅት ስታደርግ መሰንበቷ ይነገራል፡፡ ኒጀር የምድቡ መሪ በሆነችው ማደጋስካር 6 ለ2 በሜዳዋ ያስተናገደችው ሽንፈት ለአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ የነበራትን ዕቅድ ቢያበላሽባትም፣ ከኢትዮጵያ ጋር የምታደርገውን ጨዋታ አሸንፋ የጎል ዕዳዋን ለማካካስ የምታደርገው ጨዋታ በመሆኑ ይጠበቃል፡፡

ቀደም ሲል ምድቡን በቀላሉ አልፋ ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ እንደምትበቃ ቅድመ ግምት አግኝታ፣ ነገር ግን በኢትዮጵያ ያልተጠበቀ ሽንፈት ያስተናገደችው አይቮሪኮስት፣ ምድቡን በስድስት ነጥብ ከምትመራው ማደጋስካር ጋር ትጫወታለች፡፡ የሚያደርጉት ጨዋታ፣ ኢትዮጵያን በሜዳዋ ለምታስተናግደው ኒጀር በምድቡ ለመቆየት ብቻ ሳይሆን፣ ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ያልተሟጠጠ ዕድል እንዲኖራት ያደርጋል የሚሉ አስተያየቶች አሉ፡፡

ለዚህ ምክንያት ተደርጎ የሚቀርበው ደግሞ፣ አይቮሪኮስት በማደጋስካር ተሸንፋ ኒጀር ኢትዮጵያን በሜዳዋ የምታሸንፍ ከሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያን ጨምሮ ሦስቱም አገሮች እኩል ሦስት ነጥብ ይዘው በሚያስቆጥሩትና በሚቆጠርባቸው የጎል መጠን ተለያይተው ቀጣዩን የማጣሪያ ጨዋታ ስለሚጠብቁ ነው፡፡

በሦስት ነጥብና በአንድ ንፁህ ጎል ሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ ከሜዳዋ ውጪ ከኒጀር ጋር የምታደርገው ጨዋታ በብዙ መልኩ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው የሚጠቅሱ አሉ፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የኒጀሩን ጨዋታ ባደረገች በሳምንቱ በመልሱ ጨዋታ ኒጀርን በሜዳዋ ስለምትገጥም በተሻለ ውጤታማ የምትሆንበት ዕድሏ ሰፊ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ጭምር ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከነገ በስቲያ በምታደርገው ጨዋታ ነጥብ የምትጥል ከሆነ ግን፣ የሚቀራት ጨዋታ ከሜዳዋ ውጪ ከአይቮሪኮስት እንዲሁም በሜዳዋ ከማዳጋስካር ጋር ስለሚሆን የማለፍ ዕድሏን እንደሚያጠብባት የዘርፉ ሙያተያኞች ቅድመ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ አማካይነት ከአንድ ወር በላይ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ባደረገው ጥረት ሦስት የወዳጅነት ጨዋታዎች አድርጎ፣ በዛምቢያ ሁለት ጊዜ ተሸንፎ ከሱዳን ጋር ሁለት እኩል በሆነ ውጤት መለያየቱ ይታወሳል፡፡

አሠልጣኝ ውበቱ ከሦስቱ የወዳጅነት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ኒጀር ይዘዋቸው የተጓዙትን 23 ተጨዋቾች ዝርዝር አሳውቀዋል፡፡ ቀደም ሲል ከያዟቸው 26 ተጨዋቾች መካከል ሦስቱ ከኒጀሩ ስብስብ ውጪ ቢሆኑም፣ ባህር ዳር ላይ ለሚደረገው የመልስ ጨዋታ ግን በሆቴል ቆይታ የሚያደርጉ ይሆናል ተብሏል፡፡   

ወደ ኒጀር የተጓዙት ምንተስኖት አሎ፣ ጀማል ጣሰው፣ ተክለማርያም ሻንቆ፣ አስቻለው ታመነ፣ ያሬድ ባየህ፣ ወንድሜነህ ደረጀ፣ መሳይ ጳውሎስ፣ ረመዳን የሱፍ፣ አምሳሉ ጥላሁን፣ ሱሌማን ሀሚድ፣ ሽመክት ጉግሳ፣ ሽመልስ በቀለ፣ ሱራፌል ዳኛቸው፣ ይሁን እንደሻው፣ ታፈሰ ሰለሞን፣ መሱድ መሐመድ፣ አማኑኤል ዮሐንስ፣ ከነዓን ማርክነህ፣ ሀይደር ሸረፋ፣ ጋዲሳ መብራቱ፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል፣ አቡበክር ናስርና ጌታነህ ከበደ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...