Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዓለም አቀፍ የቡናና የቱሪዝም ንግድ ትርዒት የሚካሄድበት ቀን ተቆረጠ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ከቡና ወጪ ንግድ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማሳደግና የቡና መገኛ አገር መሆኗን ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል የተባለው ዓለም አቀፍ የቡናና ቱሪዝም የንግድ ትርዒት ከጥር 17 እስከ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

‹‹ፍቅር ለሕዝቦች በጎ አድራጎት›› የተባለው ተቋም አማካይነት የሚያካሂደውን ይህንን የንግድ ትርዒት አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ የቡናና ቱሪዝም ኹነት ዋና ዓላማ የቡና አምራቹን፣ ቡና አቀናባሪውን፣ ቡና ላኪዎችን፣ ዓለም አቀፍ ቡና ገዥዎችን በአንድ መድረክ ላይ እንዲገናኙ ማድረግ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ትራንስፖርተሮችና ትራንዚተሮችን ጨምሮ ሁሉንም ተዋንያንን አንድ ላይ በማገናኘት የቡና ግብይት ትስስርን በመፍጠር እንዲሁም የፋይናንስ ችግርን ማቃለል ላይ ትኩረት ያደረገ እንደሚሆንም ድርጅቱ ዝግጅቱን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡

የፍቅር ለሕዝቦች በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ ማስተር ሔኖክ መገርሳ የዝግጅቱን ዓላማ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ‹‹የአገራችን ቡና አምራች ከሚያመርተው የቡና ምርት የተሻለ ገቢ እንዲያገኝ ማስቻል ነው›› ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ  የቡና ምርት ግብይት ሒደትን ማሻሻልና ዘመናዊ የግብይት ሒደትን እንዲከተል የአቅም ግንባታ ሥልጠና፣ ቴክኖሎጂና ፋይናንስ እንዲያገኝ አመቺ መድረክ እንደሚሆንም አክለዋል፡፡

 በጥር ወር ላይ በሚሰናዳው በዚህ ዝግጅት ላይ ዓለም አቀፍ ቡና ገዥዎችና ቡና ቀማሾች ትብብር አማካይነት በሚካሄድ የቡና ጥራት ውድድር አሸናፊ ለሚሆነው የቡና መገኛ አካባቢ ዕውቅና የሚሰጥበት ነው ተብሏል፡፡

የቦርድ ሰብሳቢው አክለውም ኢትዮጵያ የቡና ዓረቢካ መገኛ አገርና የተለያዩ ጣዕም ያላቸው ቡና የሚመረትባት አገር ብትሆንም ከዘርፉ በተገቢው ሁኔታ ተጠቃሚ አለመሆኗን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የቡና ገበያ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችላትን ዕድል ለመፍጠር በዝግጅቱ ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቡና ወጪ ንግድ የተሻለ ገቢ እንድታገኝ የቡና ምርት ጥራት ከመጠበቅና በተሻለ ሁኔታ አስተዋውቆ እንደ ቡና መገኛ አገር የተሻለ የቡና ገበያና አገሪቱን የቡና ቱሪዝም መዳረሻ ተጠቃሚነትን ማግኘት የነበረባት ቢሆንም፣ ይህ ሳይሆን ቀርቶ የኢትዮጵያ ቡና ከዓለም ምርት በወረደ የገበያ ዋጋ ሲሸጥ ስለመቆየቱም የድርጅቱ መግለጫ ያመለክታል፡፡

ይህ ሁኔታ መቀየር ያለበትና ኢትዮጵያ የቡና መገኛ አገር በመሆኗ ብቻ የቡና ምርቷም ከሁሉም የዓለም ቡና ምርቶች በጣዕምም ሆነ በዓይነቱ የተለየ በመሆኑ የተሻለ ገበያ ማግኘት እንድትችል ፍቅር ለሕዝቦች በጎ አድራጎት ድርጅት ከአንድ ኢንተርናሽናል የቡና ቀማሽና የንግድ ትርዒ አዘጋጅ ከሆኑ ግለሰብ ጋር በመተባበር እ.ኤ.አ. በ2019 በፈረንሣይ አገር ‹‹የኢትዮጵያ ቡና›› የንግድ ትርዒት ለማዘጋጀት መቻሉ አንዱ ነው፡፡ በመጪው የፈረንጆች አዲስ ዓመት ደግሞ በኢትዮጵያ በሚካሄደው የቡናና ቱሪዝም ኹነት ከ40 አገሮች በላይ የተውጣጡ የቡና ገዥዎች ይሳተፉበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡

ፍቅር ለሕዝቦች በጎ አድራጎት ድርጅት ጨምሮ የገለጸው ፕሮግራሙን ከመንግሥታዊ አካላት ጋር በመተባበር የሚያዘጋጅ ስለመሆኑ ሲሆን፣ በኹነቱ ላይ የቡና ግብይት ሰንሰለት ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫና የልምድ ልውውጥ መድረክ የሚካሄድበት ከመሆኑም በላይ በቡና አብቃይ ቦታዎች መካከል የቡና ቅምሻ ውድድርና የቡና ቱሪዝምን ከማካሄድ ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች የመጎብኘት፣ የማስተዋወቅና የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች እንደሚካሄድም ይጠቅሳል፡፡

ከጋዜጣዊ መግለጫው መረዳት እንደሚቻለው በስድስት ቀኑ የቡና እና ቱሪዝም የዝግጅት መርሐ ግብር ውስጥ ተጠቃሽ የዘርፉ ተዋንያን የሚወያዩበት የፓናል ውይይት አንዱ ነው፡፡ በዚህ በፓናል ውይይቱ ከቡና አምራቹ ጀምሮ፣ ጠቅላላ በግብይት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ተዋንያን በሙሉ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማትና ከፋይናንስ ዘርፉ የበላይ ኃላፊዎች ጋር ምክክር ይደረጋል፡፡ በዚህም የፋይናንሱ ዘርፍ ለቡና አምራቹ፣ አቀናባሪውና ላኪው የተሻለ የብድርና የገንዘብ አቅርቦት እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታ የሚፈጠርበት እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡

ፍቅር ለሕዝቦች በጎ አድራጎት ድርጅት ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሲሆን፣ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎቹ የኢትዮጵያን የአገራችን የግብርና፣ ማዕድንና የቱሪዝም ሀብት በአግባቡ መጠቀምና ማልማት ይቻል ዘንድ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት አጋሮች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ አንዱ ነው፡፡ በዚህም መነሻነት ለዓለም አቀፉ የንግድ ማኅበረሰብ፣ ኢንቨስተሮችና ቴክኖሎጂስቶች ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉና ከአገራችን ከኢትዮጵያ ባለሀብቶች ጋር በሽርክና እንዲሠሩ የሚያስችሉ የቅስቀሳ ሥራዎችን የሚሠራ መሆኑንም በትናንትናው መግለጫ ላይ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች