Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየተሻሻለው የጋራ ገቢዎች ማከፋፈያ ቀመር የክልሎችን የገቢ ድርሻ በአማካይ በ700 ፐርሰንት አሳደገ

የተሻሻለው የጋራ ገቢዎች ማከፋፈያ ቀመር የክልሎችን የገቢ ድርሻ በአማካይ በ700 ፐርሰንት አሳደገ

ቀን:

የሐረሪ ክልል 2012 ሩብ ዓመት ያገኘው አምስት ሺሕ ብር ዘንድሮ ወደ 37.6 ሚሊዮን አድጓል

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ያሻሻለው የጋራ ገቢዎች ማከፋፈያ ቀመር፣ ክልሎች ሲያገኙት የነበረውን የገቢ ድርሻ በአማካይ 700 ፐርሰንት በላይ ከፍ ማድረጉ ተጠቆመ። 

ላለፉት 23 ዓመታት ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው የጋራ ገቢዎች ማከፋፈያ ቀመር፣ ባለፈው ዓመት ተሻሽሎ ተግባራዊ መደረግ የጀመረ ሲሆንየገቢዎች ሚኒስቴርም አዲሱን ቀመር በመጠቀም በዘንድሮ በጀት ዓመት ሦስት ወራት የተገኘውን የጋራ ገቢ ለክልሎች አከፋፍሏል። 

ለአብነት ያህል በአዲሱ ቀመር መሠረት በዘንድሮ የበጀት ዓመት የመጀመርያ ሦስት ወራት ለሐረሪ ክልል የተከፈለው የጋራ ገቢዎች ድርሻ ቀድም ሲል በነበረው የጋራ ገቢዎች ማከፋፈያ ቀመር መሠረት ተሠልቶ2012 የበጀት ዓመት የመጀመርያ ሦስት ወራት ለክልሉ ከተከፈለው የገቢ ድርሻ ጋር ሲነፃፀር 6,423 ፐርሰንት የበለጠ ነው። 

ይህም ማለት የሐረሪ ክልል ቀድሞ በነበረው ቀመር ተሠልቶ 2012 በጀት ዓመት የመጀመርያ ሦስት ወራት የተከፈለው የጋራ ገቢዎች ድርሻ 5,854 ብር ብቻ ሲሆንበአዲሱ ቀመር ተሠልቶ በዘንድሮ በጀት ዓመት ተመሳሳይ ሦስት ወራት የተከፈለው የጋራ ገቢ ድርሻ 37.6 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

በተመሳሳይ ሥሌት የሶማሌ ክልል ባለፈው ዓመት የመጀመርያ ሦስት ወራት የተከፈለው የጋራ ገቢ ድርሻ 448,426 ሲሆንበዘንድሮው የበጀት ዓመት የመጀመርያ ሦስት ወራት የተላከለት የጋራ ገቢ ድርሻ ግን 467 ሚሊየን 232 ሺሕ ብር መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። 

ከላይ በተቀመጠው የጊዜ እንዲሁም የቀድሞውና የተሻሻለው ቀመር ንፅፅር መሠረት በማድረግ፣ ሌሎች ክልሎች በዘንደሮው በጀት ዓመት ሦስት ወራት ያገኙት የጋራ ገቢ ድርሻም በተመሳሳይ ከፍተኛ ለውጥ አሳይቷል። 

ለምሳሌ ኦሮሚያ ክልል ባለፈው በጀት ዓመት ያገኘው 288 ሚሊዮን ብር ሲሆንበዘንድሮው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ያገኘው1.6 ቢሊዮን ብር ነው። 

የአማራ ክልል ባለፈው በጀት ዓመት ያገኘው 249 ሚሊዮን ብር የነበረ ሲሆንበዘንድሮው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ያገኘው አንድ ቢሊዮን ብር ነው። 

የአፋር ክልል ባለፈው በጀት ዓመት ያገኘው አንድ ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ በዘንድሮው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ያገኘው 140 ሚሊዮን ብር ነው። 

ይህ የጋራ ገቢ በሦስት የግብር ዓይነቶች ብቻ ማለትም ከኤክሳይስ ታክስ፣ ከቫትና ከተርን ኦቨር ታክስ ገቢዎች የተገኘ ነው፡፡ ሌሎች የታክስ ዓይነቶች ሲጨመሩ ደግሞ ገቢው ከዚህ በላይ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው ለሪፖርተር ገልጸዋል። ይህ የጋራ ገቢዎችን ብቻ እንጂ የበጀት ድጎማን እንደማይጨምር አስረድተዋል።

በአዲሱ ቀመር ማሻሻያ የተደረገባቸውን የገቢ ክፍፍል ምጣኔን ሲያስረዱም በበፊቱ ቀመር መሠረት ከኤክሳይስ ታክስና ከቫት የሚገኝ ገቢ የሚከፋፈለው ከቫት የሚገኝ ገቢ 70 በመቶው ለፌዴራል መንግሥት ቀሪው 30 በመቶ የክልል ድርሻ እንደነበር፣ በተሻሻለው ቀመር መሠረት ግን ከቫት የሚገኝ ገቢ 50 በመቶ ለፌዴራል ቀሪው 50 በመቶ ደግሞ ድርጅቱ የሚገኝበት ክልል ድርሻ እንዲሆን መወሰኑን ገልጸዋል።

ድርጅቱ ከአንድ በላይ በሆኑ ክልሎች ውስጥ ቅርንጫፎች ያሉት ከሆነ ደግሞ፣ ድርጅቱ ለሠራተኛ በሚያወጣው ወጪ መሠረት እንዲከፋፈል ነው የተወሰነው። 

ሌላው በቀመሩ ማሻሻያ የተደረገው ከማዕድን የሚገኝ ገቢ የሚከፋፈልበት አሠራር ሲሆን፣ ቀደም ባለው አሠራር ከማዕድን የሚገኝ ገቢ 60 በመቶ ለፌዴራል መንግሥት ቀሪው 40 በመቶ ደግሞ ማዕድኑ የሚወጣበት ክልል ድርሻ ነበር። 

አሁን በተሻሻለው ቀመር ደግሞ ሃምሳ በመቶ ማዕድኑ ለወጣበት ክልል ሲሆን ከዚህ ውስጥ አሥር በመቶው ማዕድኑ የተገኘበት ማኅበረሰብ በቀጥታ ተጠቃሚ እንዲሆን፣ ለወረዳ ወይምዞን የሚከፈል እንደሆነና ከተቀረው ሃምሳ በመቶ ውስጥ የፌዴራል መንግሥት 25 በመቶ ድርሻ እንዲያገኝ፣ ቀሪው 25 በመቶ ለሁሉም ክልሎች የሚከፋፈል እንዲሆን መወሰኑን ገልጸዋል። 

ምክንያቱንም ሲያስረዱ ማዕድን የአንድ ክልል ብቻ ሳይሆን የአጠቃላይ የአገሪቱ ሕዝቦች ሀብት መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

ቀደም ብሎ በነበረው ቀመር መሠረት በፌዴራልና በክልል መንግሥት በጋራ የተቋቋመ የልማት ድርጅት የትርፍ ድርሻ የሚከፋፈሉት ባዋጡት ካፒታል መሠረት እንደነበረ፣ አሁን በተደረገው ማሻሻያ ግን በጋራ ካቋቋሙት የልማት ድርጅት የሚገኝ ትርፍን እኩል ሃምሳ በመቶ እንዲከፋፈሉ መወሰኑን ገልጸዋል።

ሌላው በጋራ በተቋቋመ ድርጅት ውስጥ የሚገኝ የሥራ ግብር ገቢን የሚከፋፈሉበት መንገድን የተመለከተ ሲሆን፣ ቀደም ብሎ በነበረው ቀመር መሠረት የሥራ ግብር በእኩል ሃምሳ በመቶ ይከፈሉ እንደነበር የገለጹት ሚኒስትሩ፣ አሁን በተሻሻለው ቀመር መሠረት ግን ድርጅቱ የሚገኝበት ክልል ከደመወዝ የሚገኝን ግብር መቶ በመቶ ክልሉ እንዲጠቀምበት ሆኖ መሻሻሉን አስረድተዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...