Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየቅዱስ ላሊበላ መካነ ቅርሰ ጥገና ሒደት እምን ላይ ይገኛል?

የቅዱስ ላሊበላ መካነ ቅርሰ ጥገና ሒደት እምን ላይ ይገኛል?

ቀን:

‹‹ወዳጆቼ ሆይ! ተመልከቱ እንጂ ይህ ሰው በእጆቹ የተገለጹለት እነዚህ ግንቦች በየትም በሌሎች አገሮች አልተሠሩም፡፡ ስለእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት አሠራር በምን ቃል ልንነግራችሁ እንችላለን? የቅጽራቸውንም ሥራ እንኳ መናገር አንችልም፡፡ የውስጡንስ ተዉት ታይቶ አይጠገብም፣ አድንቆና አወድሶም ለመጨረስ አይቻልም፡፡ በላሊበላ እጅ የተሠራ ይህ ድንቅ ሥራ በሥጋዊ ሰው የሚቻል አይደለም፡፡ የሰማይን ከዋክብት መቁጠርን የቻለ፣ በላሊበላ እጅ የተሠራውን መናገር ይችላል፡፡ እናም ለማየት የሚፈልግ ካለ ይመልከት፡፡ በላሊበላ እጅ የተሠሩትን የአብያተ ክርስቲያኖቹን ሕንፃዎች ይምጣና በዓይኖቹ ይመልከት፡፡››

ይህ አንቀጽ የ‹‹ገድለ ላሊበላ›› ጸሐፊ ከስምንት ምዕተ ዓመት በፊት ስለታነፁት የላስታ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን በአድናቆት የከተበው ነው፡፡ በ1200ዎቹ መጀመርያ አካባቢ የተገነቡት እነዚህ አስደናቂ ሕንፃዎች ንጉሡ አፄ ላሊበላ ዳግማዊት ኢየሩሳሌምን በላስታ ለማስገንባት አልመው እንደሆነ በገድላቸው መጻፉን የሕይወት ከተማ ላሊበላዊ ድርሳን  ያሳያል፡፡

‹‹አዲሲቱ ኢየሩሳሌም›› የሚል ተቀጽላ ያገኙት ውቅር አብያተ ክርስቲያኑ በየዓረፍተ ዘመኑ ካገር ቤት እስከ ባሕር ማዶ የብዙዎች ጎብኚዎች፣ ተሳላሚ ምዕመናን ቀልብ መያዝ ችለዋል፡፡ በዚህም ሳይገደብ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆነዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከቅርብ አሠርታት ወዲህ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በዕድሜ ብዛት በደረሰባቸው ተፈጥሯዊ ጫና ምክንያት፣ የተወሰኑት ላይ የተደቀነባቸውን አደጋ ለመታደግ ከተወሰደው ዕርምጃ አንዱ በከባድ የብረት ምሰሶ ከለላ እንዲሆናቸው ጥላ መሠራቱ ነው፡፡ ለአምስት ዓመት ታስበው የተጋረዱት ጥላዎች አሥራ ሦስተኛ ዓመትን በማስቆጠራቸውና በኅብረተሰቡ ዘንድ ሥጋት በመፍጠራቸው ‹‹ይነሱ›› የሚል ድምፅ መስማት ከጀመረ ከራርሟል፡፡

በአሳሳቢ ሁኔታ ፈተና ውስጥ ከገቡት መካከል ቤተ መድኃኔ ዓለም፣ ቤተ አማኑኤል፣ ቤተ መስቀል ይጠቀሳሉ፡፡ በየቤተ መቅደሶቹ የቆሙት የብረት እግሮች በአካባቢው በየወቅቱ እየተለዋወጠ የሚነፍሰው የነፋስ መጠን በእጥፍ እየጨመረ መምጣቱ ብረቱን አነቃንቆ እንዳይጥለውና ጉዳት እንዳይደርስ በየጊዜው ሥጋታቸውን የሚገልጹ አልታጡም፡፡ በተለይ ከሦስት ዓመት በፊት ጀምሮ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁም ተጠሪው ተቋም የቅርስ ጥናት ጥበቃ ባለሥልጣን ለችግሩ ዓለም አቀፍ መፍትሔ በማፈላለግ ረገድ አልቦዘኑም፡፡

የአርኪዮሎጂ ጥናትና በኢትዮጵያ እንዲቋቋም በ1950ዎቹ አጋር የነበረችው ፈረንሳይ የቅዱስ ላሊበላ መካነ ቅርስን ለመታደግ የባህል ሚኒስትሯን ብቻ በመላክ አልተወሰነችም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ የፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግ በጠየቁት መሠረት አዎንታዊ ምላሽ ከማግኘት ባለፈ በላሊበላ ከተማ የተገኙት ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ አገራቸው ሙሉ ድጋፍ እንደምትሰጥ ቃል ገብተዋል፡፡ የአገር ውስጥና የፈረንሳይ ባለሙያዎችን ያካተተ የቴክኒክ ቡድን ተቋቁሞ ሥራውን ሲሠራ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ ጥገናውን ለማካሄድ በባለሙያዎች ሲካሄድ የነበረው ጥናት በኮቪድ-19 ምክንያት ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ፈረንሳይ ትብብር የቅርስ አድን ፕሮጀክት አስተባባሪ መንግሥቱ ጎበዜ (ዶ/ር) የቆመው ሥራ ዳግም መጀመሩንና የጥገና ሥራው የጥናትና ምርምር እንዲሁም የትግበራ በሚል ተከፋፍሎ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወደ ጥገናው ከመገባቱ በመካነ ቅርሱ ላይ ቀደም ሲል የተሠሩ ሥራዎች ለምን ውጤታማ ሳይሆኑ እንደቀሩ የሚፈትሽ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን አውስተዋል፡፡

ጥናትና ምርምሩን በአንድ ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዶ ዓምና በጥቅምት ወር ላይ ቢጀመርም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የፈረንሳይ ባለሙያዎች ባለመምጣታቸው ቀዳሚ ሥራው ባለፈው መጋቢት መቋረጡ ይታወሳል፡፡

ዳግም የተጀመረውና እየተካሄደ ያለው ጥናት በታኅሣሥ መጨረሻ በማጠናቀቅ ለትንተና ለማቅረብ መታቀዱንና ይሁንታን ካገኘ በኋላ በመጪው ሚያዝያ ወር ሥራው እንደሚጀመር አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡

በታሪክ እንደሚወሳው የከተማዋ የመጀመርያ መጠሪያ ሮሃ ሲሆን በ12ኛው ምዕተ ዓመት የነገሠው ንጉሥ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናቱን ያነፀው እርሱ በመሆኑ ከተማዋ ስሙን አግኝታለች፡፡

አብያተ መቅደሶቹ በሦስት የተለያዩ ሥፍራዎች ሲገኙ፣ ስድስቱ በሰሜን አቅጣጫ፣ አራቱ በሊባ (ደቡባዊ ምሥራቅ) አቅጣጫ ሆነው የሚገናኙበት መስመር ያላቸው ሲሆን፣  11ኛው በኖኅ መርከብ አምሳል የተሠራው ቤተ ጊዮርጊስ ግን ተነጥሎ ነው ያለው፡፡

በሰሜናዊ ክበብ የሚገኙ (1) ቤተ መድኃኔ ዓለም (2) ቤተ ማርያም (3) ቤተ መስቀል (4) ቤተ ደናግል (5) ቤተ ሚካኤል (6) ቤተ ጎልጎታ ሲሆኑ፣ በሊባ በኩል (7) ቤተ አማኑኤል (8) ቤተ አባ ሊባኖስ (9) ቤተ መርቆርዮስ (10) ቤተ ገብርኤልና ቤተ ሩፋኤል ይገኛሉ፡፡ በምዕራብ አቅጣጫ ለብቻው ያለው ከላይ ወደታች ተፈልፍሎ የታነፀው 11ኛው ቤተ ጊዮርጊስ ይገኛል፡፡

 የእነዚህ አብያተ ክርስቲያናትን ሥራ አስደናቂነት ለመግለጽ ቃል እንዳነሰው የገለጸው የገድለ ላሊበላ ደራሲ፣ እነዚህ ላሊበላ ባንድ ቋጥኝ ያሠራቸው፣ ሰሎሞን በጢሮስ ንጉሥ በኪራም እየተረዳ በኢየሩሳሌም ካሠራው ቤተ መቅደስ እንደሚበልጥም አመሥጥሯል፡፡ የላሊበላም ጥበብ ከሰሎሞን መብለጡን ጭምርም በመግለጽ፣ ሰው ሁሉ እየመጣ ባይኑ እያየ ሊያደንቃቸው የሚገባ መሆኑንም ‹‹በላሊበላ እጅ የተሠሩትን ዕፁብ ድንቅ ግብረ ሕንፃዎችን ለማየት የሚፈቅድ ይምጣና በዓይኖቹ ይይ (ይምጻእ ወይርአይ በአዕይንቲሁ) ነበር፤›› ያለው፡፡ ይህ አገላለጽ ዘላቂና ለትውልድ ትውልድ እንዲተርፍ የመካነ ቅርሱ ጥገናና ክብካቤ ለስምረትና ስኬት መብቃት አለበት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...