ኢትዮጵያ በፍጥነት ወደ ሰላምና መረጋጋት መመለስ ያለባት፣ ጦርነት በተራዘመ ቁጥር ያልተገመቱ ችግሮች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ነው፡፡ በትግራይ ክልል የተጀመረው ሕግ የማስከበር ዘመቻ በአስቸኳይ ተጠናቆ፣ ሰላማዊ ሕይወት እንዲቀጥል የብዙዎች ፍላጎት ነው፡፡ በአማራ ክልል በባህር ዳር ከተማ በተደጋጋሚ በሮኬት ጥቃት እየተፈጸመ፣ የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ ጦርነት ሲራዘም ከሚያደርሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት በተጨማሪ፣ ከፍተኛ ሥነ ልቦናዊ ጉዳትም ያስከትላል፡፡ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ ኢትዮጵያ ሳትወድ በግድ ከገባችበት ጦርነት ውስጥ በአሸናፊነት በፍጥነት መውጣት አለባት፡፡ ጦርነቱ ሲራዘም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ከመፈናቀላቸውም በላይ፣ በርካቶች ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሉ ወደ አደገኛው ስደት ያመራሉ፡፡ ሕፃናት፣ አረጋውያን፣ አቅመ ደካሞች፣ ነፍሰ ጡሮች፣ ጨቅላ ሕፃናትን የሚያጠቡ እናቶችና ሌሎች ንፁኃን ለአስከፊው ስደት ይዳረጋሉ፡፡ በንግድና በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ሰዎች ሥራቸው ከመታወኩም በላይ፣ በርካቶች ከዕለት ጉርስ ጀምሮ ሥራቸውን ጭምር ያጣሉ፡፡ የጦርነት አስከፊነት የተፋፋመው ውጊያ ውስጥ ካሉት ተዋጊዎች ጀምሮ ራቅ ያሉ አካባቢዎች ያሉ ሰዎችን ጭምር ስለሚያዳርስ፣ በተቻለ ፍጥነት እንዲጠናቀቅ መረባረብ ያስፈልጋል፡፡
ይህ ጦርነት ጀብደኞች የጫሩት ስለሆነና እነሱንም ለሕግ የሚያስቀርብ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ ዕገዛ አድርገው ሰላማዊ አየር መንፈስ ይኖርበታል፡፡ ሰላም በፍጥነት ሰፍኖ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን በእኩልነት የምታስተናግድ አገር ለመገንባት መረባረብ የግድ ይላል፡፡ ጦርነቱ ሲራዘም ጣልቃ ገብነቶች መኖራቸው አይቀሬ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች አማካይነት ከሚሠራጩ ዘገባዎች ለመገንዘብ እንደተቻለው፣ በትግራይ ክልል ውስጥ እየተካሄደ ያለው ሕግ የማስከበር ዘመቻ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ገጽታዎችን ተላብሷል፡፡ በአንድ በኩል ይህ ዘመቻ እንዲጀመር መነሻ የሆነው ምክንያትና አነሳሹ ማን እንደሆነ ጥርት ያለ ግንዛቤ ሲያዝ፣ በሌላ በኩል ደግሞ መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያልተረዳ አሉባልታ ያለ ገደብ እየተሠራጨ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ብዥታ ውስጥ ስለሚወድቅና አረዳዱም ስለሚዛባ፣ በእውነታ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ሲቸግረው እየተስተዋለ ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ዝንፈት ምክንያት ኢትዮጵያ ለይቶላት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ገብታለች የሚል ጥርጣሬ ወይም ግምት እየተፈጠረ ነው፡፡ ለዚህም ነው የተጀመረው ዘመቻ በፍጥነት ተጠናቆ ሰላማዊ አየር መንፈስ ያለበት፡፡ ዘመቻው ሲራዘም ከቁጥጥር ውጪ የሆኑ ጉዳቶች ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ፣ እንዲሁም የሰላማዊ ሰዎች ሕይወትም ለአደጋ የመጋለጥ ዕድሉ ስለሚጨምር ፈጣንና ውጤታማ ዕርምጃ ያስፈልጋል፡፡
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ አብዛኛው የታሪክ ክፍል ከጦርነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በታሪኳ ከድንበሯ አልፋ በሌሎች ላይ ወረራ በመፈጸም የምትታወቅ አገር ባትሆንም፣ ለቁጥር አታካች የሆኑ ወረራዎች ተፈጽመውባታል፡፡ በየዘመኑ የነበሩ ጀግኖች ልጆቿ ወራሪዎችንና ተስፋፊዎችን በመመከት ዳር ድንበሯን ሲያስከብሩ ኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን የኮሎኒያሊስቶችን ሕልም በማክሸፍ በአፍሪካ አኅጉር ብቸኛዋ በቅኝ ያልተገዛች አገር እንድትሆን አኩሪ ተጋድሎዎችን አድርገዋል፡፡ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች መመኪያ የሆነው አንፀባራቂውና ታላቁ የዓድዋ ድል፣ የጀግኖቹ ኢትዮጵያዊያን የአገር ፍቅር ስሜትና የመስዋዕትነት ውጤት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ባደረገቻቸው ራስን የመከላከል ጦርነቶች ተከብራ ብትኖርም፣ የመልማትና የማደግ ዕድሎቿ በመጨናገፋቸው ምክንያት በዓለም ጭራ ከሚባሉ ደሃ አገሮች ተርታ ተሠልፋለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተደጋጋሚ ለድርቅና ለረሃብ ተዳርጋ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ልጆቿን ተነጥቃለች፡፡ ስሟ የረሃብ ምሳሌ ሆኖ በመዝገበ ቃላት ጭምር ተከትቧል፡፡ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የረሃብ ወሬ ማጣፈጫ ሆና ለዓመታት ተዘክራለች፡፡ በእርስ በርስ ጦርነት በቆየችባቸው ዓመታትም ስሟ ሳይነሳ የዋለበት ጊዜ የለም፡፡ በዚህም ምክንያት በዓለም ዙሪያ የነበሩ ልጆቿ አንገታቸውን መድፋታቸው የተለመደ ትዕይንት ነበር፡፡ በሰላም ዕጦት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል፡፡ በፈጣንና በውጤታማ ዕርምጃ ሰላም መስፈን ይኖርበታል፡፡
ኢትዮጵያ ሰፊ ለም መሬት፣ ከፍተኛ የሆነ የውኃ ሀብት፣ በርካታ ማዕድናት፣ አስደናቂ የሆኑ የቱሪስት መስህቦች፣ ተስማሚ የሆኑ የአየር ጠባዮች፣ እንዲሁም ከምንም ነገር በላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የወጣት ኃይል ያላት አገር ናት፡፡ እነዚህን ተቆጥረው የማያልቁ የተፈጥሮ ፀጋዎች ተራራ ሊንድ ከሚችል የሰው ኃይል ጋር በማቀናጀት፣ በአፍሪካ አኅጉር አንፀባራቂ የሆነ ልማትና ዕድገት ማስመዝገብ አያቅትም፡፡ በአሁኑ ጊዜ 30 ሚሊዮን ያህል ወጣቶች በትምህርት ገበታ ላይ በሚገኙባት ኢትዮጵያ፣ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በአጭር ጊዜ ውስጥ ድህነትን ማስወገድ እንደሚቻል ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ የአገሪቱን ተቋማት መልሶ በመገንባትና በማዘመን፣ ብቁ አመራር የሚሰጡ ልሂቃንን በመመደብ፣ ሥራና ሠራተኛን በማገናኘት፣ ተቋማትን ከፖለቲካ ወገንተኝነትና ተፅዕኖ በማላቀቅ፣ ለዘመኑ የሚመጥኑ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በማውጣት የሚያሠራ መደላድል መፍጠር ከተቻለ አስደናቂ ውጤቶች ለማግኘት አያዳግትም፡፡ ሰላማዊ ድባብ የሚፈጠረውም ሁሉንም ወገኖች የሚያቀራርብ አሠራር ለማስፈን የሚያስችል ብሔራዊ መግባባት ሲኖር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ምንም ሳይጎድልባት ለተመፅዋችነትና ለተዋራጅነት የተዳረገችው፣ ሰላሟን የሚያደፈርሱና ህልውናዋን ለአደጋ የሚያጋልጡ ብልሹ አሠራሮች በመስፈናቸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የእነዚያ ብልሹ አሠራሮች ዋነኛ አጋፋሪዎች፣ የጦርነት እሳት ለኩሰው ኢትዮጵያን ሰላም ነስተዋል፡፡ የውጭ ጣልቃ ገብነት ሊጋብዙ ይችላሉ፡፡
ሰላም በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሚመጣ አይደለም፡፡ አሁን እንደሚታወቀው የጦርነቱ ሚዛን ወደ አንድ ወገን ያደላ በመሆኑ፣ ተሸናፊው በአገርና በሕዝብ ላይ ተጨማሪ ጉዳት ሳይደርስ ሽንፈቱን አምኖ መቀበል አለበት፡፡ ቀደም ሲል በውይይትና በድርድር ያልቁ የነበሩ ችግሮች ገጽታቸውን ለውጠው ጦርነት ሲነሳ፣ አሸናፊው ወገን የበላይነቱን ይዞ ሕግ ማስከበሩ ያለና የነበረ ወግ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ለሕዝብ ሰላም መስፈን ሲባል ጦርነቱ መጠናቀቅ አለበት፡፡ የራስን ባዶ ሕልም በቀቢፀ ተስፋ ለማሳካት በሚደረግ ተገቢ ያልሆነ እንቅስቃሴ የሕዝብን ደኅንነት ለአደጋ ማጋለጥ፣ በሕግም በታሪክም ተጠያቂ የሚያደርግ ወንጀል ነው፡፡ ሰላም መስፈን ያለበት የአገርን ህልውና ለማስቀጠልና የሕዝብን ፍላጎት ለማስከበር እንጂ፣ የጥቂት ጀብደኞችን ራዕይ አልባ ቅዠት በንፁኃን ደም ለማሳካት እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል፡፡ ማንም ከአገር ህልውና በላይ ባለመሆኑም በሕግም፣ በኃይልም ሰላም መስፈን ይኖርበታል፡፡ ጦርነቱ በሚካሄድበትም ሆነ በተለያዩ ሥፍራዎች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለአገር ህልውና መቀጠል ሲባል ሰላም መስፈን አለበት ማለት አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን የአገራቸው ህልውና ለድርድር መቅረብ እንደሌለበት በተባበረ ድምፅ ማሰማት ይኖርባቸዋል፡፡ ብቸኛው ዋስትናቸው ሰላም ነው፡፡ ይህ ሰላም የሚገኘው ግን ፈጣንና ውጤታማ መሆን ሲቻል ብቻ ነው፡፡
ኢትዮጵያን ከአሁን በኋላ ለግጭትና ለውድመት ከሚዳርጉ ድርጊቶች መታደግ የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል፡፡ በተለይ ደግሞ የአገሪቱ ፖለቲከኞች ራሳቸውን ገርተውና አርቀው ለሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ራሳቸውን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ገዥውን ፓርቲ ጭምር የሚመለከት ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጉልበትና ጠመንጃ መወገድ አለባቸው፡፡ ለአገር የሚጠቅም የረባ አጀንዳ ሳይኖራቸው የብሔር ሰሌዳ እየለጠፉ አገር ማመስ መቆም አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የጋራ መድረክ በመፍጠር ለሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር የሚያግዝ ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት ውይይትና ድርድር ላይ ማተኮር አለባቸው፡፡ በሕዝብ ስም እየነገዱ ሕዝብን አሳሩን ማሳየት መቆም ይኖርበታል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም በብሔርና በሃይማኖት እየከፋፈሉ ሊቆምሩበት የሚደራደሩበትን የማስቆም ኃላፊነት አለበት፡፡ ለመከላከያ ሠራዊቱ ያሳየውን ፍቅርና ክብር፣ ለአገሩ አንድነትና ህልውና፣ እንዲሁም ለአብሮነቱና ለጋራ ማኅበራዊ እሴቶቹ የገለጸውን የጋለ ስሜት አስጠብቆ ለመሄድ ጥንካሬውን በተግባር ማስመስከር ይጠበቅበታል፡፡ የተጀመረው ዘመቻም ፈጣንና ውጤታማ ሆኖ ተጠናቆ ሰላም እንዲሰፍን መረባረብ፣ ፋታ የማይሰጠው ተግባር መሆኑን መረዳት የግድ ይሆናል!