Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርአገር የማፍረስ ነውረኛ ክህደት ላይደገም መታረም አለበት!

አገር የማፍረስ ነውረኛ ክህደት ላይደገም መታረም አለበት!

ቀን:

በገለታ ገብረ ወልድ 

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊታችን ትናንም ሆነ ዛሬ የአገር ዋልታና ማገር ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተዋቀረና ኅብረ ብሔራዊነትን የተላበሰ መከታችንም ነው፡፡ አልፎ ተርፎ የአፍሪካ ኩራትና የሰላም ዘብነቱ በታሪክ የተመዘገበ መሆኑም በታሪክ የተመሰከረ ነው፡፡ ስለሆነም ባለፉት ሥርዓቶች እንደታየው ሁሉ፣ በየትኛውም የውስጥ ሽኩቻና የፖለቲካ ውዝግብ ውስጥ እንዲገባ መገደድ አልነበረበትም፡፡

ይህ የአገር ምሰሶ በዘመናዊ መልክ ተደራጅቶ እየወደቀ እየተነሳ እዚህ የደረሰው ካለፉት ስምንት አሥርት ዓመታት ወዲህ እንደሆነ ቢታመንም፣ የአገራችን ሕዝብ የወታደራዊነትና ጦረኝነት ባህሪ ተላብሶ አገራችንን ከየትኛውም የወራሪ ጥቃት ሲመክት መቆየቱ አሁን እስካለው ትውልድ የጀግንነትና ሉዓላዊነት ቀናዒ መሆን እርሾ ሆኖ እንዳገለገለው የታመነ ነው፡፡ በተለይ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ደግሞ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ጠንካራ ማኅበራዊ መስተጋብርን እስከ መፍጠር መድረሱ የታወቀ ነው፡፡

- Advertisement -

የአገራችን መከላከያ ሠራዊት በአንድ በኩል የአገር ውስጥ ፖለቲካው ተደጋግሞ በገጠመው የውስጥ ሽኩቻ እየተፈተነ፣ በሌላ በኩል ለረዥም ዓመታት  በተካሄደ የእርስ በርስ ጦርነት የመበተንና ጥልቅ ዕውቀት ያላቸውን የጦር አዛዦች የማጣት ተግዳሮት  እየገጠመው እዚህ ቢደርስም በአደረጃጀት፣ በሰው ኃይል ብዛትና ጥራት፣ በታጠቀው መሣሪያና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በሚመራበት ስትራቴጂና ተልዕኮ ከትናንት ለዛሬ እየተሻሻለና እያደገ የመጣ ኃያል ክንዳችን ነው፡፡

ጦሩ ትናንትም ሆነ ዛሬ የውጭ ኃይል ጥቃትን በመመከት እየተጫወተ ካለው ሚና ባሻገር፣ በቅርብ ጊዜም ሆነ ከዚያ በፊት በአገር ውስጥ በተዛባ  የፖለቲካ ውዝግብ ወይም በፅንፈኞች ቅስቀሳ በሕዝብና በአገር ላይ የሚቃጣ ጥቃትን በመመከትና አገርን በማረጋጋት ረገድ ታሪካዊ ኃላፊነቱን እየተወጣም ነው፡፡

በዚህም ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን በትዕግሥትና አርቆ አሳቢነት ከመወጣቱ ባሻገር፣ አገረ መንግሥቱ ትንንሽ በሚመስሉ የውስጥ ግጭቶች ተናግቶ፣ የአገር ሉዓላዊነት ለውጭ ኃይሎች ጥቃት እንዳይጋለጥ ዘብ ሆኖ መቆሙ የምልዓተ ሕዝቡን ቅቡልነት እንዲያገኝ የሚያደርገው ነው፡፡ በቅርቡ በሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ ትሕነግ በተባለው ከሀዲና አኩራፊ ኃይል የተፈጸመው ጥቃትና ትንኮሳ ግን፣ በታሪክ በአሳፋሪነቱ የሚጠቀስና እጅግ ከፍተኛ ስህተት የተፈጸመበት ሕገወጥ ድርጊት ነው፡፡     

በእርግጥ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በአገራችን ለውጥ መጀማመሩን ተከትሎ  የፖለቲካ አየሩን የሚረብሹ ክስተቶች በመስተዋላቸው፣ የመከላከያ ኃይሉንና  የፀጥታ አካላትን ጫና ውስጥ ከቶ መክረሙ ይታወቃል፡፡ በመሠረቱ ሕወሓት ብቻ ሳይሆን መላው ኢሕአዴግም በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ዘረፋ፣ ዘረኝነትና ጥላቻ በማቀንቀናቸው በአገር ላይ ጥፋት ደርሷል፡፡

ለዚህም በፖለቲካ እምነታቸው ምክንያት ብቻ የሞቱ፣ የቆሰሉ፣ የተሰደዱና የታሰሩ ዜጎች ማሳያ ናቸው፡፡ ለዚህ ሁሉ ግፍ እንደ ኢሕአዴግ ሕዝቡ ይቅርታ የተጠየቀ ቢሆንም፣ ሕወሓት ሐሳቡን ክዶ ለጥፋት መሽጎ መክረሙ ብዙ ሲያወዛግብ ነው የከረመው፡፡ በአንድ በኩል ሕግ ከሚፈቅድለት በላይ የፖሊስ፣ የልዩ ኃይልና የሚሊሻ ሥልጣና በማካሄድ ትጥቅና ዝግጁነት ሲያሟላ ከርሟል፡፡ በሌላ በኩል የአገሪቱ ሕጋዊ ተቋማትና ሕገ መንግሥታዊ አካላት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ያራዘሙትን አገራዊ ምርጫ በዕብሪት በማካሄድ፣ ጭራሽ ሌሎቹን የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ሕገወጥ ብሎ ለመፈረጅ በቅቷል፡፡ በመከላከያ ውስጥ በብሔር መልምሎ ወታደራዊ ጁንታ ፈጥሮ አደጋ ማድረሱ ግን ፍፁም የሚጠበቅ አልነበረም፡፡

ይህ ኃይል እንደ ማንኛውም በመታደስ ላይ ያለ የፖለቲካ ድርጅት ራሱን ፈትሾ ማሻሻያ ማድረግ ሲገባው፣ የተፈጠረ ስህተት ወይም የተፈጸመ ጥፋትን  በሙሉ ወይም በከፊል አምኖ ይቅርታ መጠየቅም ሲቻል በዚህ ደረጃ ብረት ነክሶ መከንቸሩ እጅግ አሳዛኝ እውነታ ነው፡፡ ሕወሓት ከሰውነት የወረደ ዘራፊ ቡድን፣ ብሎም ክህደት የተጠናወተው ነውና ያንገሸግሸዋል እንጂ፣ ዕርቅና ስምምነትን ዕውን ሊያደርገው አይችልም የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡ የአሁኑ ያልታሰበ የተንኮል ዕርምጃ የመነጨውም ከዚህ ዓይነቱ የኖረ ልክፈት እንደሆነ ብዙዎች እየተናገሩ ነው፡፡    

ዛሬ በክፋት ብዛትና ግድ ግጠሙን ብሎ በቀሰቀሰው ጦርነት እየተለበለበ ያለው፣ ይኼው ኃይል ከጭንቀት ብዛት ይቅርታ ሊል የሚያምረውና ድርድርድን የመረጠ የሚመስለው ለማዘናጊያ ነው፡፡ በመሠረቱ ይቅርታ መጠየቅም ሆነ ማድረግ ወይም ለድርድር መዘጋጀት፣ ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕይታ የሚመነጭ እንጂ አምባገነኖች የሚያደርጉት ቀርቶ የሚያስቡትም አይደለም፡፡  

ይቅርታ የታላቅነት እንጂ የሽንፈት ምልክት አልነበረም፡፡ ሕወሓት ግን ይህን ከማድረግ ተንገዳግዶ የተፈጥሮ ሞቱን የመረጠ የጥፋት ቡድን እንደመሆኑ፣ በጭካኔ አዘናግቶ ዕርምጃ ወደ መውሰድ ነው የገባው፡፡ በዚህም  እየሄደ ያለው ወደ ተፈጥሮ ሞቱ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ማሳያው ደግሞ ፀቡን ከመንግሥትና ከፖለቲከኞች ጋር ማድረግ አንሶት፣ ጀግናው የመከላከያ ኃይልን  በሴራ አዘናግቶ ከውስጥና ከውጭ (ከጀርባው) እንዲወጋ በማድረግ ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት ፈጽሟል፡፡

ለዘመናት ሕዝብ ሲበዘብዝና ሲጨቁን የነበረውና የተጀመረውን ለውጥም ሲገዳደር የቆየው ሕወሓት፣ አገር ለማፍረስ እየሠራ የነበረው ሴራም በኃይል እንዲመታ የሚጋብዝ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር  የለውጥ ኃይሉ የትሕነግ ቱባ ዘራፊዎችና ጨቋኞችን በተመለከተ ከተገቢው በላይ ትዕግሥት በማሳየቱ ‹‹ምን እስኪሆን ነው የሚጠብቀው?›› እስከ መባልም መድረሱ አይዘነጋም፡፡ ‹‹ለምን ጠበቅ ያለ ዕርምጃ አይወስድም? መዘናጋቱ እስከመቼ ነው?›› ወዘተ የሚሉ አስተያየቶችም ሲደመጡ ነበር፡፡ ትዕግሥቱ ፋሬ ሳያፈራ ቀረና ፅንፈኛ ቡድኑ ከባዱን ጥፋት ለመፈጸም መብቃቱ አሳዛኝና እልህ የሚቀሰቅስ ድርጊት ነው፡፡

በእርግጥ እነዚህ ምክሮች የሚመነጩት  በአንድ በኩል የሕወሓታዊያንና የኦነግ ሸኔ ዓይነቶቹ አክራሪ ብሔርተኛ ጭፍራዎቻቸው ከልክ ያለፈ ድፍረት ካስቆጣቸው ዜጎች ነበር፡፡ ፀረ ሕገ መንግሥትና ፀረ ሰንደቅ ዓላማ አቋማቸው ካበሳጫቸው፣ ሠልፍ በተባለ ቁጥር እየበረታ ያለው ተደራራቢ ጥፋትና ግጭት ካስጨነቃቸውና የወደፊቱ አካሄድ ካላማራቸው ዜጎችም ነው፡፡ በሌላ በኩል ሕግና ሥርዓት ለማንም ቢሆን እኩል ማገልገል አለበት ብለው የሚያስቡ ወገኖችም ሐሳቡን ሲጋሩት ቆይተዋል፡፡ ለሁሉም ትዕግሥት መጥፎ ባይሆንም በሰሜን ዕዝ ላይ ደረሰውን ጉዳት መቀነስ የሚችል ጥንቃቄ አለመደረጉ ግን በድክመት የሚጠቀስ ነው፡፡

ሕወሓት ዛሬ ፍፃሜውን መርጦ የዘመተበት የመከላከያ ኃይላችን በዋናነት ባለፉት በ30 ዓመታት በመስዋዕትነት የተፈተነ ነው፡፡ ከለውጡ ወዲህ ሪፎርም እያደረገ ቢሄድም አብዛኛውን የትግራይ ተወላጅ ነባር ታጋዮችን የያዘና የብሔር ብሔረሰቦች ልጆችን ያቀፈ መሆኑም ይታወቃል፡፡ እንደ ተቋም ያለው ግርማ ሞገስና ትዕምርት የሰንደቁን ያህል መሆኑም አይዘነጋም፡፡ ለነገሩ የአገር መከላከያ ኃይል ለአገሮች ያላቸውን ቁርጠኝነት ማሳያ፣ በዓለም ፊት መለያና መታወቂያ መሆኑም በእኛ ብቻ ሳይሆን በሁሉም አገሮች ቢሆን የሚታወቅ ሀቅ ነው፡፡ ታዲያ ሕወሓት እንዴት ይኼን ነባራዊ ሀቅ ሳተና ነው ጦሩን ሊበትን የሞከረው ነው ጥያቄው፡፡

እውነት ለመናገር ለአገሩ ደሙን ለማፍሰስም ሆነ አጥንቱን ለመከስከስ የተሠለፈውን ይህንን ኃይል ይቅርና የትኛውም ኃይል ቢሆን፣ የትግራይ ሕዝብን ከጥቃት ለመጠበቅ የተሠለፈ፣ በልማትም ሆነ በማኅበራዊ ግንኙነት የሚያገለግል፣ የተጋባና የታዋለደ ከመሆኑ ባሻገር ከሃያ ዓመታት በላይ ከሕዝቡ ጋር የኖረ ነበር፡፡ ታዲያ ለተራ የፖለቲካ ትርፍ እንዴት ይኼን ኃይል መምታትና በሴራ መበተን ተፈለገ ነው የሚያደናግረው ጥያቄ፡፡

በእርግጥ በአገራችን ከሦስት አሥርት ዓመታት ወዲህ በወረደው የዘውግ ትርክትና መነጣጠል አንድነታችን የተዳከመ ቢመስልም፣ እንደ መከላከያን በመሰሉ ተቋማት ጠንካራ የአገርና የሰንደቅ ዓላማ ፍቅር ብሎም አብሮነት ስለመገንባቱ ብዙ ማረጋጋጫዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ሕወሓት ግን በሠራዊቱ ውስጥ የነበሩ ነባርና አዲስ የትግሪኛ ተናጋሪ አባላትን በራሳቸው ወገኖች ላይ እንዲዘምቱ ማድረጉ ነው፡፡ የክህደቱን ጥግ ግፍ ያደረገው ማለት ይቻላል፡፡

የመከላከያ ኃይሉ ለብሔርና ለሃይማኖት ሳይሆን ለአገር ብቻ የቆመ መሆኑ እየታወቀ ለአገር ሉዓላዊነትና ለሰንደቅ ዓላማው ፍቅርና ክብር ባለው ውግንና ሕይወቱን ሲከፍል የኖረው ከቀደመው ዘመን ጀምሮ መሆኑም እየታመነ፣ ይኼን ሴራ ማቀድ በራሱ ከወንጀል በላይ ነው፡፡ እንዲያውም የእኛ ሥነ ልቦና ከሌሎች የተሻለ በመሆኑ እንጂ፣ ይኼ ጦር በበቀልና እልህ ተነሳስቶ ንፁኃንን በዘር እየለያየ እንዲፋጁ የሚገፋ ትንኮሳ ነበር የተፈጸመበት፡፡

አሁንም የሕወሓትን ሕገወጥነት አስተንፍሰን አገራችንን እናስከብራለን የሚለው የጦሩ መነሳሳት ከዚሁ ቁጭት የሚነሳ ነው፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ተዋግተን እንሞታለን፡፡ ወገኖቻችንን ቀብረን፣ የአገር ባንዲራውን ረግጠን አንሄድም/አንበተንም፤›› ብሎ የሰሜን ዕዝ ከበባውን ሰብሮ ፊቱን አዙሮና ሞራሉን አጠናክሮ ጦርነቱን በፅናት በመግጠም፣ የሕወሓትን አከርካሪ እየመታ ያለው ሲል መንግሥት ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

እንደ ፖለቲካ ትንታኔ ሲታይ ሕወሓት ትልቁን ነውር የፈጸመው የፖለቲካ ልዩነት በማሳየቱ አይደለም፡፡ በተቃራኒው በጠንካራ አንድነትና የአገር ፍቅር ስሜት እየተገነባ ያለውና በዲሲፒሊኑ የሚመሠገነውን መለዮ ለባሽ በጁንታ መልክ በመናድ፣ ለዘመናት ሕዝቦችን አሰቃይቶ ጋብ ያለልንን ጦርነት በመለኮሱ ነበር፡፡ ከዚህ በላይ ፍፁም በማይጠበቅ ደረጃ ንፁኃንን በጅምላ መግደሉና የተማረኩ ወታደሮችን እጅና እግር እያሰረ መረሸኑ፣ ይህ ድርጊትም ወገን በሚባል ሕዝብ ውስጥ ፍፁም ሊደረግ የማይገባው ሲሆን፣ ይህንን ኃይል እስከ ቀራኒዮ ሄዶም መፍረድ እንደሚገባ አመላካች ነው፡፡

ይህ ከትናንቱ በተሻለ በብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ስብጠር የተገነባ ኃይል፣ የፈለገው አስተሳሰብ መለዋወጥ በፖለቲካ ኃይሉ ውስጥ ቢንፀባረቅ ታማኝነቱ ለሰንደቁና ለአገር ሉዓላዊነት መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ቀሪው ሕዝብ በተለይ አዲሱ ትውልድም ትምህርት ሊወስድበት የሚገባው ይህንን የአገር ፍቅር መሆን እንደነበረበት ተደጋግሞ ሲነገር መቆየቱ የታወቀ ነው፡፡ ብዙዎች እንደሚገምቱት ግን ሕወሓት በዚህ ወሳኝ ሠራዊቱ ላይ በውስጥ ጁንታ፣ በሚሊሻም ይባል በልዩ ኃይል የዘመተበት ደግሜ ሥልጣን እይዛለሁ ብሎ ሳይሆን፣ አገረ መንግሥቱን በማተራመስ ራሱን ከተጠያቂነት ለማውጣትና አገርም ብትበተን ገላጋይ ሆኖ ለመቅረብ ነው፡፡

በመሠረቱ አይደለም በአንድ አገር በሚኖሩ 110 ሚሊዮን ሕዝቦች መካከል ይቅርና በጣት በሚቆጠሩ አንድ ቤተሰቦች ውስጥም ልዩነት መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ በአግባቡ ከተያዙ ግን ያሉት ልዩነቶች ለአንድነት መሠረት የሆኑ ፈርጦች ነው የሚሆኑት፡፡ ስለሆነም ልዩነት ለምን መጣ አይባልም፡፡ በሰዎች መካከል የቋንቋ፣ የፆታ፣ የባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ የአመለካከት፣ የሥነ ልቦና፣ የግንዛቤ፣ የሀብት መጠን፣ የፍላጎትና የዝንባሌ፣ የአስተዳደግ ሁኔታና የምርጫ፣ ወዘተ. ተቆጥረው የማያልቁ ልዩነቶች አሉ፡፡ ልዩነቶችን የሚያጠፋፉና የጋራ አገርን የሚስክዱ ሊሆኑ ግን አይችሉም፣ አይገባምም፡፡ የሕወሓት መንገድ ግን መልሶ ቀውስ ውስጥ እየከተተን ያለው ይህ እውነታ በመዘንጋቱ ነው ሊባል ይችላል፡፡

ታዲያ እንደ ሕዝብስ ይህን ዕውን ማድረግ ስለምን ይሳነናል ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ በልዩነቶች ውስጥ አንድነትን ማምጣት ስለምን አይቻልም? ለልዩነቶች ዕውቅና መስጠት ማለት በልዩነቶች ምክንያት አለመግባባት አይኖርም ማለት አይደለም፡፡ አለመግባባት ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ሁሌም ይኖራል፡፡ ነገር ግን አለመግባባቶች በሕዝብ መካከል ያለውን አጠቃላዩን ብሔራዊ ሰላም እስከሚያደፈርሱ ድረስ ዕድል ሊሰጣቸው አይገባም ነበር፡፡ ልማትና ዕድገትን እስከሚያደናቅፉ ድረስ መስተናገድም የለባቸውም፡፡ ይህን እየተገነዘቡ እንደማያውቁ መሆን ደግሞ እጅግ የከፋ ነውረኝነት ነው፡፡

ከዚያ ይልቅ የአገር መከላከያ ሠራዊታችንንና በአጠቃላይ መለዮ ለባሹ አንድነቱን ጠብቆ፣ የአገር ሉዓላዊነትና የሕዝብ ሰላምን እያረጋገጠ እዚህ የደረሰበትን ነው ልንማርበት የሚገባን፡፡ በብሔራዊ አርቆ አስተዋይነት በሰንደቅ ዓላማችን ሥር የአንድነት ጥላ በሆነችው መጠለያችን፣ ኢትዮጵያ አገራችን ለሕዝቦቿ ጥቅም ሲባል ልዩነቶችን በብሔራዊ ስሜት መቃኘት ለሠራዊቱ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ ሕዝቡም የተጣለ ኃላፊነት ነው መባሉም ከዚህ ይመነጫል፡፡ ታዲያ ሕወሓት በሠራዊቱ ውስጥ ለዓመታት ተሠልፈው የኖሩ ዜጎችን እንዴት ለቡድን ፍላጎቱ መጠቀሚያ አዘጋጃቸው ብሎ መፈተሽ ይገባል፡፡ ይኼ ሁሉ ሴራና ዝግጅት ሲደረግስ መንግሥት እንዴት መረጃና ማስረጃ አግኝቶ ዝግጅት ማድረግ ተሳነው መባልን አለበት፡፡

በነገራችን ላይ ከእኛ የባሱ ልዩነቶች ያሉባቸው ሕዝቦች በሰላምና በመቻቻል እየኖሩ የሚያስቀና ሰላምና አንድነት፣ ብሎም የሚያስደንቅ ዕድገት ላይ የደረሱ መሆናቸውን መጥቀስ ይገባል፡፡ ለምሳሌ ህንዶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ህንድ እ.ኤ.አ. በ2018 ሕዝብ ቆጠራ ውጤት መሠረት 1.3 ቢሊዮን ሕዝብ አላት፡፡ የተለያዩ ብሔረሰቦች የቋንቋ፣ የባህል፣ የሃይማኖት/የእምነት ልዩነቶቻቸው ብዛት ተቆጥሮ አያልቅም፡፡ ህንድ የራሷ የሆኑ 1,500 ቋንቋዎች አሏት፡፡ ህንድ እንደ አገር ከቆመችበት ጊዜ አንስቶ እንኳን በወታደሩ ውስጥም ሆነ በሌላውም ቢሆን ይህ ነው የሚባል የእርስ በርስ ጦርነት ታይቶና ተሰምቶ አይታወቅም፡፡

በመሠረቱ አሁንም ከምንገኝበት ጊዜ አንፃር፣ ለሕዝቡም ሆነ ለፖለቲከኛው መነገር ያለበት በሁሉም ነገር ላይ መስማማት የማይቻል መሆኑን ነው፡፡ በዋና ዋናዎቹ አገራዊ ጉዳዮች ለምሳሌ በመከላከያ ሠራዊታችን ህልውና ላይ፣ በአገር ሰላምና ደኅንነት ላይ  ከአስከፊ ድህነት በመላቀቅ ላይ፣ እንደ ህዳሴ ግድብ ባሉና በሌሎች ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ በሕገ መንግሥታዊ ግንዛቤ ላይ፣ በአገር ሉዓላዊነትና አንድነት አስፈላጊነትና ወሳኝነት ላይ ብሔራዊ መግባባት ላይ አለመድረስ አብሮ ሊያኖር አይችልም፡፡ በዚህች አገር እየገጠመ ያለው ፈተና ደግሞ ይኼው መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡

በመሠረቱ የአንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎችን ዓይን ያቀላ ተግባር ቢመስልም፣  አሁን በመከላከያ ስትራቴጂና የተልዕኮ አቅጣጫ ላይ በግልጽ ማሻሻያና ዕርምት እንደተደረገባቸው፣ የገለልተኝነት፣ የአገርና የሕዝብ ውግንና፣ የሥልጠናና የአደረጃጀት ሥልቶች ብሎም የመፈጸም አቅጣጫዎችና የኑሮ ማሻሻያ ዕርምጃዎች ሁሉ እንደ አገር ክብር መገለጫ የሚታዩ ናቸው፡፡ ይህ ጦር ከአገራችን አልፎ ለጎረቤት አገሮች የሚበጁ ትጥቆችና ዝግጁነቶችን በያዘበት ጊዜ፣ ጦርነት ለኩሶ ለእርስ በርስ መበላላት እንዲያውል መፈረድ አልነበረበትም፡፡ በመሆኑም በዚህ ነውረኛ ወንጀል ውስጥ የተሰማሩ የሕወሓት አመራሮች በፍርድ አደባባይ የእጃቸውን ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡

በመሠረቱ ይህ ዓይነቱ የክህደት አካሄድ ዛሬ በአንድ ጀንበር አልተፈጠረም፡፡ ትናንትም ሆነ ከዚያ በፊት በተለያየ መልክ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በዚህ መንገድ አገር ትጎዳለች እንጂ የተጠቀመ እንደሌለ ግን የታወቀ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ከሀዲያንን ማዋረድና አገራችንን ከፍ ማድረግ ከተቻለ፣ ተምረንበት የምናልፈው የታሪካችን አካል መሆኑ አይቀርም፡፡ በዚህ የእርስ በርስ ግጭት ግን ፅንፈኞችና ጁንታዎች ማሸነፍ አይደለም ጊዜ የሚያገኙ ከሆነ አገር መዋረዷና ሕዝቡም ለከፋ አደጋ መጋለጡ አይቀርም፡፡ ስለሆነም የመከላከያ ሠራዊቱንና መላው የፀጥታ ኃይል የጀመሩትን ትግል ይበልጥ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡ የሕዝቡም ደጀንነት መጠናከር አለበት፡፡ ግዴታችንም  ነው!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን  አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...