Friday, December 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በኢትዮጵያዊነት ላይ ጥቃት ሊሰነዘር አይገባም!

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ታይተው የማይታወቁ ጭካኔዎች እየተፈጸሙ ነው፡፡ የአገርን ህልውና የሚፈታተኑ ኃይሎች ንፁኃንን በጅምላ ሰለባ ያደረጉ ጥቃቶች እየከፈቱ አገር ሲያተራምሱ ከርመዋል፡፡ አሁን ደግሞ በሕግም ሆነ በታሪክ የሚያስጠይቁ የወንጀል ድርጊቶች ከፍተዋል፡፡ ቀደም ሲል በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በደቡብ ክልሎች በተፈጸሙ ጥቃቶች ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ቀውስ መድረሱ አይዘነጋም፡፡ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል በጉጂና በጌዴኦ ዞኖች መከከል ባጋጠመውደረሰው አደጋ በጣም ከባድ ነው፡፡ በደቡብ ክልል በጉራፈርዳና በተለያዩ ሥፍራዎች የተፈጸሙ ጥቃቶች፣ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በኦነግ ሸኔ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ፈጽሞ አይረሳም፡፡ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ከማዕከላዊ መንግሥት ርቆ ትግራይ ክልል የከተመው ሕወሓት እየፈጸመ ያለው አደገኛ ድርጊት፣ አገሪቱን ሳትወድ በግድ ወደ ጦርነት እንድትገባ አድርጓታል፡፡ በተደጋጋሚ ፊቱን ወደ ልማት እንዳዞረ ቢናገርም፣ ዋነኛ ተግባሩ ሠራዊት እያደራጀ ለጦርነት ሲዘጋጅ ቆይቷል፡፡ ከፌዴራል ሥርዓቱ አፈንግጦ ምርጫ ከማካሄድ አልፎ ጦርነት በመቀስቀስ አገሪቱን እዚህ ደረጃ ላይ ማድረሱ፣ ታሪክ ይቅር የማይለው አደገኛ ተግባር ነው፡፡ በተለይ በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመው ጥቃት በኢትዮጵያዊነት ላይ የተቃጣ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

መሰንበቻውን በሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ በትግራይ ልዩ ኃይል በተሰነዘረ ጥቃት በርካታ የሠራዊቱ አባላት መሰዋታቸው ተሰምቷል፡፡ ይህ መርዶ በግልጽ በመንግሥት ከተነገረ በኋላ ኢትዮጵያዊያንን ከዳር እስከ ዳር አስቆጥቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሰሜን ምዕራብ በማይካድራ ከተማ የአገር መከላከያ ሠራዊት ባደረሰበት ጥቃት ሲሸሽ በነበረው ኃይል፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን መጨፍጨፋቸው ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል፡፡ ይህ ጥቃት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መግለጫ በርካታ ሰዎች መጨፍጨፋቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹…ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ሽራሮን ሲቆጣጠር፣ እጅና እግራቸውን የፊጥኝ ታስረው የተረሸኑ የመከላከያ አባላትን አግኝቷል፡፡ ጭካኔው ልብ የሚሰብር ነው…›› ሲሉ፣ የተፈጸመው ድርጊት ምን ያህል አደገኛ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡  በየትም አገር ቢሆን የአገር ዓርማ የሆነ ሠራዊት እንዲህ ዓይነት ጥቃት አይፈጸምበትም፡፡ እንዲህ ዓይነት ድርጊት የሚፈጽሙ ኃይሎች በአሸባሪነት ወይም በአገር ክህደት ክስ ይመሠረትባቸዋል፡፡ ንፁኃንን በጭካኔ የሚያሰቃዩና የሚገድሉ ደግሞ በጦር ወንጀለኝነት ይከሰሳሉ፡፡ ሰሞኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕወሓት አባላት የሆኑ ተወካዮችን ያለ መከሰስ መብት ያነሳው፣ ሕወሓትም ሆነ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የትግራይ ልዩ ኃይል ፈጽሞታል ለተባለው ድርጊት ተጠያቂ ለማድረግ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ መንግሥት ዘመቻውን አጠናቆ የጭካኔ ተግባር ፈጻሚዎችንም ሆነ አስፈጻሚዎችን ለሕግ እንደሚያቀርብ ተስፋ ይደረጋል፡፡ በኢትዮጵያዊነት ላይ የተቃጣ ጥቃት ነውና፡፡

የንፁኃን ደም በከንቱ ከፈሰሰ በኋላ በሐዘን ከንፈር ከመምጠጥ ይልቅ፣ በንፁኃን ደም እጃቸውን የሚታጠቡትን በሕግ የመጠየቅ ዕርምጃ ላይ ማተኮር ይመረጣል፡፡ ይህ ዕርምጃ ተጠያቂነት እንዳለ ማረጋገጫ ይሆናል፡፡ ተጠያቂነት በመጥፋቱ ምክንያት ብቻ ከክልል ጀምሮ እስከ ፌዴራል ድረስ በየሥልጣን እርከኑ የተንጠላጠሉ ሕገወጦች አገር ሲያተራምሱ ዝም ማለት አይገባም፡፡ በሕግ የበላይነት የሚያምኑ  ንፁኃን ዜጎችን ሕገወጦች በጠራራ ፀሐይ ሲገድሉና ሲያፈናቅሉ በቸልታ መመልከት፣ አገርን የማትወጣው ቀውስ ውስጥ መክተት ነው፡፡ ነጋ ጠባ የዕልቂትና የመፈናቀል መርዶ እየሰሙ መቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን መተማመን ያስፈልጋል፡፡ አስተዋዮቹና ኩሩዎቹ ኢትዮጵያውያን በመከባበርና በመተሳሰብ ከትውልድ ወደ ትውልድ ያሸጋገሯትን አገር፣ የጥፋት እጆች ሰለባ ማድረግ አይገባም፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ልጆቿ እኩል እናት መሆኗ የሚረጋገጥበት በሕግ የበላይነት የሚመራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እየተቻለ፣ ሕገወጦች እሳት እየጫሩ እንዲያፈርሷት መፍቀድ አይገባም፡፡ ኢትዮጵያዊነት መጠቃት የለበትም፡፡

ኢትዮጵያ የወላድ መካን አይደለችም፡፡ በክፉ ጊዜ የሚደርሱላት የጀግኖች እናት ናት፡፡  እነዚህ ልጆቿ ከአራቱም ማዕዘናት በመሰባሰብ ብሔር፣ እምነት፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ የፖለቲካ አቋምና የመሳሰሉት ልዩነቶች ሳይገድባቸው ሲጠብቋት ኖረዋል፡፡ እናት አገራቸውን ከምንም ነገር የሚያስቀድሟት ልጆቿ፣ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች መመኪያ መሆን መቻላቸውን፣ ከተለያዩ የታሪክ ድርሳናት መረዳት ይቻላል፡፡ የአፍሪካውያን የጋራ መሰባሰቢያ መሆን የቻለችው ኢትዮጵያ፣ ሕገወጦች በሚቀሰቅሱዋቸው ጭካኔ የተሞሉባቸው ግጭቶች  ስትተራመስ ማየት ያማል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድን በበላይነት መምራት ሲገባት፣ የሥልጣን ጥመኞች በሚቀሰቅሷቸው ግጭቶች መተራመስ የለባትም፡፡ በአፍሪካ ቀንድ 110 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ታላቅ አገር አካባቢውን አስተባብራ የሰላም ቀጣና የማድረግ ዕምቅ አቅም እያላት፣ ትርምስ በመፍጠር ሊያዳክሙዋት የሚሹ ኃይሎችን በሕግ ማስታገስ ይገባል፡፡ አፋር በኤርትራ፣ በኢትዮጵያና በጂቡቲ አለ፡፡ ሶማሌ በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያና በኬንያ አለ፡፡ ኦሮሞ በኢትዮጵያና በኬንያ አለ፡፡ ትግሬ በኢትዮጵያና በኤርትራ አለ፡፡ የእነዚህ ሕዝቦች ማዕከልና ታላቅ መሰባሰቢያ ደግሞ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሲጠቃ ይህ ፀጋ ለችግር ይጋለጣል፡፡

ኢትዮጵያ በሴራ፣ በጥላቻ፣ በቂምና በቀል ትጎዳለች እንጂ ማደግ አትችልም፡፡ የዘመናት ታላቅና ታሪካዊት አገርን ማዳከምና ለጠላት ጥጋት ማጋለጥ ለማንም አይበጅም፡፡ ኢትዮጵያ ከተተበተበችበት ድህነትና ኋላቀርነት ብቻ ሳይሆን፣ እኔ ብቻ ነኝ የማውቅልህ ከሚባለው ጎታችና አጥፊ ጀብደኝነት መላቀቅ ይኖርባታል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ ኋላቀርነት መላቀቅ የሚቻለው ደግሞከምንም ነገር በላይ የሕግ የበላይነትን በማስከበር ነው፡፡ ሕግ ሲከበር አገር በሥርዓት ይተዳደራል፡፡ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው በተግባር ሲረጋገጥ፣ ሕገወጥነትና ገደብ አልባ ሥልጣን ተጠያቂነት ይኖርባቸዋል፡፡ አሁን ዋናው ጉዳይ መሆን ያለበት ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓት እንዲፈጠር ተግቶ መሥራት ነው፡፡ ግልጽነት ሲኖር መንግሥትም ሆነ በየደረጃው ያሉ ባለሥልጣናት ምን እየሠሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ተጠያቂነት  ሲኖር እንዳሻቸው የሚፈነጩ አይኖሩም፡፡ የአንድም ኢትዮጵያዊ ሕይወት ለአደጋ አይጋለጥም፡፡ ኢትዮጵያዊነትም አይጠቃም፡፡

የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በእኩልነት የሚኖርበት ሥርዓት ይፈልጋል፡፡ ማንም እየተነሳ የማያንገላታው፣ የማያፈናቅለው፣ የማይገድለውና ንብረቱን የማይዘርፈው በሕግ የበላይነት ሥር የሚተዳደር ሥርዓት ሲሰፍን ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ዕውን ይሆን ዘንድ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ከተመልካችነት ወደ ተሳታፊነት መሸጋገር አለባቸው፡፡ የገዛ አገራቸውን ጉዳይ በሠለጠነና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መነጋገር፣ መከራከርና መደራደር አለባቸው፡፡ መነጋገርና መደማመጥ የሰፈነባት ዴሞክራሲያዊት አገር የምትገነባው ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሲሆን ነው፡፡ ጀብደኝነትና ትዕቢት አገርን ያተራምሳሉ፣ ሕዝብን ለሰብዓዊ ቀውስ ይዳርጋሉ፡፡ ሕገወጦች ውድመትና ትርምስ ስለሚፈልጉ የተሳሳተ መረጃ እየለቀቁ ሕዝቡን እርስ በርስ ያጣላሉ፡፡ ለሥልጣናቸው ሲሉ ብቻ ማንኛውንም ዓይነት ወንጀል ይፈጽማሉ፡፡ ጨካኞች ስለሆኑም ለሰብዓዊነት ደንታ የላቸውም፡፡ ለአገር ክብርና ህልውና ግድ ስለሌላቸው ማንኛውም ዓይነት ግጭት በመቀስቀስ ሕዝቡን ለመከራ ይዳርጋሉ፡፡ ለዚህም ነው በኢትዮጵያዊነት ላይ ጥቃት ሊሰዘነር አይገባም መባል ያለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...