Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በተሽከርካሪ ላይ ብቻ የተንጠለጠለው የመድን ዋስትና ኢንዱስትሪ

የአገራችን የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪን ባህሪ ለየት ባለ መንገድ ይገለጻል፡፡ ይህም በአመዛኙ በተሽከርካሪ የመድን ዋስትና ላይ የተንጠለጠለ መሆኑና ሌላው የአገልግሎ ዓይነቱ ውስን ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡

የ2012 ዓ.ም. የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የተመለከቱ መረጃዎች የሚነግሩን ከአገሪቱ አጠቃላይ የኢንሹራንስ ሽፋን፣ ከ72 በመቶ በላይ የሚሆነውን የያዘው ለሞተር ወይም የተሽከርካሪ ኢንሹራንስ የተሰጠ የኢንሹራንስ ሽፋን ነው፡፡ በተመሳሳይ እነዚህ የኢንሹራንስ ኩባንዎች በየዓመቱ ለካሳ ከሚውሉ ወጪ ውስጥ አሁንም በአማካይ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ለዚሁ የሞተር ኢንሹራንስ ነው፡፡ አንዳንድ ኩባንያዎች በተናጠል ካየንም 80 እና 90 በመቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ከሌሎች አገሮች የኢንሹራንስ አገልግሎት አንፃር ሲታይ የተለየ ምሥል ያለው ሆኗል ሊባል የሚችለው፡፡ ጠቅለል ባለ አገላለጽ ዘርፉ በጠባብ መንገድ እየተጓዘ ያለ፣ መሥራት ያለበትን ያህል እየሠራ ነው ብለን ደፍረን የምንገልጸው ኢትዮጵያን በሚያህል አገር፣ ከ110 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ሕዝብ ተይዞ የኢንሹራንስ ተደራሽነቱ እዚህ ግባ የማይባል ተሽከርካሪዎች ውርውር በሚሉባቸው የአገሪቱ ከተሞች ላይ ብቻ የሚንቀሳቀስ እስኪመስል ድረስ ዛሬም ዋነኛ ገበያው ተሽከርካሪ የመሆኑ ነገር እስከመቼ ያስብላል? ኢንዱስትሪው ከኢትዮጵያ ጋር ከተዋወቀ ዕድሜው ከፍተኛ መሆኑን ስንረዳ ደግሞ ነገሩን በቅጡ ልናስብበት እንደሚገባ ይመክራል፡፡

ኢንዱስትሪው ብዙዎችን ተደራሽ የሚያደርጉ አገልግሎቶች የሉትም፡፡ ቴክኖሎጂ ቀመስ ከሆኑ አሠራሮች በብዙ የራቀም ነው፡፡ በተለይ የዓለም የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ቀዳሚ ሥራ የሆነውን የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ባይተዋር ነው፡፡ አሁን በኢንዱስትሪው ውስጥ ካለው የኢንሹራንስ ሽፋን ውስጥ የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ አምስት በመቶ እንኳን ያለመድረሱ፣ የአገራችን የኢንሹራንስ ዘርፍ ብዙ የሚጠበቅበት፣ ገና ያልተነኩ ሥራዎች ያሉበት ነው ማለት ይቻላል፡፡

የብዙዎቹ የኢንሹራንስ ኩባንያዎቻችን ገቢና ወጪ መዝገቦችን ስንመለከትም በትክክል ከኢንራሹንስ ሥራው የተገኘ ትርፍ ምንያህሉ ነው? ካልን መልሱ ቀላል ይሆናል፡፡

ከአንዳንድ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የሚያገኙት ገቢ፣ እንዲሁም የሚሰበስቡትን ዓረቦን በተሻለ ወለድ በባንኮች በማስገኘት የሚያገኙት ጥቅም ባይኖር ኖሮ በኢንሹራንስ ሥራው ብቻ እያገኙ ያለው ገቢ የትም ላያደርሳቸው ይችል ነበር እስከመባል ደርሷል፡፡

በእርግጥ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አንዱ ፀባያቸው በእጃቸው ያለውን ገንዘብ ኢንቨስት በማድረግም ገበያቸውን ማሳደግ መሆኑ እርግጥ ቢሆንም፣ ዋናውን ኢንሹራንስ አገልግሎት በመዘንጋት መሆን እንደሌለበት አቅምና ጥንካሬያቸውም የሚለካው በዋናው ሥራቸው መሆን ይገባዋል፡፡  

ኢንዱስትሪው የሚሰጠው ውስን አገልግሎት በመሆኑ ዘርፉ እንዲያድግ አድርጎታል ሲባል ኩባንያው የበለጠ መሥራት ሲችሉ አለመሥራታቸውን የሚጠቁም ነው፡፡ እዚህ ላይ መታሰብ ያለበት ዘርፉ የተለያዩ የመድን ሽፋኖችን አስፍቶ፣ ተደራሽነቱን ጨምሮ፣ የሚሰበስበው ዓረቦን ባደገ ቁጥር ሌሎች የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ የመሳተፍ ዕድሉ ከጨመረ፣ በአገሪቱ ኢኮኖሚው ውስጥ ያለውም አበርክቶ ከፍ ባለ ነበር፡፡

የምናየው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ የአገሪቷ ኢኮኖሚ በእርሻ ላይ የተመሠረተ ነው እየተባለ ለእርሻና መሰል የመድን ዘርፎች የሚሆን የመድን ሽፋን የሚሰጡ ኩባንያዎች አንድ ሁለት ብለን የምንጨርሳቸው ሲሆኑ እነሱም ቢሆኑ አገልግሎታቸው ውስን ነው፡፡

በተለይ የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ዓለም የተራቀቀበት የአገልግሎት ዓይነት ቢሆንም፣ አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል የደረሱበት ዋነኛ የአገልግሎት ሆኖ ሳለ እዚህ ለሕይወትና ለጤና ኢንሹራንስ አገልግሎት መስጠት ፈተና ሆኗል፡፡

ኩባንያዎቹ በዚህ ዘርፍ ላይ በግልና በጋራ ሆነው ኅብረተሰቡን አንቅተው፣ ጥቅሙን አስረድተው ገበያውን ለመፍጠር ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ባለመቻላቸው ይኼው የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ድርሻ ከአምስት በመቶ ያልበለጠ ነው የሚለው የየዓመቱ ሪፖርት የተለመደ ሆኗል፡፡

ከዚህን ያህል ዓመታት በኋላ የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ያለው ድርሻ ቢያንስ አሥር በመቶ ለምን አልሆነም ብሎ የሚቆጭና ለዚህ የሚሠራ ለምን ጠፋ? ለማንኛውም የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ለአገራዊ ኢኮኖሚ ወሳኝ የሚባል ሚና ያለው ዘርፍ ነውና ይህንን ዘርፍ አሁን ዳዴ እያለ ካለው ጉዞ ተላቆ መራመድ እንዲችልና ለእያንዳንዳችን የሚሆን የመድን ሽፋን የሚሰጠው አገልግሎቶችን ማበርከት የሚችሉ ኩባንያዎች እንዲኖሩን እንፈልጋን፡፡

ለዘመናት ከፍተኛው የዓረቦን ገቢ የተገኘው ከሞተር ኢንሹራንስ ነው፡፡ ከፍተኛው ካሳ የተከፈለው ለመኪና አደጋ ነው፡፡ እየተባለ የሚቀጥል ዘርፍ ይዘን የትም ላንደርስ እንችላለንና የኢንሹራንስ ኩባንያዎቻችን እኛን የሚመስል፣ እኛን የሚጠቅም አገልግሎታችሁን እንሻለን፡፡ ለዚህ ደግሞ ሕዝብን ማስተማር በየቤቱ ማንኳኳቱን ጭምር የሚጠይቅ በመሆኑ ይህንን ለማድረግ ወኔ ይኑራችሁ ማለት ተገቢ ይሆናል፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን በዘመናዊ ዓለም ቴክኖሎጂውን መጠቀም ወሳኝ በመሆኑ፣ በእነዚህ ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም፣ ብዘዎችን መድረስ የሚቻልበት መንገድ ክፍት ነውና የእጅ ስልካችን ለዘርፉም ለሚያገለግል፣ በዚህም መንገድ መጠቀሙ ነገሮችን እንደሚቀይር ግልጽ ስለሆነ ኢንዱስትሪውን በሁሉም ረገድ ለመቀየር መታተር የኩባንያዎቹንም ዕድገት ያፋጥናልና ከመኪናው ባንወርድም ሌሎችንም አማራጮች እንመልከት፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት