Tuesday, February 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሕወሓትና እየነጎደበት ያለው የኪሳራ መንገድ

ሕወሓትና እየነጎደበት ያለው የኪሳራ መንገድ

ቀን:

በሡልጣን ባህሩ

ሕወሓት የትጥቅ ትግል የጀመረበትና ድርጅቱን በይፋ የመሠረተበትን 45 ዓመት ባለፈ ዓመት ማክበሩ ይታወሳል። ድርጅቱ ደጋፊዎቹንና አባላቱን አነቃንቆ በዓሉን ሲያከብር ከቀደሙት ዓመታት በተለየ ሁኔታ ከአገሪቱ ማዕከል ተገፍቶ፣ በተፈጠረበት ክልል ላይ ብቻ ተወስኖ ነበር፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የልዩ ኃይል ማበራከት በሁሉም ዋና ዋና ክልሎች ተጠናክሮ የሚታይ ቢሆንም፣ ሕወሓት ግን በሠራዊቱ ድምቀትና ለየት ባለ መንገድ በቡድን የመሣሪያ ትርዒት በማሳየት አድምቆት መታየቱ አይዘነጋም፡፡

ሕወሓት ያንን ሁሉ የጦር መሣሪያ ትርዒት ሲያሳይና የበፊቱን የበረሃ ትግሉን እያስታወሰ ሲውረገረግ፣ ነገሩ ያላማራቸው ብዙ ሰዎች ጦርነት ለመጀመር ፍላጎት እንዳለው በቀላሉ መረዳት ችለው ነበር፡፡ ከፌዴራል መንግሥት መሪነት በሕዝባዊ እንቢተኝነት ተባሮ ወደ መቀሌ የሸሸው ይህ ኃላፊነት የማይሰማው ቡድን፣ ሰሞኑን የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት አካል የሆነውን ሰሜን ከኋላ እንደ ጠላት ሆኖ በመውጋት ፀረ ኢትዮጵያዊነቱን አስመስክሯል፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ለማድረግ ተፈጥሮው ያልሆነው ይህ ቡድን፣ በፊት በለመደው አምባገነናዊ መንገድ ሁሉንም ነገር ለመቆጣጠር ካለው ፍላጎት የተነሳ ጦረኛ ሆኖ ተከስቷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአገሪቱ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፌዴራል ሥርዓቱ ሕጋዊ ማዕቀፍ በማፈንገጥ የምርጫ ኮሚሽን በመሰየምና የውሸት ምርጫ በማካሄድ የለመደውን ሙሉ በሙሉ አሸናፊ ሆኛለሁ ብሏል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎት በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በሕዝብ በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀውን በመፃረር፣ የፌዴራል መንግሥቱ ጊዜው አብቅቶለታል በማለት የጦርነት ቅስቀሳ መጀመሩ አይዘነጋም፡፡ ለድርድርና ለሰላም ደንታ የሌለው ይህ ኃይል ሰሞኑን ዱላው ሲበረታበት ለመደራደር ፍላጎት ማሳየቱ ተሰምቷል፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ይህ ጦረኛና አሸባሪ ቡድን ዋጋውን አግኝቶ ሕግ መከበር አለበት፡፡ እጁን በሰላም ሰጥቶ ለሕግ መቅረብ ይኖርበታል፣ ወይም እስከ ወዲያኛው መሸኘት ይኖርበታል፡፡

ይህ ኃይል በረጅም የታሪክ ዘመን ውስጥ በርካታ ችግሮችን የፈጠረ፣ ከትጥቅ ትግል እስከ መንግሥታዊ አስተዳደር በኢትዮጵያ ፖለቲካ አየር ውስጥ አገሪቱን አሳር ያበላ ነው፡፡ ይህ ኃይል ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን እየጠላ 27 ዓመት መግዛቱ በጣም ይደንቃል፡፡ በሥልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ኢትዮጵያዊያንን በመግደል፣ በማሰር፣ በማሰቃየትና በማሳደድ ይታወቃል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎት አባላቱንና ደጋፊዎቹን ይዞ አገር በመዝረፍ ተወዳዳሪ የለውም፡፡ ኢትዮጵያዊያንን ማንነታቸውን ተገን በማድረግ እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩ፣ እንዲጋጩና አገሪቱን ቀውስ ውስጥ እንዲከቱ ከፍተኛ ደባ ሠርቷል፡፡ ከሥልጣን ከተባረረበት ጊዜ ጀምሮ አገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ሥፍራዎች በደረሱ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎችና ውድመቶች እጁ አለበት፡፡ ጋሻ ጃግሬዎቹ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ከሚሰጡዋቸው አስተያየቶችና ጥቆማዎች በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡

በዴሞክራሲ ግንባታ ረገድም አብዮታዊነት የተጠናወተውና በገደብ ላይ የተመሠረተ ስትራቴጂ ተከትሎ፣ ልዩነትን ለማስተናገድ የተቸገረና ባለ መንታ መንገድ ሥርዓት ለማንበር ከፍተኛ ጥረት ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ ከላይ ሲያዩት ዴሞክራሲያዊ ቢመስልም፣ አፋኝና የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት የገደበ አካሄዱን ማስታወስ ይቻላል፡፡ የጠላትና የወዳጅ ፍረጃና የመካረር አዙሪትን ለመበጠስ መቸገሩም የሚመነጨው ከዚሁ አደገኛ ባህሪው ነው፡፡

ከዚህ ባልተናነሰ በአገሪቱ ማኅበረ ኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ገዥው ፓርቲ በሆነው ኢሕአዴግ መሪነት በሙስና፣ በኢፍትሐዊነትና ሀብት በማሸሽ የታሪክ ክስረት ውስጥ በቅድሚያ የሚታማ ድርጅት ነው፡፡ ከመታማት አልፎም ራሱ በተግባር ያረጋገጠው ነው፡፡ ሕወሓት ገዥ ፓርቲ ሆኖ በኖረባቸው ዓመታት አባላቱንና ደጋፊዎቹን ብቻ ሳይሆን፣ የትግራይ ሕዝብን እንደ ሕዝብ ሊያስጠላ የሚችል ጭፍን ዘረፋና የኔትወርክ ንጥቂያ ውስጥ የተዘፈቀ ነበር፡፡ ሌላው ሁሉ ቢቀር ሜቴክ በተባለው መንግሥታዊ ኮርፖሬሽንና ኤፈርት በተሰኘው የዘረፋ ድርጅት አማካይነት የፈጸመውን ንጥቂያ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ለዚህ ደግሞ ብሔርን አልፋና ኦሜጋ ያደረገ አካሄዱ አመቺ መደላድል የሆነው ሲሆን፣ የእሱኑ መንገድ የሚከተሉ የፖለቲካ ኃይሎችም ተቀፍቅፈዋል፡፡ ዛሬ ባለችው ኢትዮጵያ በሕጋዊነት ከተመዘገቡት 100 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች 75 በመቶው የሚሆኑት የብሔር ፓርቲዎች መሆናቸው የአባባሉ ማሳያ ነው፡፡ ብሔር ተኮሮቹ  ክልሎች  በመካለላቸው ሚዲያ፣ ፖሊስና ልዩ ኃይል የመሳሰሉትን በአቅማቸው ልክ ብቻ ሳይሆን፣ እንዳሻቸው በመፍጠራቸውና በማዘዛቸው አጉል ፉክክር ተፈጥሮ አገሪቱን ችግር ውስጥ መክተቱ አይዘነጋም፡፡ በዚህ ላይ የፌዴራሉ መንግሥት ደከም ያለ ሲመስል ብሔርተኞች እየገነኑ የደረሰው መከራ አይዘነጋም፡፡ የእነዚህ ነባራዊ ሀቆች የነፍስ አባታቸው ደግሞ ሕወሓት ነው ማለት ስህተት አይደለም፡፡

ቀደም ባለው ታሪካችን ምንም እንኳን በአገሪቱ የብሔር ጭቆና አልነበረም ባይባልም ሕዝቦቻችን ታሪክ፣ እምነት፣ ባህልና ቋንቋቸውን ከማስፋፋትና ከማጠናከር ባለፈ በማንነት ላይ የተመሠረተ ዕድር፣ ማኅበር፣ የንግድ አክሲዮን፣ የመኖሪያ ሠፈር፣ ወዘተ. እንዲያቆጠቁጥ እስከ ማድረግ ያበረታታው የሕወሓት አክራሪ ብሔርተኛ መንገድ ነው፡፡ ከሁሉ በላይ በአንድ አገር የፀኑ የመኖሪያ ክልሎችን በብሔር ላይ መሥርቶ እንደሚያመቸው በመቀየድ፣ ለዘመናት ተሳስሮና ተዋልዶ የኖረን ሕዝብ ማንነትን በወሰንና፣ በመንደር ሀብት በማፋጠጥ አንድነትንና ኅብረ ብሔራዊነትን የሸረሸረውም  የዚሁ ኃይል ፍልስፍና መሆኑን ዛሬ በግልጽ መናገር ይቻላል፡፡

እውነት ለመናገር ‹‹የአገራችን ሕዝቦች ጨዋ፣ አንድነትና መከባበርን የሚያውቁ፣ ለዘመናት በመቻቻልና በመደማመጥ የዘለቁ፣ አንዳንዱ ሕዝብም በባህላዊ ትውፊቶቹ ዴሞክራሲያዊነትንና ዕርቅን የተለማመደ፣ ወዘተ.›› እያልን ምንም ያህል ብንዘምር፣ ከአክራሪ ብሔርተኛ ፖለቲካ ካልተወጣ ሁሉም ወደ ራሱ መሰባሰቡ ብቻ ሳይሆን መገፋፋቱም አይቀሬ የሆነው የሕወሓት አደገኛ ተንኮል ሥር በመስደዱ ነው፡፡ ይህም ኅብረ ብሔራዊ ሆነውን ሕዝብ እየገፋ፣ ያለ ጥርጥር ጠባብነትና ዘረኝነትን እያፋፋ መሄዱ በሚገባ ታይቷል፡፡ ስለዚህ አገር እንደሚወድ ዜጋ ሁላችንም ለአገር አንድነት ዘብ በመቆም፣ አገሪቱን ከዘር ፖለቲካና የጎሳ ፌዴራሊዝም ለማውጣት ሕዝብን ያሳተፈ መፍትሔ መፈለግ ግድ የሚል ሆኗል፡፡ ሕወሓት በቀደደልን ቦይ እየፈሰስን አገራችንን በዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት አይቻለንም፡፡

ይህ ማለት ግን በሕወሓት መሪነት 45 ዓመታት የኖረ አስተሳሰብ ከሌላውም ወገን የሚከተለው ደጋፊ አላፈራም ማለት እንዳልሆነ ጠቅሻለሁ፡፡ እንዲያውም አሁን ባለው ትውልድ ውስጥ አብዛኛው ትኩስ ኃይል ከአገራዊ አንድነት ይልቅ ብሔርተኝነትን፣ አለፍ ሲልም ጠርዘኛ ብሔርተኝነት (ጠባብነትን) እያቀነቀነ ይገኛል፡፡ በፖለቲካ ኃይል ደረጃም አገርን በአብሮነት ከመምራት ይልቅ፣ በብሔር ባርኔጣ ውስጥ ተደፍቀው ብሶት በመቆስቆስ ላይ የሚገኙ ድርጅቶች አሁንም እንዳሉ ናቸው፡፡ ይህን እውነት ሁላችንም የምናውቀው ቢሆንም፣ በርካቶች በተባ ብዕር የሚተቹትና የሚያወግዙት  ብቻ ሳይሆን፣ አሁን ላለው ፖለቲካዊ ምስቅልቅልም መንደርደሪያው እሱ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በተለይ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ራሳቸውን መመርመር ይኖርባቸዋል፡፡

እንደሚታወቀው ሕወሓት እያሳደደ ከሚያሰቃያቸውና ከሚገድላቸው ፖለቲከኞች መካከል በብዛት የኦሮሞ ልሂቃን እንደነበሩ ማንም አያስተባብልም፡፡ ነገር ግን በፌዴራሊስትነት ስም አምባገነኑ ሕወሓት ሥር የገቡ የኦሮሞ ፖለቲከኞች በጣም ያስገርሙኛል፡፡ ሕወሓት በፌዴራሊዝም ስም ሁሉንም ነገሮች ተቆጣጥሮ አሀዳዊ መሰል ሥርዓት ሲመራ እንደነበር፣ የኢትዮጵያዊያንን መብቶች ደፍጥጦ በርካታ ሺዎችን እስር ቤት ማጎሩ እንደማይረሳ፣ ከበርካታ ተጠቂዎች መካከል ብዙዎቹ ኦሮሞዎች መሆናቸው እየታወቀ ሕወሓትን ምሽግ ማድረግ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ መሳለቅ ነው፡፡ ለሕዝብ ሳይሆን ሥልጣን ለመያዝ ያሰፈሰፉ ፖለቲከኞች የተጀመረውን ለውጥ በመፃረር፣ ከቀድሞው አምባገነን ሕወሓት ጋር ሲሞዳሞዱ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ተገንብቶ በነፃነት ሕዝቡ እንዲኖር ማድረግ ሳይሆን ዓላማቸው፣ አገሪቱን እንደ ዶሮ ብልት በመገነጣጠል ለዘመናት የመከነ ሕልም ማሳካት እንደሆነ ማንንም ግር አይለውም፡፡

በሌላ በኩል ሕወሓትና ጀሌዎቹ ለውጡ የሰጣቸውን ዕድል ተጠቅመው እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ ለማስደሰት ከመሥራት ይልቅ፣ በየቦታው ግጭት እየፈጠሩ ሕይወቱን ለአደጋ ሲዳርጉ ነው የቆዩት፡፡ አሁን ሕወሓት ለይቶለት ትግራይን የጦር ሜዳ ሲያደርጋት ሕዝቡ ሊደርስበት የሚችለው መከራ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ በሰላም ወጥቶ መግባት ብርቅ ሆኖ የከባድ መሣሪያ ጩኸት መስማት ለሰላማዊ ሕዝብ በጣም ከባድ ነገር ነው፡፡ ዕድሜና ልምድ ሊገራቸው ያልቻለው የሕወሓት አንጋፋዎች ግን እንደ ሙዚቃ ይናፍቃቸው ይመስል፣ የትግራይን ሕዝብ መያዣ አድርገው ጦርነት ቀስቅሰዋል፡፡ ይህ ጦርነት ግን እነሱን እንደሚበላቸው መታወቅ አለበት፡፡ እነሱ የለመዱት ባህላዊ ጦርነት በጣም ከመዘመኑ የተነሳ መቼና እንዴት እንደሚማረኩ ወይም እንደሚደመሰሱ እንኳ ማወቅ እንደማይችሉ ከሰሞኑ ኦፕሬሽን ታይቷል፡፡ አንድ እርግጠኛ መሆን የሚቻልበት ነገር ግን ከዚህ ጦርነት በሰላም እንደማይወጡ ነው፡፡ ይህም ፍፃሜያቸውን ውርደት ያደርገዋል፡፡

በፊት አገሪቱ ውስት ብቸኛው ድርጅትና ጠንካራ ሠራዊት የነበረው ሕወሓት እንደነበር ይነገራል፡፡ አሁን ግን ይህ ታሪክ የሚሆንበት ጊዜ ተቃርቧል፡፡ በሁሉም ነገር የበላይ ሆኖ የመቀጠል ፍላጎቱ በጦረኝነት አባዜው ሊመክን ጫፍ ደርሷል፡፡ በኢትዮጵያዊያን ላይ እንዳሻው ሲፈነጥዝ የነበረው በኃይሉ በመመካት ቢሆንም፣ አሁን ግን በሠለጠነ መንገድ ልኩን እንዲያውቅ እየተደረገ ከመጨረሻ ምሽጉ ተጎትቶ ሊወጣ ነው፡፡ ምስኪኑ የትግራይ ሕዝብም እንደ ሌሎች ወንድሞቹና እህቶቹ የነፃነት አየር የሚቃመስበት ጊዜ ለመድረሱ ጥርጥር ሊገባን አያስፈልግም፡፡ በስሙ ሲነግድበት የነበረው ሕወሓት ወደ መቃብሩ ሲላክ በሌሎች ዴሞክራትና ሰብዓዊነት በሚሰማቸው ልጆቹ እየተመራ ወደ ነፃነት ጉዞውን ይጀምራል፡፡ ይህ ደግሞ በእርግጠኝነት ዕውን ይሆናል፡፡

ሕወሓት ከፈጠረው ምስቅልቅል ለመውጣትና አገርን ከፍ ለማድረግ የፈለጉ የለውጥ ኃይሎች፣ ሕወሓት እስከ መቃብር ድረስ የያዘውን የክፋት ዓላማ ተባብረው መቅበር አለባቸው፡፡ ይህም የብዙዎች እምነት መሆኑ በተለያዩ መንገዶች ተረጋግጧል፡፡ እውነተኛ ፌዴራሊዝም በመመካከር ለመመሥረት የሚያስችል ቅርርብ መፍጠርና በጋራ መሥራት ሲቻል፣ ሕወሓት የዘራው አረም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይነቀላል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በእኩልነት የሚኖሩበት ትክክለኛ የፌዴራል ሥርዓት በመመሥረት አክራሪ ብሔርተኞች የሚያራምዱትን አደገኛ አስተሳሰብ ማምከን ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በልጆቿ ስምምነት የሚፈጠር ፌዴራላዊ ሥርዓት እንጂ፣ ሕወሓትና ቢጤዎቹ የሚያራግቡለት በታኝና አውዳሚ ሥርዓት እንዳልሆነ ግንዛቤ እየተፈጠረ ነው፡፡ ይህም በሕወሓት መቃብር ላይ ይሳካል፡፡

እንግዲህ የሕወሓት ግልጽ አሠላለፍና አቋም ይህ መሆኑ በገሀድ የሚታየው፣  አብሮነትንና በአንድነት መኖርን የሚመርጡ ወገኖች ተሰባስበው መታገል ግድ የሚላቸው ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያዊያን አገር ከመበተንም ሆነ ነጣጥሎ ከመግዛት ለማውጣት፣ በንቃትና በሰላማዊ መንገድ የሕወሓታዊያንን አስተሳሰብ መድፈቅና ተቀባይነት ማሳጣት ነው የሚኖርባቸው፡፡ ይህን የማድረግ ጉዳይ ደግሞ ብልፅግናን ወይም ኢዜማን የመሰሉትን የመምረጥ አጀንዳ ሳይሆን፣ አገርንና አብሮነትን ጠብቆ የመቆም ርብርብ ነው፡፡ ሥልጡን የፖለቲካ ፉክክር ሊኖር የሚችለው የተሻለ አስተሳሰብ ይዞ ሕዝብ ዘንድ በመቅረብ እንጂ፣ እንደ ሕወሓትና መሰሎቹ አገር ላይ በማሴር አይደለም፡፡ ሕወሓት የረባ አገራዊ ራዕይ ስለሌለውና ለዴሞክራሲ ፍፁም ፀር ስለሆነ፣ ለሠለጠነ ፖለቲካ ባዕድ ከመሆኑም በላይ ለአገር ህልውናም ጠንቅ ነው፡፡ አገራችንን በዚህ መንፈስ ነው ከዚህ ጠንቀኛ ኃይል መጠበቅ ያለብን፡፡

በእርግጥ ይህን ለማድረግ አሁን እንደምንመለከተው ፈተናው ቀላል አይሆንም፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያዊያን አክራሪ ብሔርተኝነትን እየተላበስን የመጣን ስለሆነ፣ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ያስፈልገናል፡፡ ሁሉም ብሔርና ዘሩን ፈላጊ እየሆነ በመሄዱ የዜግነት ፖለቲካ ፈተና ሆኗል፡፡ ይህ አካሄድም የጋራ ቤትና በታሪክ የእኛ ስንላት የኖርናትን አገር ለልጆቻችን ስለማስተላለፋችን ዋስትና የሚያሳጣ በመሆኑ ትግል ሊደረግበት የግድ ነው፡፡ ይህን በእኩልነትና ዋስትና በሚሰጥ ፍትሐዊነት አለመቀየር የዚህ ትውልድ ውድቀትና ሽንፈት ስለሚሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡

አሁን ማን ይሙት የሕወሓታዊያኑ መንገድ የሆነው የብሔር ፌዴራሊዝም  አዋጭና ዘላቂ የአገር አንድነት የሚያስከብርና የኖረውን የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና  የፖለቲካ ጥያቄ የሚፈታ ቢሆንተለወጥን!” እያልን ይህን ያህል አገራዊ ትርምስ  በዚች ምድር ይታይ ነበር? እስኪ በጥሞና እናጢነው፣ እንመርምረው፡፡ የዘር ፖለቲካ አንድነታችንን የሸረሸረ ብቻ ሳይሆን፣ ፈጣኑን የልማት ጉዞም እየደፈቀ የመሆኑ ጉዳት  እስካሁን ያልተሰማውና ዋስትና ያላሳጣው ዜጋስ ይኖር ይሆን? በጥላቻና በተካረረ መንገድ ከመጠላላት የማያስወጣ ብልሹ አካሄድ መሆኑስ ማን ሊክደው ይችላል? ይህ ነው እውነታው፡፡ እውነታው ብቻ ሳይሆን የአገራችንና የሕዝባችን ደመኛ ሕወሓት እንደሆነም ግልጽ ነው፡፡

በአጠቃላይ ከትግራይ ሕዝብ አልፎ መላው የአገራችንን ሕዝብ እዚህ ደረጃ ያደረሰው ክፉው ሕወሓት፣ ከአሁን በኋላ ተገቢውን ዋጋውን አግኝቶ መሰናበት አለበት፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ በአገር ላይ የሠራው ደባና ክፋት ከዚህ በኋላ አይቀጥልም፡፡ በተለመደው መንገድ ብረት ነክሶ ወይም በተፅዕኖ አስፈራርቶ የኖረበትን መንገድ ልከተል ካለ በቀዳሚነት ውድቀቱ የራሱ ነው፡፡ ይህ ውድቀትም እየተፋጠነ ነው፡፡

ሕወሓት የመሠረተው የብሔር ጭቆናን የሚያላቅቅ የተባለ የብሔር ፌዴራሊዝምን አስተሳሰብ ዓለም እየተወው፣ የአገራችን ጠባብ ብሔርተኞች ጭቦ እንዳይሠሩበትም በፅናት መታገሉ ነው የሚጠቅመው፡፡ ይህን ካልተደረገ አደጋ ስላለው መላው የአገሪቱ ሕዝብ መመከትና መታገል ይኖርበታል፡፡ ሁላችንም እንደሚቆጨው ዜጋ በእዚህ ጉዳይ ላይ ሐሳብ መስጠት የሚያስፈልገን፣  የችግሮቹ ሁሉ ሰንኮፍ ከዘር ፖለቲካና ከሕወሓታዊያን መንገድ ጋር የተያያዘ በመሆኑና ስለማያወጣን ብቻ ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የዘር ፖለቲካ አስተሳሰብ ባለቤት የሆነው ሕወሓት እያበቃለት ስለሆነ፣ ለአገራችን ዳግም ትንሳዔ ሁላችንም በጋራ መክረን የምናፀናው ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ያስፈልገናል፡፡ ከሕወሓት ውድቀት በኋላ ቢጤዎቹም አብረው ስለሚመክኑ እዚህ ላይ አፅንኦት ማድረግ የግድ ነው፡፡

ድል ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ!

ከአዘጋጁ፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የካቲት አብዮት – ጥያቄዎችሽ ዛሬም እየወዘወዙን ነው!

በበቀለ ሹሜ አጭር መግቢያ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከ1960ዎች ወጣቶች ርዝራዦች አንዱ...

የሰሞኑ የ“መኖሪያ ቤቶች” የጨረታ ሽያጭ ምን ዓይነት ሕጋዊ መሠረት አለው?   

በዳዊት ዮሐንስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አየር ላይ ከሚንሸረሸሩ ዜናዎች...

ሁለቱ ወጎች፡ ከሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! እስከ በዓሉ ቤርሙዳ

በተክለ ጻድቅ በላቸው ሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! ከሁለት ሦስት ዓመት...

ለትግራይ ክልል ድርቅ ተፈናቃዮች አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ...