Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኤጀንሲው አዲስ ዋና ዳይሬክተር ተሾመለት

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱን ግዙፍ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በሥሩ ለያዘው፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመሆን ለረዥም ዓመታት ሲያገለግሉ በነበሩት አቶ በየነ ገብረ መስቀል ምትክ፣ አዲስ ዋና ዳይሬክተር ተሰይመው ሥራ መጀመራቸው ተገለጸ፡፡

አቶ በየነ ገብረ መስቀልን ተክተው በዋና ዳይሬክተርነት እንዲሠሩ የተሾሙት ምክትላቸው የነበሩት አቶ ሀብታሙ ኃለ ሚካኤል ናቸው፡፡ አቶ በየነ ለረዥም ዓመታት ሲያገለግሉ ከቆዩበት መሥሪያ ቤት የለቀቁት በራሳቸው ፈቃድ ሲሆን፣ ያቀረቡትም ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ በምትካቸው አቶ ሀብታሙን የሾሟቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

አቶ ሀብታሙ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ከመሰየማቸው ቀደም ብሎ በኤጀንሲው በምክትል ዋና ዳይሬክተርነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ኤጀንሲውን ከመቀላቀላቸው ቀደም ብሎ የአዳማና የሻሸመኔ ከተሞችን በከንቲባነት ሲያገለግሉ እንደነበር ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

በአገሪቱ ግዙፍ የሚባሉትን የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በሥሩ የያዘው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ፣ በአሁኑ ወቅት 21 የልማት ድርጅቶችን የያዘ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥም በአገሪቱ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በአትራፊነታቸው የሚታወቁትን እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ያሉ ተቋማትን የያዘ ነው፡፡ በተለያየ ችግር ውስጥ ያሉት የስኳር ፋብሪካዎችና ሜቴክም በዚሁ ኤጀንሲ ሥር ናቸው፡፡

በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ አስተዳደር ኤጀንሲ ሥር ያሉ 21 የልማት ድርጅቶች፣ በ2012 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 70 ቢሊዮን ብር ለማትረፍ አቅደው 55.5 ቢሊዮን ብር ማትረፍ ስለመቻላቸው ኤጀንሲው ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ ይህ የኤጀንሲው የትርፍ ግኝት አፈጻጸም ከዕቅዱ አንፃር 79 በመቶ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡፡

በተጠናቀቀው 2012 በጀት ዓመት በኤጀንሲው ሥር ከሚገኙ ድርጅቶች ውስጥ በከፍተኛ አትራፊነታቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም አንዱ ሲሆን 28.1 ቢሊዮን ብር አትርፏል፡፡

እነዚህ ድርጅቶች2013 በጀት ዓመት 376.66 ቢሊዮን ብር የምርትና አገልግሎት ሽያጭ አከናውነው 73.81 ቢሊዮን ብር ከታክስ በፊት ትርፍ እንዲያስመዘግቡ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑም ታውቋል፡፡ ይህም ዕቅድ ድርጅቶቹ በ2012 አስመዝግበውት ከነበረው ሽያጭ በ22 በመቶ ዕድገት ያለው ሽያጭ እንደሚፈጽሙ የታቀደ ነው፡፡ በትርፍ ረገድም ከታክስ በፊት በ36 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ እንዲያስመዘግቡ የታቀደ መሆኑም መረጃው ያመለክታል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች