Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉትግራይ ውስጥ ያለው መሠረታዊ ችግር ምንድነው?

ትግራይ ውስጥ ያለው መሠረታዊ ችግር ምንድነው?

ቀን:

በመታሰቢያ መላኩ

አንድ አካባቢ ለብዙ ዓመታት የቆየና በተደጋጋሚ የሚከሰት ችግር ሲፈጠር ሁሌም ወታደራዊ አቅም በመጠቀም መፍትሔ ለማፈላለግ ከመሞከር ይልቅ፣ ጥልቅ የሆነ ሳይንሳዊ ጥናት በማድረግ ችግሩ ከመሠረቱ መፍትሔ እንዲያገኝ መጣር በእጅጉ ተገቢ ነው፡፡ ወታደራዊ ዕርምጃ (ችግሮች በጊዜ ተጠንተው ከመሠረቱ መፍትሔ ማፈላለግ ከተቻለ) መውሰድ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ትግራይ ውስጥ ያለውን ችግር በሦስት ከፍሎ ነው የሚያየው፡፡

አንደኛ ትግራይ ተብሎ በአሁኑ ጊዜ የሚጠራው የአገራችን ክልል የረጅም ዘመን ሥልጣኔ ማለት ከሦስት ሺሕ ዓመታት በላይ ሥልጣኔ የተካሄደበት ቦታ በመሆኑ፣ መሬቱ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ስለሆነና የአፈር ለምነት በእጅጉ ስለተጎዳ፣ የትግራይ ሕዝብ የምግብ ዋስትና ምንጊዜም አሳሳቢ ችግር ነው፡፡

- Advertisement -

በመሆኑም በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ድህነት ይታያል፡፡ ሕወሓት ሃያ ሰባት ዓመት ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር በክልሉ ከሕዝቡ መሠረታዊ ችግር ጋር ምንም የማይገናኝ የሕንፃ ግንባታዎች፣ በበቂ ሙያተኛ ያልተጠኑ ፋብሪካዎችና ሌሎች የልማት ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም፣ እነዚህ የልማት ሥራዎች የሕዝቡን ሕይወት በመለወጥ በኩል እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ ማምጣት አልቻሉም፡፡ መሆን የነበረበት በተለይ ለዘመናት የተጎዳውን መሬት እንዲያገግም ጠንካራ ሥራ መከናወን ነበረበት፡፡

ሁለተኛ የትግራይ ክልል መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የትግራይ ሕዝብ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በንግድና በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲተሳሰር የሚመች አይደለም፡፡ በትግራይ ተወልዶ ያደገ ሰው ከትግርኛ ቋንቋ ውጪ ምንም ሳይሰማ ስለሚያድግ ዓለም ሁሉ ትግርኛ ተናጋሪ ልትመስለው ትችላለች፡፡ ትግራይ ክልል ደሴት ነች ማለት ይቻላል፡፡ ከምሥራቅ በኩል ከአፋር ክልል ጋር የሚያዋስን እጅግ ከባድ ገደል በመኖሩ፣ ሰዎች እንደ ልባቸው ተንቀሳቅሰው የኖሩበት ሁኔታ የለም፡፡

በሌላ አነጋገር የመልክዓ ምድሩ አቀማመጥ በሕዝቦች መካከል ያለ አጥር ሆኖ በመፈጠሩ፣ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የማይታሰብ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በስተደቡብ በኩል ከአፋር ክልል እስከ ተከዜ ሸለቆ ድረስ የተዘረጋ ሰንሰለታማ ተራራ አለ፡፡ ይህ የመልክዓ ምድር አቀማመጥ የትግራይ ሕዝብ ከአገው፣ ከራያና ከአማራ ሕዝቦች ጋር እንደ ልቡ እንዳይገናኝ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በስተምዕራብ በኩል የተከዜና የመረብ ወንዞችና ሸለቆዎች ስላሉ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አመቺ እንዳይሆን አድርጓል፡፡ በስተሰሜን በኩል የኤርትራ ድንበር ነው ያለው፡፡ ይህ ድንበር ለረጅም ጊዜ ሲዘጋ ሲከፈት የኖረ በመሆኑ፣ በዚህ በኩልም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ሰው ለሰው መገናኘት ቢችልም ቋንቋው አንድ ዓይነት ነው፡፡

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ እንቅፋቶች የትግራይ ሕዝብ ሁሌም በታጠረ አካባቢ እንዲኖር ምክንያት የነበሩ በመሆኑ፣ ትግራይ ውስጥ ተወልዶ ያደገ ሰው ባህሪው ለየት ያለ፣ ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር የመኖር ችሎታው የወረደ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በሌላ አነጋገር የትግራይ ሕዝብ ኅብረ ብሔራዊ አኗኗር ያልተለማመደ ማኅበረሰብ ነው፡፡

ሦስተኛ በትግራይ ባህላዊ አኗኗር ውስጥ ትግሬዎች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ሴቶቹ በጣም ተጨቁነው የሚያድጉ ሲሆን፣ ወንዶቹ ልጆች ደግሞ እንደ ልባቸው ሆነው አንድም ቁጣ ወይም ተግሳፅ ሳይደርስባቸው ስለሚያድጉ፣ ሁሉም ነገር እንደ ልጅነታቸው ስለሚመስላቸው ድፍረት የተሞላበት በርካታ ተግባራት ይፈጽማሉ፡፡ በአንድ ወቅት የመለስ ዜናዊ እናት ተጠይቀው ሲመልሱ ስለልጃቸው እንዲህ ብለው ነበር፡፡ ‹‹ልጄ መለስ በልጅነቱ ባገኘው ነገር ነበር የሚመታኝ፣ ስሜቱን መቆጣጠር አይችልም ነበር፤›› ብለው ነበር፡፡ እንዲህ ያለ የልጅ ባህሪ በየትኛውም የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የቤተሰብ ሥርዓት ማሰብ የማይችል ነው፡፡

ሌላው ፅንፍ የረገጠና እጅግ ክርር ያለ አስተሳሰብ በትግራይ ክልል በዚህ ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር ቻለ የሚለውን ጥያቄ ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች በተወሰነ መረጃ መልስ የሚሰጡ ቢሆንም፣ ሌሎች በርካታ ምርምሮች የግድ መካሄድ አለባቸው፡፡

በአጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ ገዳም ውስጥ እንደሚኖር ሰው ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር ተቀላቅሎ የመኖር ዕድል ባለማግኘቱ ከሚያውቀው ቋንቋ ብቻ ሳይሆን፣ ከሚያውቀው አስተሳሰብ ውጪ ሌላ አስተሳሰብ የመቀበል ልምድ በሁሉም ትግርኛ ተናጋሪዎች ላይ ባህርይ ነው፡፡ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ሕወሓት የማዕከላዊውን ሥልጣን ለ27 ዓመታት ተቆጣጥሮ በነበረበት ጊዜ፣ እዚህ አዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ውስጥ ንብረት አፍርተው መኖር የቻሉ ቢሆንም፣ በሚገርም ሁኔታ አስተሳሰባቸው ምንም ዓይነት ለውጥ አላመጣም፡፡

በተጨማሪ በርካታ ትግርኛ ተናጋሪዎች ባሳለፉት 27 ዓመታት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብና ሀብት ያፈሩ በመሆኑ፣ ቤታቸው ውስጥ ሁሉም ነገር ነበራቸው ማለት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን እንኳን በመመልከት ብዙ ዕውቀት ማግኘት ይችሉ የነበረ ቢሆንም፣ አሁንም ከኋላ ቀር አስተሳሰብ መውጣት አለመቻላቸው በእጅጉ የሚገርም ነው፡፡

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ቱሪስቶችን በማስተናገድ ለረጅም ጊዜ የሠራሁ ስለሆንኩ፣ ሁሉንም ሊባል በሚቻል ሁኔታ የትግራይ አካባቢዎችን ለማየት ዕድል አጋጥሞኛል፡፡ ለምሳሌ ሐውዜን የምትባለው በመሀል ትግራይ የምትገኝ እጅግ ትንሽ ከተማ ስትሆን፣ እኔ ባየኋት ጊዜ ከተማዋ ትንሽ ከመሆኗ የተነሳ የባጃጅ አገልግሎት እንኳን አልነበራትም፡፡ ነገር ግን በሳምንት ሁለቴ ነጋዴዎች ከመላው ትግራይ እየመጡ የሚገበያዩበት ገበያ አላት፡፡ በዚህ ገበያ ውስጥ በተደጋጋሚ ለመዘዋወር ዕድሉ ነበረኝ፡፡ በጉብኝቴ ወቅት ከተገነዘብኩት ነገር አንዱ ከትግርኛ ቋንቋ ውጪ ሌላ አንድም ቋንቋ ለማዳመጥ አልቻልኩም፡፡

ይህ የሚያሳየው በገበያ ቦታ እንኳን የብሔር ስብጥር አለመኖሩን ነው፡፡ እኛ የሰው ልጆች ከልጅነታችን ጀምሮ ለረጅም ጊዜ አብሮን የኖረን አስተሳሰብና ልምድ እንዲህ በቀላሉ አይለቀንም፡፡ ነገር ግን የሕወሓት አባላት ለ27 ዓመታት አዲስ አበባ ቆይተው በተጨማሪ የበላይነትን በሁሉም ቦታ ይዘው ቆሞ ቀር መሆናቸው፣ ሌላ ሰፊ ጥናት የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ በተጨማሪም እነሱ የሚያራምዱት አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ በመላው ዓለም ተቀባይነት ያጣ ሆኖ ሳለ ሕወሓቶች በዚህ መልኩ የዛሬ 45 ዓመት የጀመሩትን አስተሳሰብ አሁንም ችክ ብለው መንገታገታቸው በጣም የሚያስገርም ነው፡፡

ይህ ጽሑፍ የተጻፈው ሕወሓት በዕብሪት በከፈተው ጦርነት ምክንያት የፌዴራል መንግሥትና የክልሉ ልዩ ኃይል ጦርነት ላይ በነበሩበት ወቅት በመሆኑ፣ በዚህ ጽሑፍ ይህ አስከፊ ጦርነትን ማስቀረት ይቻል ነበር ወይ? በፌዴራል መንግሥት በኩልስ ያልተከናወኑ ሥራዎች ነበሩ ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችና ሌሎችም ጉዳዮች መዳሰስ አለባቸው፡፡ በመጀመርያ መነሳት ያለበት ጥያቄ የሕወሓት ደጋፊ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ዶ/ር ዓብይ ሥልጣን ላይ በቆዩበት ከሁለት ዓመት ተኩል በላይ እንዴት ወሳኝ ሥልጣን ላይ ሊቆዩ ቻሉ?

ሁለተኛ አሁንም የሕወሓት ደጋፊ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች እንዴት ሰሜን ዕዝ ውስጥ ሊመደቡ ቻሉ? ምክንያቱም እነዚህ የሠራዊት አባላት ከትግራይ ልዩ ኃይል ጋር ተባብረው ወንጀል ሊፈጽሙ እንደሚችሉ እንኳን ወታደራዊ ሳይንስ ለተማሩ ጄኔራሎች ይቅርና ማንም ተራ ሰው ሊገምተው የሚችለው ነገር ነው፡፡ እነዚህ ወታደሮች መመደብ የነበረባቸው ደቡብ፣ ምዕራብና ምሥራቅ ዕዝ ውስጥ መሆን ነበረበት፡፡ እንደ ሰማነው ትናንት ከሻዕቢያ ጋር በተደረገው ጦርነት ስለተሳተፉ ከሕወሓት ጋር ሊደረግ ከሚችለው ጦርነት በተመሳሳይ መንገድ ከልብ ይዋጋሉ ብሎ ማሰብ በእጅጉ የዋህነት ነው፡፡ ሌላው ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለማሳሰብ እንደ ሞከርኩት፣ የሕወሓትን ዕኩይ ተግባር ለማስፈጸም ሥራ ላይ የሚውለውን ገንዘብ እንደ ኤፈርት ያሉ ተቋማት ለሁለት ዓመት ተኩል ያለ ምንም ከልካይ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየተዘረፈ፣ የሕወሓትን ካዝና ሲያጣብብ መቆየቱ ሁላችንም የዶ/ር ዓብይን መንግሥት ልንጠይቅ የሚገባን ጥያቄ ነው፡፡

በዓረቡ ዓለም የሚኖሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሚታወቁት በሰላማዊነታቸው ነበር፡፡ ነገር ግን የነዳጅ ብር እንደልባቸው ማግኘት ሲጀምሩ ነው ሽብርተኝነት መስፋፋት የጀመረው፡፡ በእኔ እምነት ዶ/ር ዓብይ የሕወሓትን የገንዘብ ምንጭ ለማድረቅ ተግተው ሠርተው ቢሆን ኖሮ አሁን እየተካሄደ ያለው ጦርነት ባልተከሰተ ነበር፡፡ ምክንያቱም እስካሁን እየሞትን ያለነው በጥይት ሳይሆን በሕወሓት ገንዘብ ነው፡፡

የሕወሓት አባላት ለ27 ዓመታት አዲስ አበባ ተቀምጠው ኢትዮጵያዊነት ምን ያህል ሥር የሰደደ ማንነት መሆኑን እንኳን መገንዘብ አለመቻላቸው በእጅጉ ያስገርማል፡፡ እጅ ከሰጡ ወታደሮች እንደሰማነው አሁን እየተካሄደ ያለው ጦርነት የሚመራው እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ አሁን መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከኢትዮጵያዊነት ጀርባ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ቀስ በቀስ እየተገነዘቡ ያለበት ወቅት ነው፡፡ ያውም አሁን ያለው ከኢትዮጵያዊነት የሚገኘው ጥቅም አንድ ፐርሰንት እንኳን አይሆንም፡፡ በብሔር ፖለቲካ ምክንያት አገራችንን በፈለግነው ልክ ማልማት አልቻልንም እንጂ፣ ሁላችንም ተባብረን ለልማት ቆመን ቢሆን ኖሮ በአሁኑ ወቅት የሁላችንም ሕይወት በከፍተኛ ደረጃ በተለወጠ ነበር፡፡

ሕወሓቶች ሌላው የግድ ሊያውቁት የሚገባ ነገር ለአርባ አምስት ዓመታት የታገሉለት ትግራይን ወደ መንግሥትነት የመለወጥ ቅዠት፣ በምንም ሁኔታ ሊሳካ እንደማይችል ያሉትን አምስት ምክንያቶች ልጥቀስ፡፡

አንደኛ ቋሚ የሆነ የውኃ እጥረት ነው፡፡ ውኃ እንደሚታወቀው ከሩቅ ቦታ ማጓጓዝ የማይቻል፣ ነገር ግን ለሰው ልጆች ከኦክስጅን ቀጥሎ በእጅጉ የሚያስፈልግ፣ በተጨማሪም እያንዳንዱ ሰው ገላውን ለመታጠብ፣ ልብስ ለማጠብ፣ ምግብ ለማብሰልና ለመጠጣት ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ ፍጆታ የሚያስፈልግ በመሆኑ ይህንን ግብዓት ከሩቅ ቦታ ማጓጓዝ ከቶውንም የማይታሰብ ነው፡፡

ሁለተኛ የምግብ ዋስትና ፈታኝ መሆኑ ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው የትግራይ መሬት ለዘመናት ታጥቦ ያለቀ በመሆኑ፣ የትግራይ ሕዝብን የምግብ ፍጆታ በበቂ ሁኔታ ማቅረብ (ልዩ ሥራ ካልተሠራ በቀር) ምንጊዜም ፈታኝ ተግባር ነው፡፡

ሦስተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ሸቀጦች በበቂ ሁኔታ አለመኖር፡፡ እንደሚታወቀው የትግራይ ክልል የወርቅ፣ የዕምነ በረድና የብረት ማዕድን ከፍተኛ ሀብት እንዳላት አንዳንድ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ ነገር ግን ማዕድናትን የሚገዙት የበለፀጉ አገሮች በመሆናቸውና እሴት ያልተጨመረባቸው ማዕድናት ምዕራባውያን ዋጋቸው ሁሌም ዝቅተኛ እንዲሆን ተግተው የሠሩ በመሆኑ፣ የማዕድን ገቢን ተማምኖ አገር መመሥረት በእጅጉ አስቸጋሪ ነው፡፡ በመሆኑም የትግራይ ክልል መንግሥት ቢመሠረት እንደ መንግሥት የመቀጠሉ ዕድል በእጅጉ ጠባብ ነው፡፡ ኤርትራውያንም ሲገነጠሉ በማዕድን ሀብታችን ምክንያት በልፅገን እንኖራለን ብለው አስበው ነበር፡፡

አራተኛ የትግራይ ክልል የተራራ ሀብት የሌለው ክልል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቁመታቸው ከ3,900 እስከ 4,500 ሜትር ከፍታ ያላቸው ተራሮች ሃያ አምስት ናቸው፡፡ ሃያ ሁለቱ በአማራ ክልል የሚገኙ ሲሆን፣ የቀሩት ሀለቱ በኦሮሚያ የሚገኙ ናቸው፡፡ አንዱ ደግሞ በደቡብ ክልል የሚገኝ ነው፡፡ ትግራይ ክልል ውስጥ አንድም ዝናብ አምጪ ተራራ የለም፡፡ በትግራይ ክልል ያለው ከፍተኛ ቦታ በስተምሥራቅ ትግራይ የሚገኝ ከፍተኛ ቦታ ሲሆን፣ ይህም ከፍታ እስከ 2,600 ሜትር የሚደርስ ነው፡፡

አምስተኛ ትግራይ ብትገነጠል የራስ የሆነ ከንፁህ ታዳሽ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ስለማትችል፣ የዜጎች ሕይወት እጅግ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ ኢንቨስትመንትን የመሳብ ዕድልም አይኖራትም፡፡

እንግዲህ በእኔ ምልከታ ትግራይ ተገንጥላ መንግሥት ብትፈጥር ከኤርትራ የባሰ ድህነት ውስጥ ትገባለች እንጂ፣ ምንም ጥሩ ነገር አይጠብቃትም፡፡ ኤርትራውያን ከትግራይ የሚሻሉበት ሁኔታዎችን ከተመለከትን ኤርትራ ሰፊ የሆነ የባህር ዳርቻ ያላት ሲሆን፣ የቀይ ባህር ዓሳ ትልቅ ሀብት ነው፡፡ በተጨማሪም ትግራይ ስትገነጠል በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ከትግራይ ክልል ውጪ ያሉ ዜጎች ወደ ትግራይ የሚሄዱበት ሁኔታ ከተፈጠረ፣ ሊኖር የሚችለውን የኑሮ ውጥረት ለማሰብም የሚከብድ ነው፡፡

በመሆኑም ማንኛውም የትግራይ ተወላጅ ትግራይን መገንጠል በምንም ሁኔታ መተግበር እንደሌለበት ተገንዝቦ፣ መገንጠል የሚለውን አጀንዳ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ይኖርበታል፡፡ መገንጠል የማያዋጣ ከሆነስ የትግራይ ሕዝብ እንዴት ነው ከቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተግባብቶ መኖር የሚችለው?

 ሕወሓቶች ሥልጣን እንደያዙ ትግርኛ ቋንቋን የሥራ ቋንቋ ለማድረግ ሙከራ አድርገው ነበር፡፡ ነገር ግን እንደማያዋጣቸው ስለገባቸው በቀጥታ አማርኛ መማር ነው የጀመሩት፡፡ በተጨማሪ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ እርስ በርሳችን ለመግባባት ከአማርኛ ቋንቋ ሌላ ምንም አማራጭ የለንም፡፡ ነገር ግን ወደ ፊት የአገሪቱ ኢኮኖሚ እየበለፀገ ሲሄድ ወላጆች ልጆቻቸውን በተሻሉ ትምህርት ቤቶች ስለሚያስተምሩ፣ የተሻሉ ትምህርት ቤቶች ደግሞ እንግሊዝኛ ትምህርት ስለሚሰጥ በሒደት የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ እንግሊዝኛ መሆኑ አይቀርም፡፡ ያኔ በአገራችን በሚገኙ ያልበለፀጉ ቋንቋዎች ምክንያት እርስ በርስ መናቆራችን ይቀራል፡፡

በአንድ አገር የበለፀገ ኢኮኖሚ ካለ የግድ የበለፀገ ቋንቋ መኖር አለበት፡፡ አለበለዚያ መግባባት አንችልም፡፡ በመሆኑም የኢኮኖሚ ዕድገትና የቋንቋ ዕድገት የግድ አብሮ መሄድ አለበት፡፡

ካልሆነ ግን መግባባት አንችልም፡፡ በመሆኑም የኢኮኖሚ ዕድገትም የቋንቋ ዕድገትም የግድ አብሮ መሄድ አለበት፡፡ እዚህ ላይ ሕወሓት ከተወገደ በኋላ ትግራይን እንዲያስተዳድሩ የሚመደቡ ግለሰቦች አሁንም የብልፅግና ፓርቲን ፍላጎት  ለማስፈጸም ተብሎ የሚሾሙ ሳይሆኑ፣ የግድ በክልሉ ሥር ነቀል ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ፣ ከዘረኝነት የፀዱ፣ ለሚይዙት ሥልጣን የሚመጥን በቂ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው መሆን የግድ ይገላቸዋል፡፡ የትግራይ ሕዝብ በየወረዳውና በየዞኑ የራሱን ወኪሎች መምረጥ አለበት፡፡

በቅርቡ ባሳተምኩት ‹‹አቃፊ ማንነት›› በሚል ርዕስ በተጻፈ መጽሐፍ ላይ አብዲ ኢሌ በሠራው አሳፋሪና አሰቃቂ ወንጀል ምክንያት ከሥልጣን ተወግዶ አቶ ሙስጠፋ በመተካታቸው፣ በክልሉ ከፍተኛ የሚባልና ሕዝቡን ተጠቃሚ ያደረገ ለውጥ ማየት ተችሏል፡፡ ዶ/ር ዓብይ ይህንን ተግባር ለምን በሁሉም ክልሎች ለመድገም አቅም አጡ የሚለውን ጉዳይ ደጋግሜ ትኩረት እንዲሰጠው ሙከራ አድርጌያለሁ፡፡

በመሆኑም ወደፊት ትግራይን በሚያስተዳድሩ መሪዎች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላ ሥራ መሠራት ይኖርበታል፡፡ ዶ/ር ዓብይ በተደጋጋሚ ከተናገሩት ነገር አንዱ በመከላከያ ሠራዊት ላይ ከፍተኛ የሚባል ሪፎርም እንዳደረጉ ሲሆን፣ ከላይ በተጠቀሱ ምክንያቶች የተካሄደው ሪፎርም ሠራዊቱን ራሱ እንኳን ለአደጋ የጣለ ሁኔታ መከሰቱ የተሠራው ሪፎርም አጥጋቢ እንዳልሆነ፣ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩን ገምግሞ ትክክለኛ የዕርምት ዕርምጃ እንደሚወሰድ እምነቴ ነው፡፡

ሌላው በጣም የገረመኝ ነገር ከትግራይ ክልል ውጭ ያሉ የትግራይ ተወላጆች፣ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጎን መሆናቸውን የሚያሳይ ሠልፍ አለመውጣታቸው ነው፡፡ የሕወሓት አስተሳሰብ በሕወሓት አባላት ውስጥ ብቻ ያለ አስተሳሰብ ነው ብሎ ማሰብ በፍፁም ስህተት ነው፡፡ የትግራዊነት ስሜት ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች እጅግ ሥር የሰደደ አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህን ለመለወጥ ጥልቅና በሳይንስ የተደገፈ ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡

በአንድ አገር ያሉ ሕዝቦች ከመንደራቸው ውጪ ማሰብ አለመቻላቸው ከኋላ ቀርነትና ካለመሠልጠን የሚመጣ ችግር ነው፡፡ ኢትዮጵያ በድህነት እስከ ኖረች ድረስ ይህ ሁኔታ ይቀጥላል፡፡ ትክክለኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ሲመዘገብ፣ ዜጎች እንደ ልባቸው ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ፣ ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሲጠናከር፣ ነጋዴዎች ሩቅ ቦታ ሄደው መነገድ ሲጀምሩ የመንደር ቋንቋ እየጠፋ በሁሉም ነገር ማለትም በአለባበስ፣ በአኗኗር፣ በቋንቋና በሌሎችም በርካታ ጉዳዮች ሁሉም ሰው በየቀኑ በሚያደርገው ክዋኔ እየተቀራረብንና እየተመሳሰልን እንሄዳለን፡፡ ያኔ ነው ትክክለኛው ኢትዮጵያዊነት የሚፈጠረው፡፡

አሁን ባለው ኢትዮጵያዊነት መሬቱ ብቻ እንጂ የዜጎች ኢትዮጵያዊነት በበቂ ሁኔታ አለማለት አይቻልም፡፡ የዜጎች ኢትዮጵያዊነት እስኪፈጠር ገና ብዙ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡

የአገር ግንባታ ሒደት ወይም መንግሥትና የአንድ አገር ዜጎችን የመፍጠር ሒደት ለረጅም ጊዜ እልህ አስጨራሽ ነው፡፡ ይህ በተሳካ ሁኔታ ሊካሄድ የሚችለው አመፀኞችን በወታደራዊ ኃይል ዝም በማሰኘት ሳይሆን፣ ሁሉም ዜጎች የአገሪቱን ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ ሲቻል ነው፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥቱን አርመንና ሁሉንም ዓይነት መንግሥታዊ ሥርዓት አስተካክለን፣ ሁሉንም ዜጎች አሳታፊ በሆነ መንገድ አገራችንን ማልማት ስንችል ነው፡፡

በዶ/ር ዓብይ ሁለት ዓመት ተኩል የሥልጣን ዘመን ማየት የቻልነው ነገር ቢኖር፣ ከአንዱ አሰቃቂ ዜና ወደ ሌላ አሰቃቂ ዜና መሸጋገር ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ሰዎች ዶ/ር ዓብይን ‹‹እግረ ደረቅ›› እያሉ ሲጠሩዋቸው ሰምቻለሁ፡፡

ሌላው ዶ/ር ዓብይ ላይ የሚታይ ግልጽ የሆነ ባህሪ አለ፡፡ ችግር ሳይፈጠር ዕርምጃ የመውሰድ ችሎታ የላቸውም፡፡ ዶክተሩ ብዙ ከማዳመጥ ይልቅ ብዙ ማውራት ይወዳሉ፡፡ ቻይናዎች አንድ ተረት አላቸው፡፡ ‹‹የሰው ልጅ፣ ሁለት ጆሮ ሁለት ዓይን፣ አንድ አፍ ያለው በመሆኑ ብዙ ከመናገር ብዙ መስማትና ብዙ ማየት ይጠበቅበታል፤›› ይላሉ፡፡ ይህ አባባል ትልቅ ትምህርት ሰጪ ነው፡፡

ሕወሓት የፈጸመው የአገር ክህደት ወንጀል ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል አመራሮች ግድያ ወቅት፣ የሠራዊቱን አመራሮች በመግደል መከላከያን ለማፍረስ ተሞክሮ ነበር፡፡ ከዚህ ክስተት በመማር በርካታ የእርምት ሥራዎች መሥራት ያስፈልግ ነበር፡፡ ዶ/ር ዓብይ በጦርነት መሀል የጦር ኃይል ጠቅላይ አዛዥ ሹም ሽር ማድረጋቸው በምንም መመዘኛ ተቀባይነት ያለው ተግባር አይደለም፡፡ መከላከያ ፈረሰ ማለት እንደ ግብፅ ጡንቻቸውን ላፈረጠሙ አገሮች ይቅርና አልሸባብ እንኳን በቀላሉ አገራችንን ሊወር ይችላል፡፡

በጣም ደስ የሚለው ዜና ግን ከሠራዊቱ ተባረው ያለ ጡረታና ያለ ሕክምና አገልግሎት ሲሰቃዩ የነበሩ የቀድሞ የሠራዊቱ አባላት በከፍተኛ ቁጥር ለመዋጋት ዝግጁ መሆናቸውን መግለጻቸው፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቢፈርስም የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩን ለመጠበቅ ዝግጁ መሆኑን ያሳያል፡፡

ሌላው ሰሞኑን ያስገረመኝ ዜና በአገር ክህደት ድርጊት ላይ የተሰማሩ ጄኔራሎች አህያ እንደ ሰረቀ ሌባ መደበኛ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ነው፡፡ እነዚህ ጄኔራሎች በአስቸይኳ የጦር ፍርድ ቤት ተቋቁሞ በአጭር የፍርድ ሒደት የመጨረሻውን ቅጣት ማግኘት አለባቸው፡፡

‹‹አቃፊ ማንነት›› በሚለው መጽሐፌ ላይ ስለሕወሓት እንዲህ ብዬ ነበር፡፡ ‹‹ሕወሓት በጣም ዕድለኛ ነው፡፡ ሕወሓት ወደ ሥልጣን ሲመጣ ደርግ የኢትዮጵያን ሕዝብ ንብረት ወርሶ ለሕወሓት ያስረከበ ሲሆን፣ በተጨማሪም የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመብቱ የማይቆረቆርና የተኮላሸ ትውልድ አድርጎ ለሕወሓት አስረክቧል፡፡ ሕወሓት ከሥልጣን ሲወርድ ደግሞ ዶ/ር ዓብይ እጅግ ዘግናኝ ወንጀል የፈጸሙ የሕወሓት ባለሥልጣናትን በዝምታ በማለፋቸው፣ አሁን የሕወሓት ሰዎች መቀሌ ቁጭ ብለው የዘረፉትን እያጣጣሙ ይበላሉ፤›› ብዬ ነበር በገጽ 242 ላይ፡፡

አሁን የሆነው ግን የዘረፉትን እያጣጣሙ መኖር ሰልችቷቸው በድጋሚ በሕገወጥ መንገድ ወደ ሥልጣን ለመምጣት አረመኔአዊ ተግባር እየፈጸሙ ነው፡፡ ይባስ ብሎ እነዚህ ወንጀለኞች ወደ ብልፅግና ፓርቲ እንዲገቡ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ይህ ክስተት ምናልባት በዓለም የድንቃ ድንቅ ታሪክ መመዝገቡ አይቀርም፡፡

ማጠቃለያ

 የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ማንኛውንም ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ጥልቅ የሆነ ሳይንሳዊ ጥናት በማድረግ፣ ትክክለኛውን መፍትሔ ለማፈላለግ ጥረት መደረግ አለበት ብሎ ያምናል፡፡ እኔ የግሌን ጥናታዊ ዘገባ አቅርቤያለሁ፡፡ ጉዳዩ የሚያሳስባችሁ ሌሎች ዜጎች ያላችሁን ጥናት እንድትጨምሩ፣ በትግራይ ክልል ያለ ማቋረጥና በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ጦርነትና የኢትዮጵያዊነት መሸርሸር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ የበኩላችሁን እንድትሠሩ ከልብ አሳስባለሁ፡፡ ወታደራዊ ዕርምጃ ብቻ መፍትሔ አይሆንም፡፡

አሁን የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈጻሚ እያሰማን እንዳለው ነፃ የወጡ ከተሞችንና ዞኖችን በሕዝቡ ፍላጎት አመራሮችን በምርጫ መሾም የግድ መከናወን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ እየተሾሙ ያሉት ሰዎች ግን የብልፅግና ፓርቲ አባል የሆኑና ጤነኛ ያልሆነ የጀርባ ታሪክ ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ለሌላ ዙር ችግር የሚጋብዝ ነው፡፡

ትግራይ ውስጥ ያለውን የውኃ፣ የኢኮኖሚ፣ የማንነት፣ የፖለቲካና ሌሎችንም ችግሮች ለመቅረፍ ተጨማሪ ጥልቅ ጥናት ያስፈልጋል፡፡ እኔ በግሌ ያለኝን ወፍ በረር ምልከታ በዚህ ጽሑፍ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ፡፡ ይህን አጋጣሚውን ተጠቅመን ከስሜታዊነት የፀዳ ሳይንሳዊ ሥራ መሠራት አለበት እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...