Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ጦር ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተጠየቀ

በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ጦር ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተጠየቀ

ቀን:

በሰሜን ዕዝ መከላከያ ሠራዊት ላይ ወታደራዊ ሥርዓት በሚቃረን ሁኔታ የተፈጸመ ጥቃት በመሆኑ ኢሰብዓዊ ድርጊት በመሆኑ፣ የጥቃቱ ፈጻሚዎች ጦር ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ተጠየቀ፡፡ ከማዕከሉ ጋር ያለውን ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥ መደረጉ ደግሞ ከሰዋዊነት ያፈነገጠ ጭካኔ መሆኑንና ይህንን እኩይ ተግባር ፈጽመዋል የተባሉ የሕገወጡ ሕወሓት ቡድን ተጠርጣሪዎች፣ በአገር ክህደት ጦር ፍርድ ቤት ቀርበው ፍርዳቸውን ማግኘት እንዳለባቸው የኢትዮጵያ የቀድሞ ሠራዊት ድጋፍና ልማት ማኅበር አመራሮች ተናገሩ፡፡

አመራሮቹ የአገሪቱን ሁኔታ አስመልክተው ሐሙስ ኅዳር 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፣ ምርኮኛ ሲያዝ የሚጠበቅበት ራሱን የቻለ ሕግ አለው፡፡ አንድ ጠላት ከተገደለም አውሬ እንዳይበላው ይቀበራል፡፡ ከቆሰለ ደግሞ ተገቢውን ሕክምና እያገኘ በእንክብካቤ እንዲጠበቅ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

ተጠርጣሪ ቡድኖቹ ይህንን ሕግ ችላ ብለው ሠራዊቱ በተኛበት ገብተው በአሰቃቂ ሁኔታ ጥቃት መፈጸማቸውንና ሕይወታቸው ያለፈ ወታደሮች አስከሬን የአውሬ ቀለብ እንዲሆን ማድረጋቸውን ሲሰሙ፣ በእጅጉ እንዳበሳጫቸውና በድርጊቱም እንዳዘኑ አመልክተው፣ ይህ ዓይነቱ ጥፋት ከወታደራዊ ዲሲፕሊን አንፃር ሲታይ ከባድ የጦር ወንጀል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ አስነዋሪ ወንጀል ተሳትፈዋል የተባሉ የሕወሓት ሕገወጥ ቡድን ተጠርጣሪዎች ከያሉበት ተይዘው ከፍ ብሎ በተጠቀሰው ፍርድ ቤት እየቀረቡ፣ እንደ ወንጀል አፈጻጸማቸው መጠን ፍርዳቸውን ማግኘት እንዳለባቸውም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

የኢትዮጵያ የቀድሞ ሠራዊት ኢትዮጵያዊያነትን የሚያስቀድምና ሰብዕናውም የተገነባው በኢትዮጵያዊነት ላይ መሆኑን አመራሮቹ አመልክተው፣ሕገወጡ የሕወሓት ቡድን ግን ይህ ዓይነቱን ሰብዕና ማየትም ሆነ መስማት ባለመፈለጉ የተነሳ፣ ለአገሩ አንድነትና ለሰንደቅ ዓላማው ክብር መስዋዕትነት የከፈለውን ይህንን ሠራዊት፣ ‹‹ጨፍጫፊና የደርግ ሠራዊት›› የሚል ቅጽል ስም በመስጠት እንዲበተን ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡  

አሁን ደግሞ በወጣቶች የተገነባውና የቴክኖሎጂ አቅሙ እየዳበረ የመጣውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ለመበተን እንዲያመቸው፣ ‹‹የብልፅግና ሠራዊት›› የሚል ታፔላ በመለጠፍ ለመበተን ያልፈነቀለው ድንጋይ ወይም ያልሞከረው እንቅስቃሴ እንደሌለ ነው አመራሮቹ ያመለከቱት፡፡

ከአመራሮቹም መካከል የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ፣ ‹‹በቀድሞው ሥርዓት ተከስቶ የነበረውን ግጭት በሽምግልና ለመፈጸም የቀድሞው መንግሥት ከ15 ጊዜ ያላነሰ ሙከራ አድርጓል፡፡ ሕወሓት ግን 14 ሙከራዎችን እያከሸፈ ሲመልስ፣ ለመጨረሻ ጊዜ ለሽምግልና የተላኩትን የውስጥ ሱሪያቸውን አስወልቆ ገርፎ አባሯቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ሕገወጡ የሕወሓት ቡድን ሽምግልና ምን እንደሆነ እንደማያውቅና ክብርም እንደማይሰጠው ፕሬዚዳንቱ አመልክተው፣ አሁንም ‹‹እንሸማገል›› እያለ የሚያቀርበው አቤቱታ ተንኮል ለመሥራት ያሰበበት ዕቅድ መሆኑ ታውቆ ተቀባይነት እንዳያገኝ ጠይቀዋል፡፡

በመከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈረጸመውም ድርጊት ከክህደት በተለየ የወራሪነት መንፈስ እንዳለው፣ የሕወሓት ሕገወጥ ቡድን መጥፎ ተግባር ዛሬ ለኢትጵያውያን ገሃድ ይውጣ እንጂ ድርጊቱን ከበፊቱም እንደሚያውቁት፣ ዓላማውም ኢትዮጵያዊነትን መናድ፣ ሥልጣን፣ ክህደትና ሌብነትን ወደ አንድ አቅጣጫ ማምጣት መሆኑን ተናግረዋል፡፡፡

ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ፣ ‹‹ጠላት በሸሸ ቁጥር ተሸነፈ፣ ተማረከ ማለት ደግሞ አበቃ ማለት አይደለም፡፡ መልሶ ሊያገረሽበት ይችላል፡፡ በቀድሞው ሥርዓት ይዘናቸውና ተቋም ውስጥ አስገብተን ያስተማርናቸው በልዩ ዘዴ እንደገና ወደ በረሃ ተመልሰው ግንባር ላይ ሲዋጉ በድጋሚ የማረክናቸው ነበሩ፡፡ አሁንም ይህ ዓይነት ድርጊት እንዳይፈጸም ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል›› ብለዋል፡፡

የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ታመነ አባተ በበኩላቸው፣ አገር መሸጥ፣ ክህደትና መሰል የባንዳ ድርጊቶች ሕወሓት አብሮት የተወለደ ነው ብለዋል፡፡ ሕወሓት ከመጀመርያው አነሳሱ አገሪቱን በብሔር ብሔረሰብ ከፋፍሎና ነጣጥሎ የራሱን ልዩ መንግሥት ለማቋቋም እንደነበር አስረድተዋል፡፡

በቀድሞው ሥርዓት መከላከያ ሠራዊት የተቆናጠጠውን ቦታ ሕወሓት እንደተቆናጠጠው አድርጎ የሐሰት ወሬ በመንዛት፣ ኅብረተሰቡ እንዲወናበድ ያደርግ ነበር ሲሉም አስረድተዋል፡፡ አሁንም የሌለውን አውሮፕላን እንዳለው፣ መትቶ ያልጣለውን አውሮፕላን እንደመታ አድርጎ የሚያላዝነው የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ አመለካከት ለማዛባት ሲል ያደረገው መሆኑን ነው ያመለከቱት፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...