ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ የመሥራት ልምዱ አናሳ መሆኑን የፌዴራል ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
ኤጀንሲው ይህን ያለው ኅዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ከፌዴራልና ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር፣ አዲሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ አዋጅ 1113/2011 ከወጣ በኋላ በተከናወኑ ተግባራት ላይ ውይይት በተደረገበት ወቅት ነው፡፡
ከፌዴራል ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ፈቃድ ወስደው በሁለት ክልሎች ሥራቸውን የሚያከናውኑ በመሆናቸው፣ በአሠራር ክፍተት ምክንያት አንዳንድ ማኅበራት በሕዝብ ስም የመጣውን ሀብት ለግል ጥቅም እንዳይውሉ ለመቆጣጠር፣ ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚገባ፣ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ከክልሎች የተውጣጡ ጠቅላይ ዓቃቢያነ ሕጎች በመድረኩ እንደተናገሩት፣ ከፌዴራል ፈቃድ ወስደው በክልሎች ላይ የሚሠሩ አንዳንድ ማኅበራት ያልተገባ ድርጊት ሲፈጽሙ ቅንጅታዊ አሠራር ባለመኖሩ ችግር ተፈጥሯል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳስረዱት፣ ከክልሎች ጋር ተናቦ መሥራት ችግር በመኖር ማኅበራቱ በክልሎች የሚሠሩትን ሥራ ካለማወቅ በተጨማሪ፣ ሥራዎቻቸው ምን ያህል ለኅብረተሰቡ ጠቃሚና ተደራሽ መሆናቸውን ለማወቅ የመረጃ ክፍተት ነበር፡፡
ተሻሽሎ የወጣው አዋጅ እስካሁን ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው በፌዴራል ሥር በተመዘገቡት ብቻ በመሆኑ፣ በክልሎች በአቅም ውስንነትና በተለያዩ ምክንያቶች ተግባራዊ ሳይደረግ መቆየቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ አሁን ክልሎች ከፌዴራል አዋጅ ጋር የተጣጣመ ሕግ ለማርቀቅ እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው፣ በኤጀንሲው አሠራር መሠረት የፌዴራልና ክልል የመንግሥት ባለ ድርሻ አካላት፣ ከድርጅቶች ጋር በየጊዜው ምክክር፣ የልምድ ልውውጥና ክትትል በማድረግ አንድ ዕርምጃ ዘርፍን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
ሲቪል የማኅበረሰብ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ ከመከታተልና በሕግ አግባብ ሥራቸውን ማከናወናቸውን ከመቃኘት በተጨማሪ፣ ማኅበራቱን ለመደገፍና ለማሳደግ የቅንጅት ሥራው አስፈላጊነት ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በዕለቱ ኤጀንሲው በአዲሱ አዋጅ መሠረት ማኅበራቱን በድጋሚ ከመመዝገብ ባሻገር የተለያዩ ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ አደረጃጀትና መረጃ አያያዝ በጥናትና በምርምር የዳበረ አለመሆን ችግር ተብሎ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ጥናትና ምርምርን በተመለከተ ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ እየተሠራ መሆኑን አቶ ፋሲካው አስረድተዋል፡፡
ከኅዳር 4 እስከ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. በቆየው የጋራ የምክክር መድረክ በፌዴራልና በክልል ባለድርሻ አካላት የጋራ ስምምነት ተደርሷል፡፡ የዚህ የጋራ ስምምነት ሰነድ የመንግሥት ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሕግ አግባብ መሠረት እንዲንቀሳቀሱ፣ ሕዝባዊ ጥቅምን የሚያረጋግጡ ቅንጅታዊ አሠራሮች ማጎልበት፣ አፈጻጸማቸውን ማየት፣ በተለያዩ ጊዜያት ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ የሚያግዝ መሆኑን ተጠቁሟል፡፡
የኦሮሚያና የአማራ ብሔራዊ ክልሎች በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዙሪያ ያላቸውን የአሠራር ተሞክሮ ያቀረቡ ሲሆን፣ በሌላም መድረክ የሚቀጥል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡