Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኅብረት ኢንሹራንስና ናይል ኢንሹራንስ በሩብ በጀት ዓመት ትርፋማ መሆናቸውን አስታወቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኅብረት ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 597.4 ሚሊዮን ብር ዓረቦን ማሰባሰብ መቻሉንና ዓመታዊ የትርፍ መጠኑንም በ22 በመቶ እንዳሳደገ ገለጸ፡፡

ኅብረት ኢንሹራንስ ይህንን ያሳወቀው የ2012 የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ አፈጻጸሙን በተመለከተ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ ነው፡፡ ትናንት ኅዳር 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔው ላይ በቀረበው በዚሁ ዓመታዊ ሪፖርት ካሰባሰበው 597.4 ሚሊዮን ብር ውስጥ ሕይወት ነክ ካልሆነው የመድን ዘርፍ ያሰባሰበው 551.6 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ከተገኘው የዓረቦን ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ12 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ ኩባንያው ከሕይወት ነክ ከሆነው የመድን ዘርፍ ያገኘው የዓረቦን ገቢ ደግሞ 45.8 ሚሊዮን ብር መሆኑን ገልጿል፡፡ ከዚህ ዘርፍ ያገኘው የዓረቦን ገቢ በቀዳሚው ዓመት ከተገኘው የዓረቦን ገቢ ጋር ሲነፃፀር 18 በመቶ ብልጫ ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ ከሁለቱም ዓብይ የመድን ዘርፎች የሰበሰበው አጠቃላይ የዓረቦን ገቢ ሲደመር 597.4 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ከ2011 የየከደከደከደከደከደከደየሒሳብ ዓመት ከተሰበሰበው 535.5 ሚሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ12 በመቶ ዕድገት የታየበት መሆኑን የኩባንያው መረጃ ያመለክታል፡፡  

የኩባንያው የ2012 የካሳ ክፍያ በተመለከተ የቀረበው ሪፖርት ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ አጠቃላይ የከፈለው የካሳ ክፍያ ምጣኔ፣ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ቅናሽ በማሳየት 55 በመቶ ሆኖ መመዝገቡን የሚጠቀስ ነው፡፡ ይህም በቀዳሚው ዓመት ከተከፈለው 60 በመቶ የካሳ ምጣኔ ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ውጤት የታየበት እንደነበር ያመለከተው የኩባንያው ሪፖርት፣ በ2012 የሒሳብ ዓመት ለካሳ ክፍያ የወጣው ወጪ ከቀዳሚ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የስድስት በመቶ መጠነኛ ጭማሪ ብቻ በማሳየት 240.7 ሚሊዮን ብር ሆኖ ሊመዘገብ መቻሉንም አመልክቷል፡፡  

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሥራ ውጤታማነት ከሚለካባቸው መመዘኛዎች አንዱና ዋኛው ከቀጥታ የመድን ዘርፍ ወይም ከኦፕሬሽን የሚገኝ ትርፍ መሆኑን የሚያመለክተው የኩባንያው መረጃ፣ ከዚህ ዘርፍ 210.1 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ይህም ከ2011 የሒሳብ ዓመት ከተገኘው 173.5 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ21 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡  

በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከግብር በፊት ያስመዘገበው ትርፍ በ22 በመቶ ጨምሮ 147.8 ሚሊዮን ብር መድረስ መቻሉንም ገልጿል፡፡ ኅብረት ኢንሹራንስ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ያገኘው ትርፍ የኩባንያው በአንድ በአክሲዮን 299 ብር ያስገኘ ሲሆን፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት ግን 337.5 ብር ነበር፡፡ ይህም ቅናሽ ያለው መሆኑን ያሳያል፡፡

የኩባንያው ካፒታል ከ250 ሚሊዮን ብር ወደ 500 ሚሊዮን ብር እንዲያድግ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት፣ በ2012 መጨረሻ ላይ የተከፈለ ካፒታሉ 436.3 ሚሊዮን ብር መድረሱንና ጠቅላላ የባለአክሲዮኖች ቁጥርም ወደ 488 ማደጉን አስታውቋል፡፡

ኩባንያው በሪልስቴት ኢንቨስትመንት ዘርፍ በመሰማራት የአራት ሕንፃዎች ባለቤት ለመሆን የቻለ ስለመሆኑ የሚጠቅሰው የኩባንያው መረጃ፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከእነዚህ ኢንቨስትመንቶች ከፍተኛ የሆነ የኪራይ ገቢ አግኝቻለሁ ብሏል፡፡ ከዚህም ሌላ ለኪራይ ክፍያ ያወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ለማዳን ስለመቻሉም አመልክቷል፡፡ በ2012 የሒሳብ ዓመት ኩባንያችን በኅብረት ባንክ አ.ማ. እና በኢትዮጵያ የጠለፋ ዋስትና ኩባንያ አ.ማ. ካሉት ኢንቨስትንቶች የትርፍ ድርሻ ያገኘ ቢሆንም፣ በሐበሻ ሲሚንቶ አ.ማ. ካሉት አክሲዮኖች ያገኘው የትርፍ ድርሻ አለመኖሩንም ገልጿል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪን በመቀላቀል ቀዳሚ ከሆኑት ኩባንያዎች አንዱ የሆነውና 25 ዓመቱን የያዘው ናይል ኢንሹራንስ ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ ጠቅላላ ጉባዔውን አካሂዷል፡፡ ናይል ኢንሹራንስ ኩባንያ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 128.8 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል፡፡ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ያገኘው የትርፍ መጠን ከቀዳሚ ዓመት በ3.4 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው መሆኑን የኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

ከዚሁ አንፃር ኩባንያው በ2012 የሒሳብ ዓመት አንዱ አክሲዮን ያስገኘው የትርፍ ድርሻ ክፍፍል 296 ብር ሆኗል፡፡ ይህ የትርፍ ድርሻ ግን ከቀዳሚው ዓመት ተገኝቶ ከነበረው ያነሰ ነው፡፡ በቀዳሚው ዓመት የአንድ አክሲዮን ያስገኘው የትርፍ ድርሻ 327 ብር ነበር፡፡

የናይል ኢንሹራንስ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው፣ በ2012 የሒሳብ ዓመት ኩባንያው ከጠቅላላ የኢንሹራንስ ዘርፍ 446.6 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ከሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ 48.1 ሚሊዮን ብር ዓረቦን ሰብስቧል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የሰበሰበው የዓረቦን መጠን ካለፈው ዓመት አንፃር ሲታይ በ13.5 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የጉዳት ካሳ ክፍያን በሚያመለክተው መረጃ 195 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ በቀዳሚው ዓመት 188.9 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ከፍተኛ የጉዳት ካሳ የተከፈለው ለሞተር ኢንሹራንስ ሲሆን ከጠቅላላው 58.2 በመቶ ድርሻ ይይዛል፡፡

ናይል ኢንሹራንስ ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ የኩባንያው የሀብት መጠን በ2012 የሒሳብ ዓመት መጠናቀቂያ ላይ 1.55 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም በ2011 የሒሳብ ዓመት ከነበረበት 1.38 ቢሊዮን ብር አንፃር ሲታይ የሀብት መጠኑ 170 ሚሊዮን ብር ወይም የ12.3 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ነው፡፡

በሒሳብ ዓመቱ መዝጊያ ላይ የናይል ኢንሹራንስ የተከፈለ ካፒታል 448 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህ የተከፈለ ካፒታል መጠን በ2011 መጨረሻ ላይ 366.1 ሚሊዮን ብር እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ናይል ኢንሹራንስ በአሁኑ ጊዜ በመላ አገሪቱ 49 ቅርጫፎች አሉት፡፡ ኅብረት ኢንሹራንስ ደግሞ በ51 ቅርንጫፎቹ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች