በሩብ ዓመቱ ከታክስ በፊት 8.7 ቢሊዮን ብር በላይ አትርፈዋል
የአገሪቱን ባንኮች የ2013 የሩብ በጀት ዓመት አፈጻጸማቸውን የሚያሳየው ግርድፍ የሒሳብ ሪፖርት፣ አሁንም ውጤታማ ሆነው መቀጠላቸውን የሚያመለክት ነው፡፡ በተለይ በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ረገድ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበበት ሆኗል፡፡
እንደ ግርድፍ ሒሳብ ሪፖርት ሁሉም ባንኮች አትራፊ ሆነው መቀጠላቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸማቸው ጋር ሲነፃፀርም ብልጫ ያለው ትርፍ ማግኘታቸውንም የሚያሳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና 16ቱ የግል ባንኮች በ2013 የመጀመርያ ሩብ ዓመት አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠናቸው 1.14 ትሪሊዮን ብር የደረሰ መሆኑን ይኼው መረጃ አመልክቶ፣ ይህም ከዚህ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንፃር ሲታይ በስድስት እጅ ብልጫ ያለው ሆኗል፡፡
ከዚህ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ውስጥ ትልቁን ድርሻ የያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲሆን፣ በ2013 የመጀመርያው ሩብ ዓመት መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ ከ654.8 ቢሊዮን ብር በላይ ሲደርስ፣ የ16ቱ የግል ባንኮች የደረሱበት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ደግሞ ከ490 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን ያመለክታል፡፡ ይህ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በአገሪቱ ለመጀመርያ ጊዜ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡
በብድር አሰጣጡ ረገድም 17ቱም ባንኮች በ2013 በጀት ዓመት የመጀመርያ ሩብ ዓመት መጨረሻ ላይ፣ የብድር ክምችታቸው ከ623 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ የብድር ክምችታቸው መጠንም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብልጫ ያለው ሲሆን፣ በሩብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የብድር ክምችቱን 248 ቢሊዮን ብር ያደረሰ ሲሆን፣ 16ቱ የግል ባንኮች በጥቅል የደረሱበት የብድር ክምችት መጠን ከ375 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡
በብድርም ሆነ በተቀማጭ ገንዘብ መጠን የአገሪቱ ባንኮች እጅግ ከፍተኛ ውጤት ያገኙበት ሲሆን፣ በተቀማጭ ገንዘብ ረገድ በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ የሆነ ዕድገት እንዲያሳይ ካደረጉት አንዱ ከብር ለውጡ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው አጋጣሚ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዚሁ አንፃር በሩብ ዓመቱ 17ቱ ባንኮች ያገኙት የትርፍ ምጣኔም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ብልጫ ያለው ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚሁ ግርድፍ መረጃ መሠረት 17ቱ ባንኮች ከታክስ በፊት ያገኙት የትርፍ መጠን 8.7 ቢሊዮን ብር ነው፡፡
ከዚህ ከታክስ በፊት ከተገኘው ትርፍ መጠን ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3.1 ቢሊዮን ብር ሲያተርፍ፣ 16ቱ የግል ባንኮች በጥቅል ከታክስ በፊት ያገኙት ትርፍ ደግሞ 5.6 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ይህም 16ቱ ባንኮች በጥቅል ያገኙት የትርፍ መጠን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2.1 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው መሆኑን ያመለክታል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት 16ቱ የግል ባንኮች በጥቅል የሚያገኙት የትርፍ መጠን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትርፍ አንፃር ሲታይ ያነሰ ቢሆንም፣ አሁን ላይ 16ቱ የግል ባንኮች በጥቅል የሚያገኙት የትርፍ መጠን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሚገኘው ትርፍ ብልጫ እየያዘ ስለመምጣቱ የሚያመላክት ሆኗል፡፡
ከግርድፍ የሒሳብ ሪፖርቱ መረዳት እንደሚቻለው፣ ትርፍ ያስመዘገበው አዋሽ ባንክ ሲሆን፣ ይህም 1.07 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ዳሸን ባንክ ደግሞ 613 ሚሊዮን ብር ነው፡፡
እስከ 2013 የመጀመርያ ሩብ ዓመት ድርሻ ያለው የባንኮች አፈጻጸም፣ አሁንም ባንኮቹ አዲሱን ዓመት በጥሩ አፈጻጸም መጀመራቸውን የሚያሳይ መሆኑን ያመለክታል፡፡ በመጀመርያው ሩብ ዓመት ባንኮች ያስመዘገቡት ውጤት አትራፊነታቸውን ያሳየ ቢሆንም፣ በቀዳሚው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ የወሰዷቸውን ዕርምጃዎች አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፍባቸዋል የሚለው ሥጋት ግን አሁንም እንዳለ ስለመሆኑ ያነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያዎች ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
በቀዳሚው ዓመት ሁሉም ባንኮች በሚባል ደረጃ ሊያገኙ ይችሉ የነበረውን ገቢ ሊያስቀንስ የሚችል ብዙ ውሳኔዎችን መወሰናቸው፣ የብድር የመክፈያ ጊዜ ማራዘማቸው፣ የብድር ወለድ ምጣኔያቸውን መቀነሳቸውና አንዳንድ ባንኮችም ከኮቪድ ጋር በተያያዘ በእጅጉ ተጎድተዋል ለተባሉ የቢዝነስ ዘርፎች የወራት የብድር ወለድ ክፍያ ማስቀረታቸው፣ በባንኮቹ ገቢ ላይ የራሱ ተፅዕኖ ማሳደሩ ስለማይቀር፣ እስካሁኑ ጎልቶ ባይታይም በተጀመረው አዲሱ ዓመት ሥራቸው ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉ እንዳልቀረ ይጠቀሳሉ፡፡
በቀዳሚው ዓመት የተከሰተው ብቻ ሳይሆን ከወቅታዊ ሁኔታ አንፃርም ኢኮኖሚው ላይ ሊኖር የሚችለው ተፅዕኖ፣ በባንኮች ላይ ማረፉ ስለማይቀር ባንኮች እስካሁን እያደጉ በመጡበት ልክ የትርፍ መጠናቸው ሊያድግ ይችላል ብለው እንደሚያምኑም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
በአንፃሩ ግን ከኮቪድ በኋላ የብር ኖት ለውጡ ለባንኮች የሰጠው መልካም አጋጣሚ፣ ቀደም ብሎ የነበረውን ሥጋት በመቀነስ፣ ባንኮች አሁንም በተሻለ አፈጻጸማቸው እንዲቀጥሉ ያስችላል የሚል እምነት ያላቸው የባንክ ባለሙያዎች ደግሞ፣ በብር ለውጡ ሰበብ ባንኮች ማሰባሰብ የቻሉት የተቀማጭ ገንዘብ መጠን የተሻለ ብድር በመስጠት የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ይላሉ፡፡
አያይዘውም የብር ለውጡ የተረጋጋ ኢኮኖሚ ይፈጥራል ተብሎ የሚጠበቅ በመሆኑ፣ ይህ ከሆነ ባንኮች አሁንም ይገጥማቸዋል ተብሎ የተሠጋውን የገቢ መቀነስ ይሻገሩታል የሚለውን አመለካከት ሰንዝረዋል፡፡
ዓለም አቀፍዊና አገራዊ ተግዳሮቶች በተደጋጋሚ በሚስተዋልበት ወቅት፣ በአትራፊነታቸው የዘለቁት የአገሪቱ ባንኮች፣ በአሁኑ ጊዜ በመላ አገሪቱ ከ6,124 በላይ ቅርንጫፎች ያሏቸው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 1,607 የሚሆኑ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡ 16ቱ የግል ባንኮች ደግሞ 4,517 ቅርንጫፎችን ይዘው የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡