Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

እሑድ ኅዳር 6 ቀን 2013 ዓ.ም. በወጣው የሪፖርተር ዕትም ገጠመኝ ዓምድ ላይ የወጣው የአንድ ጸሐፊ ሐሳብ፣ እኔም ለዚህ ዓምድ ይህንን ጽሑፍ እንድልክ ምክንያት ሆኖኛል፡፡ ጸሐፊው በሳዳም ሁሴን ዘመነ መንግሥት የኢራቅ የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩትን መሐሙድ ሰዒድ አል ሰሀፍን፣ ከሕወሓቱ ጌታቸው ረዳ ጋር በማነፃፀር ያቀረቡት ትንበያ አስገራሚ ነበር፡፡ በተለይ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች በተለይም በፌስቡክ አላዋቂዎች በድፍረት ሲዘባርቁት የነበረውን ያጠራ፣ እንዲሁም በአሜሪካ የኢራቅ ወረራ ጊዜ የነበሩትን አል ሰሀፍና የጦረኛውን የሕወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸውን ተመሳስሎ በሚገባ ያስገነዘበ በመሆኑ ጸሐፊውን አድንቄያቸዋለሁ፡፡ እኔ ደግሞ በዚህ መነሻ ወደ ሌላ ተመሳሳይ ገጠመኝ አመራለሁ፡፡ ዓለማችን በርካታ አምባገነኖችን ያፈራች መሆኗ የታወቀ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት ሲጫወቱባት የኖሩት የሕወሓት አመራሮች ጉዳይ በቀላሉ ችላ የሚባል አይሆንም፡፡

ከ20 ዓመታት በላይ ኢትዮጵያ ላይ ነግሠው እንዳሻቸው ሲፈልጡና ሲቆርጡ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም ሲሰናበቱ፣ በተለይ የሕወሓት አባላትና ደጋፊዎች ድንጋጤ አይረሳኝም፡፡ በግል ሥራ ላይ የተሰማራሁ በመሆኔ በአጋጣሚ የተለያዩ አፍቃሬ ሕወሓቶችን አግኝቻለሁ፡፡ እኔ ለ25 ዓመታት በሥራ ዓለም ስቆይ በዕጣ ካገኘሁት፣ ባለሁለት መኝታ ኮንደሚኒየምና አሮጌ ፒክ አፕ መኪና በስተቀር ያፈራሁት ሀብት የለኝም፡፡ አያድርስና እኔ ወይም ባለቤቴ ወይም ሁለት ልጆቼ የከፋ ሕመም ቢገጥመን፣ ከፍለን ለመታከም የሚያስችለን በቂ ቁጠባ የለንም፡፡ ሌላው ቀርቶ የቤቴን ዕዳ ከፍዬ አልጨረስኩም፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ የሕወሓት ጀሌዎች ተዓምር በሚባል ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ የትልልቅ ንግድ ድርጅቶች ባለቤት ሲሆኑ፣ በርካታ ቤቶችን ከመሥራት አልፈው እጅግ በጣም ዘመናዊ የሆኑ መኪኖችን ይቀያይራሉ፡፡ አውሮፓና አሜሪካ ለእነሱ ፒያሳና መርካቶ ደረስ ብሎ የመምጣት ያህል ቀላል ናቸው፡፡ ዱባይና ቻይና ደግሞ እንደ ቤታቸው ይቆጠራሉ፡፡

ሁሉም ማለት ይቻላል የአገር ፍቅር ስሜት የሌላቸው፣ ሌላውን ሕዝብ የሚፀየፉ፣ ከሕወሓት በስተቀር አምላክ የሌላቸው ይመስል ምንም ነገር ማየት የማይፈልጉ፣ ሕዝባችን በኑሮ ውድነት እየተጠበሰ ምንጩ በማይታወቅ ገንዘብ በቅንጦት የሚንደላቀቁ፣ ሕወሓት ከሚነካ ኢትዮጵያ ብትፈርስ ደንታ የሌላቸው፣ አንድ ሰው እንዳሉት ሰይጣንን የሚያስከነዱ አጋንንቶች እንደነበሩ አውቃለሁ፡፡ አንድ ጊዜ በሥራ አጋጣሚ ያገኘኋትን ዓይን አፋር መሳይ የሕወሓት የጥቅም ተጋሪ፣ ‹‹የትግራይ ሕዝብ ሃይማኖተኛና ምስኪን ቢሆንም፣ እዚህ የማያቸው የሕወሓት ሰዎች ሕዝቡን የማይመስሉት ምን ሆነው ነው?›› ብዬ በትህትና ጥያቄ ሳቀርብላት፣ በአንድ ጊዜ ተቀያይራ ዓይናን እያጉረጠረጠች፣ ‹‹ለነፃነትህ ደሙን አፍስሶ ሰው ያደረገህን ሕወሓት እንዲህ ስትል አታፍርም?›› ብላ ስታፈጥብኝ በድንጋጤ ፈዝዤ ቀረሁ፡፡ የሚከተለውን ሳስብ ደግሞ የበለጠ ሥጋት ገባኝ፡፡

ራሳቸውን ከሕዝብ በዘረፉት ሀብት አበልፅገው አገሪቱን መጫወቻ ያደረጉ ሰይጣኖች ጭራሽ ነፃ አወጣናችሁ ሲሉ ያንገበግባል፡፡ ‹‹ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጪ›› የሚለውን የአንዳርጋቸው ጽጌ መጽሐፍ ያስታወሰችኝ ያቺ ባለጊዜ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቪኤይት የሚባለውን ዘመናዊ መኪና እየነዳች ሳያትማ መፈጠሬን ጠልቼው ነበር፡፡ ትግራይ ከአለቆቿ ጋር ከሸሸች በኋላ የደሃ ልጆች ለማስጨረስ፣ ‹‹እምበር ተጋዳላይ›› የሚለውን ዘመን ያለፈበት ዘፈን ታቀነቅን ይሆናል፡፡ የእሷና የመሰሎቿ ልጆችማ አውሮፓና አሜሪካ በምቾት ኑሮ ውስጥ እንዳሉ ብዙ የተባለበት ነው፡፡ እነዚህ ሰይጣንን በጭካኔ ድርጊታቸው አስገርመዋል የሚባሉ ጉዶች በምስኪኑ የትግራይ ሕዝብ ስም ሲቆምሩ ኖረው የማያሸንፉትን ጦርነት ቀስቅሰው ማንቁርታቸው ሊያዝ ሲል፣ በድብቅ የማርያም መንገድ ለማግኘት የአውሮፓና የአፍሪካ መንግሥታትን እየተማፀኑ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡ ሽንፈታቸውን አምነው እጃቸውን ካልሰጡና ለሠሩት ወንጀል ሕግ ፊት ካልቀረቡ በስተቀር የማይሞከር ነው፡፡

እዚህ ላይ ነው እንግዲህ አንዳንድ ጉዳዮችን ማንሳት ያለብን፡፡ ከማዕከላዊ መንግሥት ለሦስት ዓመታት በተደረገ ሕዝባዊ አመፅ ከተወገዱና ወደ መቀሌ ከሸሹ በኋላ፣ ራሳቸውን ሲያሞካሹበት የነበረውን ‹‹ግምገማ›› አካሂደው ችግራቸውን አልመረመሩም፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ምን ብንሠራ ነው እንዲህ የተጠላነው ብለው ራሳቸውን ለመውቀስና ለመታረም የሚያስችል ግምገማ አላደረጉም፡፡ ይልቁንም የትግራይን ሕዝብ የሚክሱበት ጊዜ አሁን መሆኑን ከአንገት በላይ በመናገር ልማት መጀመራቸውን ቢያስታውቁም፣ እነሱ ግን ከጦረኝነት አባዜ ለመላቀቅ ስላልፈለጉ እንደለመዱት የደሃ ልጆችን ለማስፈጀት ሠራዊት ማደራጀት ውስጥ ገቡ፡፡ አንድ አሁን የት እንደ ደረሰ የማላውቀው የትግራይ ተወላጅን፣ ‹‹እነዚህ ሰዎች አብደዋል ወይ?›› ብዬ ብጠይቀው፣ ‹‹ለኢትዮጵያ ስንትና ስንት ውለታ ሠርተው እንደ ጠላት ሲታዩ፣ ራሳቸውን ለመከላከል መዘጋጀታቸው ትክክል ነው…›› አለኝ፡፡ ‹‹ለትግራይ ሕዝብ ልማት ነው ወይስ ጦርነት የሚጠቅመው?›› ብለውም፣ ‹‹ሕዝቡ ማለት ሕወሓት፣ ሕወሓት ማለት ሕዝቡ እንደሆነ አታውቅም ወይ?›› ካለኝ በኋላ ነው፣ የሕወሓት የጥቅም ተጋሪዎች የአገር ጠላት መሆናቸው በሚገባ የገባኝ፡፡

ወገኖቼ በጀግናው የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው የክህደት ወንጀል ፈጽመው፣ በቆሰቆሱት ጦርነት ንፁኃንን እየፈጁና እያስፈጁ መቀጠል የማይችሉበት የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ እንደ ሳዳም ሁሴንና እንደ ሙአመር ጋዳፊ ከየሥርቻው እየተለቀሙ የሚያዙበት ጊዜው ቀርቧል፡፡ ይህንን ጽሑፍ ሳዘጋጅ ጀግናው ሠራዊታችን ወደ መቀሌ እየገሰገሰ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ በትዊተርና በፌስቡክ የተሰማሩ የሕወሓት ጀሌዎች እንደዚያ በጦርነቱ አሸናፊዎች ሆነው እንደሚወጡ እንዳልሰበኩ፣ የተጀመረው ጦርነት በፍጥነት ይቁም እያሉ ሲያለቃቅሱ አስተውያለሁ፡፡ ያለ እኛ ጀግና የለም ብለው ሲመፃደቁ የነበሩ ግብዞች መያዣ መጨበጫው ሲጠፋቸው የውጭ ወራሪ ኃይል ነው የወጋን፣ አፍሪካዊ ባልሆነ ኃይል ድሮን ተደበደብን ሲሉ መስማት ያሳፍራል፡፡ ለእነሱ ባህላዊ የሆነው ጦርነት እጅግ ዘምኖ በቀላሉ ሲደቆሱ ማየትን የመሰለ አስደሳች ነገር የለም፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን የትግራይ ወገናችንን ከእነዚህ የማፍያ ወረበሎች ነፃ አውጥተን፣ አገራችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዕፎይ ማስባል አለብን፡፡ የወረበላውን የሕወሓት አመራሮችና ጀሌዎቻቸውን ደግሞ ከአገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት በሠሩት ወንጀል እንፋረዳቸዋለን፡፡ አመራሮቻቸው ደግሞ ተራ በተራ እየተሻሙ ለጀግናው ሠራዊታችን እጃቸውን እንደሚሰጡ አልጠራጠርም፡፡ የንፁኃን ዕንባና ደም ይፋረዳልና፡፡

(ጌታቸው መሳይ፣ ከካዛንቺስ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...