ማክሰኞ ኅዳር 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት መግለጫ ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ማጣሪያ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ምሥራቅና ምዕራብ ግንባሮች ወሳኝ ድሎችን በመቀዳጀት ወደ መቀሌ እየገሰገሰ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የመከላከያ ሠራዊቱ በምሥራቅ ግንባር ጨርጨርንና ጉጉፍቶ መሆኒን ነፃ ማውጣቱንና በየቦታው የነበሩ ወሳኝ የኮንክሪት ምሽጎችን ማፍረሱን ገልጿል፡፡ በአሁኑ ጊዜም ወደ መቀሌ እየገሰገሰ ነው ብሏል፡፡
በምዕራብ ግንባር ደግሞ በአዲ ነብሪድና በአዲ ዳእሮ የሚገኙ ከባድ ምሽጎችን በማፍረስ ሽሬን ተቆጣጥሮ፣ ወደ አክሱም በመገስገስ ላይ እንደሆነ አስረድቷል፡፡
‹‹በውጊያው እጅግ ብዙ መሣሪያዎች ከመማረካቸውም በላይ ሕወሓት ለክፉ ዓላማው ያሠለፋቸው የትግራይ ልዩ ኃይል አባላት በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡›› ብሏል፡፡
‹‹የመከላከያ ሠራዊቱ የሕወሓት ጁንታን በሕግ ቁጥጥር ሥር ለማዋል እየገሰገሰ ሲሆን፣ የጁንታው ኃይል የመከላከያ ሠራዊቱን ክንድ መቋቋም አቅቶት ወደኋላ እየሸሸ ነው፤›› ሲል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ማጣሪያ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ሌሊት በሰሜን ዕዝ የሠራዊት ክፍሎች ላይ በሕወሓት አመራሮች ትዕዛዝ በተሰነዘረ ጥቃት ምክንያት፣ በማግሥቱ የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል ሕግ የማስከበር ዘመቻ መጀመሩ ይታወሳል፡፡