Monday, December 4, 2023

ከጦርነት ይልቅ ድርድር እንዲቀድም የሚሰሙ ድምፆች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሲወራወሩት የነበረው የቃላት ጦርነት፣ ከቃላት ጦርነት አልፎ ወደ እውነተኛ ጦርነት ከተሻገረ ሳምንት አስቆጠረ፡፡

ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት ወደ ሥልጣን በመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና በሕወሓት አመራሮች መካከል የነበረው ልዩነት፣ በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ፈርሶ ብልፅግና ፓርቲ ከተመሠረተ በኋላ ባሉት ጊዜያትና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ አገር አቀፍ ምርጫው መራዘሙን ተከትሎ፣ የትግራይ ክልል ለብቻው ምርጫ ማከናወኑ ከመጀመርያው በቋፍ የነበረውን የሁለቱን ልዩነት አሁን ወደለየለት ጦርነት ከቶታል፡፡

ማክሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ለረቡዕ አጥቢያ ንጋት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል በነበረው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመድረሱ፣ የመከላከያ ሠራዊት ዕርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡ በዚህም ሳቢያ በርካታ ኢትዮጵያውያን በድንጋጤና በጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ፡፡

የጦርነቱ መጀመርን ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ በመወትወት ላይም ናቸው፡፡ በርካታ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ መንግሥታትና ተቋማትም እንዲሁ ለጉዳዩ ሰላማዊ ዕልባት ተበጅቶለት፣ ደም አፋሳሽ ከሆነ የእርስ በርስ ጦርነት አገሪቱ በቶሎ እንድትወጣ ውትወታ ይሰማል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያ ወደ እርስ በርስ ጦርነት እያመራች ይሆን? የሚል ዘገባ በማዘጋጀትና በማሠራጨት ላይ ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በርካታ የመገናኛ ብዙኃን (በተለይ የውጭ) የእርስ በርስ ጦርነት አይቀሬነትን በተለያዩ ጽሑፎቻቸውና ፕሮግራሞቻቸው ቢያቀርቡም፣ መንግሥት በበኩሉ ይህ ዕርምጃ በሕዝቦች መካከል የሚደረግ ጦርነት ሳይሆን ሕግና ሥነ ሥርዓትን የማስከበር ዕርምጃ ነው በማለት ሥጋቱን ያጣጥለዋል፡፡

ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በትዊተር ገጻቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያ ወደ ትርምስ ትገባለች የሚለው ሥጋት የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በጥልቀት ካለመረዳት የመነጨ ነው፤›› የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ እንዲህ ወዳለ ውጥንቅጥ ልትገባ ትችላለች በሚል በአገሪቱ ውስጥ ስላለው ሁኔታ ትኩረት ለሰጡ አካላት ምሥጋና እንዳላቸውም እንዲሁ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹አሁን እየተከናወነ ያለው ሕግ የማስከበር ሥራ ሰላምና መረጋጋትን በማስፈን ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ ያለመ ነው፤›› በማለት ወቅታዊውን ሁኔታ ከማብራራት ባለፈም፣ ‹‹ኢትዮጵያ ወደ ትርምስ ትገባለች›› የሚለው ጉዳይ ሊያሠጋ እንደማይገባ ገልጸዋል፡፡

ከዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃኑ በተጨማሪ ግን እንደ አውሮፓ ኅብረትና የአፍሪካ ኅብረትን የመሳሰሉ አኅጉራዊ ተቋማትና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስን ጨምሮ፣  በርካቶች ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆምና ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲገባ በማሳሰብና በመወትወት ላይ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም አማራጭን እንዲከተል የጠየቁት ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረውን ግጭት በአጽንኦት እየተከታተሉት እንደሆነ በመግለጽ፣ ‹‹በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ከጦርነት ይልቅ የሰላምን አቅጣጫ ይምረጡ›› የሚል ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረትም ሆነ የአውሮፓ ኅብረት እንዲሁ ጦርነቱ እየሰፋ ከሄደ የሚያመሳቅለው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን ወደ ቀጣናው አገሮችም ሊዛመት የሚችል ከመሆኑ አንፃር ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆምና ለሰላም ዕድል ይሰጠው የሚል ምክር በመሰንዘር ላይ ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ሰኞ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ እንደገለጹት፣ ሁለቱም ወገኖች ተኩስ እንዲያቆሙና የተፈጠረው ጦርነት በሰላማዊ መንገድ መቋጫ እንዲበጅለት ጠይቀዋል፡፡ እንዲህ ላለ የድርድርና የሰላም እንቅስቃሴ የአፍሪካ ኅብረት ሚናውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ቦሬል እንዲሁ ሰኞ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፣ ሰላምና የፖለቲካ ውይይት ዳግም እንዲጀመር ከተለያዩ አካላት ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም መሠረት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር መነጋገራቸውን፣ የአውሮፓ ኅብረት በወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታ ያለውን ሥጋት መግለጻቸውን፣ እንዲሁም በአገሪቱ አሁን ላይ ያለው ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ የሚያሠጋው ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ቀጣናውን መሆኑን ማሳሰባቸውን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ምክንያት የአውሮፓ ኅብረት ውጥረቱን ለማርገብ፣ እንዲሁም ንግግር እንዲጀመርና በመላ አገሪቱ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን የሚደረግ ጥረትን እንደሚደግፍ አብራርተዋል፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ምክትል ፕሬዚዳንት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በተጨማሪ፣ የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር የሆኑትን የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክንና የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት ጋርም በጉዳዩ ላይ መነጋራቸውን በመግለጽ፣ ኢጋድም ሆነ የአፍሪካ ኅብረት ወቅታዊውን ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ የሚያደርጉትን ጥረት የአውሮፓ ኅብረት ለማገዝ መዘጋጀቱን እንደገለጹላቸው አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም የአውሮፓ ኅብረት ምክትል ፕሬዚዳንት በጉዳዩ ላይ ከሌሎች የአካባቢው አጋሮች ጋር ምክክር ማድረጋቸውን ያስታወቁ ሲሆን፣ ይህም ንግግርና ምክክር የሚቀጥል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከእነዚህ አኅጉራዊ ተቋማት በተጨማሪም በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች የማኅበራዊ የትስስር ገጽን ጨምሮ፣ በአገሪቱ የተከሰተው ጦርነት እንዳሠጋቸው በመግለጽ አፋጣኝ ሰላማዊ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ በመወትወት ላይ ይገኛሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በርካቶች ሁኔታው አሳሳቢና አስጨናቂ እንደሆነባቸው በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ወቅታዊ ሁኔታው እጅግ ካሳሰባቸውና ካስጨነቃቸው ኢትዮጵያውያን መካከል ደግሞ አቶ ክቡር ገና ይገኙበታል፡፡

ጦርነቱን ‹‹በጣም የሚያሳዝን›› በማለት የሚገልጹት አቶ ክቡር፣ ‹‹በእኛ ዕድሜ ጦርነት ያስከተለውን እያወቅን አንድ ኢትዮጵያዊ ሌላ ኢትዮጵያዊ ላይ እጁን ያነሳል ብዬ አላስብም፤›› በማለት የጦርነቱን አስከፊነት ገልጸዋል፡፡

‹‹በአጭር ጊዜ የሚያልቅ ጦርነት የለም›› የሚሉት አቶ ክቡር፣ ለአብነትም በአጭር ጊዜ ይጠናቀቃሉ ተብለው ተጀምረው ነገር ግን መቋጫ አልባ የሆኑ የቅርብ ሆነ የሩቅም ዘመን ጦርነቶችን አንስተዋል፡፡ በየመን የደረሰውን ዕልቂት፣ አሜሪካ በቬትናምና በአፍጋኒስታን ያደረጋቸውን ጦርነቶች ምን ያህል እንደተራዘሙና በየአገሮቹ የሚኖሩ ዜጎችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለመፈናቀል፣ እንዲሁም ለሥቃይና ለመከራ መዳረጉን በማስታወስ፣ ‹‹በአገሪቱ እየተካሄደ ያለው ጦርነት አሁን መቆም አለበት፤›› በማለት ሐሳባቸውን ለሪፖርተር አጋርተዋል፡፡

‹‹ቶሎ የሚያልቅ ጦርነት ስለሌለ ጦርነቱ አሁኑኑ እንዲቆም ሕዝቡ መጠየቅ አለበት፤›› ብለዋል፡፡ ጦርነት ሁሌም የሚቋጨው በድርድር ነው የሚሉት አቶ ክቡር ‹‹ስለዚህ ድርድር እንዴት ይካሄድ የሚለው ጉዳይ ከእጃችን ሳይወጣ በአፋጣኝ ቢጀመር መልካም ነው፤›› የሚል ምክር ለግሰዋል፡፡ እዚህ ላይ ድርድሩ በኢትዮጵያውያን መካከል መካሄዱ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት እንደሚጠቅም የገለጹት አቶ ክቡር፣ ‹‹ድርድር ሳይጀመር ጦርነቱ ጊዜ ከወሰደና ድርድሩ ከእጃችን ከወጣ አደራዳሪዎቹ የውጭ ነው የሚሆኑት፡፡ ይህ ደግሞ የድርድሩን ውጤት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ የተፈጠረውን ነገር ማስታወስ ያስፈልጋል፤›› በማለት ሳይረፍድ አገራዊ ድርድር እንዲጀመር አሳስበዋል፡፡

‹‹ማለቂያ የሌለው ጉድ ውስጥ ነው የገባነው›› የሚሉት አቶ ክቡር፣ ጦርነቱ እንዲቆም ‹‹ሊታሰብ የማይችል ነገር ታስቦም ቢሆን ጦርነቱ መቆም አለበት›› በማለት አሁን ድርድር ማድረግ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ከዚህ ውጪ ግን ምንም ዓይነት አማራጭ የለም በማለት ሳይረፍድ አሁንም ድርድር እንዲጀመር መክረዋል፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያ በበኩላቸው፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት የነበሩ ሁኔታዎች ሁለቱ ወገኖች ወደ ጦርነት እንዲገቡ እንጂ፣ ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችሉ አልነበሩም ብለዋል፡፡

የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ አካላት መካረሩ እንዳያይልና ወደ ጦርነት እንዳያመራ ያደረጉት ጥረት አነስተኛ ነው የሚሉት ባለሙያው፣ ጦርነትን ማስቀረት ይቻል የነበረ ቢሆንም ‹‹ሁላችንም ይህ እንዳይሆን አልተከላከልንም›› ብለዋል፡፡

በሰሜን ዕዝ በሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ባይፈጸምም ጦርነቱን ለማስጀመር ትንሽ ምክንያት በቂ ነበር ሲሉ አክለዋል፡፡

‹‹በሁለቱ መካከል (በፌዴራልና በትግራይ ክልል) ያለው ጦርነት ወታደራዊ የበላይነትን ለመቆጣጠር ነው፤›› የሚሉት ባለሙያው፣ ‹‹ይህ ደግሞ በማንኛውም ሰዓት ከቁጥጥር ውጪ ወጥቶ የምንፀፀትበት እንዳይሆን እሠጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

አሁን የተጀመረው ጦርነት በፍጥነት ሰላማዊ መፍትሔ ካላገኘ ለተራዘመ ጊዜ ሊቀጥል እንደሚቻል፣ ይህ ደግሞ ግጭቱ አሁን ካለበት አካባቢ ወጥቶ ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳይገባ እንደሚያሠጋ፣ በመሆኑም ሁሉም ወገን ለሰላማዊ መፍትሔ ጥሪ ማቅረብ አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡

መንግሥት ግን የአገር መከላከያ ሠራዊትን እንደ ጠላት ከጀርባው የወጋ ኃይል ትጥቁን ፈቶ ለሕግ ሳይቀርብና በትግራይ ክልል ሕጋዊ አስተዳደር ሳይመሠረት ድርድር የሚባል ነገር የለም ብሏል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -