ከነዋሪው ግማሽ በላይ ወጣት እንደሚኖርባት የሚነገርላት አዲስ አበባ፣ የማዘውተሪያ ችግር ከሚስተዋልባቸው ከተሞች አንደኛዋ እንደሆነች ይታመናል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ነዋሪዎቿ በማዘውተሪያነት ሲቀሙባቸው የነበሩ ክፍት ቦታዎች አሁን ላይ ማታ ለጠዋት በቅለው ለሚያድሩ ግንባታዎችና ተያያዥ መሠረተ ልማት ፍጆታ ተሸንሽነው እያለቁ ናቸው፡፡
በቅርቡ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽነር ሆነው የተሾሙት አቶ በላይ ደጀን፣ ከተደቀነባቸው ወረራ በተዓምር እንደተረፉ ከሚነገርላቸው ማዘውተሪያዎች፣ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ፈረንሣይ ለጋሲዮን ጨፌ ሜዳ ተብሎ የሚጠራውን የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ፣ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በአራት ወር ጊዜ ውስጥ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ የሳይት ርክክብ መከናወኑ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
እንደ አዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን መግለጫ ከሆነ፣ ለዚህ ማዘውተሪያ ግንባታ 25 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዟል፡፡ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ነዋሪዎቿ ወጣቶች መሆናቸው የሚነገርላት አዲስ አበባ የስፖርቱ መሪዎች ኃላፊነት በተቀበሉ ማግሥት ሲናገሩት የቆዩት፣ ነገር ግን ተግባራዊ ሲሆን ባለመታየቱ አሁን እየተባለ ያውን የተስፋ ቃል በጥርጣሬ እንዲታይ ማድረጉ አልቀረም፡፡
ስፖርት ኮሚሽኑ የአዲስ አበባ ማዘውተሪያዎች ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ተጨማሪ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን በማደስ የማሻሻያ ግንባታ ለማድረግ ልዩ ትኩረት ለመስጠት እቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ግንባታው ውብኮን ኮንስትራክሽን ለተሰኘ ተቋራጭ መስጠቱን ያስታወቀው ኮሚሽኑ፣ ተቋራጩ በአራት ወር ጊዜ ውስጥ ግንባታውን አጠናቆ እንደሚያስረክብ መስማማቱ በመግለጫው ተካቷል፡፡ በሳይት ርክክቡ ወቅት የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽነር አቶ በላይ ደጀን፣ የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ ተወካይ፣ የየካ ክፍለ ከተማ ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች መገኘታቸው ኮሚሽኑ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በፍጥነትና በጥራት ተጠናቆ ለስፖርት ቤተሰቡና ለወጣቱ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ ኮሚሽነሩ መግለጻቸው ታውቋል፡፡