በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሆቴሎችና ኢንዱስትሪዎች ሰላምን ሊያውኩ የሚችሉ ማንኛውም ነገሮች በመቃወምና በማጋለጥ ከፀጥታ ኃይል ጋር አብሮ ሊሠሩ እንደሚገባ ማሳሰቢያ ተሰጠ፡፡
‹‹የአሠሪና ሠራተኛ ወገኖች ለኢንዱስትሪው ክፍለ ኢኮኖሚ ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ ሚና አላቸው›› በሚል መርህ አዲስ አበባ ሠራተኞችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ያዘጋጀው መድረክ ኅዳር 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲካሄድ ነው ማሳሰቢያው የተሰጠው፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የቢሮው ኃላፊ አቶ ተፈራ ሞላ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለውን ሁከት በመቃወም እንዲሁም በየአካባቢው የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ሰላም እንዲጠበቅ ለማድረግ ማኅበረሰቡ አሠሪዎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከፀጥታ ኃይል ጎን በመቆም ያለውን ችግር መፍታት ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያ ወደ ታች ተዘፍቃ እንድትቀር የሚያደርጉ ሴረኞችን ለማስቆም ሕግ ለማስከበር ሕይወቱን እየሰዋ ላለው የአገር መከላከያ ሠራዊት በገንዘብም ሆነ በሌሎች ተግባራት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አቶ ተፈራ ገልጸዋል፡፡
ይህንንም ችግር ለመፍታት በተለያዩ ዘርፍ ውስጥ የሚገኙ ተቋሞችን በማስተባበርና ኮሚቴ በማዋቀር ከመንግሥት ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጅት መደረጉን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
‹‹ሰላምን ከማስፈን አኳያ መንግሥት እየሠራ ያለውን ሕግ የማስከበር ሥራ በመደገፍ ማኅበረሰቡ ፀጥታን የሚያውኩ ነገሮችን ለሕግ አካል ማቅረብ ይገባል፤›› ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት እየተከሰተ ያለውን የፀጥታ ችግር በመጠቀም በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የጥፋት ኃይሎት ተልዕኮን ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ ሴረኞች ሊኖሩ እንደሚችሉና እነዚህንም መከላከል እንደሚያስፈልግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ የሕዝብ አደረጃጀት አማካሪ አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ አስገንዝበዋል፡፡
እነዚህም ተቋማት ለከተማዋ ኢኮኖሚ መንቀሳቀስና ተያያዥ ጉዳዮች ሚናቸው ከፍተኛ በመሆኑ ከማንኛውም ዓይነት የፀጥታ ችግር ነፃ ሆነው የየዕለት ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመሆን አብሮ ሊሠሩ እንደሚገባ አቶ ሺሰማ ሳያሳስቡ አላለፉም፡፡
ለዘርፎቹ ማደግና ለዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሰላም የሚያስፈልግ በመሆኑ የጥፋት ኃይሉ ማለትም የሕወሓት ቡድን ያቀዳቸውን ሴራዎች ማክሸፍ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን አክለዋል፡፡
ያሉትንም ችግሮች ለመቅረፍና ሰላምን ለማስከበር የመከላከያ ሠራዊቱን መደገፍ እንዲሁም ደግሞ ለሠራተኞች ግንዛቤ መፍጠርና በየተቋማቱ የተደበቁ ተላላኪዎችን በማጋለጥ ሰላምን ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡