በምዕራብ አርሲ ዞን የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በተከሰቱ ግጭቶች ጉዳት ከደረሰባቸው አንዱ ነው፡፡ በዚህም ሰዎች ተጎድተዋል፣ ሞተዋል ንብረትም ወድሟል፡፡ ይህም በከተማዋ ያሉ የቱሪስት መስህቦት አደጋ ላይ እንዲወድቁ አድርጓል፡፡ የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም በምዕራብ አርሲ ዞን የተቀዛቀዘውን ቱሪዝም ዳግም እንዲያንሰራራ ለማድረግ በሻሸመኔ ከተማ የዓለም የቱሪዝም ቀን አክብሯል፡፡ አቶ አበራ ቡኖ አርሲ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ናቸው፡፡ በዞኑ ስላለው እንቅስቃሴ ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የዘንድሮውን የዓለም ቱሪዝም ቀን በምዕራብ አርሲ ዞን የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎችን በጉዞ ዝክር ቀን እንዲካተት አድርጎ አክብሯል፡፡ በዞኑ ያለው የቱሪዝም ዘርፍ ምን ይመስላል?
አቶ አበራ፡- የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን በግብርናው ዘርፍ ይታወቃል፡፡ ዞኑ በግብርናው ዘርፍ ከሚያበረክተው ከፍተኛ ምርት ባሻገር በቱሪስት መስህቡም የታደለ ነው፡፡ የላንጋኖ ሐይቅ፣ አብጃታ ሻላ ፓርክና ሐይቅ፣ የአዳባ ዶዶላ ኢኮ ቱሪዝምን ጨምሮ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች ይገኙበታል፡፡ ከዚህም ባሻገር በዞኑ ውስጥ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚከናወንባቸው ከተሞች ይገኛሉ፡፡ በአንፃሩ ዞኑ የበርካታ ሀብቶች ባለቤት ቢሆንም ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት በደረሰ ውድመት የነበረው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ደብዝዟል፡፡
የዓለም ቱሪዝም ቀንን በማስመልከት ቱሪዝም ለልማት በሚል ቃል ዞናችን ዕድሉን አግኝቶ እንዲከበር በመደረጉ ደስተኛ ነን፡፡ ዞኑ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ የቱሪስት መዳረሻዎች ምቹ በመሆናቸው በየዓመቱ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ሲያስተናግድ ቆይቷል፡፡ በተለይ እዚህ አከባቢ ያለውን ባህልና የቱሪዝም መስህብ በመለየት፣ የአገር ውስጥ ጎብኝዎች፣ የአስጎብኚ ተቋማት እንዲሁም የሚዲያ አካላት በዞኑ ያሉትን መስህቦች ለዓለም እንዲያስተዋውቁ ዕድል ከፍቷል፡፡
ሪፖርተር፡- ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ በአንዳንድ ቦታዎች በነበረው አለመረጋጋት እንዲሁም የድምፃዊ ሃጫሉ ግድያን ተክትሎ በተለይ ይኼ ዞን የከፋ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ዞኑ አሆን ያለበት የፀጥታ ሁኔታ ምን ይመስላል?
አቶ አበራ፡- እንደሚታወቀው ከወራት በፊት በዞኑ በተለይ ሻሸመኔ ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱ ይታወቃል፡፡ የተከሰተው ችግር ከሕዝብ የመነጨ ሳይሆን የጥፋት ኃይሎች የፈጠሩት ነው፡፡ የጥፋት ኃይሉ ዋናው ተልዕኮ ሕዝብን ከሕዝብ፣ ብሔርን ከብሔር ማጋጨትና ኦሮሚያን የግጭት ማዕከል ማድረግ ነው፡፡ ይኼንን ከአገር ውስጥም ከአገር ውጭም ሆነው የሚመሩ ባንዳዎች አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ነበር ክስተቱ የተፈጠረው፡፡ ክስተቱ በጣም አሳዛኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም የሰው ሕይወት የጠፋበት፣ ሰው የተፈናቀለበት እንዲሁም ከፍተኛ ንብረት የወደመበት ነበር፡፡ በሻሸመኔ እንዲሁም በዞናችን የደረሰው ክስተት በጣም ያሳዘነንና አንገታችንን ያስደፋን ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በማግሥቱ ሕዝቡን በማወያየት፣ ሕዝቡን ባለቤት በማድረግና ከተማዋን ወደ ቀድሞ ሰላሟ ለመመለስ ከፍተኛ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡
ሪፖርተር፡- በዞኑ እንዲሁም በሻሸመኔ ከተማ የተከሰተውን ውደመት ተከትሎ፣ በርካታ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል፣ የንግድ ሥፍራዎች ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱ ይታወሳል፡፡ በሕዝቡ ላይ የተፈጠረውን የመሸበር ስሜት ለማረጋጋት ምን ዓይነት ውይይቶችን አከናወናችሁ?
አቶ አበራ፡- ችግሩ ከተከሰተበት ወቀት አንስቶ እያንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍል አባ ገዳዎች፣ የከተማ ሽማግሌዎች፣ ሀዳ ሲቄዎች፣ ወጣቶችና ምሁራን እንዲሁም አመራሮች ሳይቀር ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቱም በውስጣችን እጁ ያለበት አመራር ጨምር የሕግ የበላይነት መከበር እንዳለበት መክሮ፣ ያጠፉትን በሕግ ጥላ ሥር እንዲውሉ ተደርገዋል፡፡ ገሚሱ ደግሞ ጉዳያቸው ታይቶና ምክር ተደርጎላቸው ወደ ሰላማዊ ሥራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ አሁን በዞናችን ሕግ ተከብሮ፣ ፍፁም ሰላማዊ ነው፡፡ በዋነኛነት የሕዝቡን ሰላም የሚጠብቀው ራሱ ማኅበረሰቡ ነው፡፡ በተጨማሪም ነዋሪው ባስቀመጥነው አደረጃጀት መሠረት በከተማ ደረጃ በቀበሌ ተደራጅቶ ሕዝቡን በሠፈር ውስጥ ተደራጅቶ ደግሞ ፀጉረ ልውጥን እንዲጠብቅና በመካከሉ ችግር የሚፈጥረውን እያጋለጠ የአካባቢውን ሰላም እንዲጠብቅ አድርገናል፡፡
ሪፖርተር፡- በሁከቱ ምክንያት ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸው ሰዎች አሉ፡፡ እነሱን መልሶ ለማቋቋም ምን እየተሠራ ነው?
አቶ አበራ፡- እንግዲህ የጠፋውን የሰው ሕይወት መመለስ አይቻልም፡፡ በቀዳሚነት የሰው ልጅ ሥነ ልቦና ላይ መሥራት ነው፡፡ በዚህም ሁሉም ሰው ይቅር ተባብሎና እንደ ወንድማማች እንዲሆን የማስረዳት ሥራ ስንሠራ ቆይተናል፡፡ ሌላኛው መልሶ የማቋቋም ሥራ ነው፡፡ በዞናችን 228 ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ ከእዚያ ውስጥ በየወረዳው ከማኅበረሰቡ፣ ከባለ ሀብቶች እንዲሁም መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በተሰበሰበ 15 ሚሊዮን ብር ቤቶቹ ተገንብተው ለተጎጂ ቤተሰቦች ተላልፈው በሰላም እየኖሩ ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ የንግድ ዘርፍ ላይ የተሠማሩ የሆቴልና የንግድ ማዕከል ባለንብረቶች እንዴት መደገፍ እንዳለባቸው ከመንግሥት ጋር እየተመካከርን እንገኛለን፡፡ ገሚሱም በሕዝቡ ድጋፍ ተደርጎለት የንግድ ቦታውን እያደሰ ወደ ሥራ እየተመለሰ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ጉዳት የደረሰባቸውን አካላት ዳግም ለማቋቋም የተለያዩ ማኅበረሰቦች ድጋፍ እያደረጉ ይገኛል፡፡ ድጋፉን በአግባቡ የማዳረስ ሥራው እንዴት እየተከናወነ ይገኛል?
አቶ አበራ፡- የተሰበሰበው ድጋፍ በዞኑ ሥር በሚተዳደሩ ከተሞችና ወረዳዎችን ታሳቢ አድርጎ እየተለገሰ ነው፡፡ ድጋፉ ለመጣው አካባቢ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ሁሉም አደጋው የደረሰባቸው አካላት የራሳቸው ኮሚቴ አላቸው፡፡ አመራሩም ያዋቀረው ኮሚቴ አለ፡፡ ከኅብረተሰቡም የተውጣጣ ኮሚቴ ስላለ ቅድሚያ ለሚሰጠውና ለቀጣይ የሚለው ተገምግሞ እየተስተናገደ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ዞኑ በከፍተኛ የግብርና ምርት ይታወቃል፡፡ በዞኑ ያለው የግብርና እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
አቶ አበራ፡- በዞኑ የሚኖሩ ሕዝቦች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ በግብርናው ዘርፍ ላይ የተሠማራው ምርቱን ሰብስቦ ለገበያ እያቀረበ፣ የሚያስፈልገውን ምርትም እየሸመተ ይገኛል፡፡ ዞናችን የኦሮሚያ መካናይዜሽን ማዕከል ሆኖ ኮምባይነሮችን እንዲሁም ትራክተሮችን እየተጠቀመ ሥራዎን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በቀጣይ መስኖን በማስፋፋት ግብርናው እንዲስፋፋ ለመሥራት ዕቅድ ነድፈናል፡፡