Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

አሜሪካ ለሁለተኛ ጊዜ ኢራቅን ወርራ የቀድሞውን አምባገነን ሳዳም ሁሴን ባስወገደችበት ዘመቻ ወቅት፣ ኢራቅ ውስጥ ከነበሩ ባለሥልጣናት አንደኛው መቼም ቢሆን አይረሱኝም፡፡ በዚያን ጊዜ የኢራቅ የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት ሻለቃ መሐመድ ሰዒድ አል ሰሀፍ፣ አገራቸው በአሜሪካ ወታደሮች ከመወረሯ በፊት በዘመናዊ ጦር ጄቶችና በክሩዝ ሚሳይል ስትደበደብ አድራ ጠዋት ይነሱና ይፎክሩ ነበር፡፡ ሚኒስትሩ በአገራቸው ቴሌቪዥን ብቅ ብለው፣ ‹‹አሜሪካኖች ኢራቅን እንይዛለን ብለው ቢሞክሩ የዘለዓለም መቃብራቸው ነው የምትሆነው…›› ማለት የዘወትር ልማዳቸው ነበር፡፡ በየቀኑ የሚሰጡዋቸው መግለጫዎች በውሸት የታጀቡ ስለሆኑ፣ የብዙዎችን አመኔታ በማጣታቸው ይታወቁ ነበር፡፡

አሜሪካኖች በጄቶችና በክሩዝ ሚሳይሎች ድብደባ የኢራቅን የመከላከያ ኃይል አዳክመው፣ በእግረኛ ወታደሮቻቸው የኢራቅን መሬት ሲረግጡ፣ ‹‹አሜሪካኖች ኢራቅ ውስጥ በገዛ ደማቸው ይዋኛሉ…›› እያሉ ሲደነፉም ይታወሳሉ፡፡ አሜሪካኖች የኢራቅን ጦር ደምስሰው ዋና ከተማዋን ባግዳድ እየተቆጣጠሩ በነበሩት ቀንም፣ በቀጥታ ሥርጭት አሜሪካኖችን ሲያስጠነቅቁ ድንገት ሥርጭቱ ተቋርጦ ሻለቃ አል ሰሀፍ ድምፃቸው ጠፋ፡፡

ከበርካታ ሰዓታት በኋላ የኢራቅ ባለሥልጣናት ተሠልፈው ለአሸናፊው የአሜሪካ ጦር እጃቸውን መስጠት መጀመራቸው ተሰማ፡፡ ሳዳም ሁሴን በወቅቱ የገቡበት ባይታወቅም፣ ዋነኛ ሹም የሚባሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ታሪቅ አዚዝ እጃቸውን መስጠታቸው ብዙዎችን አስገረመ፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ሻለቃ አል ሰሀፍ በወታደራዊ ዩኒፎርማቸው ሆነው እንዲያ ጉራቸውን ሲቸረችሩበት የነበረው ፉከራ፣ ታላቁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እጅ ከማሰጠት አለማለፉ ብዙዎችን ማነጋገሩ አይዘነጋም፡፡

ነገር ግን ቆይቶ አንድ ዜና ተሰማ፡፡ የፕሮፓጋንዳው ሹም ሻለቃው እጃቸውን ለድል አድራጊው የአሜሪካ ጦር ሊሰጡ ቢሄዱም፣ ‹አትፈለግም ወደ ቤትህ ሂድ› ተብለው መሸኘታቸው ነበር ዜናው፡፡ በዚያው ሰሞን ከወደ ኢራቅ ቀልዶች ተሰሙ፡፡ ከእነዚህ ቀልዶች መካከል ኮስታራውና ኮምጫጫው ሻለቃ አዲስ ስም ማግኘታቸው ነበር፡፡ የኢራቅ ወጣቶች እጅ ለመስጠት ፈልገው ያልተሳካላቸውን ሚኒስትር ‹ኮሚክ ዓሊ› ብለው አላገጡባቸው፡፡ እስካሁን ድረስ በዚህ ቅፅል ስማቸው ነው ዓለም የሚያውቃቸው፡፡

ይህንን እውነተኛ ታሪክ ያነሳሁት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ለረጅም ጊዜ በትምህርት ቤትም ሆነ በሥራ ዓለም የማውቃቸው የሕወሓቱ ጌታቸው ረዳ ትዝ እያሉኝ ነው፡፡ እኝህ ግለሰብ ደካማ ጎናቸው ነው ከሚባለው አልኮል አፍቃሪነትና ጊዜ ካለፈባቸው የአሮጌ አስተሳሰብ ባለቤቶች ከሆኑት የሕወሓት አዛውንቶች ቢላቀቁ፣ ብሩህ አዕምሮ ያላቸውና ለአገር ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉ እንደሆነ አምን ነበር፡፡ አሁን ግን ያ እምነቴ ተሸርሽሮ ሌላኛው የዘመናችን ‹የኮሚክ ዓሊ› እየመሰሉኝ ነው፡፡

እሳቸው ከነፍሰ በላዎች ጋር ተቀላቅለው እንደ ‹ኮሚክ ዓሊ› የማይሆን ነገር ውስጥ ገብተው ብዙ ሲዘባርቁ ከርመዋል፡፡ ሕወሓት ራሱ በቀሰቀሰው ጦርነት ሕይወታቸው ሊያልፍ፣ ወይም በውርደት አንገታቸውን ደፍተው እጃቸው ውስጥ ካቴና ሲገባ ይታየኛል፡፡ ምክንያቱም ሰውየው ከመጠን በላይ በዕብሪት ተወጥረው ለ21ኛው ክፍለ ዘመን በማይመጥን አስተሳሰብ ሲሳደቡ፣ የጦርነት ነጋሪት ሲጎስሙና ከዚያም አልፈው ተርፈው አገርን ስለማፍረስ በድፍረት ሲያወሩ በተደጋጋሚ ተሰምተዋል፡፡ በቀደም እንኳ ከመሬት በታች ያለ በሚመስል ሥፍራ ሆነው አመድ የተነፋባቸው መስለው ሲደነፉ አስገርመውኛል፡፡

እኔ ዘወትር የእሳቸውንና የቢጤዎቻቸውን ከመጠን ያለፈ የጦረኝነት አባዜ ስሰማ የሚታየኝ ውድቀታቸው ነው፡፡ ለዚህም የራሳቸውን ድክመት በመንቀስ ልንገራችሁ፡፡ ሕወሓት ከአዲስ አበባ ለ27 ዓመታት ከተንሰራፋበት ዙፋኑ በሕዝብ እምቢታ ተወግዶ ወደ መቀሌ ከመሸሹ በፊት፣ ብዙዎች ከያዘው አደገኛ ጉዞ እንዲገታ ለዓመታት አሳስበዋል፡፡ ዕብሪትና ጥጋብ ከድንቁርና ጋር የተለሰኑበት ሕወሓት ጭራሽ ለመጪዎቹ ሃምሳ ዓመታት ሥልጣን ላይ እንደሚቆይ ሲያስተጋባ፣ በእርግጥም የመጨረሻው ደረጃ ላይ መድረሱ ብዙዎችን አስማምቷል፡፡ አባላቱና ደጋፊዎቹ ጥጋባቸውን መቆጣጠር ተስኖዋቸው ምን ሲያደርጉ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ መጨረሻቸው ግን ከሕዝባዊ ማዕበሉ ከመሸሽ ውጪ ሌላ ምርጫ ስላልነበራቸው መቀሌ ገብተው መሸጉ፡፡

ትግራይ ከገቡ በኋላ ቀድሞ ይታወቁበት ነበር በተባለው ግምገማ ቁጭ ብለው ራሳቸውን ይመረምራሉ ተብሎ ቢጠበቅም፣ ምስኪኑን የትግራይ ሕዝብ ማታለል ጀመሩ፡፡ ‹አገር እንገነባለን ብለን ረስተንህ ነበር… አሁን ግን ትግራይን እናለማለን…› እያሉ ውስጡ ተደብቀው ጦር ማደራጀት ቀጠሉ፡፡ በተቀሩት የኢትዮጵያ ክፍሎች በዘረፉት ገንዘብ ወኪሎቻቸውን በማሠማራት ንፁኃንን ማስገደል፣ ማፈናቀልና የአገር ንብረት ማስወደም መደበኛ ሥራቸው ሆነ፡፡

ይህ አልበቃ ብሏዋቸው በሕገወጥ መንገድ የምርጫ ቦርድ በመመሥረት የተለመደውን የጨረባ ምርጫ በማካሄድ፣ ሌላ አዲስ አገር የፈጠሩ ይመስል የጦርነት ወሬ ከአፋቸው አልወጣ አለ፡፡ ዋና አጋፋሪያቸው ደግሞ ከላይ የተጠቀሱት ግለሰብ ናቸው፡፡ እንደ ‹ኮሚክ ዓሊ› የፈጠራ ወሬ እያሠራጩ የመጨረሻ ቀናቸውን እየጠበቁ ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ ድርጅታቸው ሕወሓትና ልዩ ኃይሉ በሰሜን ዕዝ ሠራዊታችን፣ በማይካንድራና በሌሎች ሥፍራዎች የፈጸሙዋቸው የጅምላ ጭፍጨፋዎች መጨረሻቸውን እያቀረቡት ነው፡፡ ሕወሓት በፈጸመው ፋሽስታዊ ድርጊት ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች መዝገብ ተፍቆ፣ በአሸባሪነት ተፈርጆና በጦር ወንጀለኝነት ሕግ ፊት የሚቀርብበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡

ዋናው አለቃቸው ጨንቋቸው ከአፋቸው ወጥቶ የማያውቀውን የድርድር አጀንዳ ሲጀምሩ፣ እሳቸው ደግሞ በተቃራኒ የጦርነት ልፈፋ ውስጥ ነበሩ፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ የሕወሓት አመራሮች እጃቸው ተይዞ ለፍርድ ሳይቀርቡና በትግራይ ሕጋዊ አስተዳደር ሳይመሠረት፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ ድርድር የሚባል ወሬ መሰማት እንደማይፈልግ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካይነት አቋሙን ግልጽ አድርጓል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ናቸው፡፡ የተጀመረውን ዘመቻ በበላይነት እየመሩ ስለሆነ ዘመቻው ግልጽ፣ ውስንና ውጤት የሚገኝበት ሲሉ ድሉ በእጃቸው መሆኑን እየነገሩን ነው፡፡ ያኔ ታዲያ የትግራዩን የፕሮፓጋንዳ ሹም ‹ኮሚክ ጌቾ› እያልን ልንጠራቸው ነው ማለት ነው፡፡ እኔ በበኩሌ የሚታየኝ ይኼ ብቻ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ጀብደኛው ሕወሓት ወደ መቃብሩ ተሸኝቶ አገራችን ታርፋለች፣ ሕዝባችንም በአገሩ በነፃነት ተከብሮ መኖር ይጀምራል፡፡ ወገኖቼ ይህንን አትጠራጠሩ፡፡ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡

(ዘውዱ የሺጥላ፣ ከአምስት ኪሎ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...