Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአዲስ አበባ በርካታ ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎች የተገኘባቸው 242 ተጠርጣሪዎች መታሰራቸውን ፖሊስ አስታወቀ

በአዲስ አበባ በርካታ ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎች የተገኘባቸው 242 ተጠርጣሪዎች መታሰራቸውን ፖሊስ አስታወቀ

ቀን:

  • ከሱር ኮንስትራክሽን 23 የረዥም ርቀት የመገናኛ ሬዲዮኖች መገኘታቸው ተጠቁሟል
  • ሰባት ፓስፖርትና የውጭ አገር የሥራ ፈቃድ ያለው ግለሰብም ተይዟል

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሰሞኑን በከተማው ውስጥ በግለሰቦችና በተቋማት ላይ ባደረገው ፍተሻ፣ የተለያዩ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ይዘው የተገኙ 242 ተጠርጣሪዎች መታሰራቸውን አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው እንደተናገሩት በፖሊስ አባላት፣ በፀጥታ አካላትና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ እስከ ዓርብ ኅዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በከተማው በተለያዩ አካባቢዎች በተደረገ ፍተሻ፣ በአጠቃላይ 744 የተለያዩ መሣሪያዎች የጦር መሣሪያዎች፣ 4,628 ጥይቶች ተገኝተዋል፡፡ ከዚህም ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 242 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለው 108 የምርመራ መዛግብቶች በመክፈት ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽነሩ እንዳብራሩት፣ 18 ቦምቦች (በብርበራና ተጥለው የተገኙ)፣ አንድ ፀረ ተሽከርካሪ፣ አንድ ቻይና ሠራሽ ቦምብ፣ ሁለት ፈንጂዎችና 97 የእጅ ሬዲዮኖች ተገኝተዋል፡፡ ከሱር ኮንስትራክሽን ኩባንያ 23 የረዥም ርቀት የመገናኛ ሬዲዮኖች መገኘታቸውንም አክለዋል፡፡

ቀደም ሲል በፈቃድ ከተሰጡ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎች፣ ሽጉጦችና ኤስኬኤስ መሣሪያዎች በተጨማሪ፣ 130 የጦር መሣሪያዎች ከግለሰቦችና ከተለያዩ ተቋማት መገኘታቸውንም ኮሚሽነር ጌቱ ተናግረዋል፡፡ በግለሰቦችና በተቋማት ውስጥ በተደረገ ፍተሻ 2,686 የክላሽንኮቭ ጥይቶች፣ 1,940 የሽጉጥ ጥይቶች፣ አንድ ጂፒኤስ፣ አራት ወታደራዊ የጦር ሜዳ መነፅሮችና አንድ ላውንቸር መገኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ለሕወሓት ተልዕኮ ማስፈጸሚያ የሚሆኑ ስድስት የውጭ አገር ስልክ መጥለፊያ መሣሪያዎች፣ 31 ባለ አንቴና ቻርጀሮች፣ 157 ሲም ካርዶች፣ ኬብሎች፣ ዋየርለስ ስልኮች፣ 74 የተለያዩ የፀጥታ የደንብ አልባሳትና 350 ሲም ካርዶች (ከአንድ ግለሰብ ላይ)፣ በአንዳንድ ግለሰቦች በርካታ የባንክ ደብተሮች፣ ሰባት የተለያዩ አገሮች ፓስፖርቶችና የውጭ አገር የሥራ ፈቃድ ያለው አንድ ሰው፣ 600 ተንቀሳቃሽ ስልኮችና ሦስት ድምፅ አልባ መሣሪያዎች መገኘታቸውን ኮሚሽነር ጌቱ ተናግረዋል፡፡

የጦር መሣሪያዎቹ በግለሰቦችና በተቋማት ውስጥ ተከማችተው የነበሩ፣ ሕገወጡን የሕወሓት ቡድን በማገዝ የከተማው ሰላም እንዲደፈርስ፣ ነዋሪው እንዳይረጋጋና ሥጋት ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ ታቅደው የተዘጋጁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በቁጥጥር ሥር በዋሉት ተጠርጣሪዎች ላይ 620 የሰው፣ የሰነድና የቴክኒክ ማስረጃዎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች፣ አንዳንዶች ‹‹ዘርንና ብሔርን መሠረት ያደረገ ነው›› እንደሚሉት ሳይሆን፣ በትክክለኛው በወንጀሉ የተሳተፉትንና ማስረጃ የተገኘባቸውን በመለየትና በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተያዙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ውስጥ የኦነግ ሸኔ አባላት እንዳሉበትና በወንጀሉ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ የተለያዩ ብሔር ያላቸው ተጠርጣሪዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዋናው ዓላማችን የብሔርን ተልዕኮ ይዘው ወይም ወስደው የሚንቀሳቀሱና ሽብር ለመፍጠር እየተጉ ያሉትን ለሕግ ማቅረብ እንጂ ሌላ ተልዕኮ የለንም፤›› በማለት ኮሚሽነር ጌቱ በሰውና በንብረት ላይ አደጋ ለማድረስ የተዘጋጁ ሕገወጦችን በመከታተል ተልዕኳቸውን ማክሸፍ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ሰሞኑን ሕዝቡ ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመው፣ በፌስታልና በተለያዩ መያዣዎች እየተደረጉ የሚጣሉ ፈንጂዎችና ቦምቦች እየተገኙ በመሆናቸው፣ በቆሻሻ ገንዳና የጋራ መፀዳጃ ቤቶች ላይ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ሕፃናት መጫወቻ መስሏቸው ጉዳት እንዳደርስባቸው መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግና አጠራጣሪ ነገር ሲገኝ በ991 ለፖሊስ ደውሎ ማሳወቅ የሁሉም ነዋሪ ኃላፊነት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሕወሓት ሕገወጥ ቡድን ጭካኔውና ሥራው አደገኛ በመሆኑ፣ ኅብረተሰቡ ተቀናጅቶና ተናቦ ራሱንና አካባቢውን መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ሕዝቡን ለማሸበር የሚነገረው ሁሉ ስህተትና ውሸት መሆኑን ተረድቶ፣ ሕዝቡ ተረጋግቶ መኖር እንዳለበትም አክለዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...